ሰዶ ማሳደድ ያማረው ዶሮን በቆቅ ይለውጣል! – ከአቶ ሰውየው

maxresdefaultባለፈው ወር፣ በየፓልቶክ መድረኩ (ለምሳሌ ከረንት አፌር – ዴሞን በዲሞት ፎር እያለች በቀይ ሽብሩ ወቅት የደርግ የነጻ እርምጃ ቀስቃሽና ለፍርድ ልትቀርብ የሚገባት አዛውንት ማለትም ሙያዬ ምሥክርና ሌሎችም) አማካይነት፤ የተለያዩ ራዲዮና ድህረ-ገጾችና የመሳሰሉት የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት በኢሕአፓ ለይ የተነጣጠረ ልዩ ዘመቻ ተከፍቷል። ለዚህ ወገራ በድንጋይ አቀባይነት በሰፊው የተሰማሩት ደግሞ በሚያሳዝን ሁናቴ አሕአፓ ነበርን (ነን) የሚሉን ወገኖች ራሳቸውን የእርማት እንቅስቃሴ፣ ትንሳኤ ኢሕአፓና ያው ከጥቂት ዓመታት በፊት ድርጅቱን ጥለው የወጡ ኢሕአፓ ዴ ነን የሚሉን ወገኖች ሆነው መገኘታቸው በጣም አሳዝኖኛል። በየድረ-ገጹ የተበተኑትን ሁለት በራሪ ወረቀቶችና ሁለት በቀጥታ የኢሕአፓን መሪ ኢያሱ ዓለማየሁን የሚያጣጥሉ ጽሑፎች፣ አንደኛው ኢያሱ የእንግሊዝኛ መጽሐፉ በአማርኛ በአዲስ አበባ መተርጎምና በዋቢ ሸበሌ መመረቅ አስመልክቶ ኢያሱ ከወያኔዎች ጋር እየሠራ ነው ዓይነት ክስ የሚያቀርብ ሌላው ደግሞ በእንግሊዝኛ በኢድን የኢሜል ሊስትና በተለያዩ አቅጣጫዎች የተበተነውን የእንግሊዝኛ መጣጥፍ እነሆ ከዚህ ጽሑፍ ግርጌ አባሪ አድርጌ ባቀርብኳቸው ላይ የግል አስተያየቴን አነሆ አቀርባለሁ።

በበኩሌ ኢሕአፓን እናጠናክር የሚሉን ወገኖች የሚከተሉት ሂደት በእርግጥ የማጠናከር ወይስ የማጥቃትና የማጥላላት ዘመቻ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘትና አቋም መያዝ ለድርጅቱ ከፍተኛ አክብሮት ላለን የድርጅቱ ደጋፊዎች ነን ለምንል ሁሉ ተወደደም ተጠላ ጊዜው የሚጠይቀው ግዳጃችን ነው። በሁለት ቢላ መብላት አይቻልም። በተለይም ከላይ እንደምሳሌ የጠቀስኳቸው ዓይነት መጣጥፎች የሚሰዱብን ወገኖች የሚፈልጉት ምንድር ነው? የውሸት ጋጋታውንስ ምን አመጣው? ለምሳሌ አቶ ኢያሱ ከሻዕቢያው መሪ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተስማምቶ ሳተላይት ራዲዮ ሊያቋቁም ነው በሚለው ሊረጋገጥ የማይቻል ወሬ በእንግሊዝኛ የተለቀቀው ወረቀት ውስጥ ሌላው ውሸት ደግሞ አቶ የማነ አብ ገብረ አብ (አዲስ አበባን የማያውቅ ሰው) በምንም ዓይነት ከአቶ ኢያሱ ጋር ትምህርት ቤት አብረው ሊማሩ እንደማይችሉ እየታወቀ ይሄን የዳበረ ውሸት ሳያፍሩ የሚሰዱብን ሰዎች ዓላማ ምንድር ነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ከፊታችን ግልጽ ሆኖ እናገኛዋለን። ለኔ ግልጽ ነው። አፍራሽነት! ማንአኽሎኝነት! ደካማነት! እና ንቀትም ጭምር ነው። ገና ለገና የፍኖተ-ዴሞክራሲ ራዲዮ ጣቢያን የማጠናከር ፍንጭ በድርጅቱ ደጋፊዎች አካባቢ ታየ ተብሎ አስቀድሞ የማሽመድመድ ዘመቻ! ጉድ እኮ ነው! ኢሕአፓ ውስጥ የነበረም ሆነ ዛሬም ያለ ማንም ሰው ኢያሱ አለማየሁ የጋራ አመራር ባለበት ድርጅት ውስጥ ተቀምጦ በግሉ ምንም የፖለሲ ውሳኔ በራሱ ሊወስን እንደማይችል እየታወቀ በሱና በጥቂት የአመራር አባላት ላይ የሚዘመተው ለምንድር ነው? የድርጅቱን አባላት ችሎታ መጠየቅ? ሌሎች የአመራር አባላትን መስደብ? ሕብረተሰቡን መናቅ? ወይንስ ተንኮል?

ይህም ማለት በተለያየ ምክንያት ከድርጅቱ ውስጥ ወጥተን የተቀመጥን ወገኖች የምንደረድራቸው ቅሬታዎች መሠረት (ዕውነትነትም) እንኳ ቢኖራቸው ተወደደም ተጠላ ያ ቅሬታ መስተናገድ የነበረበት ወይም ያለበት እዚያው ድርጅቱ ውስጥ ብቻ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ከድርጅቱ ውጭ ኃላፊነት በጎደለው ዓይነት የሚካሄድ ዘመቻ በእኔ ዕምነት አጠያያቂ እየሆነ ከመጣሰነባብቷል። አዎን የምሰማው ክስ ድርጅቱ ውስጥ ይህንን ቅራኔ የማስተናገድ ባሕልም ሆነ መድረክ የለም ነው። ታዲያ እኮ ያንን ባሕልና መድረክም መገንባት የለውጥ ፈላጊው ኃላፊነት ነው። የድርጅቱን ጥንካሬ የሚሻ ደግሞ ለድርጅቱ የውስጥ አንድነት ጥንቃቄ ያደርጋል። እንቅስቃሴው እኛ ብቻ ልክ ነን ሌላው ዲያብሎስ ነው በሚል ግርግር ብቻ ጋጠ ወጥ በሆነ ዓይነት በእልህ የሚገፋ ከሆነ መጨረሻው ዛሬ የምንመለከተው ዓይነት የማያባራ ክስና ንትርክ ሆኖ ይቀራል እንጂ ምንም አይፈይድም። ያ ደግሞ እንግዲህ ሁላችሁም በተለያየ ምክንያት ትግሉን ትታችሁ ብትሄዱም እኛን ለቀቅ አድርጉን፣ ያለንን ይዘን እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሳችን ትግላችንን ቀጥለናል የሚሉትን በድርጅቱ ዙሪያ ያሉትን እድገት ያጫጫል፣ ተስፋ ያስቆርጣል፣ በተለየ ጥቃቱ ጓዶች ነበርን ከሚሉ ሲሰነዘር ልብ ያደማል። ዓላማው ያ ካልሆነ በስተቀር በትግሉ ላይም የሚያደርሰው ጉዳት ደግሞ ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ጠንክሮ እንዲሄድ ነው የምንታገለው ለሚሉን እንቅስቃሴዎችም ድርጅቱ ተሰሚነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ሁናቴዎችን በመፍጠር የተፈለገው ለውጥም ሆነ ዕድገት ይመጣል ማለት ራስን ማሞኘት ነው። የሚፈለገው ለውጥም ሆነ ዕድገት የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። ኢሕአፓ-ዼ ብለው የወጡት እኮ ዛሬ ተሰነጣጥረው በዘር ሳይቀር ተቦጫጭቀው እስከሚያስገርመን ምንነታቸውን አሳይተውናል። ዛሬ እኮ ኢሕአፓ-ዼ የሚባሉት ከዚያችው ብሶ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ሲወዛወዙ የምናየው። የታለ ታዲያ ያኔ ቃል የገቡልን ጠንካራ ሆነን እንወጣለን ወሬ? ያኔ ድርጅቱን ሲከሱበት የነበረው ሁሉ ምነው ታዲያ በሥራ አልታየ? ወሬና ተግባር የተለያዩ ናቸው። በዚህ ግር ግር የሚጠቀመው ግን ፀረ-ኢትዮጵያዊው ወያኔ ብቻ ለመሆኑ ልንጠራጠር አይገባም። ለዚያ ደግሞ በመጀመሪያ ሃላፊነቱ የሚወድቀው በከሳሾቹ፣ ኢሕአፓ-ዴ፣ ኢሕአፓ ትንሣኤ እና ኢሕአፓ እርማት እንቅስቃሴ ነን ብለው በእኔ አስተያየት የማያባራ የውሸት ጦርነት በመክፈት ባደባባይ በድርጅቱና በጥቂት አመራር አባላት ላይ በሚዘምቱት ላይ ብቻ ነው። እስኪ ይሄን የምልበትን ምክንያት ላብራራ፦

እንደ ምሳሌ እኔ አቶ ሰውየው በዚህ ባለሁበት በምዕራቡ ዓለም በምሠራበት መሥሪያ ቤት እድገትና ታዋቂነትን እንዳገኝ አማራጭ የአሠራር ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ዕቅድ ላውጣ እንበል። በመጀመሪያ መረዳት ያለብኝ በምሠራበት መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ ሆኜ መቀጠል ይኖርብኛል። ሌላው ደግሞ ይህ ዕቅድ ምንም እንኳ የተሻለና ለምሠራበት ቦታ ብዙ ገንዘብ ሊያድንላቸው መቻሉን የማሳምንበት የተጨበጠ ማስረጃ በእጄ ላይ ቢኖረኝም፣ ያለኝን ዕቅድ በበላይ አለቆቼ ፊት አቅርቤ ላስረዳ የምችልበትን ሁናቴ ማመቻቸት አንዱ ኃላፊነቴ መሆኑን መረዳት አለብኝ። ይህም ዕቅድ በእጄ አለ ብዬ ባለትልቅ ዕውቀት፣ ባለትልቅ ችሎታ ከኔ ሌላ ማን አላችሁ በሚል ማንአህሎኝነት ጭንቅላቴን አሳብጬ ለቅርብ አለቃዬ እንኳን አልታዘዝም በማለት የዕዝ ሠንሰለት ላፈርስ አልችልም። ሌላው ቀርቶ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በትንሽ በትልቁ አልጋጭም። የግል ተደማጭነትና ተአማኒነት በድርጅቱ ውስጥ የሚመሠረተው በዕውቀትና በችሎታ ብቻ ሳይሆን ከሥራ ባልደረቦቼና አለቆቼ ጋር በየደረጃው የምፈጥራቸው ግንኙነቶችም ትልቅ ሚና እንዳላቸው ለማመልከት ነው። አመኔታ ደግሞ በአንድ ምሽት የሚገነባ ሳይሆን በተግባር በጥንቃቄ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ማወቅ ደግሞ ለውጥ እናመጣለን ከሚሉ ወገኖች የሚጠበቅ ዕውቀት ነው። በእኔ በኩል የሚጠበቅብኝን ካሟላሁና ዕውቀቱም ማስረጃዎቼም በእጄ ኖረው የበላይ አለቆቼን ማሳመን ከቻልኩ ያቀረብኩት ሃሳብ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች የተሻለ ሆኖ ከተገኘ በሥራ ላይ በሙከራም እንኳ እንዲውል ሊፈቀድልኝ ይችላል። ኢሕአፓ-ዴ፣ ኢሕአፓ ትንሣኤ እና ኢሕአፓ እርማት እንቅስቃሴን ስንመለከት ሁሉም ራሳቸውን ከድርጅቱ ውጪ አስቀምጠው በሌሉበት ቦታ ድርጅት ውስጥ ለውጥ እናመጣለን ሲሉን ለምን ብለን እንስማቸው? እንዲያውም ይህንን በማለቴ የሚቀርብብኝ ክስ አንተ ምናገባህና? ሊሆን ይችላል። ድርጅቱ ውስጥ የለበህበትም ለማለት ነው። መልሴም የሚሆነው እናንተም እኮ ድርጅቱ ዉስጥ የላችሁበትም ነው። ትልቁ ጥፋታችሁም በድርጅት ውስጥ የነበራችሁን መብት ጣጥላችሁ በመውጣት መሰረዛችሁ እኮ ነው! ምነዋ ይሄንን መረዳት አቃታችሁ? ነው የሚሆነው።

እንደ ኢሕአፓ ዓይነት በትግል ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ብዙ የሚጠበቅብን ኃላፊነት፣ ግዴታና ተጠያቂነትም አለ። በተለይ ከድርጅቱ ታሪካዊ ትግልና ካስከፈለውም መስዋዕትነት አንፃር አባላት ተጠራጣሪዎች ቢሆኑ አልፈርድባቸውም። ስለሆነም በድርጅቱ ውስጥ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ተራ አባላትም ሆነ የአመራር አባላት ታማኝነታቸው በጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ኃላፊነቱ የነሱ እንጂ የሌላ ሊሆን አይችልም። ስለሆነም አቀራረባችን፣ የማሳመን ችሎታችን የአባላትን በጊዜው ያለውን ነባራዊ ችሎታና ስሜት በሚዛን ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። ግልጽነት፣ ዕውነተኝነትና፣ አርቆ አስተዋይነት የለውጥ ፈላጊዎች መሠረት ነው። እኔ ልክ ነኝ ሌላው ዕብድ ነው አይሠራም! እስኪ በኢሕአፓ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ እንፈልጋለን የሚሉን ወገኖች የሚንቀሳቀሱበት ሁናቴ ችግሩ የት ላይ ነው? ገንቢ ወይስ አፍራሽ ? አቋምስ መወሰድ ያለበት ለምንድር ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች በራሴ በኩል ደግሞ መነገር ያለበትን አንዳንድ ልበል።

ይቅርታ ይደረግልኝና የኢሕአፓ ዕርማት እንቅስቃሴ ነን፣ የኢሕአፓ ትንሳኤ አጠናካሪ ነን ኢሕአፓ ዴ ነን የሚሉን አንጀኞችና አፍራሾች የናንተን አላውቅም እንጂ በበኩሌ ወያኔ ወያኔ እየሸተቱኝ ከመጡ ቆይተዋል። እዚህ እንደምታ ላይ የደረስኩት ደግሞ ሌሎች አላምጠው በሰጡኝ ሳይሆን እነዚሁ ወገኖች ባደባባይ ሳይቀድሙኝ ልቅደም ዓይነት ከጠላት ባልተናነሰ ባከታታይ በኢሕአፓና አመራሩ ላይ የሚያደርጓቸውን ዘመቻዎች በመመልከት ነው። ያ ደግሞ ለሁሉም ግልጽ ነው። አዎን! ይህንን ስላልኩ እነዚህን ወገኖች ላላስደስት እችላለሁ። ዕውነታው ግን ተሸፍኖ በይሉኝታ እየተግማማን መኖር አንችልምና ይቅርታችሁን ሊባሉ ይገባል። በተለይም ከላይ ያቀረብኩትን በድርጅት ውስጥ ለውጥ የማምጣት እንቅስቃሴ ጥንቃቄን በተመለከተ ምንም ደንታ የሌላቸውና የማይታወቅ መስሎአቸው የተለያየ አጀንዳ አንግበው ስለድርጅቱ መጠንከር አዛኝ ቂቤ አንጓች በመምሰል የሚነዙብን የውሸት መዓት እንደሆነ ደጋፊ ነን የምንል ሁላ ልናጋልጥና ወግዱልን ልንላቸው ይገባል።

ኢሕአፓ ነበርኩ ማለትና ኢሕአፓ ነኝ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ተወደደም ተጠላ በኢሕአፓ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችሉት፣ የዕርማት እንቅስቃሴውንም የማጠናከሩንም ሁሉም ነገር መሆን የሚቻለው እዚያው ኢሕአፓ ውስጥ በአባላቱ ታታሪነትና ሥራ ብቻ ነው። እንደገንቢነት ሊታይ የሚችለውም ያ ሲሆን ብቻ ነው። ዛሬ ዛሬ የምናየው የድሮ መሪዎች ተብዬዎችም ሳይቀሩ ወይም ደግሞ ኢሕአፓ ነበርን ባይ ቀባጣሪዎች በየራዲዮ ጣቢያና በየኢንተርኔቱ እየወጡ ኢሕአፓን ጥንብ እርኩሱን እያወጡ ድርጅቱን እንደ አዲስ አጠናክረን አናቋቁማለን ብሎ ባዶ ፉከራ ማሰማት ብቻ ነው። ያ ባዶ አዘናጊ ስብከት ደግሞ “ሰዶ ማሳደድ ያማረው ዶሮን በቆቅ ይለውጣል…” የሚለውን የአባቶች ብሂል ያስታውሰኛል። በፍርሻ የተካኑ፣ ሲገነቡ ያልታዩ ወሬኞችን ለምን እንመን? በዓመት እንደ መስቀል ወፍ ብቅ ብሎ የሽምቅ የውሸት ወረቀት መበተን ለውጥ ፈላጊነት ሰይሆን አፍራሽነት ነው። ለኔ ደግሞ ያ ወያኔነት ነው። ወያኔ በሀገር ቤት ባሉ የፖለቲካም ሆነ የብዙሃን ድርጅቶች የራሱ ሰዎች በአመራር ካልመጡ ድርጅቶችን ማመስ አለያም የራሱን ክሎኖች እስከ መፍጠር የደረሰበት አሠራር አለው። ብዙ ገንዘብም ያፈስበታል። የወያኔ መሠረቱ ከፋፍለህ ግዛው ንውና። የሰሞኑን የወያኔ ትዕይንት ለሚመለከት ከዚህ ለማለት የፈለጉትን በቀላሉ ይረዳል ብዬ እገምታለሁ።

በውጪም ኢትዮጵያውያን ያሉበት ድርጅቶች ሁሉ የሃይማኖር ሳይቀር የሚታመሱት በየድርጅቱ ውስጥ በተሰገሰጉ እበላ ባዮች ለመሆኑ ጠንቋይ መቀለብ አያሻም። አሁን አሁን ደግሞ የቀድሞ ኢሕአፓ፣ ኢሕአወሊና ኢሕአሠ አባላትንም ልንሰበስብና ኢሕአፓን አንደ አዲስ ልናደራጀው ነው የሚል ስብከትም በሰፊው እየቀረበልን ነው። ምናለ ሞኞች ከተገኙ ያንን ቲያትር ምናልባትም በሚመጠው በጋ በዋሺንግተን ዲሲ ከሚደረገው የኳስ ጨዋታ ጋር ተያይዞ የሚቀርብልን የዝግጅት እንቅስቃሴ ተጀምሮም ሊሆን ይችላል።

ኸረ እየተስተዋለ ወገን! የቀድሞ የምትሉን ለመሆኑ እነ ማንን ነው ጎበዝ? በዘር በመንደር በወያኔ መንገድ የነጎድነውን? ከወያኔዎች ጋር እየተሻሸን ያለነውን? ወይንስ አንደኛውን እነ በረከት ስምዖኖችና አዲሱ ለገሠዎችን ሁሉ የሚያካትት ነው? ወይንስ ላለፉት 35 ዓመታት ተኝተን፣ ከትግሉ ራሳችንን አርቀን፣ የየግል ኑሮአችንን ስናደላድል የኖርነው የኔ ቢጤዎች ተሰባስበን ቢያንስም ቢጎድልም በድርጅቱ ውስጥ ቆይተው እየታገሉ ያሉትን ወደ ጎን ገፍትረን አኛ ነን ኢሕአፓዎች ብለን ብቅ ልንል? ይሄስ ትክክል ነው ብለን እናምናለን? በየትኛውስ የሞራል ብቃታችን? በየትኛውስ ችሎታችን? የድሮ ኢሕአፓዎች የምትሉን እኮ በምዕራቡ ዓለም ከመጣን ጀምሮ እንኳንስ ለትግሉ በድርጅት መሰባሰብ (ኢሕአፓንም ብንተወው) ሌላ ድርጅት እንኳን ስንፈጥር አልታየንም። ሌላው ቀርቶ የምንቀባባርበት የመረዳጃ ማህበር እንኳ ማቋቋም ያቃተን ማፈሪያዎች ነን ከራሴ ጀምሮ። በተገናኘን ቁጥር ኢሕአፓ ምን አደረገ? ለምን ሕዝቡን ወጣቱን ማሰባሰብ አቃተው ብለን ስናጣጥለው ከመሰማት በስተቀር ስንቶቻችን ነን በአጋርነት እንኳ ለመቆም የጣርነው? አመጣጣችንስ እንዴት እንደሆነ ተረድተነዋል? ወይንስ ከኛ በፊት ቀድመው ወደ ውጪ የወጡት የሠራዊቱ ኮማንደርና የፖለቲካ መሪ ሰሞኑን በሰሜን አሜሪካ ታሪክ ልንጽፍ ነው እያሉ በንቀትና በድፍረት በየከተማው እየሰበሰቡን ሊሰብኩን እንደሚሞክሩት እኛም በፊናችን ሁላችንም የትግሉ ሕየወቴን አብረን ዘምረን ትግሉን ጣጥለን እንኳ ብንመጣ ተስፋ ሳያስቆርጣቸው ትግሉን የቀጠሉትን ታሪክ ሳይቀር ካለ ሃፍረት ሽሚያውን መያያዙ ይሻለናል? ዛሬ ዛሬ ከመቃብራችን አፋፍ ላይ ቆመን ትግሉን ትተን የመጣነው በአመራሮቹ ምክንያት ነው እያልን አደራ በላነታችንን ለመሸፈን እየተሯሯጥን ይህችን ዓለም ልናልፋት ነው ማለት ነው? ወይስ የጀመርነውን ትግል አብረን ከዳር ለማድረስ ቆርጠን መነሳታችንን በተግባር ከድርጅቱ ውስጥ ሆነው ያቅማቸውን ከሚያደርጉት ጎን ለመሰለፍ ለራሳችን ቃል በመግባት ወይ በመርዳት አለያም በመቀላቀል ከሕዝቡ ልንወግን? እኒህ በትግሉ ሜዳ ህየወታቸውን ያሳለፉትን ወገኖች ቁም ስቅል ስናሳይ ችግራችን ምንድር ነው? ለምን ትግሉን ቀጠሉ? አስቀጠሉ? እኛስ በእኛነታችን የምንቀበለው ኃላፊነትስ ምንድር ነው ብለን ከራሳችን ጋር ተነጋግረን እናውቃለን? ወይም አንዳንዶቻችን እንደምናደርገው ጣጥለን ስንነጉድ ወደኋላ ቀርተው ትግሉን ያስቀጠሉትን የፈረደባቸውን ጥቂት ጀግና መሪዎችና አባላት እየረገምን እስከ ዕለተ ሞታችን ጣቶቻችንን እንደ ቀሰርን ልናልፋት? ኸረ ፊታችንን ከመስታወቱ ፊት እናድርግና ራሳችንን እንገምግም ጎበዝ! ብዙ ምክንያት አንደርድር!

ለማጠቃለል፥

በኢሕአፓ ውስጥ ተሰባስበው ትግሉን ላስቀጠሉ ወገኖች ከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት አለኝ። ኢሕአፓዎች ከውጭ በሚሰነዘርባችው ቅጥቀጣ በውስጣቸው ጨለምተኝነት እንዲነግሥ፣ በራስ መተማመን እንዲጠፋ የኢትዮጵያዊነት ጠላቶች በየአቅጣጫው የሚሰነዘሩባቸውን ጥቃት ተቋቁመው፤ ኢሕአፓ ነበርን በምንልም ጭምር አፍራሽና ቅጥ ያጣ ዘለፋ እየወረደባቸው ዘሬም በትግሉ ውስጥ እነሆ ለ 42 ዓመታት መቀጠላቸው የሚያስደንቃቸው እንጂ የሚያስኮንናቸው ከቶውንም ሊሆን አይችልም። ይህን ኢትዮጵያዊ ድርጅት ለማጠናከር እፈልጋለሁ የሚል ወገን ሁሉ ከውጭ ሆኖ ቅስም የሚሰብር ትችት ማዥጎድጎድ ሳይሆን ለድርጅቱ ታማኝነትን ገንብቶ በቅንንነት ከድርጅቱ ውስጥ ገብቶ የፈለገውን ለውጥ ማምጣት የተገባ ነው። ካለያም ደግሞ ታማኝ ደጋፊ ሆኖ ከውጪ የሞራልም ሆነ የቁሳቁስ ዕርዳታ እያደረጉ አይዞአችሁ ማለትም ይቻላል። አንድ ሰው ደግሞ ራሱን በታማኝነትና በቅንነት ካቀረበ የድርጅቱ አባላትም ሆነ አመራር በዚህ ደረጃ ያሉ ግለ ሠቦችን ገንቢ ሂስ አይቀበሉም ማለት ይከብደኛል። የውሸት ነጎድጓድ እያዘነቡ የሚተቹትን የድርጅቱ አባላት ባይሰሟቸው አልፈርድባቸውም። የድርጅቱ አባል ነበርኩ ወይም አለሁበት በሚል ሽፋን የሚደረግ ጸረ-ድርጅት ዘመቻ ግን በፍጹም ገንቢነት አይደለም። ኢሕአፓነትም አይደለም። ድርጅቱ የሚሄድበት አቅጣጫ አላማረኝም፣ ወይም ትግል በቃኝ ወዘተ. ብለን ድርጅቱን ጥለን ከወጣን በኋላ ግን የሚጠበቅብን እንዲያው ዝምምምም ብቻ ነው። ድርጅቱን ከወያኔ ባልተናነሰ ሁናቴ መታገል በየትም ብትመዝኑት ለኔ ወያኔነትና ቅሌት ነው።

እምቢኝ ለዘረኝነት፣ ለበታኞችና፣ ለባንዶች!

ኢትዮጵያዊነት ያለጥርጥር በትግላችን ያቸንፋል!

ሀቀኛ መሪዎቻችንና ድርጅቶቻችንን እንደግፍ!

አስመሳይ መሪ ተብዬዎችንና አፍራሾችን ሳንፈራ እናጋልጥ!

 

አቶ ሰውየው (ከሰሜን አሜሪካ –

የካቲት 1 2007) (February 7, 2015)

 

-[ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]—

 

The post ሰዶ ማሳደድ ያማረው ዶሮን በቆቅ ይለውጣል! – ከአቶ ሰውየው appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.