የትግራይ ህዝብ የአርባ ዓመት ሶቆቃ – ከይኩኖ መስፍን

ካለፈው የቀጠለ ወቅታዊ ዘገባ                       

ክፍል ሶስትና የመጨረሻው    

 

ከይኩኖ መስፍን / ሰሜን አሜሪካ

 01/04/2015

Tigray_Map~0 (1)ከተወሰኑ ወራት በፊት ወደ ሀገሬ ወደ ኢትዮ}ያ ለግል ጉዳይ ሄጄ በነበርኩበት ጊዜ በተዘዋወርኩባቸው ቦታዎች ሁሉ በራሱ በነዋሪው ህዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ ፓለቲካዊና ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስመልክቶ ህዝቡ በተለይም ከሀገሩ ርቆ በዲያስፓራ የሚኖረውን ኢትዮ}ያዊ ማወቅ አለበት ብዬ ያሰብኩዋቸውን ማነቆና አንገብጋቢ ችግሮችን ባለፉት ሁለት ተከታታይ ፅሑፎቼ በሰፊው ማቅረቤን ይታወሳል:: ሶስተኛው ክፍል እንደማቀረብም በወቅቱ ቃል ገብቼ የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ የግል ጉዳይ ምክንያት በጊዜው ለማቅረብ ባለመቻሌ ይቅርታ እየጠየቅኩኝ እኖሆ ዛሬ ሶስተኛውና የመጨረሻው ክፍል ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል::

በሀገር ቤት ቆይታዬ በቅርብ ከማውቃቸው አንድ አዛውንት አንድ ቦታ ቁጭ ብለን እንዲሁ ስናወራ፣ ዝም ብዬ እንደዋዛ “በሀገራችን ለውጥ አለ? በተለይም የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል እየተባለ ይነገራልና እንዴት ነው?” ብዬ ስጠይቃቸው እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጡኝ:: “አይ ልጄ!! አሁን እኔ ለውጥ አለ የለም ብዬ አልነግርህም:: አንተ ራስህ በአካል እዚህ ስላለህ ማየት ትችላለህ:: አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት ልንገርህ:: እኛ ድሮ ከኢጣላሊያ ጋር የተዋጋነው ሌላ ፍለጋ አልነበረም ነፃነታችንና ክብራችንን ስለተነካ ነው:: አባቴ በዚያን ጊዜ ከኢጣሊያ ጋር ሲዋጉ ነው የሞቱ:: ሁለት ልጆቼም ነፃነትና ዴሞክራሲ እናመጣለን ብለው ከህወሓት ጋር ተሰልፈው የደርግ ስርዓትን ሲፋለሙ በዚያው ቀሩ አልተመለሱም:: እኔ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ውስጥ ጦርነቱን ያልነካው ቤተ ሰብ የለም ማለት ይቻላል:: በሌላ አነጋገር ድሮም ሆነ ዛሬ ለነፃነት ሲባል በገንዘብ ሊተመን የማይችል ደምና ህይወት ተከፍሏል ማለቴ ነው:: ልማት ሊኖር ይችላል ነገር ግን ማን ነው እየለማ ያለው የሚለው አንተ ራስህ መመስከር ትችላለህ:: ጥያቄው ግን ልማት መኖሩና አለ መኖሩ አይደለም:: ዓለም ሁሉ በወርቅ እንኳን ቢሸፈን ነፃነትን አይተካም ልጄ!!” ሲሉ ዐይን ዓይኔን እያዩ የነገሩኝን አንጀት የሚነካ ማስታወሻ በፍፁም ለወደፊትም ቢሆን አልረሳውም:: ከነዚህ አንደበት የተወሰደ ነበር ያለፉት ሁለት ተከታታይ ፅሑፎቼን “ነፃነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕና ሰብኣዊ መብት ሳይከበሩ ልማት ለብቻው ዘላቂነት የለውም” በሚል ርእስ ለማቅረብ ያነሳሳኝ::

አዎ!! በኢትዮ}ያ ውስጥ መንግስት በሚቆጣጠራቸው የዜና ማገናኛ አውታሮች አማካኝነት ህወሓት የተመሰረተበትን 40ኛው ዓመት በትግራይ በድምቀት እናከብራለን በማለት ብዙ እንቅስቃሴዎችንና ቅስቀሳዎችን እየተካሄዱ እንደሆነ አያለሁ:: እኔ ይህን በዓል መከበሩ ምንም ተቃውሞ የለኝም:: ነገር ግን ከበዓሉ በስተጀርባ ያሉትን ሁኔታዎችና ሌሎች መመለስ ያለባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉኝ:: ከ60 ሽሕ በላይ ታጋዮች የተሰዉበት፣ የቆሰሉበት፣ አካላቸውን የተጎዱበትና ባጠቃላይ ለበርካታ ዓመታት ያህል መራራ ትግል የተካሄደበትን ምክንያት አላማው ምን ነበር? አሁንስ ከ40 ዓመት በሗላ የትግራይ ህዝብ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የነገ ተስፋውና ዕድሉስ በምን ላይ የተመሰረተ ነው? የሚሉ ለህልውና ወሳኝ የሆኑትን መሰረታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ አለባቸው ብዬ በፅኑ አምናለሁኝ:: የዛሬው ሶስተኛው ፅሑፌም በነዚህ አንኳር ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩር ይሆናል::

  • የትግራይ ህዝብ ነፃነቱን፣ ክብሩንና ማንነቱን የተነጠቀ ህዝብ ነው::

ህወሓት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ነኝ ይበል እንጂ ተግባሩ ግን በተቃራኒው ነው:: ህወሓት የትግራይን ህዝብ የሚያየው እንደ የግል ንብረቱንና የስልጣኑን መሳሪያ እንጂ እንደ ሉዓላዊ ነፃነትና ማንነት ያለው ባለታሪክ ህዝብ አድርጎ አይደለም:: ከዚህ በመነሳት ህወሓት ከህዝብ፣ ከሀገርና ከሕግ በላይ እንዲታይ፣ ከፓለቲካዊ ድርጅትነት አልፎም በትግራይ እንደ ጣዖት እንዲመለክ፣ ከህወሓት በስተቀር ሌላ ስለሀገሩና ስለህዝቡ የሚያስብ ዜጋ እንደሌለ አድርጎ ያስባል:: በዚህ መሰረት ከህወሓት የተለየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች እንደጠላት በመፈረጅ የፓለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ሳይሆን እንደሰብኣዊ ፍጡርም በነፃ የመንቀሳቀስ መብታቸውንም በመከልከል ዓፋኝ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል:: የፓለቲካ ምሕዳሩንም በሞኖፓል ይዞ የትግራይ ህዝብ ህልውና ከህወሓት ህልውና ጋር የተቆራኘና ህወሓት ሲኖር የሚኖር ህወሓት ከሌለ ደግሞ እንደ ህዝብ ህልውናውንም አብሮ የሚጠፋ አድርጎ ያስተምራል::

ህወሓት የትግራይ ህዝብ ባለውለታ መስሎ ይቅረብ እንጂ የህዝቡን ነፃነት፣ መሬት፣ ሉዓላዊነትና ክብር በባዕዳን ያስደፈረ፣ ለወራሪ አሳልፎ የሰጠ ድርጅት መሆኑ የትናንት ትዝታ ነው:: ታዲያ የትግራይ ህዝብ የህወሓት 40ኛ የልደት በዓልን ሲያከብር ምን እያስታወሰ ነው ሰልፍ የሚወጣው? እውነት የባሕር በሯን የተዘጋ ሽባ ሀገር ይዞ በመቅረቱ፣ ያ ሁሉ ወጣት የወደቀበትን ባድመን ለሻዕቢያ መሸለሙ፣ የኢትዮ}ያ አንጡራ ሀብትና ብሄራዊ ጥቅም ለባዕዳን መሸጡ፣ ባጠቃላይ በሻዕቢያ ተደፍሮ የዓደይር እልቂትንና አሁንም ቢሆን በየቀኑ በታጣቂ ሐይሎች እየታፈኑ ወደ ኤርትራ የሚሻገሩትን ልጆቹ ሞት አሜን ብሎ በመቀበሉና በመደሰቱ ይሆን? መልሱን የጥቃቱን ሰለባ ለሆነው የትግራይ ህዝብ እተወዋለሁ::

የትግራይ ህዝብ ነፃነቱንና ክብሩን በአንድ ድርጅት ህወሓት የተነጠቀ ህዝብ ነው ስል ምናልባት ቀላልና የተለመደ አነጋገር ይመስል ይሆናል:: ምናልባት አንዳንዶቻችሁም ህወሓት በትግራይ ስለተፈጠረ በራሱ ህዝብ ላይ ያን ያህል አይጨክንም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል:: ግን አይደለም በተቃራኒው ነው:: ሌላ ቀርቶ በሌላ አካባቢ በትንሹም ቢሆን ለቀቅ የተደረጉትን መብቶች እንኳን በትግራይ የሉም:: በትግራይ ከህወሓት የተለየ ሐሳብ ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ በነፃ መደራጀት፣ የመናገር ነፃነት፣ የመስራትና ሀብት የማፍራት ነፃነት፣ የመማርና የማስተማር ነፃነት፣ የመፃፍ ነፃነት ቀርቶ ሌላ አካል የፃፈውን ፅሑፍ እንኳን የማንበብ ነፃነት የለም:: የተገደበና የተነጠቀ ነው:: የህወሓት አባልና ደጋፊ ካልሆንክ በስተቀር ሌላ አመለካከት ይዘህ ወይም ነፃ ሰው ሆነህ ማሕበራዊ፣ ኢኮናሚያዊና ፓለቲካዊ ነፃነትህን የተገደበና የተከለከለ ነው:: ባጠቃላይ ሁሉንም አማራጭ መንገዶችን በመዘጋትና በማጨለም የትግራይ ህዝብ ወደደም ጠላም ለአንድ ድርጅት ብቻ እንዲያመልክና በሞኖፓል ተይዞ የአንድ ድርጅት የህወሓት አገልጋይ ሆኖ እንዲኖር እየተደረገ ነው ያለው::

ህወሓት የትግራይ ህዝብ ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳይወጣና ሌላ ነገር እንዳያስብ እስከ ቤተሰብ ድረስ የዘለቀና የተተበተበ የስለላ መረብ፣ አንድ ለአምሰት የሚሉ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀቶች በትግራይ የባሱና የጠነከሩ ናቸው:: ከመደበኛ ታጣቂዎች በተጨማሪ ሌላ ማን እንዳደራጃቸው እንኳን በውል የማይታወቁ በአውራጃ፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ሲቪል መስለው የሚንቀሳቀሱ የስለላ ቡድኖች ተበራክቷል:: ሌሎች የመንግስት የአስተዳደርና የአገልግሎት ተቋማትም የተሞሉት በካድሬዎችና በታማኝ አባላት ነው:: እነዚህ ሁሉ ተደምረው ህዝቡን መፈናፈኛ በማሳጣት ነፃነቱንና መብቱን የሚነጥቁ ናቸው:: ይህን ሁሉ ስናይ ሊነሳ ይሚችለው መሰረታዊ ጥያቄ በህወሓት መሪነት ለአርባ ዓመታት የተካሄደው መራራ ትግል ትርፋቱ ምንድን ነው? በህዝቡ ጫንቃ ላይ የተጫነው ጭቆና እስከመቼ ይሆን? የሚለው ነው::

  • የትግራይ ህዝብ መለስን እንደ ጣዖት እንዲያመልክ እየተገደደ ነው::

ካሁን በፊት አንዳንድ ሰዎች ህወሓት እንደ ድሮ እንዳይመስልህ የአንድ ቤተሰብ ብሎም የአንድ ግለሰብ የአቶ መለስ ዜናዊ የግል ኩባንያ ሆኗል ብለው ሲነግሩኝ አባባሉ ራሱ ለማመንና ለመቀበል አይዋጥልኝም ነበር:: ምክንያቱም ስንት ታጋይ ጀግኖች የነበሩበትና የተሰዉበትን ድርጅት ከመሆኑም በላይ ሰፊው የድርጅቱን ታጋይ ዝም ብሎ ጭራሽ የአንድ ግለሰብ አገልጋይ ሆኗል ብዬ ለማመን ያስቸግረኝ ነበር:: ይሁን እንጂ ባለፈው ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ህልፈት በሗላ ትግራይ ድረስ ሄጄ ያሁትንና የታዘብኩትን ሁኔታ ግን ከገመትኩት በላይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ:: እውነትም እንዲህ ይደረጋል የሚያስብል አሳፋሪ ክስተት አይቻለሁ::

ያ ሁሉ ለዘመናት ታግሎ ሀገሩን፣ ክብሩንና ነፃነቱን ጠብቆ የኖረ አንቱ የሚባል የትግራይ ህዝብ፣ ብዙ ጀግኖችና ምሁራን እንደነ ነገድ ራስ ገብረህይወት ባይከዳይ፣ ነጉሰ ነገስት አፄ ውሃንስ አራተኛ፣ ራሰ ጅንራል ሉላ አባነጋ፣ ጀነራል ሐየሎም አርአያ እና በርካታ ስመ ጥር ኢትዮጵያውያን  እንዳላፈራ ሁሉ ዛሬ ህዝቡ በህወሓት የተፈጠረና አንድ ግለሰብ ብቻ ታግሎ ነፃ ያወጣው በማስመሰል የመለስ ዜናዊን ምስል በአቋራጭ ገብቶ እንደጣዖት እንዲያመልክ እየተገደደ መሆኑን ሳይ በጣም አዝኛለሁ:: ጠላ ቤቶችም ሳይቀር የመለስ ስእል ግድግዳቸው ወይም ቤታቸው ደጃፍ ላይ ካልለጠፉ የመለስ ራእይ ተቃዋሚ ናችሁ እየተባሉ በማስፈራራት እስከ ንግድ ፈቃዳቸው የሚነጠቁ ሰዎች እንዳሉ ተነግሮኛል:: ጉድ ነው!! መሪ ማክበር ባህላችን ቢሆንም:: መሪ እንደጣዖት ማምለክ ግን ነውር ነው::

አስታውሳለሁ ህወሓት በትጥቅ ትግሉ ዘመን የዘውድ አምላኪዎች ናችሁ እየተባሉ በህወሓት የተመቱ ባላባቶችና ደጋፊዎች ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም::የንጉስ ሀይለስላሴ ፎቶ ግራፎችና ምስሎች ከያሉበት እየተነቀሉ ሲቃጠሉና ሲወገዙ እንደነበርም የሚታወስ ነው:: በሗላም የመንግስቱ ሀይለማሪያም አብዮታዊ መሪ ፎቶ ግራፍ በየመስሪያ ቤቱና ኢሰፓ ባለበት ሁሉ ይንጠለጠሉ እንደነበር ህወሓት ራሱ ሲያወግዘው የነበረ ነው:: ሰሜን ኮሪያን ጨምሮ የኮሚኒስት ስርዓት አራማጆች የሆኑት እንደነ ቻይና፣ ሶቤትና አልባኒያ የመሳሰሉትን ሀገሮች የነ ማኦ፣ ሌኒና ማርክስ የመሳሰሉትን የአብዮታዊያን ፎቶ ግራፍ ሲለጥፉና ሲያምልኩም ታይቷል:: ታዲያ አቶ መለስ ዜናዊ ከሌላው ኢትዮያዊ በተለየ መልኩ የትግራይ ህዝብ ነብዪ ተደርጎ እንደ ጣዖት እንዲያመለክ ማድረጉ በምን ሂሳብ ነው? ከመለስ በላይ እኮ ክቡር ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ይቺን ሀገር አንድነትዋንና ክብርዋን ጠብቀው ነፃነትና ክብር ያወረሱን ሰዎች ሆን ተብሎ ስማቸው እንኳን እንዳይነሳ እየተደረገ፣ በአንፃሩ የባዕድ ጠበቃ በመሆን ክብራችንን፣ ማንነታችንና ነፃነታችንን አስደፍረው ጎደሎ ሀገርን ያስረከቡን ሰዎች እንዴት ብለው ነው የትግራይ ህዝብ ነብዪ መሆን የሚችሉ?

ይህ ብቻ አይደለም ቀደም ሲል አንድ ብር ብቻ በመክፈል ይወጣ የነበረው የቀበሌ መታወቂያ ከመለስ ህልፈት በሗላ ግን መታወቂያ ካርድ ለማውጣት ወደ ቀበሌ ሲሄዱ ለመለስ ዜናዊ ፋውንደሽን መስሪያ 100 ብር ክፈሉ እየተባሉ እንደሚገደዱ በዓይኔ አይቻለሁ:: ይህም በአንድ በኩል የህዝቡን ገንዘብ ለመዝረፍ ሆን ተብሎ የተቀረፀ ፕላን ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የያንዳንዱ ትግራዋይ ማንነት ከመለስ ዜናዊ እምነትና ማንነት ጋር እንዲያያዝ የተደረገ የስነ ልቦና ሰለባ ነው:: ይህ ዓይነቱን አሰራር የሚያመለክተው ለህዝቡ ያላቸውን ንቀትና ግምት ምን ያህል እንደሆነ ነው::

ከዚህ ተነስተን ማለት የምንችለው ነገር ቢኖር ያ ሁሉ የተደረገው ትግልና የተከፈለው መስዋእትነት አላማው አንድ ሰውን ለማንገስና ለማወደስ ነበር ወይ? የሚለው ነው::

 

 

  1. ኢትዮ}ያ ሀገራችን ደህንነትዋን አደጋ ላይ የሚጥሉና የህዝቡዋን

ሉዓላዊ አንድነትና ሰላም የሚፈታተኑ ምልክቶች እየታዩ ናቸው::

 

በአፍሪቃ ቀንድ በተለይም በኢትዮ}ያና በኤርትራ መካከል ስላለው ውስብስብ ጂኦፓለቲካዊ ሁኔታ በዚሁ አጭር ፅሑፍ ተንትኖ የሚያልቅ አይደለም:: ራሱ የቻለ በሌላ ጊዜ ሊቀርብ የሚችል ሰፊና ውስብስብ ጉዳይ ነው:: ለዛሬ ግን በዚሁ ንኡስ ርእስ በአጭሩ ለመጥቀስ የፈለኩትን ነጥብ አለ:: በሀገር ቤት ቆይታዬ በትግራይና በኤርትራ አዋሳኝ ቦታዎች ያለው የሰዎች መተላለፍ (Human trafficking) በሚመለከት ከቁጥጥር ውጭ የሆነና ለሀገራችን ድህንነት በተለይ ለአካባቢው ህዝብ ሰላምና ደህንነት አስጊ ሁኔታ መስሎ ስለታየኝ ነው:: በዚሁ ነጥብ ዙሪያ ጠለቅ ያለ ዝርዝር ጥናታዊ ዘገባ የሚጠይቅ ቢሆንም የተለያዩ ሰዎች ሲናገሩና እኔም ራሴ በአካል የታዘብኩዋቸውና አሁንም በተመሳሳይ መልኩ እተየተፈፀሙት ያሉትን አንዳንድ ፍንጭ ሰጪ ምልክቶች እንዳሉ ለመጠቆም ነው::

በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎችም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ተደጋግሞ እንደተገለፀው በየወሩ በሽዎች የሚገመቱ በስመ ስደተኝነት ከኤርትራ ወደ ትግራይ እንደሚገቡ ይታወቃል:: እነዚህ ሰዎች ዳር ድንበሩን ተሻግረው ከገቡ በሗላም በተዘጋጀላቸው የመጠለያ ስፍራ ይገባሉ ቢባልም ከትንሽ ጊዜ በሗላ በነፃ በመንቀሳቀስ በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭተው እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው በመማር ላይ የሚገኙ ናቸው:: የኔ ስጋት ለምን ኤርትራውያን ወደ ኢትዮ}ያ ገቡ አይደለም:: ከሰፊው የኤርትራ ህዝብም ምንም ዓይነት የጥላቻ ወይም መጥፎ አመለካከት የለኝም:: የችግሮቹ መንሲኤ ህዝብ ሳይሆን ማን እንደሆነ ጠንቅቄ እገነዘባለሁ:: ዋናው ጉዳይ ግን የነዚህን ሰዎች እንቅስቃሴ የሚከታተል ማን ነው? የሚለው ነው:: የሁለቱን ሀገሮች ወታደሮች በተፋጠጥ ላይ ያሉበትን አዋሳኝ ቦታዎች ከኤርትራ ድንበርን ተሻግሮ ወደ ትግራይ መሬት የሚመጣው ሰው ሁሉ እውነተኛ ስደተኛ ነው ወይ? የሚል ነው::

ከዚሁ ድንበርን ተሻግረው የሚተላለፉ ሰዎች ጋር ተያይዞ የሚታየው ሌላው ክስተት በሌሎች የዓለማችን ማዕዝናት እንደሚደረገው ሁሉ የሰዎች ዝውውር ንግድ ነው:: በሁለቱም ሀገሮች አዋሳኝ ቦታዎች አካባቢ ሰዎችን በማመላለስና በማሻገር ሕገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደላሎች እየተበራከቱ መጥቷል:: እነዚህ ደላሎችም ተራ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዶቹም እስከ ላይ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ድረስ ሰንሰለታዊ ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ናቸው:: ለምሳሌ በኢትዮ}ያ በኩል በዚሁ ሕገ ወጥ ስራ ከተሰማሩት ሰዎች ውስጥ ለጊዜው ስሙን ለመጥቀስ ያልፈለኩትን በኢትዮ}ያ የከፍተኛ ባለስልጣን የቅርብ ዘመድ (ወንድም) ይገኝበታል:: ይህ ግለሰብ በዚሁ ሕገ ወጥ ስራ በመሰማራት ኢትዮ}ያ ውስጥ በስለላ ስራ ላይ የነበሩትን ሰዎች በመኪና ጭኖ ወደ ኤርትራ ሲያሻግር እጅ ከፍንጅ ተይዞ በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን በተጨባጭ የሚታወቅ ነው:: ይህ ጉዳይ ለራሱም ትልቅ ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችል ነገር ነው::

ሌላው አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ የሻዕቢያ መንግስት ተቃዋሚዎችን እየፈለፈለ አንዱን በአንዱ ላይ እያዘመተ የአካባቢውን ህዝብ ንሮና ሰላም የሚያናጋ የጥፋትና የመበቃቀል ሰራ እየሰራ መሆኑን ነው:: ለምሳሌ ሻዕቢያ እያስታጠቀና እያደራጀ ወደ ኢትዮ}ያ ከሚልካቸው ታጣቂ ቡድኖች አንዱ የሆነውን “ደምህት” – ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ፣ በአማርኛ ሲተረጎም (የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በሚል ስያሜ የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን በርካታ ቁጥር ያላቸው በኤርትራ የመሸጉትን አባላቱ በየጊዜው ወደ ትግራይ ሸልከው እየገቡ የሚፈልጉትን ሰው ገድለው ወይም ዓፍነው በመውሰድ በሰላማዊ ህዝብ ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት ሲታይ የትግራይ ህዝብ በማያባራ ጦርነት አሁንም እየደማ እንዳለ የሚያሳይ ነው:: በዚህ ካባቢዎች ያለ የልማት እንቅስቃሴም በከፍተኛ ደረጃ ተጎደቶዋል፡፡

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት ሰዎች እንደሚሉት ሻዕቢያ ሀገራችንን ከወረረ ወዲህ ባለፉት ዓሰርቱ ዓመታት ብቻ በሑመራ አካባቢ በጀምላ ታፍሰው የተወሰዱትን ዜጎች ጨምሮ በሽዎች የሚገመቱ ወገኖችን በተለያየ ጊዜ ታፍነው ተወስዷል:: ታፍነው የተወሰዱት ሰዎችም የት እንደደረሱ ደብዛቸው ጠፍቶ ቀርቷል:: ይህ በየጊዜው የሚከሰተው ችግር በውል የሚታወቅና የጥቃቱን ሰለባ የሆኑ ያካባቢው ነዋሪዎቸች ለመንግስት ቢያመለክትም አሁንም ሰሚ ጆሮ አልተገኘም:: ሌላ ቀርቶ በዜና ማሰራጫ እንኳን አይቀርብም:: አንድ ቀን የውጭ የጀርመን ዜጎች በአፋር አካባቢ ታፍነው በተወሰዱበት ጊዜ ብቻ በዜና ሲተላለፍ ሰማን እንጂ ከዚያ በፊትም ሆነ በሗል የደረሱትን ጥቃቶች በሚመለከት የተነገረና የተወሰደ እርምጃ የለም:: አዎ “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዕድሜ ልኩን እየደማ ይኖራል” እንደተባለው ሁሉ ከአርባ ዓመት መራራ ትግል በሗላ አሁንም ይህ ዓይነት ጥቃት መታየቱ ለምን ይሆን? ይህ ሚስኪን ህዝብ ከዚህ ስጋትና ስቃይ ተላቆ እፎይታ የሚያገኝበት ቀንስ መቼ ይሆን? የኤርትራ አጀንዳ እስከ መቼ የትግራይ ህዝብ ዕዳ ሆኖ ይኖራል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለትውልድ የዘለቁ ችግሮች ናቸው::

  1. ለችግሮቻችንን መንሲኤና መፍትሄ ምንድን ናቸው? አጭር ማጠቃሊያ

የህዘባችን ሶቆቃ ትግራይን እንደ ምሳሌ አድርጌ ባቀረብኩዋቸው 3 ተከታታይ ፅሑፎቼ ውስጥ የተጠቁሱትን ችግሮች ብቻ በማንሳት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም:: የችግሩን ጥልቀትና አሳሳቢነት ከተጠቀሰው በላይ ነው:: አሁን ስላለው የሀገራችን ሁኔታ መርዶ ነጋሪ በመሆን ብቻ ችግሩን የሚቃለል አይደለም:: ችግራችንን ለይተን ማወቅና መገንዘብ አንድ እርምጃ ወደፊት ቢሆንም ዋናውና ህዝባዊ ሃላፊነትን በውል የሚጠይቅ ትልቁ ጉዳይ ግን የመፍትሄውም አካል ሆኖ መገኘት ነው::

በግሌ እንደ አንድ ኢትዮ}ያዊ ሁኘ ራሴም እዛ ውስጥ አስገብቼ ስመለከተው የችግራችንን  መንሲኤ ከስርዓቱ ባህርይ የሚመነጩ ቢሆኑም ለችግሩ መራዘምና መባባስ ደግሞ የተቃዋሚ ሐይሉ አስተዋፀዖም ቀላል አይደለም:: “የህዝብ ወገን ነን፣ ሀገር ወዳድ ነን፣ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ቁመናል፣ ያገራችን ጉዳይ እኛም ያገባናል፣ ያንገበግበናል፣” የምንል ኢትዮ}ያውያን ሁሉ አሁን ከአርባ ዓመት በሗላ የት ላይ ደርሰናል? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ነን ያለነው? ከዚሁ አስከፊ ችግር ለመላቀቅስ እስካሁን ድረስ የተማርነውና ያደረግነው ያደረጃጀት ለውጥ አለ ወይ? በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለጥቅሙና ለስልጣኑ ሲል ከጊዜ ጋር እየተሻማ፣ ስልቱንና ቀለሙን በየጊዜው እየቀያየረ ለየብቻችን ለያይቶ ሲቀጠቅጠን ያደረግነው የትግል ለውጥ አለ ወይ? ብለህ እንድትጠይቅ የሚገፋፋ ነው::

በኔ እይታ መልሱ የለም ነው:: የለም ስል ደግሞ በተናጠል ሆኖ የተደረገ ትግልና የተከፈለ መስዋእትንት የለም ማለቴ አይደለም:: በተለይም በሀገር ውስጥ ሆነው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መስእዋትነትን እየከፈሉ ለሚገኙ ታጋዮች ሁሉ ከበሬታ አለኝ:: ነገር ግን ትግሉ በተናጠልና በተበታተነ መልኩ እስከሆነ ድረስ ውጤቱ ተስፋ ሰጪ ሳይሆን ሁሉ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጥ ዜና ነው የምትሰማው:: ትግሉ በተናጠል መሆኑን ደግሞ የጠቀመው ሀገርንና ህዝብን ሳይሆን በስልጣን ላይ ያለው ጨቋኝ ስርዓትን ነው:: ይህም እኛው ራሳችንን ለችግርና ለጥቃት የተጋለጥንና የተመቻቸን እንድንሆን አድረጎናል::

ለችግራችን መራዘምና መባባስ በተናጠል ትግል ማድረጋችን ብቻ አይደለም:: የምናራምደው አመለካከትም ጭምር ነው:: ለምሳሌ አብዛኞቻችን በስልጣን ላይ ላለው ስርዓት ሁሉ ጊዜ በከፋፋይነት፣ በዘረኝነት፣ በጎጠኝነትና በፀረ አንድነት ተግባራቱንና ፓሊሲው እንወነጅላለን:: ነገር ግን ለራሳችን ከነዚህ ሗላቀር አመለካከቶች ምን ያህል የፀዳን ነን? የሚል ጥያቄ ብዙ ሊያከራክር እንደሚችል ይገባኛል:: ለአንዳንዶቻችንም እሬት እሬት የሚል አባባል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ:: ምናልባትም ከመንግስት ጋር ሲነፃፀር መጠኑ ሊለያይ ይችላል እንጂ ወደድንም ጠላንም ለበርካታ ዓመታት ለትግሉ ጎራ መዳከምና መሰነጣጠቅ ትልቅ እንቅፋት ሆነው የሚገኙ፣ በአብዛኞቻችን አእምሮ ውስጥ የተከተቡና አምርረን ልንታገላቸው የሚገባን ደካማ አመለካከቶች ናቸው::

ለችግሮቻችን መንሲኤ እንደሆን ሁሉ ከጭቆናውና ከችግሩ ለመላቀቅም መፍትሄ የምንሆነው እኛው ራሳችን ነን:: በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት በህዝባችን ላይ የሚያደርሰው ጭቆና ጉልበት ስላለው ወይም የበለጠ እውቀትና ጀግንነት ስላለው አይደለም:: የተቃዋሚ ሐይሉ መነጣጠል፣ መጠላለፍ፣ እርስ በርስ መጎነታተልና መበታተን ለነሱ ትልቅ ዕድል ሆኖ ስለቆየ ነው:: “ላንስማማ ተስማምተናል” እንደተባለው ሁሉ ህዝቡ ደጋግሞ ጥሪውን ሲያቀርብ ቆይቷል:: አሁንም እያቀረበ ነው:: “እባካችሁ ተባበሩ፣ አንድ ሁኑ፣ አትከፋፍሉን፣ ትግሉን አታበላሹ፣ እንቅፋት አትሁኑ፣ ተበታትናችሁ የስርዓቱን መጫወቻ አትሁኑ፣” እያለ ሲጮኽ ሰሚ አላገኘም:: በአግባቡ አላዳመጥነውም:: የህዝቡን ንቃተ ህሊናና ግንዛቤ ከፓለቲካ ድርጅቶች ሐይሎች በላይ ስለሄደ የማዳመጥ ዓቅሙም፣ ሞራሉም የለንም:: በሌላ አነጋገር ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ድርጅት እንኳን መፍጠር አቅቶን እርስ በራሳችን የገመድ ጉተታ ስንጫወት ጊዜው መሽቶብናል:: ስለዚህ የብሄር ብሄረሰቦቻችን ትክክለኛ ገፅታ፣ የሀገራችንን ተጨባጭ እውነታ፣ የህዝባችንን የልብ ትርታና አቤቱታ የሚያዳምጥና የሚያቅፍ የትግል መሰመርና ራእይ የያዘ ሀገራዊ ድርጅት መፍጠርና ማጠናከር የግድ ይላል:: ካልሆነ ግን ከአንድ ወንዝ የተቀዳ አመለካከት ያላቸው ጥቂት ድርጅቶች በተቃውሞ ስም የሚሰሩትን ድራማ ተመልካች ብቻ ሆነን ልንኖር ነው::

ወንድሞቼና እህቶቼ!! ተባብሮ መስራት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ በ1997 ዓ.ም የነበረው የምርጫ ዘመን አይተናል:: ነገር ግን የነበረው መተባበር ከቡድናዊ ፍቅር፣ ከስልጣን ሽኩቻና ከጥላቻ ፓለቲካ የፀዳ ስላልነበረና ከልብ የመነጨ ዝግጁነት ስላልነበረው እንደጉም ተበታትኖ ቀርቷል:: በዚህ ምክንያት የነበረው የህዝቡን መነሳሳትና የለውጥ ተስፋም ሐቀኛ የፓለቲካ መሪ ድርጅት ስላላገኘ ተኰላሽቶ ቀርቷል:: የነበረው ብሩህ ተስፋም ጨልሟል:: የስንቱ ለጋ ወጣቶች መስዋእነትም ያለ ውጤት ቀርቷል:: በ97ቱ ከነበረው እንቅስቃሴ የበለጠ ተሞኩሮ ያገኘበትና የተማረበትም ተቃዋሚው ሐይል ሳይሆን  በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ነው::

ከዚያ በሗላም ምናልባት ካለፈው ተምረው አንድ የተሻለ የትግል ስትራተጂና ራእይ ቀይሰው ይመጡ ይሆናል ብለን ስንጠብቅ “መድረክ” ተፈጠረ:: መድረክ በኢትዮ}ያ ውስጥ የነበረውና በቅንጅት ተስፋ የቆረጠውና የተበታተነው ትግል አስተባብሮ አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ድርጅት ለመመስረት ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ተብሎ በብዙ ኢትዮ}ያውያን ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ከቅንጅት በተወረሱ አንዳንድ በሽታዎች ምክንያት እንደ ታሰበው ያህል አልተራመደም:: በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረ ዳግም መነሳሳትም ቀዝቀዝ ብሏል::

ይህ ዓይነቱ የፓለቲካ አዙሪት (VICIOUS CIRCLE) አሁንም እየታየ ያለው ነው:: ዋናው ችግራችን ደግሞ አለመተባበራችን ብቻ አይደለም ከውድቀታችንና ከራሳችን ተሞኩሮም አለመማራችንም ጭምር ነው:: ስለዚህ እየወደቁ እየተነሱ የሚካሄዱ የተበታተኑ የትግል እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ድምር ውጤታቸው ሲታይ ዳገት መውጣት አልቻሉም:: ስለዚህ ይህንን አዙሪት ሰብሮ የሚወጣ የተቀናጀና የተዋሃሃደ ትግል፣ ፐሮገራም ወጥ እና ሁሉንም ሊያሳትፍ ሚችል ሃገራዊ አሰላለፍ መፍጠር አስፈላጊ ይሆናል::

ሕብረታችንና አንድነታችንን ይለምልም

አስተያየት ለመስጠት ይህን ኢሜይል ይጠቀሙ እቀበላለሁ

ኢትዮ}ያ ለዘላለም ትኑር

 

 

[email protected]

The post የትግራይ ህዝብ የአርባ ዓመት ሶቆቃ – ከይኩኖ መስፍን appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.