የባህልና ቱሪዝም ቢሮው መግለጫውን እንዲያርም ታዘዘ፤ ኢሬቻ በደብረ ዝቋላ አይከበርም

  • ፓትርያርኩ እና የመስተዳድሩ ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ መወያየታቸው ተጠቁሟል
  • ‹‹የኢሬቻ ቱሉ በዓል በክልል ደረጃ የት አካባቢ መከበር እንዳለበት ገና አልተወሰነም፡፡››
                                                         (የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የኦሮሞ አባ ገዳዎች ምክር ቤት)

zequullaየኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ‹‹ኹለተኛው ዙር የኢሬቻ በዓል በዝቋላ ተራራና በአካባቢው ይከበራል›› በሚል በሬዲዮና ቴሌቪዥን ለአስተላለፈው መግለጫ እርምት እንዲያደርግ በክልላዊ መንግሥቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር መመሪያ እንደተሰጠው ተገለጸ፡፡

የፕሬዝዳንቱ መመሪያ የተሰጠው÷ የባህልና ቱሪዝም ቢሮው ከክልሉ የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ጋራ በመኾን፣ በመጪው መጋቢት ፴ የገዳ ሥርዐት መታሰቢያ ሐውልት ተከላ እና የኢሬቻ በዓል በደብረ ዝቋላ የጠበል ሐይቅ ዙሪያ እንደሚከናወን መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በመንግሥታዊው ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ያስተላለፈው መግለጫ ከቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር፣ አገልጋዮችና ምእመናን ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው፡፡

ziquwala_17የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በኢትዮጵያ ካሉት ጥንታውያንና ታሪካውያን ገዳማት አንዱ እንደኾነ የጠቀሰው የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ መግለጫውን በመቃወም ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር በጻፈው ደብዳቤ፣ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተሰጠው መግለጫ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የእምነት ነጻነት የሚጥስ በመኾኑ በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ መተላለፉ ተገቢ እንዳልነበር ተችቷል፡፡

በመግለጫው ሳቢያ በመናንያን መነኰሳቱና በአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ የተቀሰቀሰው ቁጣ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ መንግሥት ለሚመለከተው ክፍል ተገቢውን መመሪያ እንዲሰጥ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ያቀረበውን ሰፊ ዘገባ መነሻ ያደረገው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት፣ ችግር ከመፈጠሩ በፊት መግለጫው በተላለፈበት የመንግሥት ብዙኃን መገናኛ ማረሚያ እንዲሰጥበትም የመስተዳድሩን ፕሬዝዳንት ጠይቆ ነበር፡፡

የክልሉ ፕሬዝዳንት ስለ ጉዳዩ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መነጋገራቸውን የጠቆሙት የዜናው ምንጮች፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዝቋላ ተራራና በአካባቢው የኢሬቻ በዓል እንደሚከበርና የገዳ ሥርዐት መታሰቢያ የማቆም ሥርዓት እንደሚከናወን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ለአስተላለፈው መግለጫ እርማት እንዲያደርግ በፕሬዝዳንቱ መመሪያ እንደተሰጠው መገለጹን አስታውቀዋል፡፡

የአባ ገዳ ተወካዮችን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የአስተዳደር፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የፖሊስና የጸጥታ ዘርፍ ሓላፊዎች ከገዳሙ አስተዳደር ጋራ የካቲት 25 ቀን በገዳሙ ሞፈር ቤት እና የካቲት 30 ቀን ደግሞ በአዱላላ ወረዳ ጽ/ቤት ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን ተገን በማድረግ እምነታቸውን ለመጥቀም የሚሠሩ ግለሰብ አመራሮች በተለይም ከመጋቢት ወር ፳፻፪ ዓ.ም. አንሥቶ ቦታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስፈራራትና ዛቻ እያደረሱባቸው እንዳሉ በውይይቱ ወቅት የተናገሩት የገዳሙ ተወካዮች፣ አስተዳደሩ የማያዳግም መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በቢሮው መግለጫ የተፈለገው ገዳማውያኑን ከኅብረተሰቡ ጋራ ለማጋጨት ነው ያሉት የማኅበረ መነኰሳቱ ተወካዮች፣ ከመጋቢት ፭ ክብረ በዓል በፊት መግለጫው በስሕተት የተላለፈ መኾኑ ተጠቅሶ ማስተባበያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ የሥርዐተ ገዳ ተወካዮች በበኩላቸው፣ ‹‹ዝናም እምቢ እንዳይለን በቤተሰብ ደረጃ ገዳሙን አስፈቅደን ከምንፈጽመው ሥርዓት›› ውጭ ደብረ ዝቋላ ይኹን የጠበል ሐይቁ የኢሬቻ በዓል አከባበር ታሪክ እንደሌለው አስረድተዋል – ‹‹ለኛ ዐዲስ ነገር ነው፤ ከየት አምጥተው እንዳስተላለፉት አናውቅም፤ ያስተላለፉት መጠየቅ አለባቸው፡፡››

ከመግለጫው ጋራ ግንኙነት ስለአላቸው አካላት ቀጣይ ማጣራት ተደርጎ ማስተባበያ እንደሚሰጥበትና ለዚኽም ሓላፊነቱን እንደሚወስዱ በባለሥልጣናቱ መገለጹ ተመልክቷል፡፡ አንዱ በሌላው እምነት ጣልቃ ገብቶ ጫና የሚፈጥርበት አሠራር እንደማይኖር የተናገሩት ሓላፊዎቹ፣ በክብረ በዓሉ ከተለመደው የተለየ ክንዋኔ እንደማይኖርና የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግ መመሪያ እንደተሰጠም ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡

************

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከኦሮሞ አባ ገዳዎች ምክር ቤት ጋራ በመኾን ትላንት መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የሰጠውና ማምሻውን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተላለፈው ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

(ኢቢሲ፤ ሪፖርተር በላይ ሓድጎ፤ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

EBC logoየኦሮሞ ሕዝብ በዓመት ኹለት ጊዜ ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱ የኾነው ኢሬቻ ቱሉ በዓል፣ በክልል ደረጃ የት አካባቢ መከበር እንዳለበት ገና አለመወሰኑ ተገለጸ፡፡

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ምክር ቤት ሰብሳቢና የቱለማ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ እና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ዘውዱ ማሞ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ በጋ ላይ ዝናም ሲጠፋ ሕዝቡ ወደ ተራራ በመውጣት ፈጣሪውን የሚለማመንበት የኢሬቻ ቱሉ በክልል ደረጃ የት መከበር እንዳለበት የሚወሰነው፣ የታሪክ ባለሞያዎች በሚሰጡት መረጃና በሕዝብ ፍላጎት መሠረት አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች በሚሰጡት ውሳኔ ነው፡፡

ክረምት በበጋ ሲተካ እንኳን ለብርሃን አበቃን በማለት ሕዝቡ ፈጣሪውን የሚያመሰገንበትና በውኃ ዳር የሚከበረው ኢሬቻ መልካ ደግሞ በአባ ገዳዎችና በአገር ሽማግሌዎች ውሳኔ መሠረት ከደርግ ሥርዐት ውድቀት በኋላ በየዓመቱ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ እየተከበረ መኾኑ ይታወቃል፡፡