Interview with Actress Aziza Ahmed ቆይታ ከተዋናይት አዚዛ አሕመድ

ቁም ነገር ቅጽ 13 ቁጥር 199 የካቲት 2007

ትዕግስት ታደለ

በውብ የፊት ገጽታዋ ላይ ፈገግታና ሳቅ ይቀድማታል ፤ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው የጉማ የፊልም ሽልማት ስነ ስርዓት ምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይ በመባል ለመሸለም በቅታለች፡፡ ‹ፍቅር ሲፈርድ› በተሰኘ ፊልም የጥበብ መንገዷን ‹ሀ› ብላ የጀመረችው ወጣቷ ተዋናይ ከስምንት በላይ በሚሆኑ ፊልሞችም ላይ ተውናለች፡፡ የአርትቴክት የመሆን ፍላጎት ቢኖራትም ወደ ከፍተኛ ተቋም ለመግባት የሞላችው ፎርም ግን የኬሚካል ኢንጅነሪግ ተማሪ እንድትሆን ፈርዷባታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዳንኪራ የቴሌቭዥን ብሮግራም አስተዋዋቂ ስትሆን በኢብኮ የእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም አዲስ በተጀመረው ‹መለከት› ድራማ ላይ ትተውናለች፤ የዛሬዋ እንግዳች አዚዛ አህመድ በመሿለኪያ አምዳችን ላይ እንዲህ ቆይታ አድርጋለች፡፡

ቁም ነገር፡- ደስታው እንዴት ይዞሻል? ሰሞኑን ከመሸለምሽ ጋር ተያይዞ አንቺ ጋር ያለው ስሜ ምን ይመስላል?

አዚዛ፡- እንደምታይን ነኝ፤ እስካሁን ደስታው አልጠፋም አይደል ፊቴ ላይ? በጣም ደስ ብሎኛ፡፡ ትልቅ ማበረታቻ ነው፡፡ አንድ ልጅ የሆነ ውጤት አምጥጦ ስትሸልሚው ነገ ደግሞ በየበለጠ አንደኛ ለመውጣት እንደሚጥረው አይነት ነው እኔ ጋር አሁን ያለው ስሜት፡፡ ሽልማቱ ነገ የበለጠ እንድሰራና እንድጥር ብርታት ነው የሆነኝ፡፡

ቁም ነገር፡- እናትነት ላነቺ ምንድ ነው ?

አዚዛ፡- እናትነት ብዙ ነገር ነው፡፡ እናትነት ብዙ ነገሮችን ተቋቁመሽ አንድትረኖሪ ደርግሻል፤ ምክንያቱም አንድ የፈጠርሽው ሰው ስላለ ለዛ ሠው መኖር ትጀምሪለሽ፡፡ ለሌሎችም መኖር ትጀምሪያለሽ፣ ብቻሽን ሆነሽ ትኖሪው ከነበረው ኑሮ የተለየ ኑሮ ነው የሚኖርሽ፡፡ ለኔ ፍቅር፣ ትርጉም ያለው መኖር፣ የህይወት ትርጉም የምንላቸው ነገሮች ሁሉ እናትነት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለልጅሽ ትኖሪያለሽ፣ ህይወትሽን በአግባቡ ትመሪያለሽ፣ ስራሽንም እንደዛው፡ ፡ ስለዚህ አርአያ ሆነሽ የምታልፊለት ሰው ስትይዢ ለዛ ሰው አርአያ ለመሆን ስትይ ብዙ ነገር ትሆኛለሽ፡፡

ቁም ነገር፡- እነዚህን ነገሮች ሳላደርግ መኖር አልችልም የምትያቸው ሦስት ነገሮች ጥቀሽ ?

አዚዛ፡- የመጀመሪ ከፈጣሪ ጋር ብዙ መገናኘት ስለምፈልግ ሳልፀልይ መኖር አልችለም፡፡ ሁለተኛ ካለ ልጄ መኖር አልችልም፤ ሦስተኛው ነገር ደግሞ ምንድ ነው እ /እንደማሰብ/ ከቤተሰቦቼ፣ ከጓደኞቼ ጋር ካለኝ ማህበራዊ ህይወት ርቄ መኖር አልችልም /ሳቅ…/

ቁም ነገር፡- የሠርግሽ ቀን ሙሽራሽ ቢቀር ምንድ ነው የምታደርጊው?

አዚዛ፡- እስቲ ልብ! /ሳቅ…/ ፤ሲጀምር እኔ ቀድሜው አልመጣም / ሳቅ…/፤የእውነት በጣም ከባድ ነው፡፡ ቢቀር የሆነ ዘዴ እፈጥራለሁ፤ ግን ሆደ ባሻ ስለሆንኩኝ እዛው ለተሰበሰበው ሰው ነግሬ በቃ ቀርቷል ተበተኑ የምል ነው የሚመስለኝ፡፡ ነገሮችን ፊትለፊት የመጋፈጥ አቅም የለኝም፤ትንሽ ሰነፍ ነኝ፤ እና ልክ ቀረ ተብሎ ሲነገረኝ እግዚአብሔር ይስጠው ብዬ እዛነው የማለቅስ ነው የሚመስለኝ /ሳቅ…/፡፡

ቁም ነገር፡-ትርፍ አንጀት ምንድ ነው?

አዚዛ፡- /ሳቅ……/ ትርፍ አንጀት ማለት በሰውነታችን ውስጥ አንጀት የተባለ ክፍል አለ፤ትንሹ አንጀት ትልቁ አንጀት የሚባል አለ ፤ከዛ በተረፈ እንግዲህ የሆነ ባጋጣሚ የሚመጣ በሽታ አለ መሰለኝ፤ያንንትርፍ አንጀት እንለዋለን አይደል? /ሳቅ…../ እንደዛ ነው እኔን የሚመስለኝ /…ሳቅ/ ፡፡

ቁም ነገር፡- በህይወትሽ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ምንድ ነው?

አዚዛ፡- በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው እ /እንደማሰብ/ እናቴ ትመስለኛለች፡፡ በቃ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ወልዳ ለፍታ አሳድጋኛለች፤እኔ እናት ስለሆንኩ ነው ያ ስሜት የሚገባኝ፤ እና ያንን ሁሉ ነገር ስለሆነችልኝ ለኔ በጣም ትልቅ ትርጉም አላት፡፡ ከዛ በተረፈ ደግሞ ፈጣሪዬ ለኔ በጣም ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ስወድቅ ስነሳ ማንም ዞር ብሎ ላያይሽ ይችላል፤ማንም ላያነሳሽ ይችላል፤ ሁልጊዜም ግን ፈጣሪ አይተወንም ፤ስለዚ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

ቁም ነገር፡- ፊዚክስ ፣ኬሚስትሪ ፣ባይሎጂ፤ አማርኛ ትርጓሚያቸው ምንድ ነው?

አዚዛ፡- እንዴት እንዴት? እ /እንደማሰብ/ ባይሎጂ ያው ሳይንስ ነክ ነው፡ ፡ ግን ቆይ እኔ እምለው ! አንድ ነገር ልጠይቅሽ ? እንደው ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ስንማር ፊዚክስ በአማርኛ፣ኬሚስትሪ በአማርኛ ትርጉማቸውን ምን እንደሆነ ተምረናል? አሁን ከየት እናምጣው? /ሳቅ…/ እኔ ስኖር ፊዚክስ በአማርኛ ሰምቼውም አላውቅም፡፡

ቁም ነገር፡- የአንድ በሽታ መዳህኒት የማግኘት እድል ቢሰጥሽ፤ የየትኛውን በሽታ መድሀኒት ማግኘት ትፈልጊያለሽ?ለምን?

አዚዛ፡- እኔ ሁለት እንዲሆንልኝ እጠይቃለሁ፤ምክንያቱም አምነውብኝ መድሀኒት የማግኘት ዕድሉ ከተሰጠኝ ሁለትስ ሦስትስ የማይሆን /ሳቅ…../ አንደኛ የካንሠርን ነው፡፡ በጣም ሳናቀው በተለይ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ሰው እየጨረሰ ነው ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኤች አይ ቪ ነው፡፡ ሁለቱም ውስጥ ለውስጥ ሰውን እየጨረሱ ያሉ ናቸው፡፡ ብችል የነዚህን በሽታዎች መድሀኒቶች ባገኝ ደስ ይለኛል፡፡

ቁም ነገር፡- የጋብቻውን ያህል ፍቺ መብዛቱ ምክንያቱ ምንድነው ትያለሽ?

አዚዛ፡- አለመተዋወቅ ነው፡፡ አንዳንዴ ጋብቻ ሲፈጸም ስሜታዊ የምንሆነው ነገር አለ አይደል ? ማግባት ስላለብን ብቻ ፣ወይ ደግሞ የተዋደድሽ ይመስልሽና ወይም በደንብ የተዋወቅሽ ይመስልሽና ጋብቻ ይፈጸማል ፡፡ የሆነ ሠዓት ላይ ትክክለኛ ውስጣችን፣ ማንነታችን ሲወጣ ፍቺ ይመጣል፡፡ የሰው ልጅ ከተዋወቀ መጥፎ ባህሪ ቢኖረው እንኳን ያንን ባሀሪውን ከጋብቻም ውጭም ስለሚያቀው አዲስ አይሆንበትም፤ስለዚህ አብረው ተቻችለው ይኖራሉ፡፡ የድሮ አያቶቻችን ወይም ደግሞ ቤተሰቦቻችን ስናይ የሆነ ዓመት ድረስ አይደለም የሚኖሩት ፤ ተቻችለው ጥግ ድረስ ይኖራሉ፤ይህ የሆነው ደግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ ወልደው የሆነ ደረጃ

እስኪደርሱ ድረስ በደንብ ስለሚተዋወቁ ነው፡፡ አሁን ለፍቺ ዋናው ምክንያት የሆነ ሠዓት ላይ የሚወጣው የማናቀው ባህሪ መምጣት እና ያንን ተቀብሎ መኖር አለመቻል ይመስለኛል፡፡

ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ የመጀመሪያ ፍቅር ተመልሶ አይመጣም የሚባል ነገር አለ፤ የመጀመሪ ያፍቅር ከሁለተኛው በምን ይለያል?

አዚዛ፡- ምን አስባለሁ መሰለሽ ፤ህፃን ልጅ ነጭ ወረቀት ነው አይደል? የሰጠሸውን ነገር ሁላ ይቀበላል፤ አጥፍተሸ ግን እንደ አዲስ ነጭ ወረቀት ላይ ስትፅፊው ትንሽ ደስ የማይል ነገር አለው / ሳቅ…/ ደብዘዝ የማለት ነገር፤ ሲነበብ ራሱ ለውጡ ይታያል ፤ መጀመሪያ እንደተፃፈው ጥርት ያለ ነገር አይደለም የሚታየው፡፡ የመጀመሪያ ፍቅርም ያ ነው ብዬ ነው የማስበው፤በንጹህ አዕምሮሽ፣ በንጹ እይታ የምታገኚው ነገር ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ልጄ ባትጠይቀኝ ብለሽ የምትይው ጥያቄ አለ?

አዚዛ፡- አይ ምንም የለም ፤ በተቻለኝ አቅም ማወቅ የሚገባትን ነገር በደንብ ነው ማሳወቅ የምፈልገው፡፡ በጊዜዋ ደግሞ ማወቅ የማይገባትን ነገር የሆነ ጊዜ ላይ እንድታውቀው ዝምብዬ ጫፍጫፉን ነግሬ የማሳልፋቸው ነገሮች ነው እንጂ ያሉት የምከለክላት ነገር አይኖርም ፡፡ ምክንያቱም የሆነ ሰዓት ላይ ስትደርስ ማወቋ አይቀርምና፡፡

ቁም ነገር፡- ትልቅ ወጪ አውጥተሸ ለራስሽ የገዛሽው ነገር ምንድ ነው?

አዚዛ፡- እንግዲህ እስካሁን ትልቁን ገንዘብ የያዘው መኪና ነው፡፡ ከዛ ውጪ ግን ትንንሽ ናቸው፡ ፡

ቁም ነገር፡- ቦርዴ ከምን ይዘጋጃል?

አዚዛ፡- እሚባል መጠጥ ቀምሼ እኮ አላውቅም /ሳቅ…/ ፡፡ እንዳለ ግን አውቃለሁ፤ እንግዲህ ዝም ብዬ ሳስብ ከበሶ፣ ከበቆሎ የሚዘጋጅ ይመስለኛል፤ግን እንደጠላና ጠጅ ቀጭን አይመስለኝም የሆነ በጣም ወፍራም ነገር ይመስለኛል /ሳቅ../፡፡

ቁም ነገር፡- ቆንጆ የምትይው ወንድ ወይም ሴት ለድርድር የምታቀርቢው ውበቱ ምንድ ነው?

አዚዛ፡- ቆንጆ ለኔ ውጫዊ የማየው ተክለ ቁመና ብቻ አይደለም፡፡ ሁሌም የማስበው የመጀመሪያ ውስጣዊ ውበትን ነው፡፡ ውስጣዊ ውበት ማለት ሰው ማክበር ፣ለሰው የሚኖረን አመለካከት ፣ፈርሀ እግዚአብሔር ያለው ሰው፣ለመማር ለመለወጥና ለማደግ ውስጡ የተዘጋጀ ሰው ለኔ ውብ ነው ፡፡ ከዛ ቀጥሎ ነው ውጫዊ ነገርን የማየው ፤አይን ፣ጸጉር፣ ቁመና ደስይሉኛል፡፡

ቁም ነገር፡- እነዚህ ሸቀጦች ገበያ ላይ በኪሎ ስንት ናቸው፤ ነጭ ሽንኩርት፣ ኮረሪማ፣ እጣን?

አዚዛ፡- የዛሬውን የገበያ ዋጋ ውሎ ነው? ለነገሩ ጥሩ ነው በአትክልት ተራ ጋር አልፌ ስለመጣሁ /ሳቅ…/ ኮረሪማ መቶ ምናምን ብር ነው፡፡ ነጭ ሽኩርት 38ብር እንደዛ ነው የምንገዛው፤ እጣን /ወደ ልጇ ዞራ እየጠየቀች እጣን ገዝቼ አውቃለሁ እንዴ?/ /ትንሿ የአዚዛ ልጅ እናቷን እያየች አንገቷን በመነቅነቅ ትስቅባታለች/ /ሳቅ…/ እጣን ሁል ጊዜ ከድሬዳዋ ከውጪም ሰው ነው የሚያመጣልኝ እና ዋጋውን አውቄው አላውቅም፡፡

ቁም ነገር፡- በህይወትሽ ውስጥ አስቸጋሪ የሚባል ነገር ሲገጥምሽ ምንድነው የምታደርጊው?

አዚዛ፡- እንደነገርኩሽ ሰነፍ ነኝ፤ ግን ቁጭ ብዬ ለብቻዬ ማሰብ እወዳለሁ፡፡ በቃ ከፈጣሪዬ ጋር እማከራለሁ፤እንደሌላው ሰው ሰው አግኝቼ ማማከር ችግሬን መንገር አልችልም፤ ምክንያቱም ሰው ባገኘሁ ቁጥር አይዞሽ የሚለው ነገር የባሰ ሊያስለቅሰኝ ይችላል ብዬ ነው የማስበው፤ መጠንከር ስለምፈልግ ብቻዬን እሆንና ከራሴ ጋር መክሬ መወሰን ያለብኝን ነገር እወስናለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- በቅርቡ የኦሞ ማስታወቂያ ለመስራት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዳችሁ ነበር፤በዚህ ስራ ምን የተለየ አዲስ ነገር ተማርሽበት? የስራው ሁኔታስ ምን ይመስላል? ክፍያውስ?

አዚዛ፡- ውይ ብዙ ነገሩ በጣም የተለየ ነገር ነው፡፡ ማስታወቂያውን ያሰራው ዩኒ ሊቨር ነው፡፡ ካስት ያደረጉን ቢራቢሮ ኤጀንሲ ነው ፡፡ እዛ ሄደን በቦታው ላይ ተገኝተን ያየነው ነገር እኔ እንግዲህ ሆሊውድን አይቼ አላቅም ልክ በቲቪ ሆሊውድ ውስጥ ፊሊም ሜኪንግ ተብሎ ሲሰራ የምናያቸው ነገሮች አሉ፤ልክ እንደዛ አይነት ፕሮዳክሽን ነበር የነበረው፤ሁኔታው አንድ ማስታወቂያ የሚሰራ ሣይሆን ብዙ የሚሰራ ነው የሚመስለው፡፡ የአንድ ደቂቃም አይደለም የሚመስልሽ፤ በቃ በጣም ጊዜ ወስደው እያንዳንዷን ነገር ተጠንቅቀው ነው የሚሰሩት፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ቀረጻ ላይ ነበርን፤ እያንዳንዱ ነገር ላይ የሰው ኃይል በደንብ ይጠቀማሉ፤ ለያንዳንዱ ስራ እራሱን የቻለ ፕሮፌሽናል ሰው አለ፤ እነሱ አንድ ማስታወቂያ ለመስራት ምንያህል በቴክኖሎጂው እንዳደጉ ስታይ ትደነግጫለሽ፤ለአንድ ማስታወቂያ ይህን ያህል ከተዘጋጁ ፊልም ሲሰሩ እንዴት ሊሆኑ ነው ያስብላል፡፡ በጣም ትልቅ ትምህርት ወስደን ነው የመጣነው፡፡ ክፍያም በጣም ጥሩ ነው የተከፈለን ፤እዛ የቆየንበት ጊዜ የአየር ትኬታችንን ወጪ ጨምሮ በየቀኑ የኪስ ገንዘብ ተሰጦናል፤ከዛ ውጭ ለስራው የተከፈለን ከ40 ሺህ ራንድ እስከ 60 ሺህ ራንድ ነው፡፡ ጥሩ ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- በመጨረሻ ማለትና ማመስገን የምትፈልጊው አካል ካለ?

አዚዛ ፡- ማለት እንኳን የምፈልገው ሳይሆን ማመስገን ነው፡፡ ደስ የሚለው የመጀመሪያ ቃለ መጠይቄን ከዚሁ መጽሔት ጋር ነው ያደረኩት፤አሁንም ደግሞ ከብዙ ዓመት በኋላ በድጋሚ ስላገኘኋችሁ ደስ ብሎኛል፡ ፡ ስለጋበዛችሁኝም አመሰግናለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ሁልጊዜም እየደገፉ እንድቆም ስላደረጉኝ በጣም ነው ማመስገን የምፈልገው፡፡

ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜላችሁን አስመዘግቡ።