ምስጋና – ለነፃነት ዬተስፋ አውራ! – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 04.02.2014 /ሲዊዘርላንድ / ዙሪክ/

UDJ general meeting 1ንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ በወያኔ ሴራ ከነፃነት ትግሉ ጎራ የተገለለው የአንድነት ጨርቃ ጨርቆች ማለት የተጣፉት ዲሪቶ – ተቀዳጆቹ፤ ማሽኖቹ – ተሰባሪዎቹ፤ ህንፃው ከእድሳት እጥረት ፈራሹ – ቁሶቹ ብቻ እንጂ ለነፃነት ትግሉ ተስፋ አንዱ ብሄራዊ መንገድ ለነበረው የአንድነት መንፈስ፣ አባላት፤ አካላት፤ ደጋፊዎችና ቅን ወገኖች አይደለም። ወያኔ ወልቃይት – ጠገዴን – አዲረመጽን ሰቲትንና ንጥር ሃብቱን በወረራና በዘመንተኝነት ወሰደ። የሰቲትና የአካባቢውን ዕውን መንፈስ ግን ከጎንደር መንፈስ ፈጽሞ መነጠል አይደለም ከቅርቡ መድረስ አልቻለም። ስለምን? ወያኔ በወረራ የወሰዳቸው ክልሎች ኗሪዎች የሚያቀኑት ወደ እትብት ባዕታቸው ወደ ጎንደር ነው። ለተለጣፊ ማንነት ጨዋው ህዝብ ጊዜ የለውምና።

አንድነት ከመበቻው ጀምሮ የበርካታዎችን ወገኖች ቀልብ የሳበ ብቻ ሳይሆን ያደራጀና የመራ የቅንጅት ንጹህ መንፈስ የረበበት ፓርቲ ከመሆኑም በላይ፤ ፈተናን አብዝቶ የተቀበለ አውራ ፓርቲ ነው። መስዋዕትነትንም የከፈለ። የደማ የተጎዳ። አብዛኞቹ የታሰሩት የነፃነት ትግሉ ጋዜጠኞች ቢሆኑ ለአንድነት መንፈስ እጅግ በጣም ቅርብ ናቸው። ወያኔ የማዕዘን ድንጋይ ሊሆኑ የሚችሉ ትንታግ ወጣት የአንድነት መሪዎችን አስርጎ በሳገባቸው ክህደቶች በዬጊዜው የካቴና ሰለባ ቢያደርግበትም፤ በማያቋርጥ ሁኔታ የአንድነት ኃይልና ብርታት መጠንከር፤ ጉልበታምነት፤ ዛሬ ከወሰደው ወያኔያዊ ዳፍንት እርምጃ ሌላ መስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ሀገር ውስጥ የወያኔ የስጋት ማዕከል ድርጁው አንድነት ነበር። ለጥቃቱ ቀዳሚ መስመረኛም አንድነት … ነገ ደግሞ  በአንድነት ጥላ ላይ ላይ ወመኔው ወያኔ እንደሚያነጣጥር ይታወቃል።

አንድነት እጅግ ጎምርቶ የሚነገርለት ኪንግ ማርቲን ሉተር ከፈጸመው ተግባር የላቀውን ከውኗል። አሁን መኢህድና አንድነት በባህርዳር አዘጋጅተውት የነበረው „ ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር“ ይሻላል እጅግ ሥልጡን ሰላማዊ ሰልፍ፤ አዲስ አባባ ላይ የነበረው „ዲግሪ ድንጋይ ተሸክሞ፤ እንስራ ተዝቅዝቃ በውሃ ጥማት፤ የ21ኛው ምዕተ ዓመት ሥልጣኔ ውጤት የኢንተርነት አገልግሎት እግር ከወርች ታስሮ“ ያ ዬሰላማዊ ሰለፍ ወርቃማ ዬተግባር ታሪክ እራሱ የተስፋ ገድሉን ችሎ ሊጽፈው ከቶውንም አይችልም። በልቦናችን ውስጥም ማንም ሊነቀንቀው ያልቻለና አሁንም ቅድምም እዬመጣ የሚቀሰቅስን፤ የሚያስተምረን ብቁ ያደገ ዬተግባር ተቋማችን ነው። ተደላድሎ በውስጥ ለውስጥ፤ ከውስጥ ተቀምጧልና።

በሌላ በኩል አንድነት ደፋርም ነበር። እንደ ብሄራዊ ፓርቲነቱ በጎሳ የተደራጁትን ወገኖች ቢሆን ፈቅዶ የተቀበለ። ከፍ ያለውን ቦታ ለእነሱ አክብሮ የሰጠ፤ ከራሱ ትሁት ወገኖች የቀረበበትን የሰላ ወቃሳ የቻለና በሂደቱም በጎና በጎ ባልሆኑ ገጠመኞችም የተማረ ፓርቲም ነው ማለት እችላለሁ። ይህን ሳላዬው ወይንም ይህን ሞክሬው ቢሆን የሚል ጸጸት በአንድነት ፓርቲ ሊኖር ከቶውንም አይችልም። አንድነት ፓርቲ ሁሉንም ዓይነት ፈተናዎች፤ ችግሮች፤ ስቃዮችና አሳሮች በመቻል ከውስጡ ከነቀዙ፤ ከውጪው አውሬ፤ ከለስላሳው ደጋፊ ሳይቀር የተሰነዘረበት- የተዶለተበትን፤ በተቆርቋሪነትም ከወገኖቹም ከሚሰነዘረው ተከታታይ ስሉ ወቃሳ ሁሉን ተቀብሏል። ማደጉም፣ መደራጀቱም ጎሰኛውን ወያኔ እረፍት ስለነሳው፤ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብሄራዊ የዜግነት መብቱን በአደባባይ ይሄው ተነጠቀ። ይህ ወያኔ የወሰደው ዘረክራካ  እርምጃ ወያኔ አለኝ ለሚለው የዲፕሎማሲያዊ ግኙነቱም ቢሆን እሳት የሚተፋ የነገ መጥፊያው ይመስለኛል። አንድ ብሄራዊ የህዝብ ፓርቲ እንዴት በአንድ ተማላ ቀላጤ ይሰረዛል? ቀን ያልፋል ታሪክ ግን ይዘከራል።

አንድነት ፓርቲ ለሰላማዊ ትግሉ ተስፋ ስኬታማነት ሞቷል፤ ቆስሏል፤ ታስሯል፤ ተግድሏል፤ ተሰዷል። የሞቱት ሙተው የተረፉት በርካታ ወጣቶች ከተሰደዱ በኋላ ስለማይናገሩት እንጂ በቤተሰቦቻቸው የአንድነት ደጋፊነት ምክንያትነት ሳይቀር ሀገራቸውን የለቀቁ  አባና እማ ወራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ከዚህ ሲዊዝ ውስጥ አንድ ወጣት አግኝቼ ነግሮኛል። የአንድነት መንፈስ የቅንጅት መንፈስ ነው የሚለው የመነሻ ጉዞው እርገትንም ስመረምረው በግሌ እውነት መሆኑን አገናዝቤበታለሁ። እንዴት በተመስጦ ውስጥ እንደ ነበር ወጣቱን ሳስተውለው መህተሙ …. ነገረኝ።

ዘመነ 2014 እራሱን ሸኝቶ ዘመነ 2015ን ለመቀበል በተሰናዳበት የመሰናዶ ወቅቱ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ያወያዬ በስሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ሰጪ ድርጅት አንድ የቴሌፎን ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ ነበር። ታህሳስ 28.2014 ይመስለኛል። ዕለተ ሰንበት ልክ 20.00 ነበር በሰዓቱ ስበስባው የተጀመረው። እኔም ጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራሜን እና እኔውን እራሴን ወክዬ ታዳሚ ነበርኩኝ። መቼም የእነወጣት አቶ ሃብታሙ አያሌው እስር የአንድነትን ተስፋ ጋር የነበረው መስተጋብር እጅግ ፈታኝ ስለ ነበር አሁን አንድነት እንደዛ ዓይነት ትንታግ፤ ዓላማውን ያወቀ፤ ለብሄራዊ ሰንድቅዓላማችን፤ ለብሄራዊ ማንነታችን ተቆርቋሪ ታታሪ፤ ተናግሮ የሚያሳምን ዬት ያገኛል የሚል ከፍ ያለ ስጋት እኔ በግሌ አድሮብኝ ነበር። በኋላ ግን የተከበሩ ዬአንድነት ሊቀመንበር የአቶ በላይ ፈቃዱ አጭር ክሽን ያለ መግለጫ ሳዳምጥ ተሰፋዬ አቆጠቆጠ። አብሶ ጋዜጠኛ ሃብታሙ ላቀረበላቸው ጠንካራና ሁለገብ ጥያቄ የሰጡትን መልስ ሳዳምጥ ወይ አንቺ ሀገር ስለ አንቺ የሚቆረቆሩ ጠንካራዎችን ስታመርቺ የምታዳሪ ብርቅና ውብ ሀገር ነበር ያልኩት። የእውነት የሚያኮራ ነበር። ካርዴ አቋርጦኝ እንጂ ከውይይቱ ባልወጣ በወደድኩኝ ነበር። እስከ ነበርኩበት እስከ እህት ዊንታ ጥያቄ ድርስ ታሪካችን ስለሆነም ቀድቸዋለሁም። ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው እንኳንም ነበርኩኝ፤ እንኳንም ቀዳሁት። የመጨረሻው የገናናው የአንድነት ብሄራዊ ፓርቲ የተስፋ ድምጽ ነበርና። የትናንቱ የቅንጅት መራራ ስንብት እንሆ ዛሬም ተደገመ ///  መራራ ስንብት …. ህም!

ታስታውሱ እንደ ሆነ አዲሱ የአንድነት አመራር በህጋዊ ጉባኤ ውክልና ካገኘ በኋላ ከእራሱ ከአዲሱ ብሄራዊ አመራር የሚወጡ ጹሑፎች፤ የፈጠሩት ሰብቃ ወይንም ግጭት፤ እንዲሁም የገዢው ጎሳ ድርጅት ወከባ፤ በተጨማሪም የውስጥ ተውሳኮች ጉንተላ አይሎ ስለነበር እኔ በግሌ ለአዲሱ አመራር ድርብርብ ኃላፊነትና በፈታና የታጨቁ ወቅቶች ይሆኑበታል የሚል ስጋት ነበረብኝ። ከቴሌፎን ኮንፍረንሱ ውይይት ተሳታፊዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችም በአማዛኙ ከዚህ ፈታኝ ሁኔታ ጋር የተያያዙና ተቆርቋሪነታቸውም ልብ የሚነካ ነበር። የወቅቱ የአንድነት ሊቀመንበር የተከበሩ አቶ በላይ ፈቃዱ ግን አጅግ በተረጋጋ፤ በሰከነ ደም ነበር ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት። መልሶቹ ከሆደ ሰፊነት ተነስተው፣ መዳረሻቸው የነፃነት ትግልን የተረጎመ፣ የነፃነትን ሥነ – ተፈጥሮ መንፈስን ያነበበ ነበር። እኔ በግሌ እጅግ ነበር የኮራሁባቸው። እኒህ ሰው በአመራር ዘመናቸው ለአመራር አካላቱም ሆነ ለአባላቱ ያለውን የመብት ድንበር የማይጥሱ ይሆናሉ የሚል ህልምም ነበረኝ።

አንድነት ሲመሰረት መዋቅሮቹ እጅግ ብዙ ስለነበሩ እኔ በግሌ በዛ የማለት አቋም ነበረብኝ። አንደኛው ምክንያቴ ለሥራ ቅልጥፍና ቢሮክራሲያዊ ነገሮችን ያበራክታል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የበጀት አቅሙን በማሰብ ነበር። ይህ ማለት ከአመሰራረቱም አንድነት በብቁ ሁኔታ መዋቅሩን አደራጅቶ የተመሰረተ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ ወካባ ውስጥ ሆኖ በአብዛኛው የሀገራችን ቦታዎች የነበረው እንቅስቃሴም ሆነ ተቀባይነት አጅግ ውብ አበረታች ነበር። ተስፋም።

አንድ ብሄራዊ ፓርቲ በህገመንግስታዊ መብቱ ተጠቅሞ መደራጀቱ፤ ሰፊ መሰናክሎችን አልፎ እድገቱን ሲጠብቅ እንዲህ በዓዋጅ ሲፈርስ ዓይን ባወጣ ውንብድና ፓርቲው ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቱ ሲወረር ከቅንጅት ቀጥሎ አንድነት ሁለተኛ መሆኑ ነው። ይህ አቁሳይ እርምጃ ቀጣዩን እርምጃ አሳምሞ ተስፋ ቆራጭነትን ያሳዝለው ይሆን? ይህ የሁሉም ጥያቄ ነበር …

ነገር ግን ሥልጡኑ አመራር ያደገና የበሰለ እርምጃ ነው የወሰደው። ይህ ማለት አንድነት ሲታገል የነበረው ለማልያ ፍቅር አለመሆኑን በደማቅ ተግባሩ አሳዬን። ከፍተኛው አመራር ዝቅ ብሎ ወርዶ ለብሄራዊ ነፃነታችን ተስፋ ሲል እንደ አንድ ዜጋ ይነጠፍልኝ፣ ይጎዝጎዝልኝ፣ ይጨብጨብልኝ ሳይል ከሚመስለው ፓርቲ ጋር ተቀላቀለ። ቀደመ! በለጠ! ይህም ብቻ አይደለም ለአባላቶቹና ለደጋፊዎቹ እኔ የተቀላቀልኩትን ብቻ ተቀላቀሉም አላለም። ወደ ዬሚመቻቸውና ወደ ዬሚያምኑበት ፓርቲ ተቀላቅለው የነፃነት ትግሉን በመንፈስ፤ በአካል፤ በጊዜና በፋይንስ እንዲረዱ ፍጹም የሆነ የጠራ ንጹህ መመሪያ በመስጠትም ነው። ይህም ሌላ ብልህ የላቀ የቁምነገር ታሪክ አባትነትም ነው። አባወራነት ከግራጫማ ትርጉማዊ በሳል ልቦና ጋር።

አንድነትን ተጠልለው፣ አንድነትን የደገፉ መስለው በተለጣፊነት ሲጎረጉሩ፣ ሲቦረቡሩ የነበሩት አሁን በአንድነት አደጋ ምን ተሰማቸው? ጎረበጣቸው? ይህን ለታዛቢ ትቼ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ለአደረገው እጅግ የላቀ የጀግንነት ተጋድሎ አድናቆቱን በተግባር ከጎኑ በመቆም ማስመስከር ያለበት ይመስለኛል። ጥበቃ ሊያደርግላቸውም ይገባል። አንድነት ለሰላማዊ ትግሉ የተስፋ ማህደር ነበርና።

ሌላው የሚነሳው የሰማያዊ ፓርቲን አንድነት መቀላቀል በሚመለከት የተስረከረኩ ነገሮች ሊቀርቡ ይቻላሉ። አንድ መዘንጋት የሌለበት ነገር ሰማያዊ የአንድነት የበኽር ልጁ መሆኑን ነው። የአብራኩ ክፋይ የማህጸኑ ወተት መሆኑ ነው። በሌላ በኩልም የልምድ፣ የተመክሮ ጉዳይም ተጨማሪ አነጋጋሪ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። 12 ክንድ ነጠላ 25 ሲሆን ኩታ 50 ሲሆን ጋቢ ይሆናል። ድርብ ሙቀት ከበሰለ ተመክሮ – ከአፍላ ጉልበት ጋር ገደል ይሰራል። በፓርቲ ህይወት ውስጥ የአመራር ተከታታይነት የሚባለውም ይሄው ነው። ልምድና ተምክሮ ዕድሜን ሳይሆን የሚቆጥረው ብቃትን፤ የማድረግ አቅምን፤ የመሆን መቻልን በመገኘትን ነው። አንድነት የወሰደው እርምጃ ለእኔ እንከን የለሽ ፍጹም ነው። እንኳንም የበኽር ልጁ አስቀድሞ ጎጆ ወጣለት። ጎጆ የወጣው ልጁ ደግሞ በአጭር ጊዜ በተግባር የበቀለ ሰብል ያፈራ አንቱ ነው። እኔ የቤተሰቧ እማወራዋ ችግር በደረሰብኝ ጊዜ ጎጆ ያወጣኋቸው ታናሾቼ ናቸው ህይወቴን እንዲሰነብት ያደረጉት። ለአንድ ቀንም መጠለያ ማግኘት ትርጉሙ – ጥልቅ ነው። ዬአንድምታ ዐዋቂዎች ቢያመሳጥሩት። ብሄራዊው አንድነት በመከራው ዕለት ጃንጥላ አገኘ። ጃንጥላው ደምና ሥጋው ነው። ደምና ሥጋው ህይወቱ ነው። „አይዟችሁ!“ ቃለ ወንጌል ነው ዛሬ ለአንድነት። እንኳንስ የአብርኃሙ አዕማደ ሚስጢር ዕውንነት። እርምጃው ጥልቅና ብልህም ነው። ውጪ ያለውን የነፃነት ረሃብተኛነት መንፈስንም ይገራል። ሀገር ቤት ያለውን በወመኔው ወያኔ የተናደውን ጥግ አልቦሽነትንም ይፈውሳል – ወጌሻው ጃንጥላ።

እኔ እንደማስበው ቀጣዩ ጊዜ ከመቼውም ጌዜ በመጠን የሰፋ የሱባኤ ወቅት ይሆናል። ቢያንስ በእጅ ባለ ነገር ጠንቃቃ መሆን መልካም ነው። ያተርፋል። ለምሳሌ –  ጥንቃቄ የሚያሰፈልገው ነገር  ጹሑፎች /ፌስ ቡክም ላይ ሆነ ድህረ ገጽ ላይ/ ፤ ቃለ ምልልሶችንም ቢሆኑም ማዕከላዊ ለማደረግ ቢሞከር እጅግ መልካም ነው። ግጭት ከራስ ወገን ጋር የሚፈጥሩ ጎረምሳ መንፈሶች ሁሉ አደብ መግዛት ያለባቸው – ይመስለኛል። በአጅ የተያዘ ድል እንኳን ቢሆን ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። ከመታወጁ በፊት ጊዜና ሁኔታን ማዬቱ ይበጃል። ምክንያቱም ለአለስፈላጊ መስዋዕትነት ጥበቃ ማድረግ ስለሚያስፈልግ። አሁን የእኛ አይደለም። ለእኛ ላልሆነው ዘመን ደግሞ ሁሉም የደህንነት ሠራተኛ ለብሄራዊ ፍላጎቱ መሆን አለበት።

አሁንስ ወያኔ አሰርጎ አያሰገባንም? ቀጣይ እርምጃ በሰማያዊ ፓርቲ ላይ ወያኔ ቢወስድ ምን ማደረግ ይኖርበታል? ሰላማዊ ትግሉ ቀድሞ ሊዘጋጅባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ከልብ ሆኖ መምከር፤ ማድመጥ፤ ሊያተኩርበት የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የነፃነት ትግሉ መንፈስ አሁን ሌላ ፈታኝ ሽግግር ላይ ስለሆነ ያለው ትንፋሽን ሰብስቦ፤ ደምን በረድ አድርጎ፤ ቀጣዩን ፈተና በዬአቅጣጫው በማስተዋል መመርመር ብቻ ሳይሆን መፍትሄዎችንም ቀድሞ አዘጋጅቶ መጠበቅ ይኖርበታል። ሰላማዊ ትግል ሲመሰረትም ኑሮውን ሙት መሬት በማደረግ ነው። ሙት መሬት ላይ ሆኖ ተጋድሎ ደግሞ የሚያስከፍለው መስዋዕትነት እጥፍ ድርብ – ድርብርብርም ነው። ስለምን? ገዢ መሬቱን የሚቆጣጠረው ገዢውና ጨቋኙ ጎሳዊ ድርጅት በመሆኑ። የሰላማዊ ትግሉ ያለው አንጡራ ሃብት የነጠረ እውነት ብቻ ነው። እውነት ደግሞ በፈተና ጦር የተከበበ ነው። ጥሶ ለመወጣት ጊዜና ሙሉ የህዝብ ድጋፍን ይጠይቃል። ሌላው ስጋቴ የተከበሩ አቶ በላይ ፈቃዱ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ ከነበረው ውጥረት የባሰው አሁን ይመስለኛል። ያን ጊዜ በውጪ ዲፕሎማሲው ማህበረበሰብ አነሰም በዛም የተወሰነ ተጽዕኖ ስለነበረው ይሻላል፤ አሁን እኒህ የአንድነት መሪ አውላላ ሜዳ ላይ ናቸው። ስለዚህ ለወያኔ ጥቃት በጣም የተጋለጡ በመሆኑ ጥንቃቄው ቢኖር መልካም ነው።

ይህም ማለት ከዚህ የባሰ ነገር ወያኔ ቤት አልባ ባደረጋቸው የነፃነት ትግሉ አርበኞቻችን ላይ ሆነ በሰማያዊ ፓርቲ ቢያመጣ እንኳን የነፃነት ትግሉ፤ የሰላማዊ ትግሉ አካል የሆነውን „የድምጻችን ይሰማ“ መንገድ፤ መንገዱ እንዲሁን በምልስት ሂደቱን መመርመር ያለበት ይመስለኛል። „ድምጻችን ይሰማ“ ቢሮ የለውም፤ የታወቀ አመራር አካላት የሉትም፤ መዋቅራዊ ሰንሰለትም የለውም፤ መሪዎቹ በሙሉ እስር ላይ ነው ያሉት። ነገር ግን ተግባሩ የዓለም መምህር ነው። „ድምጻችን ይሰማ“ ለእኔ የሰላማዊ ትግሉ ሐዋርያ ነው። በቅጽበት ለአባላቱ በተመሳሳይ ደቂቃ መረጃ የማከፋፈልና የመምራት አቅሙ ሰለጠኑ ከሚባሉት ሀገሮች እጅግ የበለጠ ነው። ስልቱ ልዩ ፍጹም ልዩ ነው …. እያንዳንዱን የትግል ደቂቃ ከዚህ በሳል ተመክሮ ጋር በማቀናጀት ተስፋን ማፋፋት ብቻ ሳይሆን በዚህ መስመር ተስፋንም ማግኘት ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ሌላው ቀርቶ „የድምጻችን ይሰማ አባላት“ በውጪ ሀገር ያላቸው ተሰትፎ ግንባር ቀደም ነው። በ2014 የሲዊዝ የኢሳት የድጋፍ ገንዘብ መሰባሰቢያ ስብሰባ ላይ „የድምጻችን ይሰማ አባላት“ የሮመዳን ፆማቸውን የፈቱት እዛው ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሁሉን ነገር አሰናድተው መጥተው ነበር። ለእኔ ይሄ ለነፃነት ትግል አምክንዮ ልዑቅ ጉልላታዊ ታሪኬ ነው። እንጃ መንፈሳቸውን እንዴት አድርጎ አምላኬ እንደ ቀባው አላውቅም። የነጠረ ዕንቁ ነው የትግላቸው ሂደትና ስልቱ። የትም ቦታ፤ በዬትኛውም ሁኔታ እነሱ አሉ። ቅመም ናቸው። …. እንከተለው … „ያልተሄደበት መንገድ“ የማገዶው ወንድሜ የአንድነቱ ዬአቶ ዬአንዱአለም አራጌ መጽሐፍ የሥነ ሕሊናው ዐይኑ እፍታ ……

ክውና – የተከበራችሁ የአንድነት አባላት፤ የአንድነት አመራር አካላት፤ የአንድነት ደጋፊዎች፤ የአንድነት የተስፋ ራህበተኞች ወገኖቼ ለከፈላችሁት እጅግ የመረረ መስዋዕትነት የብሄራዊ ነፃነታችን የተስፋ አውራ ባላወለታችን ጉልህ ታሪካችንም ናችሁ፤ እና እኔ ታናሻችሁ ሥርጉተ ሥላሴ ዝቅ ብዬ እግዚአብሄር ይስጥልኝ እላለሁ። አመስግናችኋለሁ! እወዳችኋለሁ። አርበኝነታችሁ አስተምሮኛል። እውነት ናችሁ። እውነት ወርቅ ነው። አይዝግም። ይፈልቃል። አይዛችሁ! መሸቢያ የተጋድሎ ጊዜ።

አንድነት ብሄራዊ መንገዳችን ነው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

The post ምስጋና – ለነፃነት ዬተስፋ አውራ! – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.