“ህወሓት ተተኪ የማፍራት ችግር አለበት” – አቦይ ስብሃት ነጋ
Highlights: * “አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብ የሚሉ ሁሉ ህወሓትን ይጠሉታል።” * “ከአሜሪካንና ከእሥራኤል ጋር ያጣላን ፕሮግራማችን ነው።” * “ተወልደ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር፤ ስዬም የመከላከያ ሚኒስትር እያሉ ኤርትራ ነፃነቷን ስታገኝ የአሰብ ጉዳይ ያለቀለት ጉዳይ ነው። ወንበር ፍለጋ ነው እንጂ የኤርትራ ጉዳይ ሰበብ ሊሆን አይችልም።” * “ህወሓት…… ለስድስት ወር ያህል ዝብርቅርቅ ያለ ፕሮግራም ተቀምጦ ነበር። ኢትዮጵያዊነትም አለ። ትግራይነትም አለ። ይሄ ጉዳይ በስድስት ወር ውስጥ እንዲጠራ ተደረገ።” (ጌትነት ምህረቴ) የመምህርነት ሙያቸውን ትተው ነበር በ1967 ዓ.ም ወደ ትግል የተቀላቀሉት። ከህወሓት ነባር ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው፤ አቦይ ስብሃት ነጋ። ህወሓት የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ዝግጅት ክፍላችን በህወሓት አመሠራረት፣ ዓላማና የትግል አግባብ ዙሪያ ከአቦይ ስብሃት ነጋ ጋር ያደረግነውን ቃለ- ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ይዘን ቀርበናል። አዲስ ዘመን፡- የንጉሡ ሥርዓት ተገርስሶ ወታደራዊ ሥርዓት ሲመጣ የነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ ምን ይመስላል? አቦይ ስብሃት፡- የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት የጣለው ሕዝቡ ነው። የጣለው ደግሞ መውደቅ ስለነበረበት ነው። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታው የከፋ ነበር። በሌላው ሀገር ኢንዱስትሪው ማቆጥቆጥ ጀምሯል። የአፄው ሥርዓት በጣም ያከረረ ፊውዳል ስለነበር በሀገሪቷ ልማት የሚባል ነገር አልነበረም። ትምህርትም ቢሆን እንደ ጠበል የሚንጠባጠብ በጣም የተወሰነ እንጂ የሰፋ አልነበረም። ሕክምናም እንደዚሁ። ሀገሪቷ ለማንኛውም አደጋ የተጋለጠች ነበረች። ሕዝቡ በረሃብ እየሞተ «ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ናት» ይባል ነበር። ሕዝቡ ኑሮው አስከፊ ሆኖ ሳለ በወቅቱ የሚነገረው ግን ኢትዮጵያ ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደገች ናት […]