ኤርትራ “የተመታሁት በእስራኤልና በሲ.አይ.ኤ ነው” አለች
ባለፈው አርብ ሌሊት በኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊ ጄቶች በሁለት ታርጌቶች ላይ ክፉኛ ጥቃት የተሰነዘረባት ኤርትራ ‹‹የተመታሁት በእስራኤልና በሲ አይ ኤ እንጂ በኢትዮጵያ አይደለም›› በማለት ዜጎቿን እየዋሸች እንደምትገኝ ተገለጸ፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣን ለኩራት ጋዜጣ እንዳረጋገጡት የኢትዮጵያ አየር ሃይል በሁለት የኤርትራ ኢኮኖሚና ወታደራዊ ታርጌቶች ላይ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ከአስመራ በ45 እና 150 ኪሎ ሜትሮች ላይ የሚገኙት ታርጌቶችን የጦር ጀቶቹ አጥቅተው ያለምንም ችግር በሰላም ወደ ጦር ሰፈራቸው የተመለሱ ሲሆን የኤርትራ መንግስት የአየር ሓይሉን ብቃት መቀበል አልፈለገም፡፡
የኤርትራ መንግስት ‹‹ጥቃቱ የተፈጸመው በሲ አይ ኤ እና እስራኤል መንግስታት ነው›› በማለት እየገለጸ የሚገኘው ለ24 ዓመታት ሰራዊትና የጦር ካምፕ በመገንባት እድሜውን ያሳለፈ በመሆኑ በኢትዮጵያ ጥቃቱ ተፈጸመ ብሎ ካመነ የሚከተለውን ፖሊሲ ስህተት ስለሚያጋልጥበት መሆኑንም ምንጩ ጨምሮ ገልጸዋል፡፡
ስለጉዳቱ መጠንም የኤርትራ መንግስት ‹‹አነስተኛ ነበር የመዓድን ኩባንያውም ጥገና አካሄዶ ስራውን ጀምሯል›› ማለቱ የደረሰውን ጉደት ለማጣጣል እየሞከረ ሲሆን ስለ ወደመው የመሳሪያ ግምጃ ቤት አንዳችም አልተነፈሰም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ጥቃቱን በሁለት ምክንያቶች ሳትፈጽም አትቀርም›› የሚሉት በኢትዮጵያ የሰላምና ደህንንት ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪና ተንታኝ ስለጉዳዩ ለኩራት ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ‹‹የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ አሸባሪ ብላ የፈረጀቻቸውን አምስት ድርጆቶች በማስጠጋት በግልጽ ድጋፍ ከማድረጓም በላይ እያስታጠቀች ወደ መሃል ሀገር በማስገባት ሽብር ለመፈጸም ሞክራለች፡፡›› ብለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ መንግስት ከእትዮጵያ ተጠልፎ የተወሰደውን የጦር ሄሊኮፕተር እንዲመለስ በሶስተኛ ወገን ወዳጅ ሃገራት በኩል በቀረበለት የሽምግልና ጥያቄ ቀና ምላሽ አልሰጠም በማለት ግልጸዋል፡፡ በእነዚህ ሁለቱ ዋና ዋና ምክንያቶች ኢትዮጵያ የኤርትራ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚል ግምት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት በልማት ስራ ላይ ተሰማርተው በነበሩ ቻይናዊያን ላይ ባደረሰው ጥቃትና ጀርመናዊያን ቱሪስቶችን አግቶ በመውሰድ ቀደም ሲል በሶስት የኤርትራ ጦር ካምፖች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ያስታወሱት ተመራማሪው ኢትዮጵያ የአሁኑን ጥቃት በይፋ መግልጽ ያልፈለገቸው ለኤርትራ መንግስት ያላትን ንቀት ለማመልከት ሳይሆን እንደማይቀር ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም በኤርትራ መንግስት የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመከላከል በማንኛውም ጊዜ ተመጣጣንኝ እርምጃ እወሰዳለሁ ብላ አቋሟን ግልጽ ያደረገች በመሆኑ የአሁኑ እርምጃ እልኋን በሟሟጠጥ ምክንያት የወሰደቸው እና የኤርትራ መንግስትም ገፍቶ ቢሄድና የተፈለገውን ጥቃት ኢትዮጵያ ማድረስ እንደምትችል ምልክት የሰጠ ነው ብለዋል፡፡ የተወሰደው እርምጃ ሀገሪቷ ያለችበትን ጠንካራ የተሟላ አቅም የሚያሳይ ነው ያሉት እኝሁ ከፍተኛ ባለስልጣን የኤርትራ መንግስት ይሄንን እውነት አምኖ መቀበል ተስኖታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግስት አቋም የለውም ›› ለማለት ስለሚፈልግ የየተወሰደበትን ጥቃት መካድ መሞከሩ በየትኛውም አለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይችል በመረዳቱ ነው ብለዋል፡፡ ለረጅም ዘመናት የጦር ካምፕና የጦር ሰራዊት ሲገነባ የኖረው የኤርትራ መንግስት እንዲህ አይነት ጥቃት በቀላሉ ማስተናገዱ ህዘቡ በመንግስቱ ላይ ያለውን እመነት የሚሸረሽርበት ስለሆነ ህዝቡን እየዋሸው ለማምለጥ ይጥራል ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሳይንስናአቅም ታላለቅ ከሚባሉት አስር የአፍሪካ ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ከመሆኗም በላይ በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሁሉንም ጎሮቤት ሀገራት እምነት ያተረፈች ናት ለሰላምና ለልማት ተባብራ እየሰራች ያለች ሀገር በመሆኗ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋራ የምታደርገው ማንኛውም አይነት ፉክክር እንደማያዋጣት ልታውቀው ይገባታል›› ብለዋል ተመራማሪው፡፡ ሁለቱ ሃገራት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ሊፈቱ የሚችሉት በውይይትና በድርድር መሆን እንደሚገባውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ምንጭ ኩራት ጋዜጣ
The post ኤርትራ “የተመታሁት በእስራኤልና በሲ.አይ.ኤ ነው” አለች appeared first on ሳተናው (Satenaw) -Latest Ethiopian News & Breaking News.