ከ28 ሚሊየን ብር በላይ የግንባታ ዕቃዎች በማጉደል ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ በ6 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ Man sentenced to 6 years for stealing 28 mil birr worth of construction material
ከ28 ሚሊየን ብር በላይ እምነት በማጉደል የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ በ6 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በ7 ሺህ ብር እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ሰሞኑን በዋለው ችሎት ውሳኔ አስተላለፈ።
የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በግለሰቡ ላይ የመሰረተው ክስ እንደሚያስረዳው ተስፉ በለጠ የተባለው ተከሳሽ የተንዳሆ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ንብረት አስተዳደር መጋዘን ሰራተኛ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ከግንቦት 1999 ዓ.ም እስከ ህዳር 2004 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተረከባቸውን የግንባታ ዕቃዎች በማጉደል ወንጀሉን ፈጽሟል።
ግለሰቡ በዚህ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለተንዳሆ ስኳር ልማት ኤጄንሲ የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች የሚሆን ቤት ለመገንባት የሚውል በቁጥር 529 የሚሆኑ፣ ግምታቸው 28,117,618 ብር (ሃያ ስምንት ሚሊዮን አንድ በመቶ አስራ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ አስራ ስምንት ብር) የሆነ የተለያዩ የግንባታ ዕቃዎችን አጉድሎ ለግል ጥቅሙ ማዋሉን ከክስ መዝገቡ ለማወቅ ተችሏል።
ተከሳሹም እምነት በማጉደል የሙስና ወንጀል ፈጽሟል በሚል ኮሚሽኑ የመሰረተበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ በ6 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በብር 7ሺህ እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሊያስተላልፍ መቻሉን ከኮምሽኑ ገኘነው ዜና ያስረዳል።
በተያያዘ ዜና ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሀብት አስተዳደር የሥራ ሂደት አስተባባሪ፣ በዚሁ ጽ/ቤት የጠቅላላ አገልግሎት ጊዜያዊ ቡድን አስተባባሪ እንዲሁም አንድ በግል ሥራ የሚተዳደር ግለሰብ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የድሬ ዳዋ ምድብ ችሎት ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ አስተላለፈ።
በፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በግለሰቦቹ ላይ የመሰረተው ክስ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ መክብብ ቦጋለ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሀብት አስተዳደር የሥራ ሂደት አስተባባሪ፣2ኛ ተከሳሽ መክብብ የኋላሸት በጽ/ቤቱ የጠቅላላ አገልግሎት ጊዜያዊ ቡድን አስተባባሪ እና 3ኛ ተከሳሽ ፍጹም ሰይፉ ከተባለ በግል ሥራ ከሚተዳደር ግለሰብ ጋር በመመሳጠር ወንጀሉን ፈጽሟል።
በወንጀል ድርጊቱ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በጨረታ ተሳታፊ ያልነበረን 3ኛ ተከሳሽ ከግዥ ሕግ ውጭ ያለአግባብ በመጥራት ያለምንም ውል በኮንትሮባንድ የተያዙ ዕቃዎችን እንዲያጓጉዝ በማድረግ እንዲሁም ለአገልግሎቱ እጅግ የተጋነነ የክፍያ ጥያቄዎችን ተቀብለው ለ3ኛ ተከሳሽ እንዲከፈል ማድረጋቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
በዚህ ሁኔታ 3ኛ ተከሳሽ ቀድሞ በሌላ አካል ተጭነው ወደ መጋዘን የገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ጭምር ራሱ የጫነ በማስመሰል እንዲሁም በአንድ ጊዜ የተጫኑ ዕቃዎችን በሁለትና በሦስት ጊዜ ምልልስ የተጫኑ በማስመሰል በሕገ-ወጥ መንገድ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የመንግስት ገንዘብ ያለአግባብ መውሰዱን ከክስ መዝገቡ ለማወቅ ተችሏል።
ተከሳሾቹ የኮሚሽኑ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመሰረተባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው 1ኛ ተከሳሽ መክብብ ቦጋለ እና 2ኛተከሳሽ መክብብ የኋላሸት እያንዳንዳቸው በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 5 ሺህ፣ 3ኛ ተከሳሽ ፍጹም ሰይፉ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 10 ሺህ እንዲቀጡ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የድሬ ዳዋ ምድብ ችሎት ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ማስተላለፉን ከፌዴራል የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮምሽን የተገኘ መረጃ ያስረዳል።
Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
በ