ሰበር ዜና – የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ከሓላፊነታቸው ተነሡ፤ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በፓትርያርኩ ብቸኛ ውሳኔ ተክተዋቸዋል
በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ተተኪ ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ለቦታው በሚመጥን መልኩ በውድድር እንዲሾሙ እየጠየቁና የፓትርያርኩን ያልተመከረበት አካሔድ እየተቃወሙ ባሉበት ኹኔታ ‹‹ነባር የቤተ ክርስቲያኒቱ ሠራተኛ ካህንና በዘመኑ ዕውቀትና በአመራር ብቃት እጅግ ሞያ አላቸው›› በሚል በፓትርያርኩ ብቸኛ ውሳኔ የተሾሙት የአማሳኞች አጋር ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ
- መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር በምክትል ሥራ አስኪያጅነት ተመድበዋል
- ብፁዕ ጠቅ/ሥራ አስኪያጁ ውሳኔውን በአስቸኳይ እንዲያስፈጽሙ በሹመት መመሪያ ታዝዘዋል
- ሊቀ ማ/ን የማነ ሥራን በመበደል፣ አእመረ አሸብር በሃይማኖታቸው ርቱዕነት ነቀፌታ አለባቸው
- የፓትርያርኩ አካሔድ በረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምንጦስ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት ነው
- ቋሚ ሲኖዶስ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚነጋገርበት ይጠበቃል
* * *
- ተተኪው ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በወቅቱ በዋና ጸሐፊነት በሚሠሩበት በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ ከመልካም አስተዳደርና ከገንዘብ ብክነት ጋራ ተያይዞ በቅርቡ ከተነሣው ተቃውሞና በነበሩባቸው አድባራት ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይልቅ ለግል ቢዝነሶቻቸው ቅድሚያ በመስጠት በሚገባ የሚታወቁ ናቸው፡፡
- ፓትርያርኩ፣ በቁጥር ል/ጽ/301/10/2007 በቀን 10/07/07 ከልዩ ጽ/ቤታቸው ባወጡት ደብዳቤ፣ የሹመት መመሪያቸው ከዛሬ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲኾን አስታውቀዋል፤ በሀገረ ስብከቱ የሚደረገውን የክፍል ሓላፊዎች ምደባና ዝውውር ይኹንታና ፈቃድ በመስጠት ጭምር ይቆጣጠራሉ፡፡
- ፓትርያርኩ ከረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው ይልቅ ከልዩ ጸሐፊአቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ የመከሩበት ዓምባገነናዊ አካሔዳቸው፣ ከፀረ – ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ፀረ – የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔዎች አቋማቸው አንጻር በመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚነሣባቸውን ብርቱ ጥያቄ ትኩረት የማስቀየስ አካል እንደኾነ እየተጠቆመ ነው፡፡