ወደ ባሕላችንና እምነታችን ስንመለስ

በሊቢያ ምድር እምነታቸው ወንጀል ሆኖባቸው በአይሲስ የተሠዉትን ሰማዕታተ ሊቢያ በተመለከተ መንግሥታዊና የሃይማኖት ተቋማት ሊያደርጉ ስለሚገባው ነገር ስንለው ስንለው ቆየን፡፡ እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ባሕላችንና እምነታችን እንመለስ፡፡
እነዚህ ወገኖቻችን ስማቸውንና ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን የምታውቁ ንገሩን፡፡ በባሕላችን መሠረት ልቅሶ እንድረሳቸው፡፡ ኀዘናቸው እነርሱ ብቻ አለመሆኑን እንንገራቸው፤ መከራቸውን እንካፈላቸው፡፡ እንደ ባሕሉ ማድረግ ያለብንን እናድርግ፡፡ ይኼ ከዘወትሩ ኀዘን ይለያል፡፡ የተሠዉበት ምክንያት፣ የተሠዉበት ሁኔታ፣ ለመሥዋዕትነት ያቀረቧቸው አሸባሪዎች ማንነት ከዘወትሩ ይለያቸዋል፡፡ ኀዘኑ የወላጅ፣ የዘመድ የመንደር፣ የዕድር ብቻ አይደለም፡፡ ከፕሬዚዳንቱ እስከ እኔ ላለነው ሁሉ ኀዘን ነው፡፡ ስለዚህም እንደየአመቺነቱ ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ በየደረጃው ያለን እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ልቅሶ እንድረስ፤ ሰውነታችንን፣ ለዜጎቻችን ያለብንን ኃላፊነት፣ ለቤተሰቦቹ ያለንን የመጽናናት ምኞት በመግለጫ ብቻ ሳይሆን በባሕሉ መሠረት እንግለጠው፡፡ ፖለቲካዊ ዲስኩሩን፣ ነጥብ ለማስቆጠር መጨቃጨቁን፣ የተለመደ ቢሮክራሲያዊ አሠራሩን ትተን ወደ ባሕላችንና እምነታችን እንመለስ፡፡ ባሕል የሌለን እምነት የሌለን አንምሰል፡፡ ለእንደዚህ ያለ ወቅት የሚሆን ወግና ሥርዓት አለን፡፡  ያለ ወግ የመየጣውን ዕዳ በወግ እንክፈለው፡፡

ታዋቂ ሰዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፣ የሞያ ማኅበራት መሪዎች፣ ባለ ሀብቶች፣ በባሕሉ መሠረት ወደ ቤተሰቦቹ ሄደን ኀዘናችንን እንግለጥ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ኀዘናችንን እንካፈለው፡፡ ልዩነታችንን ኀዘን አንድ ሊያደርገው ካልቻለ ከእንግዲህ ምን አንድ ያደርገዋል፡፡
እንደ እምነታችን ለሰማዕታቱ ተገቢውን ሥፍራ እንስጥ፤ የጸሎት ሥነ ሥርዓት በየአጥቢያው ይዘጋጅ፤ ፎቶዎቻቸው በየአጥቢያው ይለጠፉ፤ የተሠዉበት ክቡር ዓላማ ይነገር፤ በየአጥቢያው የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ምዕዳን ነገሩን ያገናዘበ ይሁን፤ ቢቻል በየ ቤተ እምነቱ ልዩ መርሐ ግብር ይዘጋጅ፡፡ ስለ ሰማዕታቱ የሚያወሳ፣ሽብርና ሽብርተኛነትን የሚያወግዝ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠነክር፤ በሐሳብ፣ በርእዮተ ዓለም፣ በአካሄድ ብንለያይም በሀገራዊ ጉዳይ አንድ መሆናችንን የሚያበሥር፣ የሰማዕታቱን ሰማያዊ ዋጋ የሚዘክር፤ ነገ ተመሳሳይ ነገር እንዳይደገም  መንገድ የሚቀይስ፣ ጉባኤ ይዘጋጅ፡፡
ይሄንን ነገር ያደረጉት አሸባሪዎች ናቸው፡፡ ይህንን ነገር ያደረጉት ኢሰብአውያን በመሆናቸው እንጂ ሙስሊም በመሆናቸው አይደለም፡፡ አንዱም ፍላጎታቸው እንዲህ ስሜት በሚነኩ ድርጊቶች ልዩነታችንን ማስፋት ነው፡፡ እኔ የብዙ ሙስሊም ወገኖቼን ስልክ ዛሬ ስቀበል ነበር፡፡ እጅግ ያዘኑ፣ የተነኩ፣ በእስልምና ስም በተፈጸመው ድርጊት ልባቸው የበገነ ሙስሊሞች፤ አማኞች እንጂ አሸባሪዎች ያልሆኑ፡፡ ሰው በእምነቱ የተነሣ መገደሉን በምንም መልኩ የማይቀበሉ ሙስሊሞች ኀዘናቸውን ሲገልጡ ነበር፡፡
ይኼንን ሰማዕታቱ የሰጡንን ዕድል ለአንድ ዓላማ ለመቆም እንጠቀምበት፤ የሰማዕታት ዓላማ ማስታረቅ ነው፤ ማግባባት ነው፡፡ ይኼንን የኢትዮጵያዊ መተዛዘንና መረዳዳት ጉዳይ ሙስሊም ወገኖቼ በእምነታቸውና በባሕላቸው አጉልተው ያሳዩናል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንዳችን በሌላችን የኀዘን ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተን ከእኩዩ ተግባር በተቃራኒ በጋራ መቆማችንን እናሳይ፡፡  
ያ ከሆነ የደሙ ልቦች ይድናሉ፣ የተጎዱ ቤተሰቦች ከልብ ይጽናናሉ፤ አራጆቻችንም የፈለጉትን ማግኘት እንዳልቻሉ ያያሉ፡፡ አሸባሪዎቹ በሰማዕትነት እንዳከበሩን ሁሉ እኛ ደግሞ የሰማዕታቱን ዓላማ በማጽናት እናዋርዳቸዋለን፡፡ ማን ያውቃል፣ የሰማዕታቱ ደም አልግባባ ላለው ልዩነታችን ሥርየት ይሆነን ይሆናል፡፡