የመርሐ ግብር ማስተካከያ፡- የነገው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የጸሎተ ፍትሐት መርሐ ግብር ለኀሙስ ሚያዝያ 15 ጠዋት ተሸጋገረ
- በነገው የአ/አበባ ነዋሪዎች የመስቀል ዐደባባይ ሰልፍ ቤተ ክርስቲያን መልእክቷን ታስላልፋለች
ራሱን አይ ኤስ እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን፣ በንጹሐን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ በፈጸመው ግፍ ለገደላቸው ወገኖቻችን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ወንጌል ለማድረግ ለነገ ከጠዋቱ 2፡30 – 4፡30 የወጣው መርሐ ግብር ለኀሙስ ጠዋት፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. መተላለፉን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
መርሐ ግብሩ የተላለፈበት ምክንያት፣ በተመሳሳይ ሰዓት መላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሊቢያውን ግፍ በማውገዝ በመስቀል ዐደባባይ ሰልፍ ስለሚያካሒድ እና ቤተ ክርስቲያንም በዚኹ ሰልፍ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት መልእክት ስለምታስተላልፍ እንደኾነ ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከሚካሔደው የመርሐ ግብር ማስተካከያ በቀር፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ባሉ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ምሕላ እንዲካሔድ የተላለፈው ዐዋጅ፣ ቀደም ሲል በተገለጸው ማለትም ከነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚፈጸም ተመልክቷል፡፡
