የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ የምድር መረጃ( Geo-spatial Information) ምርትና አገልግሎት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መመሪያ አዘጋጀ

የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ በዓዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የተለያዩ የምድር መረጃዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች ማሰራጨትና በሌሎች ተቋማት የሚመረቱ የምድር መረጃዎች በጥራት ተመርተው መቅረባቸውን መቆጣጠር፣ማረጋገጥ እንዲሁም የዘርፉ ተቋማትና ባለሙያዎች ተገቢውን ብቃት መያዛቸውን ገምግሞ ማረጋገጫ መስጠት እንደሚጠበቅበት በግልፅ ተቀምጧል፡፡
አዋጁን መሰረት አድርጎ ኤጀንሲው ያዘጋጀው የምድር መረጃ ምርትና አገልግሎት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ነሰድ ደረጃቸውንና ውቅታዊነታቸውን የጠበቁ የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያረኩ መሰረታዊ የምድር መረጃ ለማምረት እንዲሁም በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው ያሉትን ወደፊትም የሚሰማሩትን ባለሞያዎችና ተቋማት የሚያመርታቸውን የጂኦ-ስፓሺያል ምርትና አገልግሎት ጥራትና ደረጃ ወጥነት ባለው መንገድ ለመቆጣጠር ተገቢውን ብቃት መያዛቸውን ገምግሞ ማረጋገጫ ለመስጠት ዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ በኤጀንሲው የንግድ ምዝገባ ፋቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀፅ 30 ንዑስ አንቀፅ 3 መሰረት በሙያው የሚሰማሩ ባለሞያዎችና ተቋማት የትምህርት ዝግጅታቸውን፣ለሥራ የሚያስፈልግቸውን መሳሪያና ሌሎች ተጓዳኝ ግብአቶች መሟላታቸውን በማጣራት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡና ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የምድር መረጃ ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚው የሚያቀርቡበት ሁኔታ ለማመቻቸት አስቦ ሰነዱን ማዘጋጀቱን የኤጀንሲው የጥራትና ደረጃዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቄርሎስ ላቴቦ ገልፀዋል፡፡
መመሪያው የምድር መረጃ ምርትና አገልግሎት ማምረት፣ማሰራጨት፣ማማከርላይ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ ድርጅቶች፣ባለሙያዎች፣በማንኛውም የምድር መረጃ /Geo-spatial Information/ ምርት ማምረትና ተዛማጅነት ያላቸው መሳሪያዎች አስመጪና ላኪ ድርጅት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለመስጠት የወጣ መመሪያ ነው፡፡
የሰነዱ አላማ በምድር መረጃ / Geo-spatial Information/ ማምረት፣ማሰራጨትና ማማከር እንዲሁም እነዚህን ምርቶች ለማምረት፣ለማከማቸትና ለማሰራጨት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ፣የሙያ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎችና ድርጅቶች እንዲሰሩ ሀገራችንም ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አግባብ ማመቻቸት ሲሆን የተፈፃሚነት ወሰኑ በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት በተዘጋጁ እና በኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ በሚሰጡ የምድር መረጃ / Geo-spatial Information/ ምርትና አገልግሎቶች ማምረት፣ማሰራጨት እና ማማከር እንደዚሁም በእነዚህ ምርቶች ማምረቻና ተዛማጅነት ያላቸው መሳሪያዎች አስመጪና ላኪነት ስራ ላይ በተሰማሩ (በሚሰማሩ) ባለሙያዎችና፣ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ምዝገባ ለማከናወን ወደ ኤጀንሲው የሚመጡ በአዋጁና በወጣው መመሪያ የተመለከቱ አስፈላጊ መስፈርቶችን ያሟላ ተቋምና ባለሞያ የሞያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲሰጠው በፁሁፍ ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የሚቀርብ ማመልከቻ ለዚሁ ተግባር እንዲውል በኤጀንሲው በተዘጋጀ ቅጽ መሰረት ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በምድር መረጃ / Geo-spatial Information/ምርትና አገልግሎት ማምረት፣ማሰራጨት፣ማማከር እና የእነዚህን ምርቶች ማምረቻና ተዛማጅነት ያላቸው መሳሪያዎች አስመጪና ላኪነት ተግባር ላይ ለመሰማራት የሚፈልግ የውጭ ሀገር ተወላጅ በዚሁ መመሪያ መሰረት መመዝገብ አለበት፡፡
በመመሪያው መሰረት የምድር መረጃ/ Geo-spatial Information/ምርትና አገልግሎት ማምረትና ማሰራጨት ሥራ የተመዘገበ ድርጅት በድጋሚ በተመሳሳይ ባለሙያ፣መሳሪያ፣ካፒታልና የስራ ቦታ በአማካሪ ድርጅትነት ለመሰማራት የሚያስችል የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሊያወጣ አይችልም፡፡ ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት በሁለቱም ዘርፎች የምስክር ወረቀት ያወጣ ድርጅት አንዱን ለሰጪው አካል በመመለስ መሰረዝ አለበት፡፡ ማንኛውም ስሙ በመዝገብ የሰፈረ ድርጅት ወይም ባለሙያ በማመልከቻው ውስጥ የተመለከቱ በየጊዜው የተደረጉ የለውጥ ሁኔታዎች እንዲመዘገቡለት ለኤጀንሲው ማሳወቅ አለበት፡፡ ኤጀንሲውም ለውጡን መሰረት በማድረግ በመመዝገብ መዝገቡን ወቅታዊ ያደርጋል፡፡
Source:Federal Govenment Communication Affairs Office of Ethiopia