ዶ/ር አሸብር – “ኢህአዴግ የምወዳደርበትን አካባቢ ቢተውልኝ የሚጐዳው ነገር አይኖርም”

የተከበሩ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በጥርስ ህክምናው ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብት ሲሆኑ በ2002 ምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ በፓርላማ ብቸኛ የግል እጩ ሆነዋል፡፡ ዶ/ር አሸብር በፓን አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ በም/ፕሬዚዳንትነት እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡ በግንቦቱ ምርጫ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡ አዲስ አድማስ:- በግንቦቱ ምርጫ በእጩነት ይወዳደራሉ? ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ:- በምርጫው ለመወዳደር ጓደኞቼ ፊርማ አሰባስበውልኝ ለቦርዱ አስገብተናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተወዳዳሪነቴን የማረጋግጠው የእጩነት ደብተሬን ስወስድ ነው፡፡ ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ አድርጌያለሁ፡፡ አዲስ አድማስ:- የት ነው የሚወዳደሩት? ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ:- በከፋ ዞን፣ ቦንጋ ዲንቦ ጓታ ምርጫ ጣቢያ ነው የምወዳደረው፡፡ አዲስ አድማስ:- የግል ተወዳዳሪ የመሆን ጥቅሞችና ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ:- አብዛኛው ጊዜ ፓርቲዎች ሚዲያ ተጠቅመው ራሳቸውን የማስተዋወቅ እድል አላቸው። ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ ይጠቀማሉ፤ ለምርጫው ከመንግስት በጀት ያገኛሉ፡፡ ለግል ተወዳዳሪዎች ግን እነዚህ ሁሉ የሉም፡፡ እኛ የግል ተወዳዳሪዎች በራሳችን ወጪ መቀስቀስ፣ በራሳችን የቅስቀሳ አውታር መጠቀም ስለሚጠበቅብን ብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አንድ ግለሰብ ለመወዳደር ሲፈልግ፣ በዚህ ደረጃ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ አዲስ አድማስ:- ጥቅሞቹስ? ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ:- ራሱ ኢህአዴግን ብትወስድ አባላቱ ከ10 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ከህዝቡ 70 እና 80 በመቶው የፓርቲ አባል አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ ህዝቡ እኛን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ከየትኛውም ፓርቲ ገለልተኛ መሆን ለአስተያየትም ለፍርድም ይጠቅማል፡፡ ብዙ ሰው ወደ ፓርቲ አይጠጋም፤ለዚህም ምክንያቱ ገለልተኛ መሆን ስለሚፈልግ ነው፡፡ የግል ተወዳዳሪ መሆን ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ግለሰቡ ራሱ በራሱ ነው ወሳኝ የሚሆነው፡፡ […]