ባቡር በሚያልፍባቸው መስመሮች አንበሳ አውቶቡስ አገልግሎቱን እንደሚያቋርጥ አስታወቀ

በ 

መካከለኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት

የሚሰጥ የአውቶቡስ ትራንስፖርት ይጀምራል

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ወደስራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተከትሎ ባቡሩ በሚያልፍባቸው ያሉትን መስመሮቹን ሊያነሳ ነው። በዚሁ ዙሪያ ለሰንደቅ ማብራሪያ የሰጡት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አሰፋ ወደስራ ለመግባት አንበሳ አውቶቡስ የራሱን ጥናት ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይም የታሰበውን የመስመር ለውጥ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች ጋር የሚደረግ አንድ የምክክር ስብሰባ የሚያስፈልግ መሆኑን አመልክተዋል። “ባቡሩ በሚያልፍባቸው መስመሮች የአንበሳ አውቶቡስ አገልግሎትን መስጠት የሀብት ብክነት ነው” ያሉት አቶ በድሉ፤ በዚሁ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ የተያዘ መሆኑን ገልፀውልናል።

በሌላ ዜና በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንሰፖርት ችግር ለመፍታት ከታክሲ፣ ከአንበሳ አውቶቡስና ከሀይገር ባስ እንደዚሁም ከድጋፍ ሰጪ የትራንሰፖርት ስምሪቶች አገልግሎቶች በተጨማሪ መካከለኛ ገቢ ላለው የህብረሰብ ክፍል የሚያገለግሉ አውቶቡሶችም ወደ ስራ ሊገቡ መሆኑ ታውቋል። ለዚህ አገልግሎት የሚውሉትን አውቶቡሶች የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን የሚገጣጥም ሲሆን እነዚህኑ አውቶብሶች በባለቤትነት በማስተዳደር የትራንሰፖርት አገልግሎቱን የሚሰጥ ድርጅትም በቀጣይ የሚቋቋም መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወደ ስራ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ሶስት መቶ አውቶቡሶች ሲሆኑ አውቶቡሶቹን ይገጣጥማል ተብሎ የሚጠበቀው ብረታ ብረት ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን፤ በአሁኑ ሰአት ለመንግስት ሰራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት እየገጣጠማቸው ያሉትን አውቶብሶች ሙሉ በሙሉ ያላጠናቀቀ በመሆኑ ለህዝብ ትራንሰፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡትን አውቶብሶች መገጣጠም ያልጀመረ መሆኑ ታውቋል።

ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽኑ ለመንግስት ሰራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ 410 አውቶብሶችን መገጣጠም የሚጠበቅበት ሲሆን እስካሁን ድረስ 190 አውቶብሶችን ገጣጥሞ ወደ ስራ ያስገባ መሆኑ ታውቋል። አሁን እየገጣጠማቸው ያሉትን የመንግስት ሰራተኞች አውቶብሶች እንዳጠናቀቀ በቀጣይ እነዚህን አዳዲስ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶችን የሚገጣጥም መሆኑ ታውቋል።

     መካከለኛ ገቢ ያለቸውን የህብረሰብ ክፍሎች የተባሉት የህዝብ ትራንስፖርት አውቶብሶች፤ ከመቀመጫ ጀምሮ ያላቸው የውስጥ አገልግሎት ዘመናዊነትን የተላበሰ መሆኑ ታውቋል። በአሁኑ ሰአት አንበሳ አውቶቡስ ዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላላቸው የህብረተስብ ክፍሎች በስፋት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በቀጣይ የሚቀርቡት አውቶብሶች ግን የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት አማራጭ ለማስፋት በማሰብ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።