ጉዞ ዓድዋ፡- የነጻነት ተጋድሎ ክቡርና ሕያው ታሪክ ዳግማዊ ብሥራት በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
መቼም ስለ ታላቁ የዓድዋ ድል፣ ስለ ነጻነታችን፣ ስለ ስለቀደሙት አባቶቻችን አይበገሬነት፣ ለአገራቸው ሉዓላዊነት፣ ለሕዝባቸው ነጻነት ያደረጉትን አኩሪ የሆነ ተጋድሎአቸውን፣ ጀግንነታቸውን ለማውራት፣ ግዙፍና ገናና ታሪካቸውን ለመዘከር የግድ የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን መምጣት ወይም መከበርን መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በእርግጥም፣ በእውነትም ተወዳጇ አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው/ጂጂ ‹‹ዓድዋ›› በሚለው ዜማዋ፡-
ዓድዋ ዛሬ ነው፣ ዓድዋ ትናንት፣
መቼ ተረሱና የወዳደቁት …፡፡ እንድትል፡፡ በእውነትም ደግሞ ዓድዋ ዛሬ ነው፣ ዓድዋ ትናንት፣ ዓድዋ ሁሌም ነው፣ ዓድዋ መቼም ነው!! ስለሆነም ነጻነታቸውን በሚያፈቅሩ ሰው ልጆች ልብና ሕሊና ውስጥ ዓድዋ ዛሬም፣ ነገም፣ ለዘላለምም ይዘከራል፣ ይታወሳል፣ ይከበራል፣ ይገናል፡፡ ይህን ነጻነት የተበሰረበትን ታላቁን ዓድዋን ድል ተመርኩዤ ስለ ነጻነታችን እንዳወራ ያስገደደኝ ለመጀመሪያና አሁንም ደግሞ ለኹለተኛ ጊዜ ‹‹ጉዞ ዓድዋ›› በሚል በዓድዋ ጀግኖች መንፈስና ወኔ ይህን ሕያውና ክቡር ታሪካችንን ለመዘከር፣ በልባችን ውስጥ እንዲገዝፍ ለማድረግ የተነሡ ወጣቶች ናቸው፡፡
ባለፈው ዓመት የኢትዮፒካ ሊንክ የሥራ ባልደረቦችና ሌሎች ጓደኞቻቸው በዓድዋ ተራሮች ላይ ከመቶ ዓመታት በፊት አባቶቻችን ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሣይሉ በአንድነት በመተባበር ያስመዘገቡትን ታላቁንና ታሪካዊውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ለመዘከር ያደረጉት ታሪካዊ የእግር ጉዞ፣ ‹‹ጉዞ ዓድዋ›› የብዙዎችን ቀልብ የሳበና የዓድዋን ድል መንፈስ ዳግመኛ በወጣቱ ልብና መንፈስ ውስጥ ደምቆና ገኖ እንዲታይ፣ ያደረገ አጋጣሚል የፈጠረልን እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዛሬም ደግሞ ሌሎች የዓድዋ ጀግኖቻችን የመንፈስ ልጆች የሆኑ ስድስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ የዓድዋ ጀግና የእቴጌ ጣይቱ ተምሳሌት ሆና የምትጠቀስ አንዲት ወጣት ሴትን ጨምረው ጉዞ ዓድዋን ከጥቂት ቀናት በፊት አሐዱ በማለት ጀምረውታል፡፡ እነዚህ የጉዞ ዓድዋ ተጓዥ ወገኖቻችንን የዓድዋን መንፈስ፣ አባቶቻችን ለአገራቸው ሉዓላዊነት፣ ለሕዝባቸው ነጻነት የከፈሉት መሥዋዕትነት ምን ያህል ታላቅ፣ ክቡርና ግዙፍ እንደሆነ ዳግመኛ በሕሊናችን ውስጥ ሊስሉንና ሊያሳዩን ጉዞአቸውን ጀምረዋል፡፡
እግረ መንገዴንም የእነዚህ ወገኖቻችን ጉዞአቸው የተሳካና የተቃና እንዲሆንም ምኞቴን ልገልጽላቸው እወዳለኹ፡፡ እንግዲህ ይህ የወጣቶቻችን ብርቱ ቅናትና የነጻነት ፍቅር የወለደው ‹‹ጉዞ ዓድዋ›› ምክንያት ሆኖኝ ነው ስለ ዓድዋው ድል ጥቂት ለማለት ብዕሬን ያነሳሁት፡፡
ትናንትናት፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌምና መቼም በዓድዋና በሶሎዳ፣ በእነዛ ሰማይን ጫፍ የነኩ በሚመስሉ በሰሜን ግዙፍ ተራሮች ማዶ ልቆና ገኖ የሚሰማ አንድ የነፃነት ደወል ድምፅ፣ የነፃነት ልዩ ውበት አለ፡፡ በደም የተቀደሰ፣ በደም የነጻ፣ በደም የተዋበ፣ በደም ለዘመናት የጸና፣ የፋሽስቶችንና የኃያላኑን የአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችን ሕልም ያመከነ፣ ጽኑ ክንዳቸውን የረታ፣ በምንምና በማንም ያልተበገረ፡፡ ሥጋንና አጥንትን አልፎ ነፍስ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ክቡር ሕያው የነፃነት ድ-ም-ፅ!!
የእናት አገር የኢትዮጵያን ምድር በነፃነት ውብ ሕብረ ቀለም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ያሸበረቀ፣ ያስዋበ፡፡ ዘመናትን ያስረጀ፣ በምንምና በማንም ኃይል ያልተረታ፣ ከአድማስ አድማስ ያስተጋባ፣ አፍሪካን፣ መላው ጥቁር ሕዝቦችንና በአጠቃላይ ነፃነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት ያስተሳሰረ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ውብ የነፃነት ተጋድሎ ልዩ ዜማ፣ ልዩ ቅኔ፣ በደም የተዋበ በደም የተቀደሰ፣ በደም ያሸበረቀ፣ በደም የተጌጠ!!
ዛሬ እኔና እናንተ የምንተነፍሰው ውብ የነጻነት አየር፣ በዓለም ፊት ደረታችንን ነፍተን የምንናገርለት አባቶቻችን የነጻነት ታሪክ ተጋድሎ፣ በደም የተገዛ፣ በደም የከበረ፣ የብዙዎች ክቡርና ውድ ሕይወት የተከፈለበት ነው፡፡ አርቲስት እጅጋየሁ/ጂጂ በዓድዋ ዜማዋ ላይ እንዲህ እንደተቀኘችው፣
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፡፡
ምስጋና ለእነርሱ ለዓድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነጻነት ላበቁኝ ወገኖች፡፡
በእርግጥም የአፍሪካውያን፣ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ የሰው ዘር ታሪክ ነው፡፡ የሰው ዘር ምንጭ፣ ባለ ግዙፍ ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤትና እምብርት ኾና የምትጠቀሰው አፍሪካ፣ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ያላት ስፍራ ደግሞ እጅግ ደማቅ፣ ታላቅና ግዙፍ ነው፡፡ ሺህ ዘመናትን በሚያስከነዳው የአኅጉሪቱ ታሪክ ውስጥ አፍሪካውያን እንደተቀሩት የዓለም ሕዝቦች ኹሉ በታሪካቸው አያሌ የብርሃንና የጨለማ ዘመናትን ዐይተዋል፣ አሳልፈዋል፡፡ በአፍሪካውያን ካለፉባቸው የጨለማ ዘመናት አስከፊ ታሪካቸው መካከልም ትልቁንና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የአኅጉሪቱ ሕዝቦች በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር ወድቀው ያሳለፉት ይኸው አስከፊው የባርነትና ቅኝ ግዛት ዘመን ታሪካቸው ነው፡፡
መላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝብ በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር ወድቆ በሚማቅቅበት በዛ የአኅጉሪቱ የጨለማና የሰቆቃ ዘመን ታሪክ ውስጥ ጥቁር ሕዝቦችንና መላው የሰው ልጆችን ያስደመመ፣ ያስደነቀ፣ በደስታና በሐሴት ጮቤ ያስረገጠ የነጻነት ተጋድሎ ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከወደ ኢትዮጵያ ነበር የተሰማው፡፡ ነጻነታቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውን፣ ሃይማኖታቸውንና ክብራቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች በአፍሪካ ምድር አዲስ የሆነ የአይበገሬነትና የነፃነት ተጋድሎ ሕያው ታሪክን በደማቸው ጻፉ፡፡
የነጻነትን ልዩ ውበትንና ታላቅነትን በዐድዋ ተራራ በደማቸው የጻፉ የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን በአፍሪካ ምድር፣ በጥቁር ሕዝቦች ምድር አጥንታቸውን ከስክሰው ነጻነት ለሰው ልጆች ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረ የማይገሠሥ ጸጋ መኾኑን ዳግመኛ ለመላው ለዓለም አረጋገጡ፡፡ ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች የነጻነት ብርሃን ጎሕን በደማቸው ቀለምነት፣ በአጥንታቸው ብዕርነት በጻፉ፣ ባበሰሩ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል ብርሃን ሸማም ተለኮሰ፡፡
ከጥንታዊቷና ከባለ ግዙፍ ታሪኳ የኢትዮጵያ ምድር የታየው ይህ የዐድዋው የነጻነት ጎሕ በመላው ዓለም የነጻነትን ብርሃን ፈነጠቀ፣ እምቢ ለነጻነቴ፣ እምቢ ለአገሬ፣ እምቢ ለክብሬ… የሚል ወኔንና መንፈስን ናኘ፡፡ በእርግጥም ዐድዋ ለአፍሪካ፣ ለጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን ለሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ የተበሰረ የነጻነት የምስራች ደወል ነበር፣ ነውም!! ይህ መላውን ዓለም ያስደነቀና ያስደመመ የቀደሙ አባቶቻችን ነጻነት ተጋድሎ ታሪክ፣ የዓድዋው ድል በዓል ሁሌም ሕያው፣ መቼም አዲስ፣ ሕያውና ሁልጊዜም ልንዘክረው የሚገባው ታላቅ የነጻነታችንና የሉዓላዊነታችን ምልክት ነው፡፡
ዓድዋ የኢትዮጵያውያን፣ የአፍሪካ ወይም ጥቁር ሕዝቦች ብቻ ታሪክ አይደለም፡፡ ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ፣ ሰብአዊ ክብርንና ልእልናን የተጎናጸፉ፣ ለሰው ልጆች ፍቅርንና አክብሮትን የሚሰጡ ሕዝቦች ሁሉ የተቀዳጁት ታላቅ ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል የነጻነት ድል ብቻ አይደለም፡፡ ዓድዋ ፍቅርና ይቅርታ ድል የነሡበት፣ ድል ያደረጉበት ዓውደ ግንባርም ነው፡፡ ዓድዋ በአውሮጳውያኑ ዘንድ ያልሰለጠነና አረመኔ ሕዝብ ነው ተብሎ የተቆጠሩት ኢትዮጵያውያን፣ ለሰው ልጆች ኹሉ ያላቸውን ሰብአዊነት፣ ርኅራኄ፣ ፍቅርና አክብሮት የገለጡበት ዓውደ ግንባርም ጭምር ነው፡፡
ይህን እውነታ ለማረጋገጥ የሚወድ ሁሉ ለኢጣሊያውያኑ ምርኮኞች ኢትዮጵያውያኑ ያሳዩትን አክብሮትና ርኅራኄ፣ ከድሉ በኋላም አፄ ምኒልክ ለአውሮፓ መንግሥታትና ለሮማ ካቶሊክ ፖፕ የጻፉትን ደብዳቤና ያደረጉትን ድርድር ከራሳቸው ከኢጣሊያውያኑ ታሪክ ጸሐፊዎች እስከ አውሮፓውያኑ ምሁራን ጆርጅ በርክሌይና የአገራችን ጸሐፍት የታሪክ ማስታወሻዎቻቸውን ቢያገላብጥ ሐቁን ይረዳል፡፡
የዚህ ታሪክ ሐቅ ወኔያቸውን የቀሰቀሳቸው፣ ይህን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦችና የሰው ልጆች የነጻነት ጎሕ የቀደደውን የዐድዋን ፻፲፰ኛ ድል መታሰቢያ ለማክበር ባለፈው ዓመት ከአዲስ አበባ ዓድዋ ድረስ ተነስተው የተጓዙት ስድስቱ የመገናኛና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ዓድዋ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ፣ የጥቁር ሕዝቦች በአጠቃላይም ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ ድል፣ ሕያው፣ ታላቅና ግዙፍ ታሪክ እንደኾነ ያስመሰከሩበትን ጉዞ ዓድዋን በድል አጠናቀዋል፡፡ ለዚህ ትውልድም አዲስ ታሪክን ጽፈዋል፤ ሌሎች ደግሞ ያን ታሪክ ይደግሙ ዘንድ መንገዱን አሳይተዋል፡፡
የባለፈው ዓመት የጉዞ ዓድዋ ተሳታፊዎች በወቅቱም ይህ ጉዞአቸው የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንደማይሆንም ሲገልጹ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዓድዋን የመላው አፍሪካ፣ የጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ የነጻነት አምባና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም ገልጸውልን ነበር፡፡ ይህ ቃላቸው ተሳክቶና ሰምሮም ዓርማቸውን የሚያነሡ ሌሎች የዓድዋ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ጽናትና ብርታት የተጋሩ የመንፈስ ልጆቻቸው ተነሡ፡፡
ይህ አባቶቻችን ለዐድዋው ዘመቻ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያያቸው በእግራቸውና በጋማ ከብት የተጓዙበትን ታላቅ ታሪካዊ ጉዞውን ታላቁን ድል ለመዘከር በማሰብ የተካኼደው ‹‹ጉዞ ዐድዋ›› ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ተምሳሌትና መነቃቃትን የፈጠረ እንደኾነ ነው የማስበው፣ የተሰማኝም፡፡ ጉዞ ዓድዋ አሁንም በዛው መንፈስ መቀጠሉ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
የባለፈው ዓመት ተጓዦች ከአዲስ አበባ ተነስተው ዓድዋ ከተማ እስኪገቡ ድረስ በጉዞአቸው ያጋጠማቸውን፣ እንደ ማይጨውና አምባላጌ በመሳሰሉ ታሪካዊ ከተሞች ላይ ከመቶ ዓመት በፊት የሆነውን ታሪክ በተመለከተ ከአካባቢው ሕዝብና ከታሪክ ምሁራን ጋር ያደረጉትን ቆይታቸው በሚመሰጥ ኹኔታ ተርከውልን ነበር፡፡ እግረ መንገዳቸውንም የአገራችንን ሰሜናዊ ክፍል ጆኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን፣ ጫካውንና ደኑን፣ ጋራና ሸንተረሩን፣ ተራራውንና ሸለቆውን፣ ሜዳና ገደሉን በመተረክ በምናብ አብረናቸው እንድንጓዝ፣ አገራችን በሚገባ እንድናውቅ፣ ስሜታቸውንና ወኔያቸውን እንድንጋራ፣ እንድንካፈል ታላቅ ዕድልን ሰጥተውናል፡፡
እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የዓድዋ ድል በዓል የመላው አፍሪካ፣ የጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ ድል መታሰቢያ በዓል ሆኖ ይቀጥል ዘንድም የባለፈው ዓመት የዓድዋ ተጓዦች ቡድን ትልቅ ራእይ እንዳላቸውም ገልጸውልናል፡፡ ይህ ራእይ እውን ይሆን ዘንድም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራና በአንድነት ድምፃችንን ልናሰማ ይገባል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዤም አንድ ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የነጻት ተጋድሎ ታሪክና አፍሪካዊ ገናና ሥልጣኔ ወኔና ብርታት ሆኗቸው ዘረኛውንና አስከፊውን የአፓርታድ ሥርዓትን ከሕዝባቸው ጫንቃ ላይ ለማውረድ በጽኑ ለታገሉትና ለ፳፯ ዓመታት ለተጋዙት ለጀግናው ማንዴላ/ለማዲባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መታሰቢያ እንዲሆንላቸው የወሠኑ የአፍሪካ አገራትና መሪዎች፣ እንዴት ለአፍሪካ አገራትና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ትልቅ ወኔንና መነሳሳት የፈጠረው ዓድዋን በኅብረቱ አዳራሽ ቋሚ መታሰቢያ ወይም መዘክር እንዴት ሊነፈገው፣ ሊነፍጉት ቻሉ የእኛ ዝምታ ወይንስ…?! ይህንን ጥያቄ አጥብቀን፣ አብዝተን ልንጠይቅ ይገባናል፡፡
መንግሥት፣ ነጻነቱን የሚያፈቅር ኢትዮጵያዊ ኹሉ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በባህልና በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሠሩና የተሰማሩ አካላትና ምሁራንም የበኩላቸው ጥረት በማድረግ ዓድዋን የመላው አፍሪካ፣ የጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች ኹሉ የነጻነት ዓምባና የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ረገድ የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ከመቼውም በላይ ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡
በተጨማሪም ዓድዋ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ተጀምሮ የነበረውም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ በመጨረሻም በዓድዋ ጀግኖቻችን መንፈስና ወኔ፣ ብርታትና ጽናት በዚህ ትውልድ የተጀመረው ጉዞ ዓድዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ፣ እያበራ፣ እያሸበረቀ እንደሚቀጥል አምናለሁ፡፡ ፍቅር፣ ሰላምና ጤና ለጉዞ ዓድዋ ተጓዥ፣ ኢትዮጵያውያን ወጣት ወገኖቻችን እንዲሆንላቸው በመመኘት ልሰናበት፡፡
ክብር ለዛሬ ነፃነት ላበቁን ለዓድዋ ጀግኖች አባቶቻችን እናቶቻችን ሁሉ!