ሕገ መንግስቱን በጫጭቆ የጣለው ሕወሃት – ግርማ ካሳ
በኢትዮጵያ ሕግ አለ ነው የሚሉ። የሕግ ሁሉ የበለያ ደግሞ ሕግ መንግስቱ ነው። በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 21 እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡
———-
አንቀጽ 21
በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት
1. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው።
2. ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንዲጎበኛቸውም እድል የማግኘት መብት አላቸው።
——————
የሕወሃት አገዛዝ ግን ያዉ እንደለመደው ለሕጉና ለሕገ መንግስቱ ንቀት እያሳዩ ነው። ለነርሱ ሕግ መንግስቱ ተራ ወረቀት ነው። የጋዜጠኛ ተመስገን ደስ አለኝ እናት ልጃቸውን ማየት በመከልከላቸው የጻፉትን ደብዳቤ ያንብቡ።
እስቲ ፍረዱ አሁን እኝህ እናት ልጃቸውን እንዳይጎበኙ መደረጋቸው ክፋትና ጭካኔ እንዲሁም በቀል እንጂ፣ ለሕወሃት ሽፍታ አመራሮች ምን የሚያስቀርባቸው ነገር አለ ? አሁን እኝህ እናት ልጃቸውን በመጠየቃቸው የአገር ደህንነት ችግር ዉስጥ ይገባል ?
ለዚህ ሽፍታ የሕወሃት ቡድን ጥብቅና ለቆማችሁ፣ እስቲ መከራከሪያችሁን አቅርቡ። እስቲ እንደ ፋና የመሳሰሉ የሚረጩትን ተራ የካድሬ ፐሮፖጋንዳዎች ወደዚያ ጣሉና፣ ሕገ መንግስቱን አንብቡት። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሕግን የማክበር ነገር የታለ ? ሕግ አስፈጻሚው ራሱ ያላከበረዉን ሕግ ሌሎች ባያከብሩት ለምን ሊባሉስ ይችላልን ? ሕግ አስፈጻጻሚ ህግን አክብሮ ሕግ አላከበራችሁም ብሎ በሕግ ቢቀጣ ያምርበታል። ራሱ አሸባሪ ሆኖ ሌላውን ሽብርተኛ ማለት፣ ራሱ በሙስና የተዘፈቀ ሆኖ ሌላውን በሙስና መክሰስ፣ ራሱ ሕግና ሕግ መንግስቱን ባፈጠጠ መልኩ እየጣሰ ሕግ ተጣሰ ማለት አያስኬድም።