Who is the storyteller of this generation that can take the place of Ababa Tesfaye? የተረት አባት ያጣ ትውልድ:-የትውልዱ የተረት አባት ማነው?
ቁም ነገር ቅጽ 13 ቁጥር 195 ጥር 2007
መነሻ አንድ
ከጥቂት ወራት በፊት ሰይፉ ፋንታሁን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ አንጋፋውን የኢትዮጵያ ልጆች የተረት አባት አባባ ተስፋዬን በእንድነት ጋብዞ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ሰይፉ አባባ ተስፋዬን እንደተለመደው ወንበሩ ላይ ሆኖ አልነበረም ያነጋገራቸው፡፡ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ጆሮአቸው አልሰማ እያለ ያስቸገራቸው አባባ ተስፋዬን እዛው የእንግዳው ወንበር ላይ አጠገባቸው ተቀምጦ ማነጋገር ነበረበት፡፡ እኝህ አንጋፋ የጥበብ ሰው በአሁኑ ወቅት የ92 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካይነት የኢትዮጵያ ልጆችን በተረቶቻቸው ሲያዝናኑና በስነ ምግባር ሲያንፁ የኖሩ ሰው ናቸው፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ አባባ ተስፋዬን የቢጂአይ ኢትዮጵያ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነው የሊፋን የቤት መኪና ተሸልመዋል፡፡ ሽልማቱን ለማበርከት በስፍራው የተገኘው የቢጂአይ ኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ኢሳያስ አደራ ሽልማቱን ለማበርከት ወደ መድረክ ላይ እንደወጣ በሰይፉ ፋንታሁን አንድ ጥያቄ ተጠይቆ ነበር፡፡<አባባ ተስፋዬን ታውቃቸዋለህ፤ በእሳቸው ተረት ነው ያደከው?››የሚል፡፡ ኢሳያስ ብዙም ጊዜ ሳያጠፋ ‹‹በእሳቸው ተረት ያላደገ ማን ልጅ አለ? የአሁን ልጆች ናቸው ባንተ ተረት የሚያድጉት፤›› ብሎ ነበር ተመልካቹን ፈገግ ያሰኘው፡፡ ኢሳያስ ለጨዋታም ይሁን ለቀልድ ስለሰይፉ የተናገረውን ምፀት ረስተን ‹እውነት የትውልዱ የተረት አባት ማነው?› የሚል ጥያቄ ብንጠይቅ ከአባባ ተስፋዬ በኋላ የኢትዮጵያ ልጆችን የሚያንፅ የተረት አባት ስለመኖሩ በድፍረት ለመናገር አይቻልም፡፡
መነሻ ሁለት
ከጥቂት ወራት በፊት በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የጋዜጠኛ አንዱዓለም ተስፋዬ ፕሮግራም ላይ የትውልዱን ወካይ ታዳጊ ወጣቶች የአኗኗር ዘይቤ ለመፈተሽ አንድ ፕሮግራም አቅርቦ ነበር፡፡ ጋዜጠኛው የከተማው ታዳጊ ወጣቶች አዘውትረው በሚውሉበትና በሚዝናኑበት ኤድና ሞል የመዝናኛ ማዕከል በመገኘት ወጣቶቹን አንዳንድ መሰረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን ጠይቋቸው ነበር፡፡ ‹የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይባላሉ?› በሚል ላቀረበው ጥያቄ አንዱ ታዳጊ ወደ እንግሊዝኛ በሚያደላው የንግግር ዘይቤው‹I don’t know፤ በፊት መለስ ዜናዊ ነበረ፤ የአሁኑን አላውቀውም› ብሎ ሲመልስ ሌላው ታዳጊ <ኃይለማርያም ነው፤ የአባቱን ስም ግን አላውቀውም› ነበር ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹አንተ› በማለት፡፡ ጋዜጠኛው ቀጠለ ‹የትምህርት ሚኒስትሩ ማን ይባላሉ?› በጣም ያሳዝናል፤ ከወንዶቹም ከሴቶቹም አንድ ሰው የትምህር ሚኒስትሩን /አቶ ሽፈራው ሽጉጤን/ የሚያውቃቸው አልተገኘም፡፡ ተከታዩ ጥያቄ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማን ይባላሉ?› የሚል ሲሆን ከአራት ተማሪዎች መሀከል ለትክክለኛው መልስ የቀረበ ምላሽ የሰጠው አንዱ ተማሪ ብቻ ነበር ለዚያውም <ቴዲ አይደል?› በሚል ፡፡ ወጣቱ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ማለቱ ነው በሚል እንረዳው ካላልን በቀር ታዳጊ ወጣቶቹ ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታም ሆነ ስለህብረተሰቡ አስተዳዳሪዎች ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡ በመሆኑም ወጣቶቹ መሠረታዊ የሚባሉ የሀገሪቱን ጉዳዮች አያውቁም ወይም ለማወቅ ፍላጎት የላቸውም፡፡ እነሱ በጣም የሚያስጨንቃቸውና የሚያሳስባቸው ዘወትር አርብ አርብ ኤድና ሞል የሚከፈተው የሆሊውድ ፊልምን ለመመልከት እንዴት በሰዓቱ እንደሚደርሱ ቀዳሚው ሲሆን በሳምንቱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የነማንቼስተርና የነአርሴናል ውጤት ሌላው የጭንቀታቸው መሠረት ነው፡፡
መነሻ ሶስት
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በስፋት መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መሀከል አንዱ በአንድ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ በሴት ተማሪዎች አማካይነት ሲደረግ የነበረ የዳንስና የጭፈራ ዝግጅት ቪዲዮ ነው፡፡ የትምህር ቤቱን ስም /ለወላጆች ክብር ስንል/ ደብቀን በቪዲዮው ላይ የሚታየውን ትዕይንት ለሚመለከት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የታዳጊ ወጣቶቻችንን የስነምግባር ሁኔታና የትምህርት ቤት ህይወት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በዚህ ቪዲዮ ላይ አንዲት ታዳጊ ወጣት በተለቀቀላት የእንግሊዝኛ ሙዚቃ ታጅባ ለራቁት የቀረበ ብጣሽ ቀሚስ አድርጋ መድረኩ ላይ በተቀመጠላት ወንበር ዙሪያና ከላዩ ላይ በመውጣት የምታሳየው የዳንስ ትርኢት በአውሮፓና በአሜሪካ የሚደረጉ የራቁት ዳንስ ደናሾችን ያስንቃል፡፡በዙሪያዋ የተሰበሰቡትና ትርኢቱን እየተመለከቱ ያሉት የትምህርት ቤት ጓደኞቿ/በቪዲዮው ላይ በአብዛኛውን የሚታዩት ሴቶች ናቸው/ በልጅቷ ወሲብ ቀስቃሽ ትርኢትና ስታጎነብስ በሚታየው የውስጥ ሱሪዋ በመማረክ በፋጨት ሲጮሁ ይታያል፡፡ ጥቂት ቆይቶም ክብ ሰርተው ከሚመለከቷት ሴት ተማሪዎች መሀከል አንድ ሁለቱን ጋብዛ ወደ መድረክ በመጥራት ተመሳሳይ የወሲብ ቀስቃሽ እንቅስቃሴያቸውን በደቦ ሲፈፅሙ ይታያል፡፡ይህ ትዕይንት በትምህር ቤቱ ግቢ ውስጥ ሲፈፀምም ሆነ በሞባይል ተቀርጾ ሲወጣ የትምህርት ቤቱ አስተዳደርም ሆነ መምህራን የት ሄደው ነበር ያሰኛል;;
አባባ ተስፋዬ ወዴት አሉ?
‹ጤና ይስጥልኝ ልጆች! የዛሬ አባባዎች የነገ ፍሬዎች፤ እንደምን አላችሁ ልጆች!› በሚል አባታዊ ለዛ ታጅበው ከ40 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት እየቀረቡ ተረት በማውራት ህፃናት ልጆችን ሲያንፁ የኖሩት አባባ ተስፋዬ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ውስጥ ዘወትር የሚታወሱ የሞራል መምህር ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ክብረ በዓል ዋዜማ በአባባ ተስፋዬ ስራና ሕይወት ዙሪያ እንዲያጠነጥን ታስቦ የተዘጋጀው በነፃ የሚሰራጭ አንድ መፅሔት ‹እንደምን አላችሁ ልጆች;የዛሬ አባባዎች የነገ ፍሬዎች፤› በሚለው ተወዳጅና ምንግዜም ከልጆች ልቦና የማይጠፋ ሰላምታቸውን በማስቀደም ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ወደየቤታችን የመጡት ህዳር 1 ቀን 1957 ዓ.ም /የዛሬ 50 ዓመት/ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አየር ላይ የዋለው ተረታቸው ስለ ጦጣ ብልጥነት የሚተርክ ነበር፤ እንግዲህ ከዚያች ዕለት ጀምሮ በይፋ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት እስከተሰናበቱበት መስከረም 30 ቀን 1999 ዓ.ም ድረስ የእያንዳንዱ ቤተሰብ የየሳምንት እንግዳ፤የእያንዳንዱ ህፃን መካሪ፤አስተማሪና አጫዋች በመሆን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለምም እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ሙያዊ የዜግነት አደራቸውን ሲወጡ ኖረዋል>ይላል ፡፡
አባባ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተረት ማቅረብ የጀመሩበትን አጋጣሚ አስመልክቶ በተደጋጋሚ እንደተናገሩት በ1957 ዓ.ም የእንግሊዟ ንግስት ዳግማዊት ንግስት ኤልሳቤጥ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ ከላይ አስከ ታች የአቀባበል ሽር ጉድ በተጧጧፈበት ጊዜ አንድ ለኢትዮጵያውያን አዲስ የሆነ ክስተት መጣ፡፡ የንግስቲቱን ጉብኝት ያስከተለው ይህ አዲስ ክስተት ቴሌቪዥን ነበር፡፡የዚህ ሃላፊነትና እልቅናም የወቅቱ የተስፋዬ ሣህሉ አለቃ ብላታ ግርማቸው ተ/ሃዋርት ተክለማርያም ነበሩ፡፡በአጋጣሚ በቴሌቪዥን ስለሚቀርቡ ዝግጅቶች የፕሮግራም ዝርዝር ወጥቶ ያዩት አባባ ተስፋዬ ሳያቅማሙ አለቃቸውን ደፈር ብለው ‹ይህን ሁሉ ፕሮግራም ስንለማመድ ልጆችን የተመለከተ ነገር አለመኖሩ ለምንድነው?› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ብላታ ግርማቸውም ‹‹የለም እንዴ እስቲ አጣራለሁ›› አሉና እንግሊዛዊውን ሀላፊ አስጠርተው ጠየቁት፡፡
ለሀገራችን ብርቅ የሆነው ቴሌቪዥን ከመምጣቱ በፊት አልፎ አልፎ በሬዲዮ ተረት ከማቅረብ በቀር ልምድ አይኑራቸው እንጂ ከስቱዲዮ ገብተው በተቀረፁ ጊዜ እንግሊዛዊውን ሳይቀር አስደንቀውት ነበርና ‹አንተ እኮ በጣም ችሎታ አለህ፤እዚህ ሀገርም ትሰራለሁ?› ሲል ጠይቋቸው ነበር፡፡ቆፍጣናውና ሀገራቸውን ከልባቸው የሚወዱት አባባ ተስፋዬ ግን እንዲህ ነበር ያሉት <እንዴ ህዝቤ መች ጠገበኝና ነው ከሀገሬ የምወጣው?> ከዚያች ዕለት ጀምሮም ከስራ እስከ ተባረሩበት ዕለት ድረስ አባባ ተስፋዬና የሚወዱት ህዝብ ሳይጠጋገቡ ኖረዋል፡፡
የትውልዱ የተረት አባት ማነው?
አያከራክርም፤ ላለፉት 50 ለሚጠጉ ዓመታት ያለፈውን ትውልድ በተረታቸው ሲመክሩና ሲያዝናኑ የኖሩት አባባ ተስፋዬ ናቸው፡፡ በድንገት ከኢትዪጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ላይ እንዲገለሉ የተደረጉትአባባ ተስፋዬ በወቅቱ ከቁም ነገር መፅሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ (ቁም ነገር መፅሔት 6ኛ ዓመት ቅፅ 6 ቁጥር 62 መጋቢት 1999 ዓ.ም) ላይ <ፍላጎቴ ልጆች እንዲማሩና ጎበዝ እንዲሆኑ ነው፤ለልጆች በነፃም ስራ ብባል እሰራለሁ፡፡ ከቴሌቪዥን ብወጣም ከኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ አልወጣሁም> ይላሉ በየሄዱበት ቦታ ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂው በሚያሳያቸው ፍቅር በመደሰት፡፡
የአባባ ተስፋዬ ተረቶች ልጆችን የሚያዝናኑ ብቻ አይደሉም፡፡ መልካም ስነ ምግባርንም ይሰብካሉ፡
ለእናትና አባት የመታዘዝን የሞራል ስንቅ ያስጨብጣሉ፡፡ ሀገርንና ወገንን የማገልገል ሃላፊነት ያስገነዝባሉ፡፡ ሀገሪቱ ራሷን ልትችል የምትችለው በዜጎች ጥረትና ትጋት በመሆኑ ስለ ስራ ክቡርነት ያስተምራሉ፡፡ ሌሎች ማህበራዊ እሴቶችን በልጆች ህሊና ውስጥ በማስቀመጥ ዜጎቿ ሁሉ ለሀገራቸው ዘብ እንዲቆሙ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ የእሳቸውን ተረቶች እየሰሙ ያደጉ ልጆች በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ዛሬ እየተሸረሸረ የመጣው የስነ ምግባር ችግር የሚታይባቸው እንዳልሆኑ መመስከር ይቻላል፡፡
አባባ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ከጠፉ ወዲህ በተደጋጋሚ <የት ጠፉ?>የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ ጣቢያው እኝህን የመሰለ አንጋፋና የኢትዮጵያ ልጆችን የሞራል መምህር በአንድ ብጣሽ ወረቀት ሲያሰናብት ተተኪ ባለሙያ ስለማዘጋጀቱ ማንም አልጠየቀም፤ አንጋፋው ጣቢያም ለዚህ የሚሆን መልስ ስያቀርብ አልተሰማም፡፡ ለዚህም ይመስላል ጣቢያው እሳቸውን ካባረረ በኋላ የሚያቀርባቸውን የህፃናት ፕሮግራሞች በቀደመው መልኩ በልጆች ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ መቀጠል አቅቶት ተከታታይና ተመልካች ሊያጣ የቻለው ለማለት ይቻላል፡፡
ለዛሬ ልጆች በዕድሜቸው ልክ ታስቦበትና ተጠንቶ የሚቀርብላቸው የልጆች ፕሮግራሞች ስለሌለ ብዙዎቹ የአውሮፓና አሜሪካ የጌም ዞን ታዳሚዎች ሆነዋል፡፡ በሀገራቸው ተረትና የተረት መፅሐፍት ራሳቸውን ከማነፅ ይልቅ በቀላል ዋጋና በርካሽ የሚገኙ ጌሞችን ይዘው ነው የሚታዪት፡፡ ወላጆችም ለልጆቻቸው እንደ አባባ ተስፋዬ አይነት የሞራል መምህር በማጣታቸው ትንሽ ሳንቲም እየሰጡ ልጆቻቸውን የጌምና የፊልም ተከታታይ ለማድረግ ሲተጉ ነው የሚታዩት፡፡እነዚህን ዘመናዊ ጌሞች ለልጆቻቸው ለመግዛት አቅም ያጡ ወላጆችም በአረብ ሳትና በናይል ሳት ላይ የሀገራችንን ባህልም ሆነ ቋንቋ ያልተከተሉ የአረብ ፊልሞችን በመክፈት ከትምህር ቤት መልስ የሚጋበዙት <ሠላም> ማግኛ መሳሪያዎች ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡ እነዚህ የአረብ ፊልሞች በጊዜ ሂደት በልጆቹ ስነ ልቦና ላይ ስለሚፈጥሩት አሉታዊ አስተሳሰብ ግን ጥናት አካሂዶ <እንዲህ ነው> ያለ የዘርፉ ባለሙያ የለም፤ በመንግስት በኩልም ስለ ነገው ትውልድ ማንነት የተደረገ የማስተካከያ እርምጃ እስከ ዛሬ ድረስ አልታየም፡፡
ያለፉት ቢያንስ አስር ዓመታትን የኢትዮጵያ ወጣቶችን አዳዲስ ባህሪያት በጥሞና ለመከታተል ለቻለ ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ፈር እየለቀቀና የአውሮፖና አሜሪካን የአኗኗር ዘይቤ በስፋት እየተስተዋለ እንደሆነ መታዘብ ይቻላል፡ ፡ አልፎ አልፎም ከየቦታው የሚሰማው ሰቅጣጭና ዘግናኝ የወልጀል ድርጊቶች በታዳጊ ህፃናትና ለአቅመ አዳምና ሔዋን ባልደረሱ ልጆች መሀከል ተፈፅሞ መመልከት የትውልዱን አካሄድ አመላካች ነው፡፡ከዘመን አመጣሹ ጌምና ፊልሞች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ታዳጊ ወጣቶች ሞባይሎች ላይ የሚታዩት ነውረኛ ፊልሞች እንደ አባባ ተስፋዬ አይነት የተረት አባትና መምህር ከማጣት የሚመነጭ ድርጊት እንደሆነ ለመናገር ፈላስፋ መሆን አይጠይቅም፡፡
ተተኪው የተረት አባት ማነው?
ኮሜዲያን አስረስ በቀለ ከአባባ ተስፋዬ ስር ባለመጥፋት የእሳቸውን ዱካ ለመከተል ጥረት ያደርግ የነበረ አርቲስት ነበር፡፡ በተለይም ወደ መድረክ የመጣው የእሳቸውን ድምፅ አስመስሎ ተረት በማቅረብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አባባ ተስፋዬ ራሳቸው <የእኔ ተተኪ አስረስ ነው> ብለው እስከመናገር የደረሱበት ጊዜ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ከአባባ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መባረር ከጥቂት ጊዜያት በኋላ አስረስ ከጣቢያው ጋር የነበረው ውል ተቋርጧል፡፡መምህሩንም ሆነ ደቀ መዝሙሩን በተከታታይ ያጣው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለኢትዮጵያ ልጆች ተተኪ ባለሙያ ማቅረብ እንዳለበት እስከዛሬ ድረስ ረስቶታል ወይም ማስታወስ አይፈልግም፡፡ድራማና ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን <እባካችሁ በጋራ እንስራ> በሚል በተደጋጋሚ ማስታወቂያ የሚያወጣው ጣቢያው ለህፃናት የሚሆን የተጠናና የነገዋን ኢትዮጵያ የሚያንፁ ታዳጊዎችን የተመለከተ ፕሮግራም የሚሰሩ ድርጅቶችን ሲጋብዝ አይሰማም፡፡በባዕላት ወቅት እንኳ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕግራሞች ሲታቀዱ ህፃናትን እንደ አባባ ተስፋዬ የሚያስታውሳቸው የለም፡፡ በመሆኑም በባዓላት ቀናት ህፃናት ልክ እንደአዋቂ ከወላጆቻቸው ጋር ተቀምጠው <የነ ፍልፍሉን የተጨቆኑ ቀልዶች> ይኮመኩማሉ፡፡ ነገ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር የሚያወሯቸውን የብልግና ቃላት ከእነዚህ ቀልዶች ላይ እንደሚቀዱ ማንም ልብ አይልም፡፡
ጣቢያው ለህፃናት ፕሮግራም ሳይሆን ለሌሎች ፕሮግራሞች ቅድሚያ እንደሚሰጥ አንጋፋው አርቲስት አስረስ በቀለ ያማርራል፡፡ ትውልዱ የራሱ የተረት አባት የማጣቱንም ነገር አስረስ ያሳስበዋል፡፡ የተረት መፅሐፍት እጣ ፈንታ አባባ ተስፋዬም ሆኑ አስረስ በቀለ እንዲሁም ሌሎች ደራሲያን የተለያዩ የተረት መጽሐፍትን ለኢትዮጵያ ልጆች አሳትመው አቅርበዋል፡፡ በሰለጠነው ዓለም ቢሆን ኖሮ እነዚህ የተረት መፅሐፍ ደራሲያን የሚኖሩት የንጉስ አኗኗር ነበር፡፡ የኛዎቹ ግን ሶስት ሺህና አራት ሺህ ኮፒ መፅሐፍትን ሸጠው ለመጨረስ ያለባቸው ፈተና የነዳጅ ዘይትን ከምድር በታች ቆፍሮ ከማውጣት ጋር ይነፃጸራል፡፡በተለይም አባባ ተስፋዬን የመሰለ አንጋፋ የተረት አባት አልሸጥ ያሉ የተረት መፅሐፍቶቻቸውን ተሸክው ለመሸጥ ከዓመታት በፊት በየካፌውና በየምግብ ቤቱ ሲዞሩ መመልከት ህሊና ላለው ሰው ያማል፡፡ እርግጥ ከመንፈሳዊ እውቀቶች ይልቅ ለቁሳዊ ንብረቶች ቅድሚያ በሚሰጥ ማህበረሰብ ውስጥ ከነአባባ ተስፋዬ አይነት ሰዎች ይልቅ ፎቅና መኪና ለያዙ ሰዎች ቅድሚያ ወንበር ሲሰጣቸው ማየት ላይገርም ይችላል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ መፅሐፍት ለልጆች የትምህርት ድርጅት በተባለው ተቋም በ1999 ዓ.ም ተሸላሚ የነበረውና በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኘው ረዳት ፕሮፌሰር ዓለም እሸቱ ከ15 በላይ የተረት መፃህፍት አሳትሞ ለአንባቢያን ያቀረበ ሲሆን መፅሐፍቱ አሁንም ድረስ ከገበያ ላይ የአንባቢ ያለህ የሚሉበት ደራሲ ነው፡፡ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅና በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ ፅሑፍ መምህር የነበረው ዓለም ከመፅሐፍቱ መሀከል ሶስቱ <ለማዳው አንኮ፤ ካሳሁንና ብርቅዬዎቹ የዱር እንስሳት እና መላኩ ጨበሬው> የተሰኙት መፅሐፍት ለልጆች ባላቸው ሞራላዊ እሴት ለማስተማሪያነት በሚል በፊንላንድ ቋንቋን በሚስስ አሊጃ ካተሪና አማካይነት የተተረጎመለት የመጀመሪያው አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ የህፃናት መፅሐፍት ደራሲ ነው፡፡ ከ15 በላይ የተለያዩ የተረት መፃህፍትን ያሳተመው ረዳት ፕሮፌሰር ዓለም ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት መፃህፍቱ ተሸጠው አለማለቃቸው ሁሌም ግርምት እንደፈጠረበት ነው፡፡
የህፃናትን አዕምሮ ጌሞችና ፊልሞች በተቆጣጠሩበት እና እንደ አባባ ተስፋዬ አይነት ተረት ተራኪ ከሚዲያው ላይ በተገለሉበት በአሁኑ ሰዓት የተረት መፃህፍት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመናገር አይከብድም፡፡ህፃናትን ከልጅነታቸው ጀምሮ በተረት መፃህፍት አንፀን ካላሳደግናቸው በምዕራባውያን ፊልሞችና ጌሞች ተውጠው መኝታ ቤታቸው ገብተው ወላጆቻቸውን ቢረሱ አይፈረድባቸውም፡፡የወላጅ ክትትልና ምክር የተለየው ወጣት ደግሞ ከቤተሰብ አልፎ የመላ ማህበረሱ አደጋ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ጊዜያቸውን ዋልጌ ፊልሞችን በመመልከት የሚያሳልፉ ወጣቶችም ሴት ልጆችን በመንጋ የመድፈር አድቬንቸር ቢያዳብሩ የሚገርም አይሆንም፡፡
አስረስ በቀለ የተቻለውን ያህል ለህፃናት የሚሆኑ የተረት መፅሐፍትን ከመፃፍ ቦዝኖ እንደማያውቅና ስለ አስፈላጊነቱ ይናገራል ‹እያንዳንዱን መጽሐፍ ለማሳተም ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ድጋፍ የሚያደርግልኝ ሰው እፈልጋለሁ፡፡ ብዙ እሯሯጣለሁ፡፡ ግን ሰው አይረዳህም፡፡ የህጻናት መጽሐፍ ምን ያተርፋል፤ ምን ያደርግልሃል፤ ለምን ሌላ ስራ አትሰራም ይሉሃል፡፡ እኔ ደግሞ ስሜቴ የልጆችን መጽሐፍት ማሳተም ነው፡፡ መጽሐፍቱ ታትመው ሳያቸው በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አሁን እኔ ፊልም እሰራለሁ፡ ፡ መስራትም እችላለሁ፡፡ ግን ዳይሬክተሮችንና ፕሮዲዩሰሮችን ማባረር ሰለቸኝ፡፡ ፊልም ካሰሩህ በኋላ የት እንደሚገቡ አታውቅም፡፡ እልም ይላሉ፡ ፡ ስልክ ይቀይራሉ፡፡ አድራሻ ይቀይራሉ፡፡ ፖሊስ እንኳ ፈልጎ የሚያገኛቸው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከነሱ ጋር ከመሯሯጥ ልጆችን በስነ ምግባር በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ የሚያስችሉ ታሪኮችን እየጻፍኩ ደስ ሚለኝን ስራ መስራትን መርጫለሁ፡፡›
መደምደሚያ
ትውልዱ የተረት አባት በማጣት እየባዘነ
እንደሆነ ወጣቶቹ በየትምህርት ቤታቸው ከሚያደርጉት ድርጊትና ከሚውሉበት ቦታ ምርጫ አንፃር አይቶ መፍረድ ይቻላል፡፡ ለአደገኛ ወንጀሎች መፈልፈያ የሆኑ የውጪ ፊልሞችንና ወላጆች የማያውቋቸውን ጌሞችን ከአካባቢያቸው በማራቅ በሀገራዊ ወግና ተረት ወጣቶቹን አርቆ ማሳደግ የትውልዱ ፈታኝ ጥያቄ ነው፡፡ አለበለዚያ በነ ሀና ላላንጉ ፤ በነ ካሚላት፤ በነሄርሜላና፤ በነፍሬህይወት ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች መሰረቱ ያለው በአስተዳደግ ላይ ስለሆነ ስለ ፆታ ምንነትና ስለ ማህበረሰብ ሃላፊነት ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በወጉ ማስተማር ያለባቸው ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡
ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ቀጥሎ ተማሪዎችን ለረዥም ሰዓት ይዞው የሚያቆዩ ተቋማት በመሆናቸው ከመደበኛው የትምህርት ሰዓታቸው ጋር በተጓዳኝ ስለማህበረሱ እሴቶችና ባህሎች በቂና ተከታታይነት ያለው የስነ ምግባር ትምሀርት መስጠት አለባቸው፡፡ ይህንን ተላልፈው እንደከዚህ ቀደሙ ባዶ ገላቸውን እያሳዩ ከጣራ በላይ በተለቀቀ ሙዚቃ ግቢው ውስጥ ሲያብዱ አይቶ እንዳላየ ማለፍ ትምህርት ቤቶቹን ከሃላፊነት አያድናቸውም፡፡ ትውልዱ ተጣሞ እንዳያድግ በማድረግ ረገድ የሞራል ተጠያቂነት አለባቸውና ፡፡ የዘመኑን መንፈስና የስነ ምግባር ውድቀት ለመመዘን ብዙ ምርምርና ፍልስፍና እንደማይጠይቅ በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ የአማርኛ ፊልሞችንና ዘፈኖችን ይዘት መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡
‹መገን የጎጃም መገን የጎንደር
ባንዘልቅ እንኳን አብረን እንደር›
የሚለውን የጃኖ ባንድ ዘፈን በብሔራዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሲቀርብ የሚደነግጥ ሰው እየጠፋ ነው፡፡ የፊልሞቻችንስ ርዕሶች ‹ሚስቴን ቀሙኝ፤የፍቅሬ ፍቅረኛ፤ሳመኝ፤ የሌባ ልጅ፤ባትመጪም ቅጠሪኝ፤ወ/ሪት ድንግል፤ አይደል?ቁ
Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።