ስለ ኮንዶሚኒየም በእኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ Condominium home lottery winner shares how he lost his house
የወርሐ መጋቢት የ7ተኛ ዙር የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሲወጣ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ የምኖረው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 5 ቀበሌ 07 ውስጥ ሲሆን፣ ዕጣውን ያየሁት ግን በድንገት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20 የሕዝብ መዝናኛ ክበብ ጊቢ ውስጥ ተለጥፎ ነው፡፡
የዚያች ቀን ደስታዬ ቢለካ ለ22 ዓመት በኪራይ የኖርኩበትን የስቃይ ዘመን በደቂቃ ያጠፋው ስሜት መግለጽ እስከማይቻለኝ ድረስ ነበር፡፡ ወደ ሰፈሬ ስሄድ በመኪና እንዳልሆነ አውቃለሁ 20 ግን ደቂቃ አለፈጀብኝም፡፡ ቅርብ ለሆኑ ጓደኞቼ ሁሉ ስልክ እየደወልኩ ነገርኳቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የደስታዬ ተካፋይ ሆኑ፡፡ እድለኛነቴን የነገሩኝ የማውቃቸውም፣ የማላዋቃቸውም ነበሩ፡፡
ታዲያ ቀኑ ደረሰና ክፍለ ከተማ ቅረቡ በተባለበት ጊዜ ካርዴን ይዤ ቀረብኩ፡፡ ጀሞ የሕንፃ ብሎክ 3 -15/11፣ የቤት ቁጥሩ ደግሞ 120/60 ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ፎርም ተሰጥቶኝ ስሞላ በፎርሙ ላይ በአምስት ቀን ውስጥ ባንክ ቅድመ ክፍያ ከፍለው ይምጡ ይላል፡፡ ባለ ሁለት መኝታ፣ ካሬ ሜትሩ 70.72 ነው፡፡ ቅድመ ክፍያው ደግሞ 33,000 ብር ከልዩ ልዩ ወጪዎች ጋር በድምሩ 36,000 ብር ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ በጣም ትልቅ ሥጋት ተፈጠረ፡፡ ይህ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ለእኔ ከ1,000 ብር በታች ደመወዝተኛ ለሆነ ሰው የሚቀመስ አይደለም፤ ተራራ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎችን ጠየኩ፣ በጣም ግራ ተጋባሁ፡፡ ደስታዬን የሚያደበዝዝ እየሆነ መጣብኝ፡፡ ክፍለ ከተማ ሄጄ ችግሬን ልገልፅ ሞከርኩ መፍትሔ ግን አላገኘሁም፡፡ በዚያው ሳምንት መክፈል ያልቻሉ አንድ ወር ጊዜ ይሰጣቸውና ከዚያ በኋላ እንደገና ዕጣ ይወጣበታል፤ ባለዕጣነታቸውም ይሰረዛል የሚባል ነገር እየታሰበ መሆኑን ሰማሁ፤ አነበብኩም፡፡ ደስታዬ ሁሉ ወደ ሐዘን ተለወጠ፡፡ መሸብኝ፣ ተስፋ አጣሁ፡፡ ምርር ብዬ አለቀስኩ፡፡ ለተቀጠረንበት ቀን ሦስት ቀን ሲቀረው ደግሞ አንድ አዲስ ነገር ተፈጠረ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር፣ አዋቂና የትውልድ አደራ ያለበት፣ ለብዙኃን የሚያስብና የሚያዝን ተቆርቋሪ ከሚፈጠርበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ሰው ተገኘ፡፡ እኔ መፍትሔ አለኝ አለ፡፡ ባዶህን ከምትወጣ በብድር ትፈርምልኛለህ፤ ገንዘብም ታገኛለህ እኔም እጠቀምበታለሁ አለና አግባባኝ፡፡ ችግር ቢፈጠርስ ስለው ለእኔ ተወው አለኝ . . . ዕውቀት አለው፣ ዘመድ አለው፣ ገንዘብም አለው አልኩና አመንኩት፡፡ ዘመዶቹ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ምሁራንና ደላሎች ጭምር ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ዕውቂያው ብዙ ነው፡፡ ሀብታሞች፣ ልዩ ልዩ የመሥሪያ ቤት ሰዎች አሉት፡፡ በትርፍ ጊዜውም ያስተምራል በጥሩ ቦታ ወታደሮችን፣ መኮንኖችን አባሎችን ሳይቀር ሌትም ቀንም ለሥጋና ለነፍሳቸው እንዲሁም ለአገራቸው የሚፀልዩትን ክርስቲያኖችም ያስተምራል፡፡
ይህ ሰው ሰዎችን ይጎዳል ቢባል ተናጋሪውን ነው ሐሰተኛ የሚያስብለው፡፡ ይህ ግለሰብ ደስ ያለውን የገንዘብ ቁጥር መጠን ጠቅሶ አስፈረመኝ፡፡ ይህን አድራጎቴን ብዙዎች ትልቅ ስህተት ብለው ይፈርጁታል፡፡ አንድ መቶ ሺሕ ብርም ሰጠኝ፡፡ መጀመርያ ደስታ ከዚያ በኋላ ሐዘን፣ አሁን ደግሞ ተመልሶ ደስታ መጣ ተባለ፡፡ ይኸው ደስታ ግን ከጥቂት ወራት ሳይቆይ ግለሰቡ የተሰጠኝን ገንዘብ አብረን ባንክ ያስገባነውን በፍርድ ቤት ቀድሞ በማሳገድ ብድር አበድሬው አልመለሰልኝም በማለት የክስ ቻርጅ ሰጠኝ፡፡ ደስ የሚለው ገንዘቡን አልነካሁትም ነበር፡፡ ያልመለስኩት ግን መጠኑ ልብ ወለዳዊ የሆነውና ያስፈረመኝን ነው፡፡ በቀጠሮው ቀን ስሄድ የመከላከያ ማስፈቀጃ እንጂ መልስ አልተባልክም ተብዬ ወዲያው ተፈረደብኝ፡፡ ዕድለኛ ነው፡፡ ለብዙዎቹ ፍርድ ቶሎ አይደርስም እሱ ግን በአሥር ቀን ውስጥ BPR ችሎት ነው ፈጥኖ የደረሰለት አሉ፡፡ ስለዚህ ተፈረደለት፡፡ የሰጠኝንም ገንዘብ እንዲወስድ ለባንኩ ተጻፈለት፡፡ ቤቱም ገንዘቡንም ለራሱ አደረገ፡፡
በተጨማሪም የሚያስፈራሩ፣ መደበኛ ሥራቸውን ወደ ጎን አድነው የሚያንገላቱትን ላከብኝ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ገባሁ፡፡ ይኽም አልበቃ ብሎ ሌቦችና ወንበዴዎች የእኔን ቤት አጥንተው ልብሴን፣ ሰነዴንና የትምህርት ቤት ማስረጃዬን፣ በቤት ውስጥ ያሉኝን ቁሳቁሶች ሁሉ አስጠርጎ አስወሰደብኝ፡፡ የእኔ ዕጣ ፈንታ እንደነገርኳችሁ ማዘን ብቻ ነው፡፡ ወደ ጎፋ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አመለከትኩ፡፡ በCR-679 ተመዝግቦ ነበር እንዲሁ ቀረ እንጂ፡፡ በወገኔ ላይ ምንም ባይደርስበት ደስ ይለኛል፡፡ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ቤቴን፣ የልጆቼን ዕጣ ፈንታ፣ ባለቤቴን፣ የሰጠኝን ገንዘብና የነበረኝን የራሴ የሆኑትን መጠቀሚያ ዕቃዎችና ሽልማት ጭምር አጣሁ፡፡
ዛሬ እጥፍ በበዛ ሐዘን ላይ ነኝና የኮንዶሚኒየም ዕጣ የሚደርሳችሁ ወገኖቼ ትምህርት እንዲሆናችሁ በሚል ሕይወቴን አካፈልኳችሁ፡፡
(ተጎጂ አማረ መኮንን ተሰማ፣ ከአዲስ አበባ)
Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
