ዝቋላ ሀገሩ የት ነው? – ከዳንኤል ክብረት

የዚህች ሀገር ባለቤቶች ሁላችንምካልሆንን በቀር በተናጠል ማንም ባለ ግዛት ሊሆን አይችልም፡፡ ሉሲ አማራ ትሁን ኦሮሞ፣ አፋር ትሁን ሶማሌ፣ ጉሙዝ ትሆን ትግሬ፣ወላይታ ትሁን ጋሞ የሚያውቅ የለም፡፡ በአኩስምና አካባቢው በተገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ነገሥታቱ የሚገዙትን ሀገር ሕዝቦች ስም ይዘረዝራሉ፡፡ እጅግ የሚገርመው ግን ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካና የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የምንሻኮተው ብዙዎቹ ጎሳዎች/ነገዶች ስማችንየለም፡፡ ሁላችንም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከተለያየ ቦታ መጥተን የሠፈርንበት ላይ ረግተን ነው ዛሬ የምንገኘው፡፡ የሕዝብ የሥፍራንቅናቄ የታሪኳ አንዱ መገለጫ በሆነቺው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ሌላውን ሀገርህ አይደለም፣ ክልልህ አይደለም፣ መሬትህ አይደለም እንደማለትያለ ታሪካዊ ኃጢአት የለም፡፡ ትንሽ በታሪክ ወደኋላ ስንጓዝ ዛሬ ክልልና መንደር በመሠረትንበት ቦታ ሌሎች ሲኖሩበት እናገኛለን፡፡አሁን የያዝነው ቦታ ከምእተ ዓመታት በፊት የሁላችንም አልነበረም፡፡ ሁሉም ሠፋሪ ነው፡፡ ነባር መሬቱ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የምታዋጣን የሁላችን እንድትሆንአድርገን ከሠራናት ነው፡፡ እንደ አጥር ሠሪ እንስሳት(territorial animals) ከዚህ በመለስ ማንም አይገባብኝም፡፡ እኔን ያልመሰለውን በዚህ አካባቢ ላየውአልፈልግም የሚለው ሂደት መጨረሻው መበጣጠስ ነው፡፡ የልዩነትን ያህል ተመሳሳይነት ሰፊ አይደለም፡፡ ተመሳሳይነት እጅግ ጠባብ ነው፡፡አንድ ነኝ ብሎ በሚያስብ ‹ብሔርም ሆነ ብሔረሰብ› ውስጥ አያሌ ልዩነቶች አሉ፡፡ የጎሳ፣ የቤተሰብ፣ የአካባቢ፣ የእምነት፣ የፍላጎት፣የርእዮተ ዓለም፣ የጾታ፣ የሀብት ደረጃ፣ የሥልጣን፣ ምኑ ቅጡ፡፡ ሁሉም ተመሳሳዩን ፍለጋ ከሄደ መጨረሻው ግለሰብ ነው፡፡ በሰውነትክፍላችን እንኳን ተመሳሳያቸውን ከሚያገኙት ይልቅ የማያገኙት ይበልጣሉ፡፡ ሰው እንኳን በግለ ሰብእነት ሕልው የሆነው ልዩነትን በአንድኑባሬ ውስጥ በማስተናገድ ችሎታ ነው፡፡ አንድን አካባቢ ‹በተመሳሳይነት ሚዛን› አንድነቱን ጠብቆ ማቆየት አይቻልም፡፡

ያማ ቢሆን ኖሮ ሶማልያን የመሰለጠንካራና የማይናወጥ መንግሥት አይኖርም ነበር፡፡በእምነትና በቋንቋ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይሄ ተመሳሳይነታቸው ግን አንድነታቸውን ሊጠብቅላቸውአልቻለም፡፡ ትኩረታቸው ‹ተመሳሳዩን ብቻ ፍለጋ› በሚለው ላይ ስለነበር ወደ ነገድ፣ ወደ ጎሳ፣ ወደ ጎጥ፣ ወደ ቤተሰብ እየወረዱነው በጦርነት ሲታመሱ የኖሩት፡፡ ለሶማልያ ችግር መፍትሔው ተመሳሳይን መፈለግ አይደለም ልዩነትን ለማስተናገድ መቻል ነው፡፡ ተመሳሳይነትጠባብ ነውና፡፡ ጠባብነት ከሚመነጭባቸው ምንጮች አንዱም ‹ተመሳሳይን ብቻ ፍለጋ› ነው፡፡

የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስገዳም ዛሬ በሚታወቅበት ቦታ ላይ ከተገደመ ከ700 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚያ አካባቢ አያሌ መንግሥታትና ሕዝቦች ተፈራርቀዋል፡፡ገዳሙ ግን መከራ ሲገጥመው እየቀዘቀዘ፣ መከራውን አሸንፎ ደግሞ እንደ ፍግ እሳት እንደገና እየጋመ ከእኛ ዘመን ደርሷል፡፡ ወደዚያገዳም የሚገቡ መነኮሳት ሰማያዊቷን ሀገር የሚናፍቁ፣ ጾምና ጸሎትን ገንዘባቸው ያደረጉ፣ የጻድቁን ቃል ኪዳን የሚጠብቁ ናቸው፡፡የመነኩሴ ሀገር የለውም፡፡ መነኮሳት እንኳን ከእናትና አባታቸው በተወለዱበት ሀገር ቀርቶ ስማቸውና ታሪካቸው በማይታወቅበት ሀገርም‹ሀገርህ የት ነው?› አይባሉም፡፡

ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ግብጽ ውስጥኖረዋል፣ ሊባኖስ ውስጥ ኖረዋል፣ ሶርያ ውስጥ ኖረዋል፤ ግሪክ ውስጥ ኖረዋል፣ ሮም ውስጥ ኖረዋል፡፡ አርመን ውስጥ ኖረዋል፡፡‹ሙሳ አል ሐበሽ› ሶርያ ውስጥ የታወቀ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ነው፡፡ የሶርያ ድርሳናት እንደሚነግሩን ሙሳ (ሙሴ) የዐፄ ገብረ መስቀልልጅ ነው፡፡ ዛሬ ከኢትዮጵያ በላይ ሀገሩ ሶርያ ናት፡፡ በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያውያን መነኮሳት ገዳም በሊባኖስ ውስጥ በቁፋሮተገኝቷል፡፡ ቫቲካን ውስጥ የኢትዮጵያውያን መነኮሳት ማረፊያ ለታሪክ ቆሞ ይታያል፡፡ አርመን ውስጥ ኤቺሚዚን የአቡነ ኤዎስጣቴዎስገዳም ዛሬም አለ፡፡

እንዲያውም ዛሬ የዝቋላ መነኮሳትእንደገጠማቸው ያለ ‹ሀገርህ አይደለም› የሚል ሰውነት ያልገባው ፈተና ሲገጥማቸው ራሱ ፈጣሪ ነበር ይገሥጽላቸው የነበረው፡፡ በተአምረማርያም ላይ የተጻፈውና ኢየሩሳሌም በጦርነት ምክንያት በተዘጋች ጊዜ በ13ኛው መክዘ አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘው ኢትዮጵያዊታሪክ ለዚህ ማሳያ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይህ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች ሁሉ የታወቀውና ዛሬም ድረስ በጎልጎታ መግቢያ በር ላይ ምልክቱንትቶ ያረፈው ታሪክ እንዲህ ነበር የተፈጸመው፡፡
ከዛሬ 700 ዓመታት በፊት አንድኢትዮጵያዊ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዛል፡፡ ከአፍሪካ ምድር የሄደ ብቸኛ ሰው ነበር፡፡ የትንሣኤ በዓል ሲከበር የትንሣኤውን መብራት ከመቃብሩየሚያወጡት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ ግን ብቻውን ስለነበር ማንም ከቁም ነገር አልቆጠረውም፡፡ እንዲያውም በመልኩ ምክንያት ተንቆ ‹ያለ ሀገርህ ለምን መጣህ፣ ውጣ› ተባለ፡፡ እርሱምወጥቶ መግቢያው በር ላይ ሲያለቅስ በላዩ ላይ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ታየ፡፡ ተሳላሚው ሁሉ እምነቱንና ታላቅነቱን አደነቀ፡፡ ብርሃኑየወረደበት ቦታም ተሰንጥቆ እስከ ዛሬ ድረስ ይታያል፡፡ ወደ ጎልጎታ የሚገባም ሁሉ ይሳለመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በሌሎችሀገሮች ሄደው በኪደተ እግራቸው የባረኩት ሁሉ ሀገራቸው ሆኖ መኖራቸው ብቻ አይደለም የሚገርመው፡፡ ከመላው ዓለም የመጡ መነኮሳትምበዚህች ሀገር ውስጥ ‹ከየት መጣችሁ? የማንስ ወገን ናችሁ?›› ተብለው ሳይጠየቁ እንደ ሀገሬው ዜጋ ኖረዋል፡፡ አባ መጣዕ(ሊባኖስ)፣ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ አርባ ሐራ፣ አምስቱ የመንዝ ቅዱሳን፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እጨጌ ዕንባቆም፣ ማኅበረ ጻድቃን፣ እነዚህሁሉ ኢትዮጵያ መጥተው ኖሩ፡፡ እዚህችም ሀገር ዐረፉ፡፡ ገዳማቸው ገዳማችን፣ ታሪካቸው ታሪካችን ሆነ፡፡

ዛሬ ያ ሁሉ ተረስቶ ነው የዝቋላገዳም መነኮሳት ዝቋላ ‹ሀገራችሁ አይደለም›› የተባሉት፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውያን አይደሉምን? እዚህ ቦታኮ ከ700ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ እዚህ አካባቢ ከ700 ዓመታት በፊት የነበሩ ዜጎች አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሲመጡ ‹ኦቦ› ብለው ተቀበሏቸውእንጂ ‹ሀገርዎ አይደለም ይውጡ› አላሏቸውም፡፡ ዛሬ በሥልጣን ላይ ካሉትና ገዳሙን በኢሬቻ መተካት ከሚፈልጉት ሰዎች ይልቅ ያኔየነበሩት ሰዎች ልበ ሰፊዎች፣ አስተዋዮች፣ የሰውነት ክብር የገባቸው፣ የሀገርን ትርጉም የተረዱ፣ ከዘር ይልቅ ለሰውነት ታላቅ ቦታየሚሰጡ፣ ሰውን በምግባሩ እንጂ በቋንቋውና በቀለሙ፣ በዘሩና በአጥንቱ የማይለኩ ነበሩ፡፡
የአንድ ክልል የቱሪዝም ቢሮ አንድንገዳም ነጥቆ በገዳሙ ሥርዓት የማይፈቀድ ሌላ እምነትን ለመተካት ማነው ሥልጣን የሰጠው? በዚያ ገዳም ክልል ውስጥ ሊከበሩ የሚገባቸውሃይማኖታዊ በዓላትንስ በምን ቀኖናዊ ሥልጣኑ ነው የሚወስነው? ለምንስ ነው እነዚህን መነኮሳት እየጠራ የሚያስፈራራው? ይኼ ገዳምኮዘመናትን ሁሉ ተሻግሮ እዚህ እንዲደርስ ያደረገው በእምነቱ ጽኑ የሆነው የአካባቢው የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ ሕዝቡ እዚያ ገዳም ለጸሎትየተጉ መነኮሳት እንደሚገኙ፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የቃል ኪዳን ቦታ እንደሆነ የሚያምን ነው፡፡ በየዓመቱ በጥቅምትና በመጋቢት5 ወደ ቦታው በመሄድ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል ከሚያከብረው ሕዝብ አብዛኛው የአካባቢው የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ ታድያእነዚህ አካላት ይህንን አስተሳሰብ ከየት አመጡት?

ይኼ ተልዕኮ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ አይደለም፡፡ የጠብ ጫሪነት ተልዕኮ ነው፡፡ በሰላም የኖረውን ሕዝብ የማበጣበጥ ተልዕኮ ነው፡፡ መጋቢት 5 ቀን በአቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ በዓል ‹ኢሬቻን በጠበሉ ቦታ እናከብራለን፣ ሐውልት እናቆማለን› ብሎ በሕዝብ መገናኛ ማወጅ ጠብ ያለሽ በዳቦ እንደማለት ነው፡፡ማንኛውም ሰው ያጸድቀኛል ብሎ ያሰበውእምነት ሊከተል ይችላል፡፡ ሁለት እምነቶች ግን በአንድ ቤተ መቅደስ ሊመለኩ አይችሉም፡፡ ሁሉም የየራሱን ነው መከተል ያለበት፡፡‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣልና አልጋሽን ልቀቂለት› የሚለው ብሂል ግን ዛሬ የሚያዋጣ አይመስልም፡፡ የሃያ አንደኛው መክዘ ኢትዮጵያንምበጤና አውሎ አያሳድራትም፡፡ በዝቋላ ገዳም ላይ የተጀመረው ርስትን የመንጠቅ ሥራም በዝቋላ የሚያበቃ አይሆንም፡፡ ‹መንግሥታዊ ሃይማኖትየለም› ከተባለ መንግሥታዊ መዋቅሮች አንድን እምነት ደግፈው ሌላውን እምነት ለመጫን እንዴት ቻሉ?

ስለዚህም
1. ቅዱስ ፓትርያርኩ ሁኔታውን በተመለከተ ለሚመለከታቸው ድብዳቤ መጻፋቸው የሚገባ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ግን ይህንን ነገር በዕንቁላሉ ለመቅጨት መወሰንና መሥራት ያለበት ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ መነኮሳቱና ሀገረ ስብከቱ የጻፏቸው ደብዳቤዎች በገዳሙ ስለደረሰው መከራ ብዙ የሚናገሩትነገር አለ፡፡ በስብሰባዎች የደረሰባቸው ጫና፣ በየጊዜውም የሚደርስባቸውን እንግልት ገልጠውታል፡፡ ሲኖዶሱ ገዳማትን ከመጠበቅ የሚቀድም ሌላ ኃላፊነት የለውም፡፡

2. ምእመናንም ገዳሙን በንቃት መከታተልና በተለይም በመጋቢት 5 ቀን በክብረበዓሉ በመገኘትና በዓሉን በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በማክበር ለቅዱሱ ሥፍራ ያለንን ፍቅር፣ ለመነኮሳቱ ያለንን የዓላማ አንድነት፣ሁላችንንንም ለሚያቅፈው ኢትዮጵያዊነት ያለንንም ክቡር ሥፍራ ማሳየት አለብን

3. መንግሥትም በጥባጭ ካለ ጥሩ ለመጠጣት አይቻልምና በሚዲያ የተሳተው በሚዲያ፣ በአሠራር የተበላሸውም በአሠራር እንዲታረም ማድረግ ይገባዋል፡፡10997517_791126460966050_8641839399444988911_n

551560_791126484299381_4950994060407097428_n

10407949_791126477632715_8979969589721469085_n

10409013_791126490966047_1857581258527330205_n