በእኔ እምነት እና መረዳት – በዘር ጉዳይ ላይ – ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ

በእኔ እምነት እንኳን ‘አማራ’ ‘ኦሮሞ’ና ትግሬ . . . የሚባል ማንነትም የለም – በግድ በቋንቋ ‘አንድ ናቸው’ ካልተባለ በስተቀር (እሱም ቢሆን ዘየው የተለያየ ነው – የሀረሪ ኦሮምኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ከጂማው ኦሮምኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ በቋንቋ ደረጃ እንኳን ልዩነት አለው – እንደ አይሪሽ እና ስኮት አርጋችሁ አስቡት) በተመሳሳይ መልኩ የተንቤኑ ከአድዋው ትግርኛ ተናጋሪ በተለየ ቅላፄ እና ዘዬ አለው፡፡ የጎጃም ሰው ከወሎ ሰው የተለየ አማርኛ ይናገራል፡፡ ይህ ታዲያ ሌሎች ባህል ነክ እና ሃይማኖታዊ የሆኑ በርካታ ልዩነቶችን ትተን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በኔ እይታ – ማንነት በቋንቋ ብቻ ይገለፅ ካልተባለ በስተቀር አሁን በተካለለው መልኩ ‘አማራ’ም ይሁን ‘ኦሮሞ’ . . . ማንነት ሊሆኑ አይችሉም!

ከዚህ ባለፈ ግን ላለፉት 3 እና 4 አስርት ዓመታት ለፖለቲካል ሞብላይዜሽን (ዘመኑም ይፈቅደው ስለነበር) በቋንቋ ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ ማንነት ለመፍጠር ብዙ ተለፍቷል፡፡ ሊናቅ በማይችል መልኩም ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ያ አሁን ያለንበት ነባራዊ እውነት ነው፡፡ ይህን ማንም ሊክደው የሚቻለው አይመስለኝም፡፡
እኔ በግሌ ከላይ እንዳሰፈርኩት እንዲህ አይነቱን የማንነት መደብ የማልቀበለው ብቻ ሳይሆን የምቃወመውም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን . . . በዚህ በሰለጠነ ዓለም ላይ እየኖርኩኝ – የሞደሬት ሌበራሊዝም አራማጅ ሆኜ – ‘አሮሞ’ ነኝ ብሎ ተሰባስቦ የመጣን ቡድን ‘ኦሮሞ’ አይደለህም የምልበት ሞራል የለኝም፡፡ በተመሳሳይ ‘አማራ’ ነኝ ብሎ የሚንቀሳቀስ ቡድንን አየደለህም ልል አልችልም፡፡ ነኝ ካለ እኔ ማነኝና አይደለህም ልለው ይቻለኛል?
የኔ መንገድ –
አሁን ያለንበትን ውስጣዊና ውጫዊ ነባራዊ እውነታ ከግንዛቤ በማስገባት የ 50 ዓመት ጦስ እና ተያያዥ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉበትን እና የማልማትን ታላቋን ኢትዮጵያ (ጅቡቲን እና ኤርትራን ጨምሮ) ዳግም እኔም ባልሆን ልጆቼ በፍቅር እንዲኖሩባት – በዓለም ላይም የምትታፈር እና የምትከበር . . . እጅግ ሪች እና ዳይቭረስ ባህል ያላት ታላቅ ሀገር እንድትኖረን የሚያስችለንን መሰረት የምንጥልበት – ለሁሉም አመለካከት የሚበጀውን የነፃነት ትግል ማካሄድ ነው፡፡ ሀሳብ የሚፋጭበት ህዝብ የሚፈርድበት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር መታገል የእኔ ምርጫ ነው፡፡ የኔ መንገድ ነው!! ለዚህም በዘመኑ ጓዶች የተሞላውን ሰማያዊን እንዲያታግለኝ መርጫለሁ፡፡
አሁን ላይ ሆኘ ከላይ ስለሰፈረው መሰል ክርክርም ሆነ ውይይት ማካሄድ እርባና ቢስ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢሊት ፖለቲካ ታክቶኛል ለሀገሬም ሲበጅ አይታየኝም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ይመስለኛል – ይኸውም አሁን ባለንበት ሁናቴ እንዲህ አይነት ክርክር ተካሂዶ መሬት ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችልበት፤ ህዝቡ ፈራጅ ሊሆን የሚችልበት መድረክ የለምና! ያው እንደተለመደው አንዱ ጉልበተኛ ቦታ ቀይሮ ያሻውን ሊግተን ካልሆነ በቀር!
ህዝቡ ክርክር አድምጦ ፍርድ ካልሰጠ ወይም ያን እየሸሸን “እኛ ያልነው ነው የህዝቡ እውነት – ሌላው ሁሉ ስህተት ነው” ማለት አሁንም ሀገሪቱ በጥቂት ምሁራን እንድትዘወር መፍቀድ ነው፡፡ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እታገላለሁ የሚል ማንኛውም አካል የያዘው ማናቸውንም ሀሳብ አቅርቦ ከስልጣኑ ባለቤት ከህዝብ ፍርድ ለማግኘት መጀመሪያ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን መታገል አለበት፤ የታሪክም የህሊናም ተጠያቂነት አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አሁን ላይ ያለው እንካ ስላንቲያ በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን አምባገነንነት ከማሳየት ባለፈም ለነፃነት የሚደረገው ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እንደመቸለስ ነው፡፡
ቸር ሁኑ!