የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ መሪዎች የማያባራ ንትርክና ኢ-ክርስቲያናዊ ምግባር
ዲ/ን ሙሉጌታ ውልደገብርኤል
“በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን ነገር ግን የዚች ዓለም ጥበብ አይደለም ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የሰወረውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔር ጥበብ በሚሥጢር እንናገራለን። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰውን ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።” የሚለውን አምላካዊ ቃል ለዛሬ ዕለት መልዕክቴ መግቢያዬ ነው።
ይቅር የቤተ-እምነቱ ተከታይ በውጭም በሀገር ውስጥም የሚኖር ዜጋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ያለችበትንና የምትገኝበትን አስከፊና አስፋሪ ሁኔታ የማያውቅ ይኖራል ብዬ አላምንም። በተራራ ላይ እንዳለች ማብራት የመሪዎችዋ የማያባራ ንትርክና ኢ-ክርስቲያናዊ ምግባር ለፍጥረት ሁሉ የተገለጠ ነው። የዚህችውን እናት ቤተ-ክርስቲያኔን ችግር ለመቅረፍ/ በማስመልከት የበኩሌን ድርሻዬን መወጣት (በጽሑፍ) ይህ ለመጀመሪያ ጊዜዬ አይደለም።
በተለያዩ ጊዜያትና ወቅቶችን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ክርስያናዊ አመለክከቴን ሳካፍል መቆየቴ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ደግሞ በቤተ-ክርስትያኒትዋ ዙሪያ እንያጃበበ ያለውን የጥፋት ደመናን በማስመልከት የቤተ-ክርስቲያኒትዋን ህልውና እና የተከታዮችዋ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል እንዲህ ያለ መልዕክት ማስተላለፍ ጊዜውና ሰዓቱ የጠበቀ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ከላይ ከፍ ስል በመግቢያዬ ለመግለጽ እንደተሞከረ መንፈሳዊ ችግርን የሚቀርፈው መንፈሳዊ ጥበብ እንጂ ሊሌላ ሊሆን አይችልምና ሁሉም በያለበት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ወገን ሁሉ መጽሐፍ ከሚለው ጎን በመቆም ማንኛውም ዓይነት ኢ-ክርስቲያናዊ የሆነ እንቅሳቃሴ ይቃወም ዘንድ ጥርዬን አቀርባለሁ።
በመሰረቱ የእነዚህ ጎራ ለይተው እየተቧቀሱ ያሉ ሁለት አካላት (“የኃይማኖት መሪዎች”) ችግር ምንድ ነው? ኃይማኖታዊ ወይስ ፖለቲካዊ ችግር? ችግሩ ኃይማኖታዊ ችግር ከሆነ በመንፈሳውያን መካከል ለሚፈጠረው ችግር መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) በማን እና እንዴት ሊፈታ ይገባዋል ብሎ ነው የሚያስተምረው? የግለሰቦች ፖለቲካዊ ቀውስና አለመግባባትስ ቢሆን ኃይማኖታዊ ሽፋን ተሰጥቶት የክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን ማተራመስና ምዕመናን ግራ መጋባት የተገባ ነው ወይ?
እንግዲህ ችግሩ የፖለቲካ ችግርም ቢሆን “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ አይቻለውም ሆኖንብ እንጂ የኃሳብ ልዩነት ማለት ገለሰብአዊ ጸብ/ችግር ባላስከተለ ነበር። ካመጣም ፖለቲካዊ ልዩነትን በማጥበብ በአንድነት ለአንድ ዓላማ ለመስራትና ለመትጋት ሰዎች መስማማት በሚገባቸው መንገድ ማስማማትና ዕርቅን ማድረግ የሚቃወም ማንም የለም። ዛሬ በቤተ-ክርስቲያኒትዋ እየተፋፋመ ያለው ቀውስ እውነቱን ለእኛ ለውስጥ አዋቂዎች አንዳች የተደበቀ ባይሆንም ብዝሐኑ በሰሙትና ጥቂቶቹ በሚያራግቡት ተንሳፋፊ ክስ መነሻ በማድረግ እንነጋገር ቢባል እንኳ የመጀመሪያ የውግዘትን ጠጠር ተወረወረ አካል ምክንያት አድርጎ ያቀረበውና አሁን እንደተልባ በትር እያሽሞነሞነው ያለው ምክንያት በውጭ የሚገኙ የቤተ-ክርስቲያኒትዋ የቀድሞ የሥራ ባለደረቦች አሁን የሚገኙበት ሁኔታ እንዲህና እንዲያ ናቸው ይህን አይቀበሉም ይህን ክደዋል ተብሎ ነው።
ቃለ ውግዘቱም የሚጀምረው “የአጽራረ ቤተ-ክርስቲያን በታኝ ተግባር የሚፈጹሙት ከሐዲዎች ቤተ-ክርስቲያን ከምትወደው ሕዝብዋ ሕዝቡንም ከሚወዳት ቤተ-ክርስቲያኑ ሊለያዩ ሆን ብለው በመነሳት የእግዚአብሔርን ቃል፣ የሐዋሪያት ሲኖዶስ፣ የአበውን ኃይማኖት፣ ሕገ ቤተ-ክርስቲያንና ሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያን በመጻረር” በማለት ነው። ለበለጠ መረጃ የውግዘቱ ቃለ-ጉባኤ ያጠቃለለ “ቀኖና ቤተ-ክርስቲያን ያፈረሱት አባ መርቆሬዎስና ተከታዮቻቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ተወህዘው ተለዩ” በሚል ርዕስ ሚያዝያ 1999 ዓ/ም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን መነበረ ፓትሪያሪክ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተዘጋጀ መጽሐፍ ያንብቡ።
ያሳፍራል ስል ወደ ስጠሁት የርዕሴ ስያሜ ስመጣ ችግሩ የግልም ሆነ የስልጣን የጎሳ ልዩነት ያስከተለው ሹኩቻም ሆነ የፖለቲካ ቀውስ ወረደም ወጣም አለመግባባቱ ከዚም አለፎ ለከፋ ልዩነት የዳረጋቸው ትልቁ ምክንያት መንፈሳዊ ክህደት /ምንፍቅና ነው ከተባለ ይህን (እንዲህ ያለውን ችግር) የመፍታች ስልጣን ያለው ማን ነው? መንፈሳውያን ወይስ ባለሙያዎች? መጽሐፍ በቤተ-ክርስቲያን መካከል ለሚፈጠረው ችግር ማን እና እንዴት እንዲፈታ ነው የሚያስተምረው? በውኑ ይዳኙና ያቀራርቡ ዘንድ የተቋቋሙ ግለ ሰቦችም ሆኑ አካል በማን ጣልቃ ገብነት/ጥያቄ የተቋቋሙ ናቸው የሚለው ዓቢይ ጥያቄ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን “አስታራቂዎች” የችግሩ/የልዩነቱ መንስኤ ሆነዋል በተባሉ ጉዳዮች ያላቸውን እውቀት የሁለቱም አካላት አመለካከትና አስተምህሮ ሰምተው ነገር አመሳጥረው አርቅቀውና መጥቀው የመዳኙቱ መንፈሳዊ ዕውቀታቸው ምን ያህል ነው?
ተጠየቂ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ/ያን ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቂምን? በዓለምስ ላይ ብትፈረጂ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርጂ አትበቂምን? (ችግሩ ኃይማኖታዊ ችግር አይደለምና) ከዚህስ በላይ ሰማያና ምድር የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር በአደባባይ መሳደብና ማሰደብ ምን አለ? ለችግሮቻችሁ መፍትሔ መንፈስ ቅዱስን መጠቀቅ አቅቶአችሁ ውሎ አድሮ በሚገረሽ የሰዎችን ጥበብ ፍለጋ ደጅ የምትጸኑ ቆባችሁ ላይ ምን ቢሰፍር ነው?
የሰሚ ያለህ! ቤተ-ክርስቲያን በባለ ሞያዎች አትዳኛም!! በምንም ዓይነት መልኩና ተአምር በህጋዊም ሆነ በሌላ መንገድ ስማቸው ይፋ የሆኑ ግለሰቦች በቤ/ያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብተው የማስታረቅ ድርሻ ሊፈጽሙ አይችሉም። የቤ/ያን ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ነው። ቤተ-ክርስቲያን የማንም ልትሆን አትችልም ቤ/ያን የአዋቂዎች የጠቢባንም አይደለችም የደም ዋጋ የተከፈለባት ቤ/ያን የመንፈሳውያን ናት። ማናችሁም ተሟጋቾችም ብትሁኑ አሁንም በቤ/ያን ላይ ያላችሁ የይገባኛል ጥያቄአችሁን አንሱ። ሥጋ ለባች በቤ/ያን ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም። ምን ነው? ቢሉ ቤ/ያን የቢዝነስ ማዕከል አይደለችምና።
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ተከታዮች ምእመንና ሆይ እውነት የሚመስል ሁሉ ትክክል አይደለምና በሚመስል ነገር እየታለልን ከዚህም ከዚያም ሳንሆን ከየዋህነታችንን የተነሳ አጨብጫቢዎች ብቻ ሁኑን እንዳንቀር እፈራለሁ። በአንድም በሌላም ተብሎ የሚሰራ የመንፈስ ቅዱስ ስራ የለም። መንገዱ አጭር፣ ግልጽ፣ አንድና አንድ ነው ይኸውም እውነትና ጽድቅን ያላማከለ ዕርቅ ከእግዚአብሔር አይደለም ተብሎ ሲነገርህ ድምጽህን ማሰማትና መቃወም ያለብህን ሁሉ በጊዜው መቃወም የሚበጀው አንተን ነው። ክር ካማሰርና በጭፍን ከመሟገት ያለፈ ስራ በፊትህ ነውና ውጣና ድምጽህን አሰማ።
ቤ/ያን የእግዚአብሔር እስከሆነች ድረስ በቤ/ያን መካከል ለሚፈጠረው ማንኛውም ዓይነት ትልቅም ሆነ ትንሽ ችግር የመመገብ፣ የማስተማርና የመምራት (የማስተዳደር) ጸጋ አብ ኃይለ ወልድና ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ባላቸውና በተሰጣቸው ቅዱሳን ነው። (አስታራቂዎች ርኩሳን ናቸው አላልኩም) የካህናትን ነገር የሚፈታ ካህን ነው። ይህ ቋንቋ ምን ለማለት እንደተፈለገ በቤተ-ክህነት አከባቢ ያደገም ሆነ ለቤተ-ክህነተ ሰው ግልጽ ነው። እንዲህ ባይሆንና ቤ/ያን በአላፊው አግዳሚው ወጪ ወራጁ የምትነዳና የምትዳኝ ብትሆን ኖሮ ሐዋሪያው በቤ/ያን መካከል ለተፈጥር ችግር ለመቅረፍ የደም እንዳ እያነባ ባለመናቸውና መዳኘትም የሚገባቸው በመንፈሳያን መሆኑን ግጥም አድርጎ ባልጻፈ ነበር።
አይደለም! ይህቺ ቤ/ያን (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያንም ሆነች መሪዎችዋ) መጽሐፍም ሆነ አንተ እንደምትለው ሳትሆንና ሳይሆኑ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ዛሬ ታይቶ ነገ እንደ ጥላ በሚያልፈት የየኢህአዴግ መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በውስጥም በውጭም የኢትዮጵያ ህዝብ የአፍዝ አድንግዛቸውን መርፊ የሚወጉባትትና መርዛቸውን የሚረጩባት ጤና ኬላ ናት ቤ/ያትዋ ምስረታም ሆነ የመሪዎችዋ አገልግሎትና ተጠሪነታቸው ፈሪሃ እግዚአብሔር ላልፈጠረባቸው ዓለማውያን ናት/ናቸውም ከሆነ ቁርጡ በይፋ ይነገርና እኛም በገና ለሚያፈልገው በገና እንደረድር ዘንድ እናንተም ስራችሁን መሆን የምትፈልጉትን በነጻነት ታደርጉ ዘንድ እርዱን እንርዳችሁ።
የማስታረቅ ስራ ማለት በአሁን ዘመን አንድ ራሱን የቻለ ተቋም ነው። እነዚህ አካላት ደግሞ በሞያቸው የተመሰከረላቸው ለዳኝነታቸውም ይግባኝ የሌለው ግራ ቀኝ ሰምተው የችግሩ መንስኤ አጥንተው በሚሰጥዋት ብይን ሳታላምጥ ቢከፋህም ቢለማህም ለመቀበል በመፈራረም ነው የዕርቁን ሂደት የሚጀምረው። የእኛዎቹስ ምን በማለት ይዳኙ ይሆን? (ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ገጽ 10 ይመልከቱ) “የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ወላዲተ አምላክ ከሆነችው ከእናታቸው ከቅድስት ድንግል ማርያም ነጥለው ከፀረ-ማርያሞች በረት ለመክተት የፀረ ማርያምነት ዓላማ ውዳሴ ማሪያም፣ መልክአ ውዳሴና መልክአ ስዕል እንዳይደርስ ተአምረ ማርያም እንዳይነበብ፣ የሐውሪያት አመክንዮ ቅዳሴ ማሪያም እንዳይቀደስ፣ ከቅዳሴ መጻህፍት ውስጥም ዐሥራ አንዱ በሙሉ እንዳይጸለይባቸው፣ የቅዱስ ያሬድ ዜማ አሮጌና አሰልቺ ስለሆነ አገልግሎት ላይ እንዳይውል፣ የቅዳሴ ጸሎት በፒያኖ፣ በኦርጋንና በመሳሰሉት ዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲቀደስ፣ ያለ ጽላት ቅዳሴ እንዲቀደስ በማድረግ የቅዱስት ድንግል ማርያምና የተዋህዶ ሃይማኖታችን ክብር ተዳፍረዋል። ይህ ሁኡ የኑፋቄ ግንብ እየተገነባ በመፈንስ ቅዱስ መሪነት ቤተ-ክርስቲያኗን የሚመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ነገሮችን በትዕግስት የሚያልፋቸው ሆነው አላገኛቸውም።” እንዲል
ማን በሐስት ውንጀላው ተከሶ ማን ደግሞ በስህተቱ ተጸጽቶ በይፋ የተገለጠ ወንጀሉና ስህተቱን አምኖ ንስሃ ይገባ ይሆን? ኧረ ለመሆኑ “ለሊቃነ ጳጳሳቱ” ስንሃ የሚሰጥ ማን ሊሆን ይሆን? “ያስታርቁ” ዘንድ የተመረጡ ዜጎች? ያሳፍራል!! ወይስ ንስሃ ግራ ቀኙን ለማያውቁ ለምእመናን እንጂ ለእኛ ለትላልቆቹ የተገባ አይደለም ተብሎ በይፋ ፍጹም የሆነ የክህደት ዘመቻ ያካሂዱ ይሆኑ?
እንግዲህ ከአደራዳሪዎች ይህን እንጠብቃለን፥
አባ መርቃሪዎስ የሚል የማዕረግ ስማቸው ተነስቶ አባ ሊባኖስ ፈንታ ተብለው በቀድሞ ስማቸው ይጠሩ ዘንድ የተደረጉ የቀድሞ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ፓትሪያሪክ ስልጣናቸውን የለቀቁ በፈቃዳቸው ወይስ ተገደው? የሚለው አንድ ሲሆን የአባ ጳውሎስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የበላይ ተደርገው ሲሾሙስ አስታራቂው አካል ትክክል ነው ይል ይሆን? (የነገር ሁሉ መሰረታዊ ጥያቄች ናቸውና)። ሌላውም በቅድስት ድንግል ማርያም ዙሪያ ለተነሳ ጥያቄ ይሆናል ይኸውም ቅ.ድ. ማርያም የአዳም ኃጢአት ያለፈባት (ጥንተ አብሶ) አለባት የለባትም ለሚልም ሕዝብ አንድ ዕልባት አለባት የለባትም የሚል መልስ ይጠበቃል።
በአጭሩ የሚሳፍረው ችግሩ ዶክትሪናል ትምትርት ላይ የተመሰረተ ልዩነት ከሆነ ለማስታራቀ የታጩ አካላት ፍጹም አይመለከታቸው ባይ ነኝ መጽሐፋን ተንተርሼና እያመሳከርኩና። ለአለመግባት ተግባብተው እንዲኖሩ (በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሆነው እንዲኖሩ ማለት ነው) እንዲያደርጉ ካልሆነ በስተቀር እነዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በማያሻማ መልኩ መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። አንድ ነገር አውቃለሁ እነዚህ የሀገር ፍሬ የሆነ ምሁራን እንዲሁ አነተም ተው አንተም ተው ለማለትና ራሳቸው ለትዕዝብት ላይ ለመጣል ረብ ለሌላው ነገር እንደማይሰለፉ በሚገባ እረዳለሁ ቢሆንም ግን ጃንሆይ “እኩይ ለእከዩ ሃይማኖት ያለበሳ” እንዳሉት የሃይማኖት ሽፋን የተሰጠው ፖለቲካዊና የሥልጣን ጥያቄ ለመዳኘት ከልሆነ በቀር አሟግተውና አፋትገው ኃይማኖታዊ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ ብሎ ማንም አይጠብቅም። ለማንኛውም ማናችንም ብንሆን እንደ ቤ/ያን ልጅነታችን መጽሐፍ የሚለውን በይፋ ለማለት ሕዝብንና ቤ/ያን ለመጠበቅ የእነዚህ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ በጉጉት ይጠበቃል።
ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ!
(ዲ/ን ሙሉጌታ ውልደገብርኤል፣ E-mail [email protected])