ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የአባይ ወንዝን ለመጠቀም የደረሱት ስምምነት ሰነድ ሙሉ ቃል እና ማብራሪያ
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር ወደ ፖለቲካ ኮሚቴ ከፍ በማድረግ ለወራት የዘለቀ ድርድር በሶስቱ አገራት ረዕሰ መዲናዎች ላይ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። እነዚህ ድርድሮችም ፍሬ አፍርተው አገራቱ የአባይ ወንዝን ዓለም አቀፍ መርህዎችን ተከትለው ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት በሱዳን ካርቱም ተፈራርመዋል። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ በግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ ኤልሲሲ እና በሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር መካከል የተፈረመው ስምምነት ሶስቱንም አገራት እኩል ተጠቃሚ እና ዓለም አቀፍ መርህዎችን መሰረት ያደረገ ነው ተብሎለታል። የዚህን ስምምነት ሰነድ ሙሉ ቃል ከአስረጅ ጋር እንደሚከተለው ቀርቧል። መግቢያ የግብፅ አረብ ሪፐብሊክ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊያዊ ዴሞክራሲያ ሪፐብሊክ እና የሱዳን ሪፐብሊክ እየጨመረ የሚገኘውን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶቻቸውን የመጠቀም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የናይል ወንዝ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ህይወት እና ልማት ምንጭ የሆነ ሀብት መሆኑን በመገንዘብ ሶስቱ አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለተዘጋጁት ቀጣይ መርህዎች ይሰራሉ። በዚህ የስምምነቱ የመግቢያ ክፍል ላይ ቀደም ሲል ግብፅ የናይል ወንዝ ለግብፃውያን የህይወት ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን ግን የቅንጦት ያህል ለመልማት ብቻ የሚፈልጉት አደርጋ የያዘችውን አቋም በመቀልበስ ናይል ለሶስቱም አገራት ዜጎች ህይወት እና ልማት መሰረት መሆኑን በእኩል እውቅና የሰጠ ነው። 1. የትብብር መርህ – በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ትብብር፣ የጋራ ፍላጎት፣ መልካም አሳቢነት፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እና የአለም አቀፋዊ ህጎች መርህዎችን የተከተለ – የታችኛውም ሆነ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት […]