ቂርቆስ በኀዘን ማቅ

click here for pdf

ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ከፖኤቲክ ጃዝ አባላትና ከሌሎች የኪነ ጥበብ ሰዎች ጋር ወደ ቂርቆስ ሄጄ ነበር፡፡ ያቺ ሳቂታዋና ተጫዋቿ ቂርቆስ ኀዘን ወርሯታል፡፡ የቂርቆስን ልጆች አውቃቸዋለሁ፡፡ ማልታ፣ ግሪክ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ስዊዘርላንድ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ መሳቅ ነው፣ መጨዋት ነው፡፡ መቀለድ ነው፡፡ ችግር እነርሱ ጋር የለም፡፡ ካገኙ ተካፍለው ካጡ ተሳስቀው ያልፉታል፡፡ መተዛዘን፣ መረዳዳት፣ ነገር ማቅለል ማን ይችላቸዋል፡፡ እንግሊዝ ሀገር የደረሱት በመንገድ ያለቁትን የሚያስቡበት ዓመታዊ የመታሰቢያ ቀን አላቸው፡፡
ከቂርቆስ ልጅ ጋራ አብረው ቢሰደዱ
ቢያገኝም ያበላል ቢያጣም ያዝናል ሆዱ
ይላሉ የማልታ ልጆች፡፡

ዛሬ ያ ሁሉ ሳቅና ጨዋታ በኀዘን ተቀይሯል፡፡ የልጆቻቸውን መሞት በቪዲዮ በተመለከቱ ወላጆች፣ ማንነታቸውን ከቪዲዮው ለመለየት አቅቷቸው በሰቀቀን ውስጥ በሚገኙ ወላጆች፣ የልጆቻቸውን መረጃ ፈልገው መልስ ባጡ ወላጆች ቂርቆስ ተሞልታለች፡፡ ትጠይቃለች፤ መልስ ግን አላገኘችም፡፡ እንዴት ያለው ትምህርት፣ እንዴት ያለው ጥበብ፣ እንዴት ያለው ብልሃት እንደሚያጽናናት እንጃ፡፡  
እኔ በልቅሶ ቤት ሄጄ ብዙም አላለቅስም፡፡ ዛሬ ግን አለቀስኩ፡፡ በተለይ የባልቻ እናት ‹ፍቅር እስከ መቃብር› እያሉ ሲያለቅሱ ስሰማ ዕንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ኢያሱና ባልቻ ሲበሉም፣ ሲጠጡም፣ ሲሄዱም፣ ሲቀመጡም የማይለያዩ አብሮ አደጎች ናቸው፡፡ ሲሰደዱም አብረው ነው የተሰደዱት፤ መሥዋዕት የሆኑትም አብረው ነው፡፡ ለዚህ ነው ‹ፍቅር እስከ መቃብር› የሚሉት የባልቻ እናት፡፡ እናቱን ሊረዳ እንደሄደ፣ ድሮም በእምነቱ ቀልድ እንደማያውቅ፣ ብዙ ተስፋ ሰጥቷቸው እንደነበረ እያነሡ ያለቅሳሉ፡፡ ‹‹እኔ ሲሞት እንዳላየው ብሎ አንገቱን ዘንበል አደረገ››  ይላሉ፡፡
 አያሌ የከተማው ሕዝብ ለእግር መቆሚያ እስኪጠብ ድረስ ሠፈሩን አጨናንቆታል፡፡ ኡኡታ፣ እሪታ፣ ሰቆቃ፣ ቁጭት፣ ሰቀቀን፣ ይነበባል፡፡ የባልቻ እናት ከልጃቸው ሞት በላይ አሁንም በሊቢያ የሚገኙ ሌሎች ወገኖቻችን ያሳስቧቸዋል፡፡ ስለ እነርሱም ያለቅሳሉ፣ ይወዘወዛሉ፡፡ አይ ኢትዮጵያዊት እናት፡፡