ቦርዱ የፈለገው የምርጫው ላይ ኢህአዴግን እንድናጅበው እንጂ እንድንፎካከረው አይደለም ሲል ራሱን ከምርጫው ሊያገል እንደሚችል ምንጮች ለኢትዮ-ምኀዳር አስታወቁ፡፡

የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አሳወቁ::
ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ ባለመስራቱና የገዢውን ፓርቲ ዓላማና ፍላጎት የሚያስፈጽም ተቋም ሆኖ በምርጫ መወዳደር ለተቋሙ ኢ-ፍትሃዊ ተግባር እውቅና መስጠት ነው ያሉት በአቶ አበባው መሐሪ የሚመራው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ስብስብ የህዝብ ግኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋሁን አለምነው እራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አስታወቁ፡፡
መኢአድ እንደ ፓርቲ በምርጫው የሚሳተፍ ቢሆንም፣ እኔ ግን በግሌ ከምርጫው ራሴን አግልያለሁ ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ፓርቲው የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ሊብራል ዲሞክራሲ በመሆኑ ማንኛውም ሰው የራሱን ፍላጎት በነጻነት ማራመድ ስለሚችል፤ በእኔ እምነት አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ መሳተፍ ተገቢ ሆኖ እኔ አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ምርጫውን አልሳተፍም ብለዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የአቶ አባውን ሕጋዊ ኘሬዝዳንትነት አላረጋግጥም እያለ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ውህደትን ሲያሰናክልብንና ብዙ ሲያንከራትተን ከቆየ በኋላ፣ ከሌሎች ተለጣፊ ፓርቲዎች ጋር በህዝቡ ዘንድ አሜኔታ እንዳይኖር ሲሰራ ኖሮ አሁን እጩ ለማስመዝገብ 6 ቀን ሰጥቻችኋለሁ ተወዳዳሪ አስመዝግቡ ማለቱ ቀልድ ነው፡፡

በእኛ ፓርቲ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሴራ መስራቱን እና የምርጫ ቦርድ ተቋም እንደተቋም በአዎንታዊ ጎኑ ሲቀየር ነው እንጂ አሁን ራሱን ገለልተኛ ሳያደርግና ዳኛውም እራሱ በሆነበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት የገዢው ፓርቲ አጃቢ ከመሆን በስተቀር ምንም ትርጉም እንደሌለው ተገንዝቤያለሁ ብለዋል፡፡ እጩዎቻችንም እንዳይመዘገቡ የቀበሌ መታወቂያችሁ አልታደሰም፣ መታወቂያ የላችሁም የሚል ሰንካላ ምክንያት እያቀረበ ተመዝጋቢ እጩዎቻችንም ወደ ቀበሌ ሄደው መታወቂያ ለማሳደስም ሆነ ለማውጣት በሚሄዱበት ወቅት ቀበሌው ስለሚዘጋ ማውጣት አልቻሉም፤ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ያስመዘገብናቸውን እጩዎችም እየሰረዙብን ነው፤ ይሄ ሆን ተብሎ የተደረገ ሴራ ነው፤ ምርጫ ቦርድ የገዢው ፓርቲ መጠቀሚያ በሆነበት ሁኔታ ወደ ምርጫው መግባት በግሌ ተስፋ ስለሌለው አልሳተፍም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመኢአድ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በተለይ ለኢትዮ-ምህዳር እንደገለጹት መኢአድ ምርጫ ቦርድ አስወጣው ሳይሆን፣ ራሱ መኢአድ ከምርጫው ወጣ እንዲባል ተቋሙ እየሰራ በመሆኑ፣ በምርጫ ጣቢያው የምናቀርባቸው እጩዎች የትውልድ ቦታቸው እዛው የሆነና እና ተቀባይነት እንዳላቸው ምርጫ ቦርድ በማወቁ በገዢው ፓርቲ ድምጽ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ በማለት ማጽዳት ስለፈለገ እንዳይመዘገቡ እና የተመዘገቡትም እንዲሰረዙ በማድረጉ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ስለሆነብኝ መሳተፉ ለገዢው ፓርቲ እውቅና እንደመስጠት ይቆጠራል በሚል ነው ራሴን ከምርጫ ያገለልኩት ብለዋል፡፡ መኢአድ ከምርጫው ራሱን ሊያገል ነው በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ን እንዲመራ ሕጋዊ እውቀና የተሰጠው በአቶ አበባው መሐሪ የሚመራው የመኢአድ ስብስብ፣ ቦርዱ የፈለገው የምርጫው ላይ ኢህአዴግን እንድናጅበው እንጂ እንድንፎካከረው አይደለም ሲል ራሱን ከምርጫው ሊያገል እንደሚችል ምንጮች ለኢትዮ-ምኀዳር አስታወቁ፡፡

ገዢው ፓርቲ በእነ አቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲን ከምርጫ ጫወታ ውጪ ሲያደርግ መኢአድን እንደ “መናጆ” አንድ ላይ ተጠቅሞበታል፤ አሁን በመንግሥት የተፈለገው መኢአድ መዋቅሩንና አባላቱን ሳያካትት እንደ “የምርጫ ጊዜ አጃቢ ፓርቲዎች”..፣ ኢህአዴግን ለምርጫው እንዲያጅብ ነው የተፈለገው ያሉት የፓርቲው ምንጮች የፓርቲውን ሥም ላለማጉደፍ እና ምርጫ ያልሆነ ምርጫን ለመቀበል አመራሩ ስለተቸገረ ራሱን ከምርጫ ውድድር ውጭ ማድረግ ጥሩ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል መኢአድን እንዲመራ በቦርዱ ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው የአቶ አበባው አመራር፣ ቦርዱ ሕጋዊ እውቅናውን ለመስጠት ሆን ብሎ ጊዜውን አዘግይቶብናል ያለ ሲሆን፣ ለምርጫ ቦርድ የምርጫ እጩዎችን የማቅረቢያ ጊዜ በአንድ ሣምንት ይራዘምልን ሲል ያቀረበውን አቤቱታ ተቀባይነት አለማግኘቱን ሊቀመንበሩ አቶ አበባው መሐሪ ለኢትዮ-ምኀዳር መግለጻቸው የታወሳል፡፡

አሁን ባለው የቅድመ ምርጫ ሂደት ደስተኛ ያልሆነው የአቶ አበባው ስብስብ፣ ፓርቲው በአዲስ አበባ ለእጮነት ያቀረባቸውን አብዛኛዎቹ በምርጫ ቦርድ ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2007 ዓ.ም ውድቅ እንደተደረገበት የገለጹት የፓርቲው ምንጮች፣ በየክልሉም ለእጩነት ያቀረባቸው አባላት ውድቅ እየተደረገ፣ እየተዋከቡና እየታሰሩ እንደሚገኙ ለኢትዮ-ምኀዳር ገልጸዋል፡፡ የመኢአድ የምዕራብ ቀጣና ኃላፊ አቶ ብሩ ደሲሳ በሚወዳደሩበት አሶሳ ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2007 ዓ.ም ታስረዋል ያሉት የፓርቲው ምንጮች፣ በደቡብ ክልል ጋሞጎፋ ዞን፣ ከፋ-ቦንጋ ዋቻ- ቀና በኦሮሚያ ግንደበረት፣ በሀረር ጀጎል፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ – አሶሳ፣ ወላይታ ሶዶ- ቦሎሶ ሶሮ ምርጫ ጣቢያ፣ በአማራ ክልል፡- በጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ የፓርቲው እጩ ተወዳዳሪዎች ከምርጫ ውድድር እንዲወጡ ሆን ተብሎ ውድቅ እየተደረጉ፣ እንግልት እየበዛባቸውና እየታሰሩ ነው ብለዋል፡፡