የዋሽንግተን ዲሲ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ቦርድ አቶ አዲሱ አበበን ከአባልነት አስወገደ

በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ የምትገኘው ርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/የባለአደራዎች ቦርድ አቶ አዲሱ አበበን ከአባልነት አስወገደ። “ቤተክርስቲያናችን ውስጥ የመከፋፈልና የማፍረስ እንቅስቃሴ ለማስቆም” በሚል ርዕስ ከቤተክርስቲያኒቷ የባለአደራዎች ቦርድ “ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ” በሚል ባሰራጨው ግልጽ ደብዳቤ እንዳመለከተው አቶ አዲሱ አበበ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ሲያደርጉ የነበረውን አፍራሽ እንቅስቃሴዎች በዝርዝር አቅርቦ አቶ አዲሱ ከሚያካሂዱት አፍራሽ ድርጊት እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ተመክረው ሊመለሱ እንዳልቻሉ ተጠቁሟል። ለአቶ አዲሱ የተጻፈላቸውን እራሱ አስረጅ የሆነውን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። አቶ አዲሱ አበበን አስመልክቶ የተሰራጨው ግልጽ-ደብዳቤ

አቶ አዲሱ ለረዥም ዓመታት ቤተክርስቲያኒቷ በተለያዩ ባለሞያዎች ያስጠናችው ዕቅድና ፕላን በአባላት ከጸደቀና የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ሥራው ከተጀመረ በኋላ ከእንቅልፋቸው ባነው እንደ አዲስ የሚያነሱት ሃሳብ ሥራውን ወደኋላ የሚጎትት፣ጊዜ የሚያባክንና አማራጭ የሌለው ስለሆነና እንዲሁም ከእርሳቸውና ከጥቂት መሰሎቻቸው በስተቀር ደጋፊ የሌለው ሃሳብ ስለሆነ ከጀመሩት አፍራሽ ተግባር መቆጠብ ይኖርባቸዋል። እስከ አሁን የተሰሩት ሥራዎች በርካታ ገንዘብ፣ጊዜና ጉልበት የወጣባቸው ስለሆነ ምዕመናንን ሳይከፋፍሉና ንፋስ ሳያስገቡ በዕቅዱ መሠረት ከመስራት ሌላ አማራጭ የለም።

ወደኋላ ተመልሰን እንመልከት ከተባለ ቤተክርስቲያኒቷ መገንባት የነበረባት የመኪና ጋራዥ የነበረ ቦታ ላይ ሳይሆን ሌላ የተሻለ ሥፍራ ላይ እንደነበር ማንም አይስተውም። ቤተክርስቲያኒቷ የተሻለ ቦታ ይዛ ቢሆን ኖሮ አሁን ከተገባበት ውጣውረድና ችግሮች ያድን እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነው። በመሠረቱ ስህተት የሰራው የአሁኑ የባለአደራዎች ቦርድ ሳይሆን፣ ከሃያ አመት ገደማ በፊት ያውም በወቅቱ የቦታ ዋጋ ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የተሻለ በነበረበት ጊዜ የመኪና ጋራዥን ወደ ቤተክርስቲያን ለመለወጥ ይህንን አርጌ ጋራዥ እንዲገዛ የወሰነው ቦርድ ነው። የአመራር ችሎታ የሚለካው ዕጅ ላይ በጨበጡት ነገር ብቻ ሳይሆን አርቆ በማሰብ ወደፊት የሚፈጠረውንም ሁኔታ አሻግሮ በማየትና ሊፈጠሩ ለሚችሉ ሁኔታዎች አስቀድሞ በመዘጋጀትም ጭምር ነው። ጋራዡ በተገዛ ወቅት የነበሩ አንዳንድ ምዕመናን እንደሚናገሩት የቤተክርስቲያኒቷ መስራች የሚባሉት ግለሰብ የዚህን ጋራዥ ወደ ቤተክርስቲያንነት መለወጥ ዋና አቀንቃኝ ስለነበሩ ምንአልባት እሳቸውን ላለማስቀየም የተደረገ ሊሆን ይችላል ይላሉ። እኝህ መስራች ግለሰብ ለቤተክርስቲያኒቷ ያበረከቱት አስተዋጾ ሁልቆ መሳፍርት ቢሆንም “ቋሚ የባለ አደራዎች ቦርድ አባል” በሚል ለእሳቸው ብቻ በቋሚነት የተመደበላቸው ቦታ አግባብበት የሌለው ነው። እንደዚህ ዓይነት አሰራር በሌሎች ቤተክርስቲያኖች ተሰምቶም አያውቅም። አቶ አዲሱ አበበም ሆኑ አሁን አብረዋቸው የቆሙ ምዕመናን ያኔ ይህ ጋራዥ ሲገዛ ተቃውመው እንደነበር የተናገሩት ምንም ነገር የለም።

ምዕመናን በሚያዋጡት ገንዘብ  የሚካሄድና በአባላት በሚመረጥ የባለአደራዎች ቦርድ የሚተዳደር ቤተክርስቲያን እስከሆነ ድረስ እኝህ “መስራች” ግለሰብም እንደሌሎች የቦርድ አባላት የአገልግሎት ዘመናቸው የተገደበ መሆን አለበት። የሃይማኖት ተቋምን የሚያስተዳድር ቦርድ “ቋሚ” የሚባል አባል ሊኖረው አይችልም። ቋሚና ዘላለማዊ ፈጣሪያችን  አንድ እግዚያብሔር ብቻ ነው። እንድ ግለሰብን ቋሚ አባል ማድረግ እጅግ የማይገባና ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው።  ግለሰቡ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተለያዩ ነገሮችን ለምሳሌ ለስማቸው መጠሪያና መታሰቢያ የሚሆኑ ነገሮችን ማድረግ ይቻላል። ደግሞስ ለነፍስ ተብሎ የሚሰራ የቤተክርስቲያን ስራን እግዚያብሔር ይመልከት እንጅ ከሰው የሚሰጥ ሙገሳና አድናቆትስ ምን ይጠቅማልና? በመንፈሳዊ ቦታ አለማዊ እውቅንና ምስጋና መፈለግ መንፈሳዊ በረከትን ከማሳጣት ሌላ ምንም ጥቅም የለውም። ስለሆነም ቤተክርስቲያኑ የምዕመናን እስከሆነ ድረስ ለወደፊቱ ይህ መተዳደሪያ ደንብ መስተካከልና ከሌሎች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያናትጋር መመሳሰል ያስፈልገዋል።

ከዚህ ቀደም አቶ አዲሱ አበበ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋዜጠኝነታቸውና በግላቸው በተለይ የቤተክርስቲያንን ጉዳይ አስመልክተው በሚወስዱት አቋም መካከል በሚፈጠረው መደበላለቅ ምክንያት የተለያዩ ነቀፋዎችና ትችቶች ሲቀርቡባቸው እንደነበረ ይታወቃል። በዚህም መሠረት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በአሁኑ ጊዜ ካሏት ታላላቅ ሊቃውንት መካካል አንዱ የሆኑት ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ታህሳስ 2007 ዓ.ም. “ሰይፈ ነበልባል፤ ክርስትንና ጋዜጠኝነት ሲዋሃዱ ወደ ሰይፈ ነበልባልነት ይለወጣሉ”  በሚል ርዕስ ለአቶ አዲሱ ተግሳጽና ምክር ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም። ይህንን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። ሰይፈ-ነበልባል

ከዚህም በተጨማሪ አቶ አዲሱ በሚሰሩበት የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ መዘገብ የሚገባቸውን አብይ ጉዳይ እሳቸው የሚደግፏቸውን ሰው ስለሚያስቀይም ሳይዘግቡት አልፈውታል። ለምሳሌ ቀድሞ ቀሲስ ታደሰ ሲሳይ ይባሉ የነበሩ ግለሰብ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እምነትና ሥርዓት ውጭ በሰሩት ጥፋት በሶስት ካህናትና የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ምዕመናን ፊት ሲወገዙና ሥልጣነ ክህነታቸውን ሲገፈፉ አቶ አዲሱ እስፍራው የነበሩ ቢሆንም ይህንን የመሰለ ታላቅ የቤተክርስቲያን ዜና ያወገዙትን ካህናት ሲለሚቃወሙና የተወጋዡ ደጋፊ ስለሆኑ ሽፋን ሳይሰጡ አልፈውታል። በአንጻሩም በቅርቡ ሚኒሶታ ከተማ ውስጥ የተፈጠረ በመገናኛ ብዙሃን መነገር የሌለበት፣ አስተማሪነትም ሆነ የመርሃ ግብርሽፋን ሊሰጠው የማይገባ ነውረኛ ድርጊት በሬዲዮ አቅርበው በርካታ የሬዲዮኑን አድማጮች ከማሳዘናቸውም በላይ የሬዲዮኑንም ደረጃ ወደታች አውርደውታል።

አቶ አዲሱ አበበ ከየካቲት 4 ቀን እስከ 9፣ 2004 ዓ.ም. (ከፌብሪዋሪ 13-17፣ 2012) ፊኒክስ፣ አሪዞና ውስጥ በውጭ በሚገኘው ሕጋዊው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስና አገርቤት በሚገኘው ሲኖዶስ መካከል ተካሂዶ በነበረውና በከሸፈው ድርድር ላይ ተገኝተው በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ላይ ከስፍራው ትክክለኛ ያልሆነና የተጣረሰ ዘገባ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ “በድርድሩ ላይ የተገኘሁት በግሌ ነው” በማለት ከጋዜጠኝነት ስነምግባር የራቀ ተራ የደፈጣ ስራ ሰርተዋል። አቶ አዲሱ እንደ ማንኛውም ግለሰብ በግላቸው የሚፈልጉትን አቋምና አመለካከት የመያዝ መብት አላቸው። ሆኖም ጋዜጠኛ እንደመሆናቸው መጠን፣ የግል ስሜታቸውና አመለካከታቸው በዕለታዊ ስራቸው ላይ ጫና እንዳይፈጥርባቸው ጥንቃቄ መውሰድ ይገባቸዋል። ከዚህም በላይ የሚሰሩበት መስሪያ ቤት በግብር ከፋዮች የሚተዳደር የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ መጠን በግል የሚወስዱት አቋም በመስሪያ ቤታቸውም ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንጸባረቁ እንደማይቀር ሊያስተውሉት የሚገባ ጉዳይ ነው።