የኤርትራ ነገር፤ የኛ ችግር፤ መርህ አልባ ፍቅር – ተክለሚካኤል አበበ ሳሕለማርያም

1-የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደዋሽንግተን ዲሲ መጥቶ ከኢሳት ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ ተከትሎ፤ በመስከረም 2013 በጻፍኩት ጽሁፍ፡ በቃለምልልሱ ላይ አቶ ይሳያስ አፈወርቂን መስቀልና ማጋነን እንዳልነበረበት ተችቼ የሚከተለውን ጽፌ ነበር፡፡

በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያንን ደም ያፋሰሰ ታሪክ እንዳልተፈጠረ አድርገን መናገር አንችልም። አንክድም። … ስለ ሻእቢያና ኤርትራ ክፉ ሳይወጣን፤ ስለኢሳያስ ቅንነትም ብዙ ሳናጋንን፤ ከኤርትራ ጋር ስለመስራት አስፈላጊነት ልንናነገር እንችላለን። … በዚያ ቃለምልልስ ላይ፤ ከኤርትራ ጋር የመስራትን ሀሳብ ለማሳመን ሲል ብቻ አቶ አንዳርጋቸው አቶ ኢሳያስን ያልሆኑትን አድርጎ ሳላቸው። በዚህ የአንዳርጋቸው ቅብ፤ ራሳቸው አቶ ኢሳያስና ኤርትራዊያን የሚከፉ ይመስለኛል። አፍንጫው ድፍጥ ጥየሆነውን ሰው አፍንጫ ሰልካካ፤ አንገቱና ትከሻው የተጣበቀውን የኔ ቢጤ ጉጣ መለሎ አስመስለው ቢስሉት እንደስድብ ይቆጠራል።

ለፕሮፓጋንዳው፤ የኢቲቪ ግልባጭ፤

2-እነሆ አንዳርጋቸውና ግንቦት ሰባት የቀየሱት በደንብ ያልተተነተነ የስህተት ፕሮፓጋንዳ ገፍቶ፤ ያንን መንገድ ሲጠራጠሩ የነበሩት ሁሉ የዚያ ወንጌል ሰባኪ ሆነው ከች ብለዋል፡፡ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ግንቦት ሰባትንና “ይሄንን ኤርትራ ወይም ሞት” ፕሮፓጋንዳ ስናማ እንደተስማማነው፤ ኢሳት ኤርትራ መሄዱ ተገቢ ቢሆንም፤ ከኤርትራ መልስ የሚሰማው ፕሮፓጋንዳ ግን፤ ልክ ኢትዮጵያ ሄደው የሚመጡ ሰዎች “ፎቅ ታንጾዋል፤ መንገድ ተሰርቷል፤ ግድብ እየተገደበ ነው፤ የከተማ ባቡር ገብቷል፤ ስለዚህ ዝም በሉ” ብለው እንደሚያወሩት ነው የመሰለኝ፡፡ ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ጋር መስራቱ ከጥንትም ስገፋፋው የነበረና የምስማማበት ነገር ነው። ለምሳሌ በነሀሴ 2000 ዓ.ም. ገና ግንቦት ሰባት በይፋ ሳይገባበት፤ ስለፍኖተ-ኤርትራ ይሄንን የድጋፍ ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡

3-ችግሩ፤ ግንቦት ሰባትም ይሁኑ ኢሳት፤ ኤርትራን የተመለከተ በቂ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ትንተና የሚጎድለው ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ገብተዋል። ለምሳሌ፤ ይሄ የአቶ ኢሳያስ ቆሞ ግድብ ማሰራት ጉዳይ መደበቅ እንጂ መደነቅም መዘገብም የሌለበት ነገር ነው፡፡ አሁን የምንመለከተው ኤርትራንና ሻእቢያን ወይንም አቶ ኢሳያስን ቀና የኢትዮጵያ አጋር አድርጎ የመሳል ፕሮፓጋንዳ፤ የኢህአዴግ አቶ መለስን የኢትዮጵያ ህዳሴ አድርጎ የመሳል ፕሮፓጋንዳ ግልባጭ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ፤ “አቶ መለስ ዜናዊ የህዳሴውን ግድብ መሰረት ጣሉ፤ አቶ መለስ 30 ዩኒቨርስቲ አሳነጹ፤ የህዳሴው ግድብ 33 ከመቶ መጠናቀቁ ታወቀ፤ የእድረገትና ለውጥ እቅዱ የአቶ መለስ ጽንስ መሆኑ ተነገረ” የሚለው ዜና የሰለቸን ሰዎች፤ ለምን የአቶ ኢሳያስ ቆሞ ግድብ ማሰራት እንዳስደነቀን፤ እንደውም ለዜናነትም እንደበቃም አይገባኝም፡፡ በመሰረቱ ያንድ አገር ፕሬዚደንት፤ የፖለቲካ መሀንዲስ እንጂ የግድብ መሀንዲስ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቆሞ ግድብ ማሰራቱ፤ ወይም ግድብ ግንባታ ላይ በሚያጠፋው ግዜ፤ ሌላውን የሚመለከተውን ስራ እንደበደለ የሚያሳይ ነው፡፡

4-በዚህ ሰሞን ኤርትራን በተመለከተ የኢሳት ዘገባ ላይ፤ የኢሳትንና የግንቦት ሰባትን ተልእኮ መለየት ተስኖኛል፡፡ ኢሳት ወደኤርትራ መጓዙና እዚያ አካባቢ ያለውን ነገር መዘገቡ ትክክል ነው፡፡ የዘገበውን ነገር መልቀቅ በቂ ሆኖ ሲገኝ፤ ያንን ቪዲዮ ይዞ በየከተሞቹ የመዞሩ ፋይዳ የተመለከቱትን የመዘገብ ብቻ ሳይሆን፤ በዚህ መንገድ መጓዝ አለብን በሚለው ሀሳብ የማጥመቅ ሙከራም ይመስላል፡፡ “በኤርትራ ያለው ሁኔታ ተስፋ ስለሚሰጥ፤ ዝም ብላችሁ ያንን መንገድ ተቀበሉ” የሚል ይመስላል፡፡ ኢሳት እዚህ ጋር ሚናውን ረስቷል፡፡ የኢሳት ስራ መዘገብና ማቅረብ እንጂ፤ ማሳመንና ማጥመቅ አይደለም፡፡ ኢሳት በቅን ልቡና፤ ትግሉን በቋሚነት በማይጠቅም ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ተዘፍቆ ተመልክቼዋለሁ፡፡

5-የኢትዮጵያ ህዝብ በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትብብር እንዲቀበል ለማድረግ መዝፈን ምንም ስህተት የለበትም፡፡ ያንን ፕሮፓጋንዳ ግን በተሳሳተ ቅኝት መዝፈን የለብንም፡፡ ለምሳሌ ይሄ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ስለኤርትራ ወታደሮችና ስለአቶ ኢሳያስ ቀናነት ለኢትዮጵ ህዝብ ለማስረዳት መሞከር ድፍረትም ስህተትም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አቶ ኢሳያስን የተመለከተ በቂ ተሞክሮ አለው፡፡ ይልቅስ ኢሳት ማተኮር የነበረበት፤ በሁለቱ አገሮች/ህዝቦች መካከል ስለነበረው ታሪካዊ ትስስርና ችግር፤ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ እንዲገነጠሉ ስላደረጋቸውና አቶ ኢሳያስ ተዛባ ስለሚሉት ታሪክ፤ ስለሁለቱ አገሮች ብሄራዊ ጥቅምና ሁለቱ አገሮች አንዳቸው ያንዳቸው ስጋት ሳይሆኑ ስለሚኖሩበት ሁኔታ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚኖር ሰላማዊ ግንኙነት እንቅፋት ስለሚሆኑ ነገሮች፤ ወደፊትም ስለሚጋጥሙ ተግዳሮቶች ነው፡፡ ይሄ “እኛ እኮ አንድ ነን፤ መልካችን አንድ ነው፤ አማርኛ ይናገራሉ፤ የጥላሁንን ዘፈን ይዘፍናሉ” የሚለው ፕሮፓጋንዳ፤ በምንም መልኩ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ታሪካዊና ፖለቲካዊ ቁርሾ አይፈታውም፡፡ አዳራሽ ውስጥ የሚደረጉ ጭብጨባዎችና ሽንገላዎች ብቻቸውንም የሚፈይዱት ነገር የለም፡፡

አርበኞች ግንት ሰባት፤ አንድም ሁለትም ነን

6-ሌላው በዚህ የኢሳትና ግንቦት ሰባት የኤርትራ ጉዞ በዋንኛነት የተዘገበው ነገር የግንቦት ሰባትና አርበኞች ግንባር ውህድት ነው፡፡ በዚህ ላይ ጥቂት ነገሮችን እንበል፡፡ አንደኛው፤ ብዙ ግዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት/ግንባር ምስረታ ከነፍትወቱ በሚመነኩስ መነኩሴ ይመሰላል፡፡ ግንቦት ሰባትና አርበኞች ከተዋሃዱ ስማቸውን ወደአንድ ኢትዮጵያ ነክ ስም የማይለውጡበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ሁለቱም ያልሞተ ኢጎ ከሌላቸው በስተቀር፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ጽኑእ የስም ፍቅር አላቸው፡፡ ኢህአፓዎች ስማቸውን ወይ በኩራት ባደባባይ አይጠራቡት፤ ወይ ቤተመዘክር ውስጥ አያስቀምጡት፤ ለምን ስማችሁን አትለውጡም ሲባሉ፤ ሰዎች ተሰውተውበታል ይላሉ፡፡ ኢዴአፓና መድህን ሲዋሃዱ፤ ኢዴአፓ-መድህን፡፡ አንድነትና መኢአድ ሊዋሃዱ ሲሉ አንዱ ያጨቃጨቃቸው የስም ጉዳይ ነበር፡፡ ግንቦት ሰባት-አርበኞች፤ “ድርጅታችንን አምክነን ተዋህደናል፤ ግን አንድም ሁለትም ነን” እንደማለት ነው፡፡

7-ሁለተኛ፤ ይሄ በተልእኮ/በርቀት የሚመራ መሪ ነገርም አይገባኝም፡፡ በርግጥ ይሄ የድርጅቶቹ ጉዳይ ቢሆንም፤ በዚህ ውህደት ውስጥ፤ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋን ሊቀመንበር አድርጎ መምረጥም ስህተት ይመስለኛል፡፡ እስከምናውቀው ድረስ፤ ብርሀኑ ነጋ የሙሉ ግዜ መምህር/ፕሮፌሰር ነው፡፡ በዚያ ላይ ቤተሰብም ግዜ ይፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ትግሉም ሌላ የሙሉ ጊዜ ስራ ነው፡፡ የሙሉ ጊዜ ጠላትን በትርፍ ጊዜ ትግል አናሸንፋም፡፡ ጠላቶቻችን ያሸነፉንም የሚመሩንም በሙሉ ጊዜ ትግል ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ሰሜን አሜሪካ የሚኖርን ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም አጠገብ የሚታገል ድርጅት መሪ አድርጎ መመረጥ ብቻውን፤ የስልታችንን ጉድለት ያሳል፡፡ ሊቀመንበሩ፤ በዚህ ብዙ በተነገረለትና ትግሉን ወደሌላ ምእራፍ እንደሚያሻግር በተተነበየለት ውህደት ላይ ቢገኝ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ በድርጅቶቹ የአንድ ሳምንት የውህደት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ከአባላቱና ከአስተናጋጇ ኤርትራ መሪዎች ጋር ለመነጋገር ያልቆረጠ መሪ፤ እንዴት የድርጅቱ መሪ ሊሆን እንደሚችልና ወደድል እንደሚወስደን አይገባኝም፡፡ ይሄ በጉዞ ሰነዶችና አንዳንድ ጉዳዮች አለመሟላት መገኘት አልቻሉም የሚለው ሰንካላ ምክንያት አያሳምንም፡፡ አንድም ጉዳዩ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ አለያም ብርሀኑ በዚህ የኤርትራን ትግል አላመነበትም፡፡ ስድስት ሰባት አመታት መሪው እግሩን ያልጣለባት አገር ዋና መቀመጫው የሆነ ድርጅት መሪ፤ የድርጅቱ መሪ ባይሆን ይመረጣል፡፡

ወደኤርትራ ጉዳይ ስንመለስ፤ ግንኙነቱ እንዴት ይቃኝ

8-ከላይ እንዳልኩት፤ ከኤርትራ ጋር መስራት ምርጫ አይደለም፡፡ ከኤርትራ ጋር መስራት የግድ ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር አብረን ካልሰራን፤ ጠላት ሆነን እንቀጥላለን፡፡ አንዳችን አናት ሌላኛችን ሸሆና ስንቀጠቅጥ እንኖራለን፡፡ ችግሩ፤ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ፤ አሁን ያለው የግንቦት ሰባትም ይሁን በኤርትራ በኩል የሚሰሩ ሌሎች የብሄርም ሕብረ-ብሄርም ድርጅቶች፤ ተስፋ የሚጣልበት አመራር ማሳየት አልቻሉም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰኔ 2004/2012 ከኤርትራ ጋር ስለመስራት አንድ ጽሁፍ ጽፌ፤ በዚያ ጽሁፍ ላይ የሚከተለውን ብዬ ነበር፡፡

ከኤርትራ ጋር የኤርትራን ሉአላዊነት ያወቀና የኤርትራንም የኢትዮጵያንም ብሄራዊ ጥቅም ያስቀመጠ ውል መግባት አንዱ የትግል አማራጫችን ነው። በኤርትራ በኩል ያለው ትግል (ወደፊት) ያልገፋው ከኤርትራ ጋር በግልጻና በይፋ የሚዋዋል ጠንካራና ደፋር ሀገር ወዳድ ድርጅት ስላልተገኝ ነው። ያንን ክፍፈት ሊሞላ የሚችል ደግሞ ከግንቦት ሰባት የተሻለ የለም። ግንቦት ሰባት ግን እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተሻሸ እንጂ አልቆረጠም።

9-ግንቦት ሰባት ኤርትራ ከገባ ጥቂት አመታት ቢያልፈውም፤ እስካሁንም ድረስ ከኤርትራ ጋር የተድበሰበሰ እንጂ፤ በግልጽ ሰነድና ውል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት አልፈጠረም፡፡ ከኤርትራ ጋር ለመስራት ግልጽ የሆነና የሁለቱን አገሮች ብሄራዊ ጥቅም ከግምት ያስገባ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የኤርትራን ጉዳይ መወሰን ወይንም “ከኤርትራ ጋር የሚኖረንን የውጭ ግንኙነት የመወሰን ስልጣን የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ወይም ሕዝቡ የሚመርጠው ዴሞክራሲያዊ መንግስት ጉዳይ ነው፤ እኛ አሁን አንወስንም” የሚለው የግንቦት ሰባት አባባል፤ አንድም ሀላፊነትን ሽሽት ነው፤ ሌላም በሻእቢያ ዘንድ አመኔታን የሚያሳጣ ነው፡፡ አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ አውጣኝ ብሎ የላከው ድርጅት የለም፡፡ ስለዚህ የህዝብ ውክልና የምንጠብቅ ከሆነ፤ ኤርትራ በመግባት ጉዳይ ላይ ራሱም ህዝብ ድምጽ አልሰጠበትምና ስህተት ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ሻእቢያ ከጥንትም የአንድነቱን ሀይል ይጠራጠራል፡፡ ሻእቢያዎች በፖለቲካውና ትግሉ ውስጥ ብዙ ቆይተዋል፡፡ ለጊዜው ያለምንም ስምምነት እርዳታቸውን እንቀበልና ከድል በኋላ እንፈነግላቸዋለን ብለን የምንሸውዳቸው ሀይሎች አይደሉም፡፡ የኤርትራን ሉአላዊነት በግልጽ ሳንቀበል፤ የባህርበርን ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደፊት ይወስናል እያልን የምንቀርበው የኤርትራ መንግስት፤ እንዴት አድርጎ በሙሉ ልብ ተማምኖብን እንደሚረዳን አይታየኝም፡፡

የኤርትራና የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መርህ-አልባ ግንኙነት

10-አሁንም ቢሆን፤ ከኤርትራ ጋር ለመስራት የሚያስፈልገን፤ ሻእቢያን/ኢሳይያስን ቅዱስ አድርጎ የመሳል አካሄድ ሳይሆን፤ የሁለቱን ሀገሮች መሰረታዊና ብሄራዊ ጥቅም ከግምት ያስገባ ፕሪንሲፕልድ የሆነ አካሄድ ነው፡፡ ኤርትራ አገር ነች፡፡ ቢቆጭም፤ ያጣናቸው ሀሰብና ቀይባህርም የኤርትራ ናቸው፡፡ ይሄንን በደንብ በይፋ ማመንና መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ሁልግዜም ቢሆን ፈተና ላይ የሚወድቀው በኤርትራ በኩል መሆኑንና ሁለቱ አገሮች በምስራቅ አፍሪካውና በቀይ ባህር በኩል ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መተባበራቸውና አብረው መስራታቸው የግድ እንደሆነ ከግምት ያስገባ፤ ኢትዮጵያ ደህንነቷ፤ ኤርትራም ህልውናዋ ተጠብቀው ሊኖሩ የሚችሉት አንዳቸው ካንዳቸው ጋር መስራት ከቻሉ ብቻ እንደሆነ ባሰመረ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና እንድትቀጥል በኤርትራ በኩል ያለው ደህንነቷ አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ ኤርትራም ያለስጋትና ሰቀቀን እንድትኖር የኢትዮጵያ ቡራኬ ያስፈልጋታል፡፡ ግንቦት ሰባት፤ ይሄንን የሁለቱን አገሮች ብሄራዊ ጥቅም በግልጽ ያስቀመጠ ስምምነት ላይ ማተኮር ተስኖት፤ ደረጃወን ባልጠበቀና ውሀ በማይደፋ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ሲዳክር፤ ኢሳትም የዚህ የግንቦት ሰባት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆነ መስላል፡፡

11-በኤርትራና በኢትዮጵያ በነበረው የታሪክ ኡደት፤ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወታደሮችና ሲቪሎች ሞተዋል፡፡ አያሌ ሺኆች አካለጉዳተኞች ሆነዋል፡፡ ብዙዎች ተዋርደውና እርቃናቸውን ተፈናቅለዋል፡፡ የአገሮቹ አንጡራ ሀብትም በጦርነት ባክኖ ሕዝቦቹን ለድህነትና ለሰቆቃ ከዳረጉት ነገሮች ዋንኛው ይሄ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረው ረጅም ጦርነት ነው፡፡ በዚህ ጦርነት አያሌ ሺሆችም ያለወላጅ ቀርተዋል፡፡ ኢሳትም ይሁን ሌሎች ተቃዋሚ ሀይሎች ከኤርትራ ጋር መስራት ካለባቸው ይሄንን ያለፈ ቁርሾ እያነሳን ባናለቅስበትም፤ ምንም እንዳልተፈጠረና አንድ እንደሆንን አድርገንም ወሬ ማብዛት የለብንም፡፡ ይልቅስ ፕሮፓጋንዳው ማተኮር ያለበት፤ የሁለቱን አገሮች ብሄራዊ ጥቅሞች መሰረት ያደረጉ ውይይቶችና ጥናቶች ላይ ነው፡፡ እንደውም በኢትዮጵያና አካባቢው ታሪክ ውስጥ እንደኤርትራ ጉዳይ ለሰፊ ውይይትና ትንታኔዎች የሚመች ጉዳይ የለም፡፡ የኤርትራ አካባቢ ከአጼ ዮሀንስ እስከ አጼምኒሊክ፤ ከጣሊን ወረራ እስከ ኤርትራ ቅኝ-ግዛት፤ ኤርትራውን ከኢትዮጵያዊን ጋር ወይም የኢትዮጵያ አካል ሆነው ካደረጉት ተጋድሎ እስከ መጀመሪያው ድምጸውሳኔ፤ የሻእቢያ የሰላሳ አመት የነጻነት ትግል፤ ሁለተኛው የኤርትራውያን ውሳኔድምጽ፤ የኢህአዴግና የሻእቢያ ግንኙነቶች፤ የቅርብ ግዜው የሁለቱ አገሮች ጦርነት፤ ሰፊ ውይይት ሊደረግባቸው የሚገቡና አሁንም ድረስ የአካባቢችንን ፖለቲካ የሚዘውሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ሳናነሳ የምናደርገው የኤርትራ ጉዞ ለድልም ለገድልም አያበቃንም፡፡ እንጂ አሁን እንዳደረግነው፤ የፕሮፓጋንዳውን ቅኝት የአቶ ኢሳያስ ደግነት ላይ መትከል የዋህነት ነው፡፡

12-ግንቦት ሰባትና ኤርትራም አብረው መስራት ካለባቸው በሁለቱ አገሮች መካከል የተካሄደውን የሰላሳ አመት ጦርነት እንዳልነበር ረስቶ፤ ወይንም የሁለቱ አገሮች ችግር ኢህአዴግ/ሕወሀት የፈጠረው አይነት አስመስሎ በመናገር መሆን የለበትም፡፡ በዚህ መርህ አልባ በሆነ አካሄድ ተሂዶ ኢህአዴግ ከስልጣን ቢወገድም እንኳን፤ በሁለቱ አገሮች መካከል፤ ሻእቢያና ሕወሀት ደርግን ከጣሉ በኋላ እንደተፈጠረው አይነት የተዛባ ግንኙነት መፈጠሩና፤ በዚያም ወደሌላ ጦርነት እንደማንገባ ዋስትና የለም፡፡ ግንቦት ሰባት ይሄንን ጉዳይ ፊትለፊት መግጠም ፈርቶ በይደር ትቶታል፡፡ ኢሳትም በቋሚ ጥቅሞቻችን ላይ የተሰመረት ጥልቅ ታሪካዊ፤ ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ስትራቴጂካዊ ውይይት ማድረግና ማመቻቸት ሲገባው፤ በመርህ-አልባ ፍቅር ያበደ፤ ግለሰቦችን መሰረት ያደረገና፤ የተመረጡ ቃለምልልሶች ላይ ያተኮረ የብሽሽቅ ዝግጅት ላይ አተኩሯል፡፡ ለብሽሽቅ ለብሽሽቅ እኔ ከሶፊያ ጋር ያደረኩት ቃለምልልስ በቂ ነበር፡፡ ብሽሽቅ ሲያልፍ ግን፤ እውነተኛ ፖለቲካ እያደር ፈጦ ይጋፈጠናል፡፡ ስለዚህ ግንቦት ሰባትም ኢሳትም መርህን መሰረት ወዳደረግ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትና ጉዳይ ያተኩሩ፡፡

እንደማስታወሻ፤ ይሄንን የምጽፈው ለምንድነው? አንድም ስለሚያገባኝ ነው፡፡ ሌላም በንጽጽር፤ ኢትዮጵያን ሊያድን የሚችል፤ ነገር ግን ካቅሙ በታች እየሰራ ያለ ድርጅት ግንቦት ሰባት ነው ብዬ ስለማምንና፤ ግንቦት ሰባት ምናልባት አስተያየቴን ከተቀበለው፤ ቅኝቱን እንዲያስተካከል እድል ለመስጠት፤ እንዲሁም ትችቴ ሀሜት ሆኖ እንዳይቀር ለማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ ታዲያ ለምን በግል አትነግራቸውም፤ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ለዚህ ብዙ መልስ አለኝ፡፡ ዋንኛው ግን፤ በግል ሲነገሩ ትኩረት የማንሰጥባቸው ነገሮች፤ ባደባባይ ሲነገሩ የበለጠ ትኩረት ያገኛሉ፤ የሚለው ነው፡፡ በተጨማሪም፤ ይሄንን የምጽፈው፤ አለሁ፤ ለማለትም ነው፡፡ ከጠፋሁም፤ በዚህ ተጠምጄ ነው፡፡ ማስታወቂያ ነገር መሆኑ ነው፡፡

ተክለሚካኤል አበበ ሳሕለማርያም፡፡ ቶሮንቶ፤ መጋቢት ፳፻፯፡፡ ለጤናማ አስተያየት፤ [email protected]