ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ሰማዕታት – ዳንኤል ክብረት
በተለያዩ የባለ ሥልጣናትና የእምነት መሪዎች መግለጫዎች ላይ በሊቢያ ምድር የተሠዉትን ሰማዕታት በኢትዮጵያዊነታቸው ወይም በስደተኛነታቸው ብቻ አደጋ እንደደረሰባቸው ተድርጎ እየተነገረ ነው፡፡ እነዚህ ክቡራን ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተሠዉትም እምነታቸውን አንለውጥም ስላሉ ነው፡፡ አይሲስ የሠዋቸው በኢትዮጵያዊነታቸው አይደለም፡፡ አይሲስኮ ዜግነት የለውም፡፡ ዐረቦች፣ አውሮፓውያን፣ አፍሪካውያን እስያውያን የተቀላቀሉት አሸባሪና አሰቃቂ ድርጅትና አስተሳሰብ ነው፡፡ እንዲያውም ባለፈው ሰሞን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከእንግሊዝ ወደ አይሲስ ለመግባት ያደረጉትን ጥረት በመገናኛ ብዙኃን ሰምተን ነበር፡፡ አይሲስ አገር የለውም፡፡
እነዚህ ወንድሞቻችንማ ማተብ የሚያደርጉበትን አንገት ለእምነታቸው ሲሉ የሰጡ ቅዱሳን ሰማዕታት ናቸው፡፡ እኛ በቃል ብቻ የምንናገረውን ሰማዕትነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በተግባር ያሳዩ የተግባር ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ምናልባት ባለ ሥልጣናቱና ሚዲያዎቹ ይህንን ለመናገር የከበዳቸው ሌሎች አማኞችን እናስከፋለን ብለው አስበው ይሆናል፡፡ እውነት ለመናገር ግን በግድ ሃይማኖታቸውን ወደ እስልምና (ያውም አይሲስ ወዳጣመመው የእስልምና አመለካከት) መቀየር ነበረባቸው ብሎ የሚከራከር ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ቢኖርም አመለካከቱን እንዲፈትሽ ማድረግ እንጂ እርሱን ላለማስቀየም እውነቱን መካድ አያስፈልግም፡፡ የአይሲስን ሐሳብ ተቀብለው፣ እምነቱን አራምደው፣ ከእርሱ ጋር ተቀላቅለው ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን እድሜ ለማራዘም ቢፈልጉ መንገዱ ነበረ፡፡ ወላዋዮች፣ ለእምነት ግድ የለሾ፣ እምነታቸው እንደ ሸሚዝ ለመቀያየር የሚፈልጉ አቋም የለሾች ቢሆኑ ኖሮ ሞት ሩቅ ነበረ፡፡ እነ ኢያሱ፣ እነ ባልቻ፣ እነ ተስፋየና እነ ዳንኤል ግን እንደዚያ አልነበሩም፡፡ በእምነታቸው ጸኑ፤ በክርስቲያንነታቸው ታረዱ፣ ሰማዕትነትንም ተቀበሉ፡፡ይኼንን እውነታ መካድ ሰማዕታቱን ሁለት ጊዜ መግደል ነው፡፡ ከሞታቸው በላይ የሞቱበትን ክቡርና ቅዱስ ዓላማ መካድ አብልጦ ይገድላቸዋል፡፡ደግሞም ስደተኛነታቸው ለአደጋው ምክንያት ሆነ እንጂ የተሠዉት በስደተኛነታቸው አይደለም፡፡ ስደተኞችም ሆነው እምነታቸውን ለመለወጥ ቢፈልጉ ኖሮ ይችሉ ነበር፡፡ የተሠዉት በክርስትናቸው ነው፡፡ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አንገታቸውን የሰጡት ለክርስቶስ ነው፡፡ እንደ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ አነጋገር ‹እንደ ንጹሕ መገበሪያ ስንዴ ሆነው› ለአምላካቸው ነው በመሥዋዕትነት የቀረቡት፡፡ እነርሱ አንገት የሰጡለትን ክርስትና እኛ ለመናገር ለምን ፈራነው?