የግርማን መንገድ አፈረሱት – ዳዊት ሰሎሞን

Girma Seifu

ግርማ ሰይፉ ማሩ

የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን በአጭር አረፍተ ነገር ግለጽ ብባል ‹‹ ስልጡን ፖለቲካ ለማራመድ ነፍስያው የምትጨነቅበት፣ ሲበዛ ሊበራሊስት የሆነና ሐይማኖቱ ላይ ብቻ ወግ አጥባቂ ወይም ዶግማቲስት የሆነ››የምል ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሀሳብ፣የፖሊሲ፣የፕሮግራምና የክርክር የበላይነት የሚታይበት ሜዳ እንዳይሆን ሁልግዜም ወደ ቤተ መንግስት የሚገባው በጉልበት ነው፡፡
ከአጼዎቹ ዘመን አንስቶ እስካሁን ኢትዮጵያ ለጉልበተኞች እንጂ በስልጡን መንገድ ለሚመጡ አልሆነችም፡፡እናም የግርማን መንገድ የሚከተሉ ሁሉ ስማቸው አጎብዳጅ፣ፈሪ፣የፓርላማ ደሞዝ የሚፈልጉ ወዘተ ሆኗል፡፡

ስልጣን በጉልበት መንገድ የጨበጠው እነ ግርማ በመረጡት መንገድ ሲሳለቅና ባገኛቸው አጋጣሚ ሁሉ እንደ ዕባብ ጭንቅላታቸውን እየቀጠቀጠ ወህኒ ያጉራቸዋል ::
አንድነት ፓርቲ በዘንድሮው ምርጫ መሳተፍ እንደሚገባው ጠንካራ አቋም በመያዝ ይከራከሩ ከነበሩ አመራሮች ዋነኛው ግርማ ነበር፡፡በእነርሱ ሜዳ ፣ዳኛና ኮሜንታተሮች ተጫውተን ከህዝብ ጋ እናሸንፋለን ይል የነበረው ግርማ በገዢው ቡድን የጠራራ ጸሐይ ውንብድና ፓርቲው ፈርሶ ለእበላ ባዮች እጅ መንሻ ሲደረግ በማየቱ ከመንገዱ ወጥቶ ዛሬ ይህንን ብሏል፡፡
‹‹ለማንኛውም ተመስገን በግፍ መታሰር ሳያንሰው፣ ከህግ አግባብ ውጭ በወዳጅ ዘመዶቹ እንዳይጎበኝ የተደረገበት ሁኔታ ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል፡፡ ይህ አስተያየት ከእኛ እንዳይቀር ብለን ነው እንጂ ገዢው ፓርቲም ሆነ ይህን የሚተገብሩ አካላት ያዳምጣሉ ከሚል አይደለም፡፡ ለማንኛውም ተሜን በአካል ባናየውም በመንፈስ አብሮን ነው፡፡ ምርጫ! ምርጫ! … ስንል ለነበርን ለእኛ “የምን ምርጫ!!” ይለን የነበረው ተመስገን፤ በወህኒ ቤት ሆኖ ልክ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ የምን ምርጫ!!!!!››

ገዢዎቻችን በዕውር ድንብር የወሰዱት ህገ ወጥ እርምጃ እንደ ግርማ ተስፈኛ የነበሩ የአገሬ ልጆችን ህልም አምክኗል፡፡መንገዳቸው በመፍረሱም እግሮቻቸውን በሌሎች መንገድ ውስጥ ለማስገባት ተገደዋል፡፡ማን ነበር የማርያም መንገድ ሲከለከል በገብርኤል መንገድ የሚመጣ አይጠፋም ያለው … አስራት አብርሃምም አይደል እነዚህ ሰዎች የስንቱን መንገድ አፈረሱት…!!

The post የግርማን መንገድ አፈረሱት – ዳዊት ሰሎሞን appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.