ዓለም አቀፍ የሳተላይት ጣቢያ ለማቋቋም፣ በተመረጡ ቦታዎች ሥራ ተጀመረ ሼክ ዓሊ አል አሙዲን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል
- በ ፋኑኤል ክንፉ
በኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሳተላይት ጣቢያና የምርምር ማዕከል ለማቋቋም በተመረጡ ሁለት ትልልቅ ተራሮች ላይ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማሟላት በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሥራ እንደሚገባ የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጽ/ቤት ዋና ስራአስኪያጅ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገለፁ።
የጽ/ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ባቡ እንደገለፁት፣ “ሳተላይት ጣቢያዎቹ የሚገነቡት በአማራ ክልል ሲሆን ሁለት የወረዳ ቦታዎችን ተመርጠው ወደ ሥራ መግባታቸውን አረጋግጠዋል። የተመረጡት ቦታዎች አንደኛው፣ በላስታ ወረዳ በአቡነ ዮሴፍ ተራራ ጫፍ ሪም ገደል አካባቢ ሲሆን የተራራው ከፍታም 5ሺህ 394 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ነው። ሁለተኛው፣ በግዳን ወረዳ በባሆይ ተራራ ለምድ ጣቢያ አካባቢ ሲሆን የተራራውም ከፍታ 5ሺህ 251 ሜትር ከባህር ወለል በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም በሁለቱ ወረዳዎች ለሳተላይት ጣቢያው የሚያስፈልገውን መሰረተ ልማቶች እና ተመራማሪዎች የሚያርፉበት የመኖሪያ ቦታዎች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም አስፈላጊውን የቅድመ ጥናቶችና ተመራማሪዎቹ ካደረጉ በኋላ ለአጠቃላይ ለጣቢያው ግንባታ ሊረዱ የሚችሉ ግብዓቶችን ይሰበስባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
“ይህን የስፔስ ሳይንስ የምርምር ተቋም በአቅም የማደራጀቱን ሥራዎች በጣም ፈታኝ ነው ተብሎ ይታሰባል። በጽ/ቤታችሁ በኩል አቅም የማደራጀት ሥራዎችን እንዴት ነው የምታከናውኑት?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አማረ የሰጡት ምላሽ “አቅማችን በማደራጀት በኩል የክብር ዶ/ር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲን ድጋፍ አይነተኛ አስተዋጽኦ አለው። በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና የምርምር ማዕከል የተተከሉት ሁለት የኢንፍራሬድ እና የኦብቲካል ትልልቅ ቴሌስኮፖችን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገው የገዙልን እሳቸው ናቸው። ግዢው የተፈጸመው ከአንድ ከጀርመን አስቴልኮ ከተባለ ኩባንያ ነው። የቴሌስኮፕ ተከላውም ሲከናወን የጀርመን ኩባንያ ባለሙያዎችን ሙሉ ወጪ የሸፈኑት እሳቸው ናቸው። እንዲሁም የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና የምርምር ማዕከሉን ግንባታዎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገውም አሰርተዋል” ብለዋል።
አቶ አማረ አያይዘውም “መንግስት እና የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ አባላቶች ለስፔስ ሳይንስ ምርምር ማዕከል እዚህ መድረስ የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አስረድተዋል። አያይዘውም “የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት እና አሁን የበላይ ጠባቂ ለሆኑት ለአቶ ተፈራ ዋልዋ የማዕከሉን መቋቋም አስፈላጊነት አስበው በማስጀመራቸው ምስጋና ይገባቸዋል” ብለዋል።
በአሁን ሰዓት የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና የምርምር ማዕከል የማስተርስ እና የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል።
እንደሚታወቀው የፎርብስ አምደኛና የቢሊየነሮችን ግለ-ታሪክ እና ቢዝነሳቸውን በመዘገብ የምትታወቀው ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና በኢኮኖሚክስ ሪፖርቲንግ የማስተርስ ዲግሪዋን የወሰደችው ታቲያና ሰራፊን በአንድ ወቅት ለዶ/ር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲን “ለበጎ አድራጎት ስራዎች ቅድሚያ የሚሰጡት ለየትኛዎቹ ዘርፎች ነው” በሚል ላቀረበችላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “መጀመሪያ ለትምህርት ቅድሚ እሰጣለሁ” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በተያያዘ ዜናም ዶ/ር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲን ከሳዑዲና ከደቡብ ኮርያ ኢንቨስተሮች ጋር በመሆን በሳዑዲ ዓረቢያ የኦቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል የተባለ የመኪና ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነቡ መሆኑ ታውቋል። የመኪና ፋብሪካው ፕሮጀክት የመነሻ ሃሳብ የመነጨው በኪንግ ሳዑዲ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዶ/ር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲን የ275 ሚሊዮን ዶላር የአክሲዮን ድርሻ ክፍያ ለመፈጸም ቃል ገብተዋል። ለመኪናው ማምረቻ ፋብሪካ “ጋዛል አንድ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
Watch Ethiopian movies legally. Upto 5 movies added daily. Here are the top 10 most viewed movies today.
Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
