ስለ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአጭሩ – ከ አርአያ ማጁ
በአብዛኛዎቹ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገረሮች የቅርብ ጓደኞቼ ናቸው ብዙ ጊዜ አንዱን ጥዬ አንዱን ማንሳት ይከብደኛል ስለ ሁሉም ለማለት ደሞ ስንቱ ይወራል?
በተለይ በቅርብ ጓደኛዬ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዙርያ ብዙ ጊዜ ለመጻፍ እሞክር እና ስሜታዊ ሆኜ ብዙ ሰዎችን አስከፋለሁ ብዬ ስለማስብ እተወዋለሁ፡፡

ዛሬ ግን ስለተመስገን በአጭሩ የሆነ ነገር ለማለት ፈለኩ፡፡ ማጋነን ባይሆንም በአንድ ወቅት በተለይ ፍትህ ጋዜጣ በነበረችበት ሰዓት የተመስገን ዝና ጣራ ነክቶ ነብር፤ ምግብ ቤት ገብቶ ምሳ በልቶ ሂሳብ መክፈል እንኳ አይቻልም ነበር፡፡ በጣም አስገራሚ ገጠመኞች እኔም ለማየት ችያለሁ በአንድ ወቅት የወዳጃችን አቤ ቶክቻው/Abebe Tolla/ ባለቤት ሮሚን አንኳን ማርያም ማረችሽ ለማለት በአንድ ካፍቴሪያ ኬክ ለመጋዛት ስንገባ በአካባቢው የነበሩ ወጣቶች መጥተው ምሳ ካልጋበዝንህ ብለው ያስቸግራሉ ሆኖም አንደምንቸኩል እና ቢሮ ቢመጡ ሊያወሩ እንደሚችሉ ነግሯቸው አድራሻ ይሰጣቸዋል በዚህ መሀል አንዱ አንገቱ ላይ ያለውን ወርቅ አውልቆ ይሄንን ካላጠለኩልህ በፍጹም አታልፍም በሚል ከረጅም ደቂቃ ንትርክ በኋላ ወርቁን ተመስገን አንገት ላይ አጥልቆለት ተለያየን፡፡ ይሄ ከበርካታ ገጠመኞች አንዱ የነበረውን ዝና የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም ይሄ መወደዱ እና ክብሩ የማይወጣላቸው የስርዓቱ ሰዎች ብቻ አልነበሩም እንደውም በሚዲያው ዙርያ ያሉት ጓዶቹም ጭምር እንጂ፡፡ የተመስገንን ስብዕና ግን አብረውት የሰሩ ሊመሰክሩለት ይችላሉ፡፡ ተመስገን ከፍትህ ጋዜጣ ጀምሮ አዲስ ታይምስ – ልዕልና – ፋክት ሚዲያዎች ላይ ሲሰራ አብረውት የሚሰሩ ባልደረቦቹ ብቻ ሳይሆኑ ከአንጋፋዎቹ እስከ ወጣቶቹ አምደኞች በጽናት ሳይበታተኑ ለአመታት ተጉዘዋል፡፡ ምን አይነት አክብሮት ቢኖራቸው ነው? እኔ አያምርብኝም መወደስ እንዳይሆን ሌላ ሰው ቢያወራው እመርጣለሁ፡፡
በተቃራኒው በተለይ አንዳንድ በስደት ላይ ያሉ ጋዜጠኖች በተመስገን ዙርያ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፤ ለምን አይታሰርም? ለምን እንደኛ አልተሰደደም? እንዴት እንዲህ በድፍረት ይጽፋል? የሆነ ነገር ከጀርባው ቢኖር ነው እንጂ አይነት አሉባልታዎችን ሲያናፍሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በአጋጣሚ ካገኘኋቸው የአለም ዓቀፍ ተቋማት ሀላፊዎች ሁለቱ በተለያየ ጊዜ ዳር ዳር እያሉ እንዚህ ሀሜቶችን እንደሰሙ ነግረውኛል ከማንም እንደሰሙ ለማወቅ ችያለሁ፤ እዚህ ጋር ማውራት ጠቃሚም አይደል፤ ከዛም አልፎ በዲሲ ካፌዎች ጭምር በአደባባይ እሱ ምን ስለሆነ ነው የማይታሰረው የሚል አርእስት ከፍተው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታዬ ነው፡፡ አንኳን ደስ አላችሁ ይሄው ዛሬ መታሰር ብቻ አይደለም ከሌላው እስረኛ በተለየ ማንም አይጠይቀው ማንም አያወራለት፣ ምግብ አይገባለት፤ እሚጮህለት የለ፡፡ ያማል ከምር ያማል ሁሉም ነገር በቲፎዞ ሁሉ ነገር በደቦ፡፡ ለነገሩ አንደኔ አይነቱ ገና ጃስ ሲሉት ለሚፈረጥጥ የተመስገን ተጋድሎ ያሳጣዋል አውቃለሁ፡፡ ተመስገን የፍርሀት ቆፈናችንን አደባባይ አውጥቶ ያሰጣብን እንደሆነም አውቃለሁ፡፡
ብዙ ባወራ ብዙ ሰው አስከፋለሁ ግን እንዴት አንድም ጋዜጠኛ ስለተመስገን ሲጽፍ አላይም ስሙንም ማንሳት አይፈልግም ለምን እንደሆነ ደሞ በደንብ አሳምሬ አውቃለሁ ከሱ ጋር የተገናኘ ሳይሆን እሱን ማንሳት እራስን ማኮሰስ ስለሚመስላቸው ነው፡፡
ተመስገን ምን የሚቆጨው ነገር ይኖር? መናገር ያለበትን እስከጥግ በአደባባይ ተናግሮ የወጣለት ሰው ነው፡፡ ዛሬ እሱ ያበረከተውን አስተጽኦ ማየት ባንፈልግም፣ እውቅና መስጠት ባንሻም ግድ የለም ታሪክ አንድ ቀን ያየዋል፡፡
ተሜ አንተ ነጻ ሰው ነህ! ያሻህን ተናግረህ ያሻህን አድርገህ ከነነጻነትህ በቦታ ብቻ ተከልለህ አለህ፡፡ ይብላን ለኛ የምናወራውን ለማንሆን የራሳችንን ነፃነት በሌለው ፍርሀት ለምንለካ፡፡
አዎ ተሜ አንተ ነፃ ሰው ነህ!
Source- Araya G Maju
The post ስለ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአጭሩ – ከ አርአያ ማጁ appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.