ለሕጋዊው ሲኖዶስ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ
ከፖርትላንድ ኦሬገን ቅድስት ማርያም ምዕመናን
ከሁሉም በፊት የእግዚአብሔር ሠላምታችን እናስቀድማለን። ይህን ግልጽ ደብዳቤ እንድንጽፍ ያነሳሳን ወይም ያስገደደን በአጥቢያ ቤተክርስትያናችን ማለትም በፖርትላንድ ኦሬገን የደብረ-ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አገልጋይ ካህን በሆኑት ቀሲስ ኤፍሬም የኋላሸት እና በምእመናን መካከል ያለው ሥር የሰደደ ችግር ነው።
የፖርትላንድ ማርያም ቤተክርስትያን በሕገ-ደንባችን መሠረት በስደት ላይ የሚገኘውን ሕጋዊ ሲኖዶስ የምትቀበል እንደመሆኗ መጠን በቤተክርስትያናችን ውስጥ ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በቅርበት የሚገኙትን የሲያትል ገብርኤል አባቶቻችን ለማነጋገር ሙከራ ተደርጓል። በዚህም ረገድ ችግሩን ለማጥናትና መፍትሔ ለመስጠት በአካል ፖርትላንድ ድረስ የመጡ አባቶቻችን አቡነ ዮሐንስና አባ ገብረሥላሴ ጥበቡን ልናመሰግን እንወዳለን። አቡነ ዮሐንስ እና መምህር አባ ገብረሥላሴ ጥበቡ ለሁለት እና ሦስት ሳምንታት ያህል በጋራና በተናጠል የተመላለሱ ቢሆንም የቤተክርስያናችን ችግር ግን መፍትሔ አልተገኘለትም፤ ተባባሰ እንጅ።
ስለሆነም የአለብንን ችግር አይታችሁ በመፍትሔ እንድታግዙን ይረዳ ዘንድ ጉዳያችንን በግልጽ ወደ እናንተ ለማድረስ ወደድን። ተገቢ የሆነ መፍትሔ እንደምትሰጡንም እንተማመናለን። የችግራችንን አነሳስ ምንጭና የነገሩን ከየት እስከየትነት ትረዱት ያስችል ዘንድ ወደኋላ በመመለስ ታሪኩን በአጭሩ ለማቅረብ ሞክረናል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ባለማወቅ የተላለፍነው ጉዳይ ቢኖር እንኳ አባታዊ ይቅርታችሁ እንዳይለየን አስቀድመን ይቅርታችሁን እንለምናለን።
ቀሲስ ኤፍሬም የኋላሸት ማን ናቸው?
ቀሲስ ኤፍሬም በፖርትላንድ ኦሬገን የምትገኘው የደብረ-ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አገልጋይ ካህን ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ያስመጧቸው ብሩኩ አባታችን ብጹእ አቡነ ዜናማርቆስ ነበሩ። አቡነ ዜናማርቆስ ቤተክርስትያናችን ባርከውና መርቀው የከፈቱልን ቸር አባታችንም ነበሩ። አቡነ ዜናማርቆስ ከቀሲስ ኤፍሬም በፊትም ቀሲስ አንዱዓለም ይርዳውን እንዲሁ ከኢትዮጵያ አስመጥተው ለቤተክርስትያናችን እንዲያገለግሉ መድበውልን እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም በዲቪ ሎተሪ የመጡ ቀሲስ ታፈሰ የተባሉ ካህን የቤተክርስትያናችን 3ኛ ካህን ሆነው ያገለግሉ ነበር። በአጠቃላይ በአንድ ወቅት በሦስት ካህናት ትገለገል የነበረችው ቤተክርስትያናችን አሁን ያሏት ካህን ቀሲስ ኤፍሬም ብቻ ናቸው። ለምን? ታሪኩ በአጭሩ እንደሚከተለው ነው።
ቀሲስ ታፈሰን በተመለከተ ቀሲስ አንዱዓለም እና ቀሲስ ኤፍሬም በጋራ ሆነው የክህነት ምግባር ይጎላቸዋል (ቁርባን አልቀበልም ይላሉ፣ ለብሰውት ባደሩት ፒጃማ ቅዳሴ ይገባሉ፣ በኪዳን ጊዜ አይደርሱም…ወዘተ) በመሆኑም ከእርሳቸው ጋር አብረን አንቀድስም በማለታቸው ጉዳይ በቤተክርስትያናችን የሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ቦርድ አባላት እና በቤተክርስትያናችን ሽማግሌዎች አማካኝነት እርቅ ለማድረግ ቢሞከርም ሊሳካ አልቻለም። በመሆኑም በቤተክርስትያናችን ህገደንብ መሠረት ጉዳዩ ለጠቅላላ አባላት ጉባዔ ቀርቦ በአባላት ውሳኔ ቀሲስ ታፈሰ ከቤተክርስትያናችን አገልግሎት እንዲነሱ ተወሰነ። ይህ የሆነው በ2006 ዓ.ም. ነበር።
በ2007 ዓ.ም. ማገባደጃ ላይ ደግሞ ከዚህ ቀደም የሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ቦርድ ሊቀመንበር አለመሆናቸው ቅር አሰኝቶአቸው የቆዩት ቀሲስ አንዱዓለም በስደት የሚገኘው ሕጋዊው ሲኖዶስ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት መሾሙን ተከትሎ ከዚህ በፊት ተቀብለውት የኖሩትን በመተው ሹመቱን እቃወማለሁ፣ ሲኖዶስ አይሰደድም፣ ከዚህ በኋላ አቡነ መቆርዮስን በቅዳሴ ጊዜ ስማቸውን አልጠራም፣ የአቡነ ጳውሎስ ስም መጠራት አለበት… ወዘተ በማለታቸው በአባላት መካከል ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት ተቀስቅሶ ነበር። በመጨረሻም የሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ቦርዱ በህገደንቡ መሠረት በወሰደው እርምጃ ቀሲስ አንዱዓለም ከቤተክርስትያናችን አገልግሎት ተሰናበቱ። ቀሲስ አንዱዓለም ለምን ወደዚያ አቋም ሄዱ የሚለው የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ስላልሆነ ታሪኩን በዝርዝር ለማቅረብ አልወደድንም። በነገራችን ላይ ሁለቱም ቀሳውስት ከቤተክርስትያናችን አገልግሎት ከተሰናበቱ በኋላ በዚሁ በከተማችን ውስጥ የየራሳቸውን ቤተክርስትያን መሥርተው አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል።
በመሆኑም ቀሲስ አንዱዓለም ከቤተክርስትያናችን አገልግሎት ከተሰናበቱበት ከ2007 ዓ.ም. ማገባደጃ ጀምሮ ቀሲስ ኤፍሬም በፖርትላንድ ኦሬገን የምትገኘው የደብረ-ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ብቸኛው አገልጋይ ካህን ናቸው። ቀሲስ ኤፍሬም ከክህነት ስራቸው በተጨማሪም (በበለጠም) በከተማችን በሚገኘው አየር ማረፊያ ተቀጥረው ይሰራሉ። ከዚህ በመቀጥል ቀሲስ ኤፍሬም በአገልግሎት ጊዜያቸው በብጹአን አባቶቻችን፣ በመዘምራን፣ በቤተክርስትያናችን አባላት፣ በሰበካ ጉባኤ ቦርድ አባላት እንዲሁም በህገደንባችን ላይ የፈፀሙትን በደል እና ያደረሱትን ጥፋት ለማቅረብ እንሞክራለን።
ከብጹአን አባቶቻችን ጋር ያላቸው ግንኙነት፤
በሰኔ 2008 ዓ.ም አካባቢ የቤተክርስትያናችን አባላት የሆኑ ጥቂት ግላሰቦች ሲያትል ከተማ ድረስ በመሄድ በሲያትል ገብርኤል ለሚገኙ ብጹዓን አባቶቻችን ለግላቸው ጥቅም (personal favor) የጠየቁት ጥያቄ በአባቶች ተቀባይነት ሳያገኝ ይቀራል። በዚህ የተበሳጩት እነዚህ ግለሰቦች የሲያትል ቅዱስ ገብርኤል አባቶቻችንን ማለትም አቡነ ዜናማርቆስ (ነፍሳቸውን ይማርልን)፣ አቡነ ሉቃስ፣ አቡነ ዮሐንስ እንዲሁም ሌሎች አባቶች፣ መምህራን፣ ዲያቆናትና መዘምራንን ወደ ፖርትላንድ ማርያም እንዳይመጡ ሲያትል ስልክ ደውለው የምንላችሁን ካልሰማችሁ ወደ ቤተክርስትያናችን እንዳትመጡ የሚል መልዕክት ተናገሩ። የሰበካ ጉባኤ ቦርዱም ሆነ የቤተክርስትያናችን አባላት ሳያውቁት አባቶችን ስልክ ደውለው አትምጡብን፣ አትድረሱብን ያሉት እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ድርጊቱን የፈጸሙት በማን አለብኝነት እና በማን አህሎኝነት ትዕቢት ተሞልተው እንጅ ጉዳዩ በህገደንባችን መሠረት ትክክል አለመሆኑን አጥተውት አልነበረም። የግለሰቦቹ እርምጃ ህገደንባችን የጣሰ ቢሆንም ለቤተክርስትያን አባላት ሰላምና አንድነት ሲባል ችግሩን የፈጸሙ ግለሰቦች በጉዳዩ ሳይጠየቁ ወይም ሳይወቀሱ ጉዳዩ በሽፍንፍን ታለፈ። ጉዳዩ በሽፍንፍን መታለፉ ለዛሬው ችግራችን ያበረከተው አስተዋጽኦ ስለመኖሩ አሌ የሚባል አይደለም።
በዚህም ወቅት የቤተክርስትያናችን አገልጋይ ካህን የሆኑት ቀሲስ ኤፍሬም ትላንት ቀሲስ አንዱዓለምን “አባቱን የካደ አረመኔ” እንዳላሉ ሁሉ እርሳቸውም የግል ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው ሲሉ ከኢትዮጵያ ያመጧቸውን አባቶች እነ አቡነ ዜናማርቆስን ወደ ፖርትላንድ ማርያም እንዳይመጡ በመከልከሉ ምክር ተስማምተው እንደነበር ይታወቃል። የቤተክርስትያናችን አባላትም አባቶች ወደ ፖርትላንድ ማርያም እንዳይመጡ መከልከላቸውን እንዲቀበሉ ለማድረግ የአድማ መልእክተኞቻቸውን በየአባላት ቤት እየላኩ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። ቀሲስ ኤፍሬም በዚያ ወቅት አባቶች ወደ ፖርትላንድ እንዳይመጡ ከመስማማት አልፈውም የቤተክርስትያናችን አባላት አባቶችን በጥርጣሬ እንዲመለከቷቸው ለማድረግ በሲያትል አባቶቻችን ላይ የማጥላላት ዘመቻ አካሄደዋል። ለአብነት ያህልም አቡነ ሉቃስ የፖርትላንድን ቤተክርስትያን ጥለህ፣ አባላቱንም በትነህ ወደ እኛ ና ብለውኛል፣ አቡነ ሉቃስ ለቤተክርስትያናችሁ እዳ መክፈያ ገንዘብ እንረዳችኋለን ብለው ቃል ከገቡ በኋላ ቃላቸውን ስላጠፉ የሚታመኑ አይደሉም፣ አቡነ ሉቃስ የፖርትላንድ ማርያምን ህንፃ በእሳቸው ስም እንዲሆን ጠይቀውኛል፣ የህዝቡን ንብረት በራሳቸው ስም ሊያደርጉት ነው፣ አቡነ ሉቃስ እና አባ ገብረስላሴ የኋላሸት የቤተክርስትያናችን አባሎችን በትውልድ ቀያቸው እንዲሁም በዘር ሐረጋቸው ተሳድበዋል… ወዘተ በማለት በተለይ በአቡነ ሉቃስ እና አባ ገብረስላሴ የኋላሸት ላይ አባላትን የማነሳሳት እና የማጥላላት ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። ሌላው ቀርቶ በቤተክርስትያናችን አባላት ክስ እስከቀረበባቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አቡነ ሉቃስ እና አባ ገብረስላሴ የኋላሸት ወደ ቤተክርስትያናችን እንዲመጡ እንደማይፈልጉ ይታወቃል። ቀሲስ ኤፍሬም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ማለትም አዲስ አበባ ለሚያሰሩት የ 1.5 ሚልዮን ብር መኖሪያ ቤት ቦታ የገዙላቸውንና ሌሎች የገንዘብ እርዳታና ብድር የሚሰጧችውን ግላሰቦች ለማስደሰት ሲሉ እርሳቸውን ወደ አሜርካ ያስመጧቸውን አባቶቻችን ክደው እንደቆዩ እንኳን ፖርትላንድ ያለነው አባላት ሲያትል ያሉት አባቶችም የሚያውቁት እውነታ ነው።
ከመዘምራን ጋር ያላቸው ግንኙነት፤
የቤተክርስትያናችን መሪ ካህን የሰንበት ት/ቤትን (መዘምራንን) ማደራጀት፣ ማሰልጠን፣ መምራትና መቆጣጠር እንደሚገባቸው በቤተክርስትያናችን ህገ-ደንብ በግልጽ ተቀምጧል። በዚህም መሰረት መዘምራንን መዝሙር ማስጠናት፣ መንፈሳዊ ስነ-ምግባር (ግብረገብነት) ማስተማር፣ ወጣቶች የቤተክርስትያን ፍቅር እንዲያድርባቸው ማበረታታት፣ በፍቅርና በመቻቻል እንዲኖሩ አርዓያ መሆን፣ ካጠፉም በጥፋታቸው እንደወጡ እንዲቀሩ ሳይሆን እንዲመለሱ መምከር እና መውቀስ…ወዘተ ከቀሲስ የሚጠበቅባቸው የክህነት ኃላፊነት ነበር። ይሁንና በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ቀሲስ ኤፍሬም መዘምራንን በማበረታታት ፈንታ በጉባኤ ፊት ሲነቅፏቸው ይታያል።
* ቀሲስ ኤፍሬም መዘምራንን አንድ ቀን መዝሙር አስጠንተው አያውቁም። እለተ-ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ መዘምራንን የሳምንቱን መዝሙር ሊያስጠኑ ይቅርና አንዳንድ ጊዜ ከደጀ ሰላም በኋላ ስብሐት እንኳን ሳይሉ ምዕመናንን ጥለው ወደ የአየር ማረፊያ የግል “ሥራቸው” ይሄዳሉ። ሌላው ቀርቶ የሰኔ ማርያም በዓላችንን ለማክበር ከሲያትል ገብርኤል እና ከቫንኮበር-ካናዳ ማርያም ቤተክርስትያናት ለበዓል የመጡ ብጹዓን አባቶች እና ምእመናን ወደየመጡበት አገር ሳይመለሱ እርሳቸው እንግዶቻችን ጥለው ወደ “ሥራቸው” ቀድመው ይሄዳሉ። ምእመናን ከሥራቸው ፈቃድ ጠይቀው ለአመታዊ በዓላችን ሲገኙ ታቦት ተሸክመው ያረፈዱት ቀሲስ ኤፍሬም ግን ታቦቱም ሳይከብዳቸው አባላትና እንግዶችን ሜዳ ላይ ጥለው ወደ ግል “ሥራቸው” ይሄዳሉ። አባቶቸንና እንግዶች ምእመናንን ጥለው ወደ ግል ስራቸው የሚሄዱት ምን አልባት እርሳቸው በስብከታቸው ደጋግመው እንደነገሩን ወደ አሜርካ የመጡት ለገንዘብ ስለሆነ ይሆናል።በጣም ያሳዝናል። የገንዘብ መውደድ ነገር ከተነሳ ከዚህ በፊትም በከተማችን አቶ ሽመልስ የሚባል ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ከዚህ ዓለም በድንገተኛ ሞት በተለየ ጊዜ “ሥራ ሰዓት ደርሶብኛል” በማለት ፀሎተ-ፍትሐቱን አቋርጠው መሄዳቸው ስንቱን እንዳሳዘነ የከተማችን ነዋሪ ሁሉ የሚያውቀው አሳዛኝ እውነታ ነው። ለቀብር ሥነ-ሥርዓት የተሰባሰበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሥራ-ፈት ሆኖ አልነበርም። እርሳቸው ግን 50 ዶላር የማይሞላ ገንዘብ ለማግኘት ብለው ፀሎተ-ፍትሐቱን አቋርጠው ሄዱ። በመሆኑም እንደርሳቸው ሌላ ስራ አለብኝ፣ አይመቸኝም፣ ጊዜ የለኝም…ወዘተ ምክንያት ሳይደረድሩ ከትምህርትና ከስራ ጋር በሌለ ጊዜያቸው ወጣቶች ተለማምደው ያቀረቡትን መዝሙር በማያንጽ መልኩ በጉባኤ ፊት መንቀፉ በይዘቱ አስተማሪ ሊሆን አይችልም።
* በሌሎች የኢትዮጵያውያን አብያተ-ክርስትያናት እንዳየነው የእናቶች፣ የወጣቶች፣ የታዳጊ ወጣቶች …ወዘተ መዘምራን ተደራጅተው አገልግሎት እያቀረቡ ይገኛል። በቤተክርስትያናችን ግን በስብከተ ወንጌል ጊዜ በጉባኤ ፊት ቀሲስ ኤፍሬም እድሜው 17 ዓመት ያለፈ ሰው መዘመር አይገባውም በማለታቸው የተነሳ በመዝሙር አገልግሎት እየተሳተፉ የነበሩ በርካታ ምዕመናን ሞራላቸው ተጎድቶ ከመዘምራን አገልግሎት እራሳቸውን እንዲያገሉ ተደርገዋል።
* ቀሲስ ኤፍሬም አዲስ አበባ ለሚያሰሩት ቤት ማሟያ ከብዙ ምእመናን ገንዘብ ይጠይቁ ነበር። በዚሁ ወቅት 1000 ዶላር በስጦታ የሰጠቻቸውን አባል ለማስደሰት ሲሉ ብቻ አራት የመዘምራን አባላትን ያለጥፋታቸው ከመዘምራን አባርረዋል። በወቅቱ የተለያዩ ስዎች ለምን መዘምራንን እንዳባረሩ ሲጥይቋቸውም የልጆቹን ስብዕና የሚነካ የፈጠራ ክስ (በባለ ትዳሮችም ላይ ሳይቀር) አቅርበው ነበር። ከዚሁም ጋር በተያያዘም ከሲያትል ገብርኤል እየመጡ የሚያገለግሉን ዲያቆናት እና መዘምራን አገልግሎታቸው የተቋረጠበት ሁኔታ ተፈጥሮአል። በቀሲስ የቀረበው ክስ ገንዘብ የሰጣቸውን ሰው ለማስደሰት የተካሄደ የፈጠራ ክስ ስለመሆኑ ብዙዎች አባላት ያውቁታል። ከተባረሩት አራት የመዘምራን አባላት ውስጥ አንዷ ወደ ሌላ ክፈለ-ግዛት (State ) የሄደች ሲሆን ሌላዋ ደግሞ ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከቤተክርስትያን እርቃ እንደቆየች ይታወቃል። ዛሬም ድረስ ከመዘምራን አባልነት እንደወጣች ትገኛለች። የመዘምራን አባላት መንፈሳዊ ሥነ-ምግባር አጓድለው ከተገኙና በምክር ሊስተካከሉ ካልቻሉ ከአገልግሎት ሊታገዱ ይችላሉ። በቀሲስ ኤፍሬም የተፈፀመው ግን ከዚህ በጣም የራቀ ነበር። ገንዘብ የሰጣቸውን ሰው ለማስደሰት ሲሉ ቤተክርስትያንን የሚያገለግሉ ወጣቶችን ስም አጥፍተው አባረሯቸው። ይህ በራሱ ለቤተክርስትያናችን የአባላት ቁጥር መቀነስ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሕገ-ደንብን አለማክበር፤
በቤተክርስትያናችን–የፖርትላንድ ማርያም ቤተክርስትያን– የመተዳደሪያ ሕገ-ደንብ መሠረት ካህናት የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርድ አባል መሆን እንደማይችሉ በግልጽ ተደንግጓል። ከዚህ በፊት በቀሲስ አንዱዓለም መሪ ካህንነት ጊዜ ለነበረው ችግር አንዱ አካል መሪው ካህን የሰበካ ጉባኤው አስተዳደር ቦርድ ሊቀመንበር ሊሆን ይገባዋል የሚለው አመለካከት ነበር። ይህ ጉዳይ ከብዙ ውይይት በኋላ የቤተክርስትያናችን ሕገ-ደንብ በአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ሲጸድቅ ካህናት የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርድ አባል መሆን እንደማችሉ ተወስኗል። ይህን ደግሞ ቀሲስ ኤፍሬም ጠንቅቀው የሚያውቁት ብቻ ሳይሆን በሕገ-ደንቡ መሠረት ቀሲስ አንዱዓለም ከቦርድ አመራር አባልነታቸው እንዲወርዱ በተወሰነ ጊዜ አብረው የተስማሙበት ጉዳይ እንደሆነ ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው። ቀሲስ አንዱዓለም ከቦርድ አባልነታቸው ሲወርዱ “የቀኖና ጥሰት ነው” የሚል ድምፅ ያላሰሙት ቀሲስ ኤፍሬም ዛሬ የቀደመ ሀሳባቸውን ምን ወይም ማን እንዳስቀየራቸው በትክክል ባይታወቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እርሳቸው “በካህንነቴ የሰበካ ጉባኤው ሊቀመንበር መሆን አለብኝ” በማለት በአደባባይ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው። ይህን የሚያደርጉት በሕገ-ደንቡ መሰረት የቦርድ አባልነት እንደማይፈቀድላቸው ሳያውቁት ቀርተው አይደለም።
በተመሳሳይ ሁኔታም ቀሲስ ኤፍሬም የቤተክርስትያናችን ተቀጣሪ መሆናቸውን ዘንግተው እርሳቸውን በማይመለከታቸው የቤተክርስትያናችን የውስጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባታቸው አልቀረም። ለምሳሌ ያህልም ቦርዱ ያልመከረበትንና የማያውቀውን ጉዳይ ከሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርዱ እውቅናና ይሁንታ ውጭ ለምእመናን ያቀርባሉ።
* በአንድ ወቅት ለቤተ-ክርስትያን ትልቅ የብር መስቀል ያስፈልገኛል በማለት ለመስቀል መግዣ 6000 ዶላር አዋጡ በማለታቸው የቤተክርስትያን አባላትም ማዋጣት ጀምረው ነበር። መስቀል ለመግዛት ማሰባቸው ምንም ክፋት የለውም። ነገር ግን ገንዘብ የማሰባሰቡ ሥራ አስተዳደራዊ እንደመሆኑ መጠን የመስቀል ግዢ ጥያቄያቸውን ለቦርዱ አቅርበው በቦርዱ በኩል መሰራት ሲገባው ቀሲስ ኤፍሬም እራሳቸው ጥያቄ አቅራቢ፣ እራሳቸው ውሳኔ ሰጪ፣ እራሳቸው በጀት መዳቢ፣ እራሳቸው ገንዘብ ሰብሳቢ፣እራሳቸው ሻጭ አፈላላጊ፣ እራሳቸው ግዥ ፈፃሚ…ወዘተ መሆን መፈለጋቸው ጉዳዩ ምን ያህል ያስተዳደር ግድፈት እንዳለው ያሳያል። ከዚያም በላይ ጉዳዩ ከአስተዳደር ጣልቃ-ገብነት ባለፈ የህዝቡን (የአባላትን) ገንዘብ ለግል መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎት የለም ለማለት አያስደፍርም።
* በሌላ በኩል ደግሞ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርዱ መክሮና ዘክሮ የወሰነውን አስተዳደራዊ ጉዳይ ውሳኔዎች ለምዕመናን ሲያቀርብ ቀሲስ ኤፍሬም የቦርዱንም ሆነ የማስታወቂያ አቅራቢ ግለሰቦችን መብትና ክብር በሚነካ፣ ከካህን በማይጠበቅና ለምዕመናንም መጥፎ መልዕክት በሚያስተላልፍ መልኩ ስድብ ቀረሽ ውርጅብኝ በቤተመቅደስ ይናገራሉ። አባላት የመረጧቸውን የአስተዳደር ቦርድ አባላት ያቃልላሉ። ከአቶ ለማ ጉልቴ–የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርድ ሊቀመንበር–ጋር በአንድ ወቅት ከቅዳሴ በኋላ ያደረጉት እሰጥ አገባም የዚሁ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።
በመሆኑም ቀሲስ ኤፍሬም በአንድ በኩል መተዳደሪያ ደንቡ የሰጣቸውን ኃላፊነትና የጣለባቸውን ግዴታ አይወጡም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ደንቡ ያልሰጣቸውን መብትንስ ስልጣን ይገባኛል ይላሉ። እርሳቸው ደንቡን የሚቀበሉት የግል ጥቅማቸውን የሚደግፍ ሆኖ ሲያገኙት ብቻ ነው። ይህ እንግዲህ እርስ በእርሱ ያለውን ሕገ-ደንባዊ ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስትያናችን ሕገ-ደንብም ያላቸውን ግድየለሽነት እና የኃላፊነት መጓደልንም ያሳያል።
ከቤተክርስትያናችን አባላት ጋር ያላቸው ግንኙነት፤
የቀሲስ ኤፍሬም ሌላው ዋናው እና መሠረታዊው ድክመት የቤተክርስትያናችን አባላትን በእኩልነት ያለመመልከት ችግር ነው። ይህም ሲባል ሀብታምና ድሃ፣ የራሱ ቤት ያለው እና በመንግስት ቤት የሚኖር፣ የዚህ ብሄረሰብና የዚያ ብሄረሰብ ተወላጅ፣ የዚህ ክ/ሀገር አውራጃ ጎጥ እና የዚያ ክ/ሀገር አውራጃ ጎጥ፣ ገንዘብ የሚሰጥና ገንዘብ የማይሰጥ፣ እነርሱ እና እኛ…ወዘተ በማለት የአንዲት ቤተክርስትያን አባላት የሆነውን ኢትዮጵያውያን የመለያየት እና እርስ በእርስ የማነካከስ ችግር ነው። ቀሲስ ኤፍሬም የእግዚአብሔርን አገልግሎት ሳይቀር መድሎ ይፈጽሙበታል። እርሳቸው የኔ ናቸው ለሚሏቸው ሰዎች በየወሩ ሳይሆን በየቀኑ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ፀበል ይረጫሉ፤ የኔ አይደሉም፣ ጥቅም አላገኝባቸውም ለሚሏቸው አባላት ከሆነ ግን ለክርስትና፣ ለሰርግ፣ ለልደት፣ ለጸበል ፃዲቅ… ወዘተ እንዲባርኩ ቢጠሩ እንኳን “ሥራ” አለብኝ በማለት አይሄዱም። የተጣላ አይስታርቁም፤ የታመመ አይጠይቁም። የማይፈልጉት ሰው ሲሆን በቀብር ስነ-ስርዓት ላይ እንኳን ሳይቀር የሥራ ሰዓት ደረሰብኝ ብለው ጸሎተ-ፍትሐቱን አቋርጠው መሄዳቸውን ልብ ይሏል።
በተጨማሪም ቀሲስ ኤፍሬም በተለያዩ ሁኔታዎች ለእርሳቸው ቁሳዊ ጥቅም የሚሰጡ አባላትን ለማስደሰት ሲሉ ብቻ ከካህን በማይጠበቅና በሚያሳዝን ሁኔታ በሌሎች የቤተክርስትያናችን አባላት ላይ የማጥላላት፣ የመሳደብ፣ የስም ማጥፋት…ወዘተ ዘመቻ ያካሂዳሉ። ሌላው ቀርቶ የስብከት ጊዜውን እንኳን ሳይቀር “የእኔ ሰዎች አይደሉም” የሚሏቸውን በአሽሙር ለመሳደብ ይጠቀሙበታል። ከዚህም በላይ የሚከፋው ደግሞ “የእኔ ሰዎች አይደሉም” የሚሏቸውን አባላት ለንስሐ የተናገሩትን ኑዛዜ ሳይቀር ለሌላ ሰው ያወሩባቸዋል። ይህ ድርጊታቸው የክህነት ግዴታ ሞራልና ሀላፊነታቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተክርስትያናችንን ሕገ-ድንብና የአባላትን መብት መተላለፋቸውንም ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ ቀሲስ ኤፍሬም የክህነት ግዴታቸው የሚጥልባቸውን በጥቅም ሳይደለሉና ድሃና ሀብታም ሳይለዩ ለሁሉም በእኩልነት የማገልገል መንፈሳዊ ሀላሃፊነቸውን ዘንግተዋል። ይባስ ብለውም የእርሳቸውን ደመወዝ ለመክፈል የሚያስችል ወርሃዊ ክፍያ የሚያዋጡትን የቤተክርስትያናችን አባላት ተሳድበዋል። በሀብት መጠን፣ በተወለዱበት ቦታ፣ እንዲሁም በዘር (ብሄረስብ) ምክንያት መለያየት፣ አድሎ መፈፀም ወይም ማጥላላት ምንጊዜም የሚያጸይፍ እድፍ ሲሆን ጉዳዩ በቤተክርስትያን ውስጥ እና በካህናት ሲፈፀም ደግሞ ጉዳቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።
ችግሩን የመፍታት ሙከራና ሂድቱ፤
ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ የቤተክርስትያናችን አባላት በግልና በጋራ በመሆን ቀሲስ ኤፍሬም ችግሮችን እንዲያስተካክሉ በተለያዩ ጊዜያት አነጋግረዋቸል፤ ምክርም ለግሰዋቸውል። ይሁንና ቀሲስ ኤፍሬም የመሻሻል ሁኔታ ሊያሳዩ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የቤተክርስትያን አባላት አንዳንዶቹ እራሳቸውን ከአባልነት ማግለል በመጀመራቸው የአባላት ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየሳሳ መሄድ ጀመረ። ይህ ጉዳይ እና የቤተክርስትያናችን የወደፊት እጣ ፈንታ ያሳሰባቸው የተወሰኑ አባላት ችግሩ እንዲፈታ በጋራ በመፈራረም ለሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርዱ በጽሑፍ ጥያቄ አቀረቡ። የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርዱም በቀረበው ጥያቄ ላይ ውይይት ካካሄደ በኋላ ችግሩን የሚያጠናና የመፍትሔ ሀሳብ የሚያፈላልግ ሰባት አባላት ያሉት የአማካሪ ኮሚቴ አቋቋመ።
እነዚህ የአማካሪ ኮሚቴ አባላት አብዛኛዎቹ የቤተክርስትያን መስራች አባላት ሲሆኑ ሁሉም በቤተክርስትያናችን አባላት ተቀባይነትና ተሰሚነት ያላቸው፣ በእድሜም ሆነ በሥራ ተመክሮ የዳበረ ልምድ ያላቸው፣ ጉዳዩን በእርጋታ እና በገለልተኛነት ማየት የሚችሉ የቤተክርስትያናችን አንጋፋ አባላት ናቸው። የአማካሪው ኮሚቴ አባላት ጉዳዩን ለወራት ከመረመሩና ካጠኑ በኋላ (ቀሲስ ኤፍሬምንም አነጋግረዋል) የቤተክርስትያናችንን ሰላምና የአባላትንም አንድነት ለመጠበቅ ያስችላል ያሉትን የመፍትሔ ሀሳብ ለሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርዱ አቅርበዋል። ከቀረቡት የመፍትሄ ሀሳቦች ውስጥም የሚከተሉት ይገኙበታል።
* ሲያትል ቅዱስ ገብርኤል የሚገኙት ብጽአን አባቶቻችን ቀሲስ ኤፍሬምን ከፖርትላንድ ማርያም እንዲያነሷቸውና በምትካቸውም ሌላ አገልጋይ እንዲልኩልን፣
* ለጊዜው ምትክ የሚሆን ሌላ ካህን የማይገኝ ቢሆን እንኳን ሌላ ካህን እስከሚገኝልን ድረስ አባቶች እየተመላለሱ እንዲያገለግሉን እና ይህንም ሁኔታ በሰላም ለመጨረስ ቦርዱ ከአባቶች ጋር እንዲነጋገር፣
የአማካሪ ኮሚቴው አባላት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በቀላሉ እንዳልሆነ መገመት አያስቸግርም። ጊዜ ወስደው ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ ግን ቀሲስ ኤፍሬም መምህር ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ የቤተክርስትያናችንን ሰላምና የአባላትንም አንድነት ለመጠበቅ እንደማይቻል የጋራ ግንዛቤ ላይ ደርሰዋል።
ይህ በአማካሪ ኮሚቴው ተጠንቶ የመጣውን የውሳኔ ሀሳብ የሰበካ ጉባኤ ቦርድ አባላት ከተወያዩበት በኋላ በህገ-ደንባችን መሰረት ጉዳዩ ለአባላት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲቀርብ በብዙሃን ድምፅ ወስነዋል። ነገር ግን ቤተክርስትያናችን በስደት ላይ የሚገኘውን ሕጋዊ ሲኖዶስ የምትቀበል እንደመሆኗ መጠን የመፍትሔ አሰጣጡ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን በማሰብ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ከመጠራቱ በፊት በቅርብ የሚገኙትንና ካህን የሚሰጡንን የሲያትል ገብርኤል አባቶቻችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል። በዚህ አጋጣሚ ዘግይተውም ቢሆን ችግሩን ለማየት በአካል ፖርትላንድ ድረስ የመጡትን አቡነ ዮሐንስን እና አባ ገብረሥላሴ ጥበቡን ልናመሰግናቸው እንወዳለን። እነዚሁ ሁለቱ አባቶች የችግሩን መነሻ ሁኔታና የመፍትሄ አፈላለግ ሂደቱን በተመለከተ ከአስተዳደር ቦርድ አባላት ጋር ለአራት ሰዓታት፣ ከቦርድ አማካሪ ኮሚቴው ጋር ለአራት ሰዓታት በጠቅላላው ለስምንት ሰዓታት ያህል ውይይት አካሄድዋል። ስለጊዜያቸው እጅግ አድርገን እናመሰግናቸዋለን። በውይይቱ መጨረሻም ሁለቱ አባቶች ጉዳዩን ሲያትል ካሉት ሌሎች አባቶች ጋር መክረው መልስ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ወደ ሲያትል ተመለሱ። በመቀጥልም በሳምንቱ አቡነ ዮሐንስ በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ አባ ገብረሥላሴ ጥበቡ በተናጠል ተመላልሰዋል። ችግሩ ግን ተባባሰ እንጅ መፍትሔ አላገኘም።
ችግሩ ስለተባባሰበት ምክንያት ግልፅ ግልፁን፤
ሁለቱ አባቶቻችን ችግሩን ለመፍታት የተከተሉት አካሄድ ለመፍትሔ ማጣቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ አላደረገም ማለት አይቻልም። በአንድ በኩል ስለጉዳዩ ገና ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸውን ቢገልጹም ከቅዳሴ በኋላ ለህዝቡ ካስተላለፉት ትምህርት መረዳት እንደሚቻለው ቀሲስ ኤፍሬም በምንም ሁኔታ ቢሆን ከፖርትላንድ እንዳይነሱ መወሰናቸውን መረዳት ይቻላል። ይህም የነበረውን ችግር በሁለት መንገድ አባብሶታል። አንደኛው ለቀሲስ ኤፍሬም አባቶች ከእኔ ጋር ከሆኑ ማንም ምንም ሊያደርገኝ አይችልም የሚል የተሳሳተ መልእክት ያስተላልፋል። ቀሲስ ኤፍሬምም ከአባቶች ደርሶ መመለስ በኋላ “ማንም አይነካኝም!!!” በማለታቸው ግምታችን ከእውነት እንዳልራቀ ወዲያውኑ አይተነዋል። ሁለተኛው ደግሞ የአስተዳደር ቦርዱ እና የአማካሪ ኮሚቴው አባላትን ችግሩን ለመፍታት ብቁ አይደሉም እንዲሁም በየሰንበቱ በቀሲስ ኤፍሬም ስንቆስል ለኖርነው ምእመናን ቁስላችሁ አይሰማንም የሚል መልእክት ስለሚያስተላልፍ ነው። አባቶች ከተናገሩት ውስጥ በአስረጅነት አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት።
* “ሕገ-ደንብ አያስፈልግም። የክርስትያን መመርያው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።” (አቡነ ዮሐንስ ከተናገሩት) እርግጥ ነው አባታችን እንዳሉት የክርስትያን መመሪያ ከሆኑት ውስጥ አንዱና ዋነኛው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ብቸኛው መመሪያ እንዳልሆነ ግን እርሳችውም እንደማያጡት ይገባናል። ለመሆኑ በዚህ ዘመን ያውም በምድረ-አሜርካ ያለ ህገደንብ የሚተዳደር ቤተክርስትያን አለ ወይ? ህጋዊውን ሲኖዶስ እንደምንቀበል እውቅና የሚሰጥውም እኮ ህገደንባችን ነው። ህገደንባችን ባይኖር እኮ የአባ ጳውሎስ እንሁን ያሉትን ቄስ ማስወገድ አይቻልም ነበር። በህገደንባችን መሰረት ካህን በአባላት ውሳኔ ሊባረር ስለሚችል እና የቀሲስ ኤፍሬም እጣ ፈንታም ወደዚያ ሊያመራ ስለሚችል እርሳችውን ለመጠበቅ ሲባል የተናገሩት አያስመስልባቸውም እንዴ? ህዝቡንስ ማን ይጠብቀው? እኛስ ስለህገደንባችንም እግዚአብሔርን እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
* “ኮሚቴው ቀሲስ ኤፍሬምን የጠየቃቸውን ጥያቄዎች አይተናል። አብዛኛው የሚያስቅ ተራ ጥያቄ ሆኖ አግኝተነዋል።” (አባ ገብረሥላሴ ጥበቡ ከተናገሩት) አባ ተራ ያሏችው ጥያቄዎች የትኞቹ ይሆኑ? ቀሲስ በዘርና በጎጥ አባላትን ይከፋፍላሉ የተባለው ይሆን? ከጥቅመኞቻቸው ጋር ሆነው አባቶች እንዳይመጡ ማስከልከላቸው ይሆን? በአቡነ ሉቃስ እና በአባ ገብረሥላሴ የኋላእሸት ላይ በተለይ ያካሄዱት የማጥላላት ዘመቻ ይሆን? ገንዘብ የሰጣቸውን ሰው ለማስደሰት መዘምራንን ማባረራችው ይሆን? ወይስ ደግሞ ለንስሐ የተነገራቸውን በወንፊት መዝራታቸው ነው? አባ ተራ ያሉት ጥያቄ የቱ እንደሆን አልገባንም። ያም ቢሆን እኮ ችግሩን ለመፍታት ለወራት የለፉትን የኮሚቴው አባላት ዋጋቢስ ለማድረግ እንደመሞከር አይመስልባቸውም ወይ? ቀሲስ ኤፍሬምን ለመደገፍ ሲባል ብቻ ካልሆነ የኮሚቴን ሥራ “የሚያስቅ” ብሎ ማቃለሉ በእውነት መፍትሄ ይሆናል ብለው ይሆን?
* “ቀሲስ ኤፍሬም ወርቅ ናቸው፤ ከወርቅም ይበልጥ እንቁ ናቸው።” (አቡነ ዮሐንስ ከተናገሩት) በአባታችን ችግራችን ባላገናዘበና ስሜታችን ባልጠበቀ ንግግር በጣም አዘን። በተለይም ይህ አባባላቸው አባታችን የእኛን የልጆቻቸውን ለቅሶ በልቦናቸው ይቅርና በጀሮአቸው ሊያዳምጡ እንዳልፈቀዱ ያሳያል። ይህ እውነት በሁለት በኩል በሰላ ቢላዋ ልብን ከመውጋት አይተናነስም። የብሩኩ አባታችን አቡነ ዜናማርቆስን ሞት ጉዳት ዳግም አየነው።
በንግግራቸው ግድየለሽነት (insensitivity ) ልባችን ቆሰለ። ቀሲስ ኤፍሬም እንቁ አለመሆናቸውን ለእኛ ለፖርትላንድ ምእመናን ነጋሪ የሚያስፈልገን አይደለንም። ቀሲስ ኤፍሬም በግድ እንቁ ናቸው ከተባለም የእኛ ጥያቄ እንቁው በርቶ የሚታይበት ሌላ ቦታ ይፈለግላቸው ነው። በስደት ከሚገኘው ሕጋዊ ሲኖዶስ ጋር ያለን ግንኙነት ቀሲስ ኤፍሬምን በመቀበል ባለመቀበል መለካት የለበትም። አይኖርበትምም። ቀሲስ ኤፍሬም ሄዱም ቀሩም ከሕጋዊው ሲኖዶስ የሚለየን የለም።
ቀሲስ ኤፍሬም ከፋፋይ፣ ፍቅረ-ነዋይ የሚያጠቃቸው ሰው ብቻ ሳይሆኑ ምእመናን ለንስሃ የነገሯቸውን ኑዛዜ ለሌላ ሰው የሚያወሩ ሰው እንደሆኑ ከላይ ተገልጿል። አባ ገብረሥላሴ ጥበቡ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቅዳሴ በኋላ ሲያስተምሩ “ዛሬ ፖርትላንድ ሪከርድ ልትበጥሱ ነበር። አንድ ሰው ብቻ ነው የቆረበው። ሌሎቻችሁም መቁረብ አለባችሁ” ብለው ነበር። በእርግጥ አባ ትክክል ናቸው ነገር ግን እንደሚታወቀው ለመቁረብ ንስሐ ያስፈልጋል። ታድያ ንስሐችን በወንፊት እየተዘራ ለማን ንስሐ እንናገርና እንቁረብ? እንዲህ አይነቱን “ካህን” ክህነቱን መያዝ ሲገባ ይባስ ብሎ “እንቁ” ነው እያሉ ማሞካሸትና መወድስ መደርደርን ምን አመጣው? እኛስ ብንሆን ልጆቻችሁ አይደለንም እንዴ? ልባችን ደማ። አድምጠን ዝም ማለታችን ለአባቶቻችን ባለን ክብር እንጅ ስለቀሲስ የሚሰበከው ውዳሴ ሳያሳዝነንን ቀርቶ አይደለም።
የአባቶች ምላሽ እንዴትነት እና መላምቱ፤
ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸው ቀሲስ ኤፍሬም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ አቡነ ዜናማርቆስ (በአጸደ ሥጋ በነበሩ ጊዜ) እና ሌሎችም አባቶች ወደ ፖርትላንድ እንዳይመጡ በመከልከሉ ምክር ተሳትፈዋል፣ አባላትን ይከፋፍላሉ፣ ይለያያሉ፣ ያዳላሉ፣ በገንዘብ በጎጥ… ወዘተ ይከፋፍላሉ፣ የምእመናንን የንስሃ ሚስጥር ለሌላ ሰው ያወራሉ፣ ሕገ-ደንባችን አያከብሩም… ወዘተ። ታዲያ አባቶቻችን ይህን እየሰሙና እያወቁ ለምን ቀሲስ ኤፍሬም እንቁ ናቸው ወደሚለው ሀሳብ ሄዱ የሚል ጥያቄ ማንሳታችን አልቀረም። በዚህ በኩል ሁለት መላምት ማቅረብ ይቻላል።
* አንደኛው እዚሁ ከተማችን ውስጥ የሚገኙ ከቀሲስ ኤፍሬም ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦች ለአባቶች የፈጠራ አሉቧልታ ነግረዋቸው ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ከቀሲስ ኤፍሬም ጋር በጥቅም የተሳሰሩ፣ ከዚህ በፊት እነአቡነ ዜናማርቆስን ወደ ፖርትላንድ እንዳይመጡ በመከልከሉ አድማ የተስማሙ፣ ለቀሲስ ኤፍሬም አዲስአበባ ላይ የመኖሪያ ቤት ቦታ የገዙላቸው፣ የገንዘብ እርዳታ የሚያደርጉላቸው እናም በዚሁ ውለታቸው ቀሲስ ኤፍሬምን የግል መጠቀሚያቸው ያደረጉ ጥቂት አባላት መኖራቸው አልቀረም። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ለአባቶቻችን የተሳሳተ መረጃ ነግረዋቸው ሊሆን ይችላል። ይህን ጥርጣሬያችን የበለጠ ያጎላው ደግሞ አቡነ ዮሐንስና አባ ገብረሥላሴ ጥበቡ ወደ ፖርትላንድ በጋራ በመጡ ጊዜ ቀሲስ ኤፍሬምን አባራችሁ በምትካቸው ከዚህ በፊት ከቤተክርስትያናችሁ ተባረው የቆዩትን “ቀሲስ ታፈሰን ለመመለስ አስባችኋል”፤ በተጨማሪም ሌላ “አዲስ …. ቄስ አምጥታችኋል” የሚል “መረጃ” እንደደረሳቸው መናገራቸው ነው።
እውነቱ ግን በመግቢያችን ላይ እንደገለጽነው ሁሉ ቀሲስ ታፈሰ ከቤተክርስትያናችን አገልግሎት በአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በ2006 ዓ.ም. ከተባረሩ በኋላ በከተማችን ውስጥ መድኃኒዓለም የሚባል አዲስ ቤተክርስትያን መስርተው በአባ ጳውሎስ ሥም እየተዳደሩ ይገኛሉ። የእኛ ቤተክርስትያን በአቡነ መርቆርዮስ በሚመራው ሕጋዊ ሲኖዶስ ስር እንደመሆኗ መጠን ቀሲስ ታፈሰ እንዴት ተደርጎ ይመለሳሉ እንደተባለ አልገባንም። ህገደንባችንም አይፈቅድም። “አዲስ …. ቄስ” ስለተባሉትም አዲስ የመጡ እንግዳ የቤተክርስትያናችን አባላት የምናውቀው ምንም ነገር የለም። ምክንያቱም በቤተክርስትያናችን ውስጥ ሲቀድሱ አላየናቸውምና ነው። ካህን ናቸው፣ ተዋወቋቸው በማለት ለህዝቡ የገለጹትም እራሳቸው ቀሲስ ኤፍሬም ናቸው። አባላት እንግዳውን ቄስ መሆናቸውን ያወቅነውም ከዚያ በኋላ ነው። አባቶቻችን የተሰጣቸው “መረጃ” ስህተት መሆኑን ሲያረጋግጡ መረጃ ያቀረቡላቸውን ግለሰቦች ፍላጎትና ዓላማ ቆም ብለው ሊመረምሩ በተገባ ነበር። ነገር ግን “ቀሲስ ኤፍሬም እንቁ ናቸው” በሚለው ጸኑ።
* ሁለተኛው ደግሞ ስዊድን አገር የሚኖሩት የቀሲስ ኤፍሬም የኋላሸት ወንድም ቀሲስ ጌጡ የኋላሸት በስዊድኑ ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ኤልያስ በኩል ቀሲስ ኤፍሬም ከፖርትላንድ እንዳይነሱ አሜርካ ለሚኖሩት ሊቃነ-ጳጳሳት ተማጽኖ አቅርበዋል ይባላል። በርቀት እንደሰማነው ከሆነ አቡነ ኤልያስም ሆኑ ቀሲስ ጌጡ ከኢትዮጵያ እስከ ጅቡቲ፣ ከጅቡቲ እስከ አውሮፓ እንዲሁም ከዚያ ባሻገር ለእውነት ስለእውነት በእውነት የቆሙ ሰዎች ናቸው። ምናልባትም አቡነ ኤልያስና ቀሲስ ጌጡ እዚህ በቅርቡ ሆነው ችግራችን ቢመለከቱ ኖሮ ባልፈረዱብንም ነበር። ሰምተውም ባዘኑልን፤ አይተውም በራሩልን። ቀሲስ ኤፍሬምን ባሉበት እንዲኖሩ እርዷቸው የሚል ምልጃ ለአባቶች ማቅረባቸውም የእኛን የልጆቻቸውን መበደል በቅርበት ሆነው ስላላዩት ይሆናል። ይህን ማመልከቻችን ካገኙ በኋላ ግን እንደማጨክኑብን ተስፋ እናደርጋለን።
ስለወደፊቱ ሁኔታ– እንደማጠቃለያ፤
ከላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደተሞከረው በአሁኑ ወቅት ቤተክርስትያናችን በከባድ ፈተና ላይ ትገኛለች። ይህን ችግር ለመፍታት የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርዱ በቅርብ የሚገኙ አባቶችን የማነጋገር ሙከራ አድርጓል። በዚህም ረገድ ለኦሬገን ጠቅላይ ግዛት የተመደቡት ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ እንዲሁም መምህር አባ ገብረሥላሴ ጥበቡ በጋራ እና በተናጠል ወደ ከተማችን በመጡበት ጊዜ ስለችግሩ ውይይት ለማድረግ ተሞክሯል። ይሁንና ችግሩ ዛሬም ቢሆን መፍትሄ አላገኘም። በመሆኑም የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ቦርድ ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት በቤተክርስትያናችን ሕገ-ድንብ መሰረት የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ለጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠርቷል። ነገር ግን የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ መጠራቱ ሲሰማ አንዳንድ አባቶቻችን “በዚህ ጉዳይ አባላት አያገባቸውም፤ እኛ ነን የምንወስነው።” ማለታቸውን እየሰማንና እያየን ነው። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ ሌላ የበለጠ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በመሆኑም ካለንበት የከፋ ሌላ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ጉዳዩን ለሚመለከተው የበላይ አካል በግልጽ ለማሳወቅ እንደሚገባ በማመን ይህን ግልጽ ደብዳቤ ለመፃፍ ተገደናል።
በቤተክርስትያናችን ሕገ-ደንብ መሰረት የቤተክርስትያናችን የበላይ እና የመጨረሻው የስልጣን አካል የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ነው። የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ በአብላጫ ድምፅ የወሰናቸው ማንኛውም ውሳኔዎች ተግባራዊ ይሆናሉ። የአስተዳደር ቦርዱ በጠቅላላ ጉባኤ የሚወሰኑ ወሳኔዎችን ህገደንባችንና የምንኖርበትን አገር ህግ መሰረት በማድረግ የማስፈፀም መብትና ስልጣን በህገደንቡ ተሰጥቶታል።
የፖርትላንድ ኦሬገን ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን በአቡነ መርቆርዮስ የሚመራውን በስደት የሚገኘውን ህጋዊ ሲኖዶስ ብትቀበልም አስተዳደር ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ የምትመራውና የምትተዳደረው በአባላት ጠቅላላ ጉባኤና በስሩ በሚገኘው የአስተዳደር ቦርድ ነው። ይህንን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ በመተዳደሪያ ደንባችን ውስጥ አንቀጽ 2፣ ንኡስ አንቀጽ 3 ላይ የተደነገገውን እንዳለ እናቅርበው፤
“አስተዳደርና በጀትን በተመለከተ የቅድስት ማርያም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ከማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሐይማኖታዊ ተቋሞች ጋር ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ ግንኙነት የላትም፤ ከማንኛውም ሐይማኖታዊ ተቋም አስተዳደርና ቁጥጥር ነፃ በሆነ መንገድ አስተዳደሯንና በጀቷን የምታስተዳድረውና የምትመራው ይህ የመተዳደሪያ ደንብ በሚያዘው መሠረት ብቻ ነው።”
በመሆኑም ቀሲስ ኤፍሬምን በጀት መድቦ በደመወዝ የሚያስተዳድረው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ እንደመሆኑ መጠን ጉባኤው ካልፈለገ ደግሞ በወሰነ ጊዜ ሊያሰናብታቸው እንደሚችል ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለናል። ቀሲስ ታፈስም ሆነ ቀሲስ አንዱዓለም ከቤተክርስትያናችን አገልግሎት ሲሰናበቱም የተፈፀመው ይሄው ነበር። ዛሬም ከዚያ የተለየ አካሄድ ሊፈጠር አይችልም፤ ምክንያቱም ሕገ-ደንቡ አይፈቅድምና።
እውነታው እና ሕጋዊ አካሄዱ ይሄ ሆኖ ሳለ “የአባላት ጉባኤ ይህን ሊወስን አይችልም፤ ወሳኞቹ እኛ ነን” የሚለው አካሄድ ችግር ፈቺ ሆኖ አላገኘነውም። አንድን ግለሰብ ለመጥቀም ተብሎ የብዙሃን ምእመናንን አቤቱታ ማቃለልም አንድነታችን የሚያጠብቀው አይመስለንም። የምንኖርበት አገር የህግ የበላይነት የሰፈነበት እንደመሆኑ መጠን ሕገ-ድንብ የጣሰ አካሄድ በሕግ ፊት እንደማያዋጣ ሁላችንም አንስተውም። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ችግራችንን በውል ተመልክቶ ችግሩን በሰላም ከመፍታትና አንድነታችን ከመጠበቅ አንፃር ለቀሲስ ኤፍሬም ከተቻለ ሌላ ቦታ እንዲፈልግላቸው ፤ ይህ ካልተቻለ ደግሞ በህገ-ደንባችን መሠረት ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚካሄደው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቤተክርስትያናችን አባላት ችግሩን ለመፍታት ለሚወስዷቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት አስፈላጊው ትብብር እንዳይለየን በታላቅ ትህትናና አክብሮት እንጠይቃለን።
የሠላም ንጉሥ የሆነው እግዚአብሔር ሠላማችን ይጠብቅ፤ አሜን።
ከፖርትላንድ ማርያም ልጆቻችሁ
ለጥያቄ፣ ምክር፣ ተግሳጽ እንዲሁም ለማንኛውም አስተያየት [email protected] መጠቀም ይቻላል።