ፓትርያርኩ ዛሬ በሕግ አፍራሽነት ይጠየቃሉ
- ፓትርያርኩ ‹‹አልመራኹትም›› በሚል ያፈኑት የረዳት ሊቀ ጳጳሱ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና የዋና ሥራ አስኪያጁ ጥያቄ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አቅራቢነት ቋሚ ሲኖዶሱ ዛሬ ይወያይበታል
- ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ ፓትርያርኩ መመሪያቸውን ከቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ሕግና ከሀ/ስብከቱ ዘለቄታዊ ሰላም አንጻር መዝነው የእርምት ማስተካከያ እንዲያደርጉ በድጋሚ አሳስበዋቸዋል
- የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት በወረራ መልክ በመቆጣጠር ስለ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆቹ ምደባ ያብራሩት እነዘካርያስ ሓዲስ፡- ‹‹ወደ ቤታችን ገባን፤ ትክክለኛ ቦታችንን ይዘናል›› እያሉ ነው
- በየአጥቢያው ኑፋቄንና ግብረ ሙስናን ለማጋለጥ የሚደረገውን ጥረት በማስተባበር አስተዋፅኦ ያለውን የሀገረ ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር የማፍረስ ዕቅድ ተይዟል
- ሰንበት ት/ቤቶች፣ አማሳኝ አለቆች እንዲገሠጹ ቅ/ሲኖዶስ ያሳለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲኾን መጠየቃቸውን ተከትሎየአንድነቱ አመራሮች ‹‹ወፍ ዘራሾች›› በሚል በፓትርያርኩ ተዘልፈዋል
- ውዝግቦችን በመፍጠርና በሽፋንነት በመጠቀም ከምዝበራ ተጠያቂነት ራሱን ለማዳን የሚላላጠው ቀንደኛው አማሳኝ ኃይሌ ኣብርሃ፡- ‹‹መንግሥት ሐራ ብሎግን እንዲዘጋልን›› ሲል ጠይቋል
* * *
- ‹‹እርስዎ ሲያጠፉ የሚያርምዎ ይህ ጉባኤ ነው፤… የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነቱ ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ ነው፤ በሥራ አስኪያጁ ሥያሜ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ይኹንታውን ካልሰጠ እንዴት እና ከማን ጋራ ነው ተስማምተው የሚሠሩት?››
/ከትላንት በስቲያው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ‹‹እኔ ያልመራሑበትን አጀንዳ ልትነጋገሩበት አትችሉም›› በሚል ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ እና ከዋና ሥራ አስኪያጁ በተደጋጋሚ የቀረቡላቸውን ማሳሰቢያዎች እና ማስታወሻዎች ላፈኑት ለፓትርያርኩ ከጉባኤው አባላት የተሰነዘረ ምክርና ጥያቄ/
* * *
ኹላችንም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት በየደረጃው ተሰጥቶናል፤ የቆምንለት ዓላማ ለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ታማኝ መኾንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ነው፤ ቅዱስነትዎ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደመኾንዎ መጠን ለሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መከበርና ማስከበር ግንባር ቀደም ሓላፊነት እንዳለብዎ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በቅዱስነትዎ የተላለፈው መመሪያ ተቀራርቦና ተወያይቶ በመተማመን ቤተ ክርስቲያኒቱን የመምራትና የማስተዳደር መንፈስን የሚጋፋ ከመኾኑም በላይ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን አንቀጽ 53/8 እና በሥሩ ያሉትን ንዑሳን አናቅጽ በእጅጉ የሚፃረር ነው፡፡
ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሚመደበው፣ በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመርጦ ሊቀ ጳጳሱም በሕጉ መሠረት የመረጡትን ሥራ አስኪያጅ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በማቅረብ ሲኾን በቀረበው ሥዩም ላይ ፓትርያርኩ ሲስማሙ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ፊርማ ይሾማል፤ ይላል፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን አድሏዊ አሠራር እንዳይኖርና የጋራ ስምምነቱ ለሰላም ያለውን ሚና በመገንዘብና እርስ በርስ ያለውን መዋቅራዊ መከባበር የሚያሳይ ነው፡፡
የተላለፈው መመሪያና ትእዛዙ፡- መሠረታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሕግ፤ የሕግ የበላይነት የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ፤ የሀገረ ስብከቱን፣ የሠራተኞችንና የምእመናንን አንድነትና በመንፈሳዊ ሕይወት ተከባብሮና ተፋቅሮ የመኖር ኹኔታን እንዲኹም ሰላምን የሚሸራርፍ በመኾኑ በአፈጻጸም ለመተግበር በእጅጉ እንቸገራለን፡፡ መመሪያውን ከቤተ ክርስቲያኗ መሠረታዊ ሕግ፣ ከሀገራችን ነባራዊ የሕግ ድንጋጌዎች አንጻርና ከሀገረ ስብከቱ ዘለቄታዊ ሰላምና የልማት አቅጣጫ አኳያ እንዲገመግሙትና የእርምት ማስተካከያ እንዲያደርጉ በድጋሚ አሳስባለኹ፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ‹‹በተሰጠው መመሪያ ላይ ቅዱስነትዎ ከቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ሕግ፣ አሠራርና ሰላም አንጻር ማስተካከያ እንዲደረግበት ማሳሰብን ይመለከታል›› በሚል ለኹለተኛ ጊዜ ለፓትርያርኩ በአድራሻ ከጻፉት ማሳሰቢያ/
Source:: haratewahido
The post ፓትርያርኩ ዛሬ በሕግ አፍራሽነት ይጠየቃሉ appeared first on ሳተናው (Satenaw) -Latest Ethiopian News & Breaking News.