Interview with Dr. Zewdu Terefewerk founder of MRC ET Laboratory ‹የዲኤንኤ ምርመራ ለሁሉም ህመሞች ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ ምርመራ ነው› ዶ/ር ዘውዱ ተረፈ ወርቅ ‹ኤም አር ሲ -ኢትዮ ላቦራቶሪ ሞሎኪዩላር ዲያግኖስቲክስ› ከፍተኛ የህክምና ተቋም ባለቤት

ቁምነገር መፅሄት 196

ዶ/ር ዘውዱ ተረፈ ወርቅ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ሊጋባ ቢሮ የሚባለው አካባቢ ባህታ ሰፈር ነው የተወለዱት፡የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ኢትዮጵያ አንድነት ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በቀድሞው በዳግማዊ ምንሊክ የአሁኑ መስከረም ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት፡፡ዘጠነኛና አስረኛ ዳግማዊ ምንሊክ ተምረዋል፡፡ አስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛን አለማያ የተማሩ ሲሆን በባዮሎጂ መምህርነት በዲፕሎማ ተመርቀው በሐረር በመድሃኒያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምረዋል፡፡ ለረጅም ዓመታት በሆላንድና በተለያዩ ሀገራት በስራ ላይ የቆዩት ዶ/ር ዘውዱ በቅርቡ ደግሞ ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው ገብተው ‹ኤም አር ሲ -ኢትዮ ላቦራቶሪ ሞሎኪዩላር ዲያግኖስቲክስ› የተባለውን ከፍተኛ የህክምና ተቋም ከፍተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ከዶ/ር ዘውዱ ጋር ያደረግነው ቆይታ ይህንን ይመስላል፡፡

ቁም ነገር፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ የሄዱት ወደ የት ሀገር ነበር?
ዶ/ር ዘውዱ፡- መጀመሪያ የሄድኩት ወደ ራሺያ ሲሆን ከዚያም አንድ ሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ፊንላንድ ነው ሄጄ ከፍተኛ ትምህርት የተማርኩት፡፡
ቁም ነገር፡-ምን ተማሩ?
ዶ/ር ዘውዱ፡- የመጀመሪያ የማስተርስ ድግሪዬን የተማርኩት አፕላይድ ኬሚስትሪና ማይክሮ ባዮዎሎጂ ነው፡፡ ውጤቴም በጣም ጥሩ የሚባል ስለነበር በኢንተርናሽናል ጆርናል ላይ ታትሞ ስለነበር ለምን በዛው የዶክትሬት ድግሪህንም አትሰራም ተብዬ ዕድሉ ሲሰጠኝ እዛው የተማርኩበት ኮሌጅ ውስጥ እያስተማርኩኝ የዶክትሬት ትምህርቴን ጀመርኩ፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላም ትምህርቴን ጨርሼ ከተመረቅሁ በኋላ በዛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያስተማርኩና በተመራማሪነት ለሰባት ዓመታት ያህል ከሰራሁ በኋላ ወደ ሆላንድ ሄድኩ፡፡
ቁም ነገር፡-ለምን?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ሆላንድ በአመስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባለ የጥርስ ህክምና ፋካሊቲ ውስጥ የማይክሮ ባዮዎሎጂ ተመራማሪ ያስፈልጋቸው ስለነበር ነው የሄድኩት፡፡ይህ ምርምር የሚያተኩረው በጥርስ ውስጥ ያሉ ባክቴሪያዎች ያላቸውን ምንነት እና ምን እንደሚያደርጉ ማጥናት ላይ ስለነበር ይህንን የሚያሳይ የሞሎኪዩላር ቴክኒክን ለማበልፀግ ነበር እዚያ የሄድኩት፡፡ይህ ምርምር ውጤታማ ስለነበር ትላልቅ የጥርስ ሳሙና አምራች ኩባንያዎች ወስደውኝ እስከ አሜሪካ ድረስ ሄጄ ምርምሩን በተመከለከተ ስልጠና ሰጥቼ ነው የተመለስኩት፡፡ ከአሜሪካ መልስ ከአመስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ከለቀቅሁ በኋላ በዘር የሚተላለፉ በሽታዎችን /የጄኔቲክስ ቴስቲንግ/ የሚመረምር ኬሚካሎችን የሚያበለፅግ አንድ ተቋም አለ እዛ ገባሁ፡፡ ተቋሙ እነዚህን በዘር የሚተላለፉ የዘር በሽታዎችን የሚለየውን ኬሚካል አበልጽጎ ለተለያዩ ተመራማሪዎችና ለህክምና ተቋማት ያቀርብ ስለነበር በዚህ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ተመራማሪነት ነው የተቀጠርኩት፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ አንድ ሶስት ዓመት ያህል እንደሰራሁ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ እመላለስ ስለነበር ከዚህ በኋላ ለምንድነው የያዝኩትን እውቀት ይዤ ወደ ሀገሬ ገብቼ አንዳንድ ስራዎችን የማልሰራው ብዬ ወስንኩ ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ የህክምና ስራ ይሰሩ ነበር?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ወደ ሀገር ቤት ስመጣ የተለያዩ ስልጠናዎችንና ትምህርቶችን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እሰጥ ነበር፡፡ በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮዎሎጂ ዲፓርትመንት፤ የህክምና ፋካሊቲና እንዲሁም የህፃናት ህክምና ዲፖርትመን ጋር ውስጥ ካሉ መምህራን ጋር እንተዋወቅ ስለነበር በመጣሁ ቁጥር ያለኝን አዳዲስ እውቀቶች እያስተማርኩ ነበር የምመለሰው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የጄኔቲክስ ቴስቲንግ ፋሲሊቲ እንደሌለ ተመልክቼ ስለነበር ሆላንድ ውስጥ እኔ እሰራበት ከነበረው ተቋም ይህንን ፋሲሊቲ መጠቀም እንደሚቻል ተነጋግሬ ነበር፡፡የተወሰኑትን የምርምር ኬሚካሎች እዚህ ላሉ ወዳጆቼም አምጥቼ ሰጥቻቸው ስለነበር ውጤት አግኝተውበታል፡፡ እርግጥ ነው አዲስ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ወደ ሶስተኛው ዓለም ሀገራት ሲገባ የተወሰኑ መስፈርቶች ሊበጅለት ይገባል፤አዲስ ቴክኖሎጂ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ እውቀቶችን ለህብረተሰቡ ማምጣት አለበት፡፡በዘር የሚተላለፉ በሽታዎችን በዚህ ኬሚካል አማካይነት የመለየቱ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ የህብረተሰቡንም አቅም ባገናዘበ መልኩ መሆን ስላለበት የምሰራበት ተቋምም እናግዝሃለን ብለውኝ ስለነበር ነው ጠቅልዬ ወደ ሀገር ቤት የመጣሁትና በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የጄኔቲክ ቴስቲንግ ማዕከል የከፈትኩት፡፡
ቁም ነገር፡- ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ የሚያተኩረው ምን ላይ ነው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ከቴክኖሎጂው ስንነሳ በቀላሉ በዲኤንኤ ላይ የተመሰረተ የህክምና አገልግሎት ነው ፡፡ዲኤን ኤ ማለት ማንም በህይወት ያለ ፍጡር ከትንሷ ባክቴሪያ ጀምሮ እስከ ትልቁ ሰው ልጅ ወይም ግዙፉ አሳ ነባሪ ድረስ ሰውነታቸው የሚሰራውን ስራ የሚይዝ በኮድ መልክ የተቀመጠበት ሞሎኪዩል ነው፡፡ይሄ ዲኤን ኤ የአንድን ፍጡር ማንነት ብቻ ሳይሆን ምንነቱንም ጭምር ይገልፃል፡፡እኛም የሰው ልጅ ምንነታችንን የሚገልፅ ሞሎኪል በሴላችን ውስጥ ይዘን ነው

የምንኖረው፡፡ይህ ዲኤንኤ የሚባለው ሞሎኪዩል ከትውልድ ወደ ትውልድ የእየተላለፈ የሚመጣ
በዘር የሚተላለፍ ነው፡፡የኛ የዲኤንኤ አሻራ ከዛሬ ሚሊዮን ዓመት በፊት ከነበረችው ከሉሲ አሻራ
ጋር የሚመሳሰልበት ነገር እንዳለው የሚረጋገጥበት ነው፡፡ በሰለጠኑት ሀገራት የህክምና ቴክኖሎጂው
እያደገ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ህክምና ከዲኤንኤ ምርመራ ጋር በማቆራኘት በቀላሉ
ህክምና መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በዲኤን ኤ ምርመራ አንድ ሰው ምኑ ሲቀንስ ምን እንደሚሆን፤ ምን ሲበዛ ምን እንደሚታመም
የሚታወቅበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ በመሆኑ የተነሳ ለእያንዳንድ ሰው የግለሰብ ህክምና ደረጃ
እየወረደ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ምን ማለት ነው የግለሰብ ህክምና ማለት?
ዶ/ር ዘውዱ፡- የግለሰብ ህክምና ማለት የአንድ ሰው ምንነት በዲኤንኤው አማካይነት
በትክክል በመታወቁ ለእርሱ ብቻ ተብሎ የሚሰጥ መፍትሔ ማግኘት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ይህንን
ህክምና መስጠት የሚቻለው የግለሰቡን ሁኔታ የሚገልፀውን ምርመራ በዲኤንኤ በማድረግ ነው፡
፡በመሆኑም በዘር ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ በሽታዎችን በዲኤንኤ ምርመራ
ማረጋገጥ ስለሚቻል ነው ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ቤት በማስገባት ህብረተሰቡ ምርመራ
በማድረግ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ለችግሩ የበለጠ እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማገዝ
ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡
ቁም ነገር፡- በመድሃኒት አወሳሰድ ላይስ የዲኤንኤ ምርመራውን ቀድሞ ማድረግ ምን ያህል ጠቀሜታ አለው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- በጣም ይጠቅማል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ትንሽ መድሃኒት ወስደው የሚድኑ ሰዎች አሉ፤ ለነዚህ ሰዎች ብዛት ያለው መድሃኒት
መስጠት አያስፈልግም፡፡ መሉ ለሙሉ ደግሞ መድሃኒት መውስድ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ መጠን
ያለው መድሃኒት መውሰድ ያለባቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ይሄንን ለማወቅ የዲኤንኤው ምርመራ
ግልፅ መረጃ ይሰጣል፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን የህክምና ታሪኮች ለማወቅ ይጠቅማል፡፡
ቁም ነገር፡- ከዘር ጋር የተቆራኙ እንደ ስኳር ያሉ ህመምተኞች ላይ ያለው
ጠቀሜታስ?
ዶ/ር ዘውዱ፡- እንደ ስኳር ብቻ ሳይሆን የአንጀት ካንሰር እና የጡት ካንሰርን ጨምሮ
ለማከም ከዘር ጋር ያለውን ቁርኝት እስካላወቅን ድረስ የምንሰጠው ህክምና የተሟላ አይሆንም
ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ለምሳሌ የስኳር ህምም በዘሩ ውስጥ እንዳለ የሚያውቅ ሰው በስኳር በሽታ
እንዳይጠቃ ወይም የሚጠቃም እንኳ ቢሆን ቀሪ ህይወቱን እንዴት በሰላማዊ መንገድ መምራት
እንዳለበት በቀላሉ ማወቅ ይችላል፡፡የአንጀት ካንሰር በቤተሰቡ ውስጥ ያለበት ሰውም የአመጋገብ
ሁኔታውን በማስተካከል ብቻ ከበሽታው ራሱን መጠበቅ ይችላል፡፡ካንሰር ማለት በአንድ ጊዜ
መመረት ካለበት መጠን በላይ ብዙ ሴሎች መመረት ወይም የማይገባቸው ሴሎች ተመርተው
መገኘት ማለት ነው፡፡ ሁሉም ካንሰር ግን አጥፊ ነው ማለት አይደለም፡፡ የካንሰሩን ምንነት ለማወቅ
የሚቻለው የሴሎቹን ሞሎኪዩላር ስትራክራቸው ወይም ቁጥር በመመርመር ነው፡፡ በዲኤንኤ ምርምራ ነው
የሚታወቀው፡፡ ይህንን የካንሰር ስፔሻሊስት ሀኪሞች ናቸው ይህንን በደንብ የሚያውቁት፡፡
ቁም ነገር፡- ከእርግዝና ጋር በተያያዘስ ቴክኖሎጂው ምን ያህ ጠቀሜታ አለው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ለምሳሌ አንድ እናት አርግዛ
ገና በሽል ደረጃ ፅንሱ እያለ የእናቲቱን የሽንት ውሃ በመውስድ ብቻ ከህፃኑ ገላ ላይ እየተቀረፉ የሚወድቁ
ቆዳዎች ላይ ያለውን ዲኤንኤ በመመርመር ወደ ፊት ልጁ የሚያጋጥመውን የጤና ችግር ከወዲሁ ማወቅ ይቻላል፡
፡ሴቶች እድሜ ከገፉ በኋላ ከሚፈፀም እርግዝና ጋር በተያያዘ በልጆች ላይ የሚከሰትን የአዕምሮ ዝግመትና
ኦተስቲክ አይነት እግሮችን አስቀድሞ ማወቅ ይቻላል፡፡ አስቀድሞ ከታወቀ ደግሞ በእናቲቱ ጤና ላይ ችግር
የሚፈጥር ከሆነ የሚወለደው ልጅም የሚይቆይ ከሆነና ሌሎች ችግሮች የሚመጡ ከሆነ አስቀድሞ እርምጃ
ለመውስድ ይህ የጄኒቲክስ የናሙና ምርምራ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡በመሆኑም ቴክኖሎጂው በእናቶችና
በጨቅላ ህፃናት ሞት ላይ ያለውን ሁኔታ ከወዲሁ መታደግ የሚቻልበትን አማራጭ የሚያስገኝ ቴክኖሎጂ
ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ በሀገራችን የተለመደው ሰዎች የዲኤን ኤ ምርመራ የሚያደርጉት ታመው
ሀኪም ቤት ከሄዱ በኋላ በሀኪም ትዕዛዝ ነው፤ ግን ከዛ በፊት ማንኛውም ሰው ጤነኛ ሆኖ ነገር ግን
የቤተሰቡንና በዘር የወረሰው ነገር እንዳለ ለማወቅ ይችላል?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ይችላል፤ለምሳሌ በቤተሰብ ውስጥ አባት ወይም አያት፤ወደታች አክስተና አጎት
በተመሳሳይ መልኩ በአንድ አይነት በሽታ የተያዙ እንደነበር የሚያው ሰው በዘሩ ምክንያት እሱም በዚያ
በሽታ የመያዝ ዕድል ሊኖረው ስለሚችል መጥቶ በምርምራ ማረጋገጥ ይችላል፡፡ይህንን ምርምራና
ምክር እኛ ጋር መጥተው ሲወስዱ የግድ የሀኪም ትዕዛዝ አያስፈልግም፡፡ በእርግጥ ሀኪም አዞ የሚመጡ
ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የወደፊት አኗኗርን ከወዲሁ ለማስተካከልም ምርመራውን አድረጎ ራስን ማወቅ
ይቻላል፡፡ምርምራውን አድርገው ችግሩ እንዳለባቸው በዲኤንኤ ምርምራ የተረጋገጠላቸው

ሰዎችም ምን ማድረግ እንዳለባቸው በዘርፉ ስፔሻይዝድ ወዳደረገ ሀኪም እንልካቸዋል፡፡በሌላ መልኩ ብዙ ጊዜ
የሚወለዱት ህፃናት ጤናማ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ወላጆች ችግር ያለባቸው የተለየ ባህሪ የሚያሳዩ
ህፃናትን ሊወልዱ ይችላሉ፡፡ የዛን ጊዜ መጥተው ምርመራ በማድረግ ያ የታየው ችግር በትክክል መኖሩን ማየት
ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከተወለዱት ልጆች መሀከል አንዱ የአዕምሮ ዘገምተኛ ወይም ጡንቻዎቹ ያልጠነከሩ ሊሆኑ
ይችላል፡፡ እነዚህን በአይን አይቶ ብቻ ላይታወቅ ይችላል፡፡ በዲኤንኤው ላይ በሚደረግ ምርመራ ግን ቤተሰብ
እውነታውን እንዲያውቅና የአማራጭ ህክምና ለመጀመር ይቻላል፡፡
የተለመደው ነገር ግን ከቤተሰብ ውስጥ አንዱ ልጅ ብቻ የዚህ አይነት የተለየ
ባህሪ ሲያሳይ ከተለያዩ ባዕድ ምልኮ ጋር በማያያዝ ጉዳዩን በሌላ መልኩ
ለመፍታት ይሞከራል፤ ይህ ከሚሆን ይልቅ ግን ምርመራ በማድረግ ነው
መፍታት የሚቻለው፡፡
ቁም ነገር፡- በዚህ ማዕከል ውስጥ የሚሰጡት ምርመራዎች ምን ምን ናቸው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ለምሳሌ በሂሞግሎቢን አይነት በመቀየር የተነሳ የሚመጣን የደም ማነስ ማወቅ
ይቻላል፡፡ ደማቸው በቆሰሉ ሰዓት ቶሎ የማቆምላቸው ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሰዎች የጂን ችግር እንዳለ
በቤተሰባቸው ውስጥ ማወቅ ይቻላል፡፡ የደም ካንሰርን ሉኬሚያን ማወቅ ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት የአዕምሮ
ዝግመት ያለበት ልጅ የወለዱ ወላጆች ቀጣዩ ልጃችን እንደዚህ ይሆናል ወይ? የሚለውን ለማወቅ የሚፈልጉ
ወላጆች በምርመራ ሁኔታውን ማወቅ ይቻላል፡፡ከዚያም ከማህፀን ሀኪም ጋር እንዲገናኙና ሰፋ ያለ ህክምና
እንዲያደርጉ ለማድረግ ይቻላል፡፡
የማህፀን ሀኪሞች ናሙና ከወላጆች ላይ በመውስድም የሚልኩልንን በመመርመር በዚህኛው ልጅ ላይ
ችግሩ ሊኖር ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ለማወቅ ይረዳል፡፡
ቁም ነገር፡- ወላጆች በዘራቸው ችግር እንዳለባቸው የሚታወቅ ከሆነ ልጅ እንዳይወልዱ ለማድረግ ይቻላል?
ዶ/ር ዘውዱ፡-እርግዝና በመሰረቱ በአጋጣሚ የሚከወን ነው፡፡ ሁሉም ሴቶች በአንድ ጊዜ አያረግዙም፡፡ ያም ሆኖ ግን በዘር የሚወረስ ችግር በጂን ዲፌክቲቨ የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ችግሩ በሁለቱንም ወገኖች በኩል ሊኖር
ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎችን እንዳይጋቡ መከልከል ያስቸግራል፤ ነገር ግን ልጅ እንዳይወልዱ መምክር
ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም በዘራቸው የወረሱት የጂን ችግር ስላለ በሚወልጁት ልጅ ላይ ወይ
ሙሉ ለሙሉ ወይ በግማሹ ወይም ከዚያ ባነሰ የጤና ችግር ይዘው ሊወለዱ ይችላል፡፡ ያ የጤና ችግር
ብዙ ሳይቆዩ ሊገላቸው ይችላል፡፡
ወይ ደግሞ ከነችግሩ ለተወሰነ ዓመት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያ ደግሞ በመላጆች ስነ ልቦና ላይ ከባድ ችግር ያስከትላል፡
፡ከስነ ልቦናው ችግሩ በተጨማሪም የህክምና ወጪ ጉዳይ የአንድን ቤተሰብ ሰላም የሚያናጋበት አጋጥሚ ብዙ
ነው፡፡ ለምሳሌ ከአርባ ዓመታት በኋላ የሚከሰቱ በሽታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡
፡ እነዚህ አይነት ነገሮች በፊት ለፊት የሚታዩ ሳይሆኑ በዲኤንኤ ምርመራ ብቻ የሚታወቁ በመሆኑ አስቀድሞ
ምክር ማግኘት ይቻላል፡፡ለምሳሌ ሀቲንተን ዲዚዝ የሚባል በሽታ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚታየው አርባ ዓመት
ባለፋቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ ከአዕምሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ግለሰቡ ይህንን በሽታ ለልጅ ልጆቹ ያስተላልፋል፡፡
ስለዚህ እያንዳንዱ ቤተሰብ የቤተሰቡን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደውም የቤተሰብን ታሪክ መዝግቦ የመያዝ
ልምድ ሊዳብር ይገባል፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ይህንን ምርመራ የምትሰሩበትን መሳሪያዎች በጣም ዘመናዊ ናቸው፤ ከዛው ከሆላንድ የመጡ ናቸው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ የመጡት ከሆላንድ ነው፡፡ የተወሰኑትን እዛው
ሆላንድ የነበርኩ ጊዜ ስንጠቀምባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹን ግን አዲስ ተገዝተው የመጡ ናቸው፡፡ እዚህ
ሀገር ቴክኖሎጂውም ስለማይታወቅ አዲሶች ናቸው፡፡
ቁም ነገር፡- ቀደም ሲል ከጥርስ ሳሙና ጋር በተያያዘ ጥናት ማድረግዎን ጠቅሰውልኝ ነበር ምንድንው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- አመስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ፋካሊቲ ውስጥ በምሰራበት ጊዜ አንድ ምርምር አድርጌ ነበር፡፡ አፍ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ባክቴሪያዎች አሉ፡፡ በላብራቶሪ በማሳደግ ከሚታወቁት ውጪ በማሳደግም የማይታወቁ
ነገር ግን በአፍ ውስጥ መኖራቸው የሚታወቁ ባክቴሪያዎችን አሉ፡፡ እነዚህን መኖራቸውን በዲኤንኤ
ምርመራ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ ከ500 በላይ የሚሆኑ የባክቴሪያ
አፋችን ውስጥ አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ለጤና ጎጂ አይደሉም፡፡ ነገር ግን የተወሰኑት ከምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ ስኳሩን ወስደው አብላልተው አሲድ የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡፡ የሚፈጥሩት አሲድ ደግሞ ኢናሜል
የሚባለውን ነጩን የጥርሳችንን ክፍል ይበሉታል፡፡ አፕላይ ማይክሮ ባዮዎሎጂ የተባለው የምርምር
መፅሔት ላይ የታተመው የኔ ምርምር ውጤት በአፍ ውስጥ ያለውን ምራቅ ዲኤንኤ በመመርመር ወደ 50
የሚሆኑ ባክቴሪያዎችን መኖራቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸውስ ምን ያህል
ነው? የሚለውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ የምርምር ውጤት በመፅሔቱ ላይ ታትሞ ሲወጣ የኮልጌት የጥርስ
ሳሙና አምራች ካምፖኒ ሳይኒቲስቶች መጥተው እኛም ይህንን የምርምር ውጤት ልንጠቀምበት እንፈልጋለን
አሉና ፋካሊቲውን ጠየቁ፤ የምርምሩም ባለቤት አሰልጣኙም እኔ ስለሆንኩ ወደ አሜሪካ ሄጄ ኒውጀርሲ ስቴት
ውስጥ ትልቅ የምርምር ምዕከል አላቸው ስልጠናውን ለነሱ ሰጥቼ ነው ወደ ጄኔቲክስ ምርምር እንደገና
ፊቴን ያዞርኩት፡፡እንግዲህ እነሱ በሚያመርቱት ኮልጌት ውስጥ እነዛን ባክቴሪያዎችን ሊያጠፋ የሚችለውን
ኬሚካል በምን ያህል መጠን ነው መጨመር ያለብን የሚለውን እንያውቁ ያግዛቸዋል ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ምን ያህል ጊዜ ሆነው ክሊኒኩ ከተከፈተ?
ዶ/ር ዘውዱ፡- አሁን ወደ ስምንት ወር ሆኖታል ክሊኒኩ
ከተከፈተ፤ ቁም ነገር፡- አንድ ሰው የዲኤንኤ ምርመራ ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል?
ዶ/ር ዘውዱ፡- በአብዛኛውን ሁለት ሳምንት ይስዳል፤ ነገር ግን እንደ በሽታው አይነት ይለያያ፤ ለምሳሌ
የምንወስደው ናሙና ብዙ ጂኖችን ብዙ ክሮሞዞሞችን የሚይዝ ከሆነ ሊቆይ ይችላል፡፡እንደገና ተጨማሪ
ማረጋገጫ የሚፈለግ ከሆነ ወደ ሆላንድ ልከን ተጨማሪ ማረጋገጫ እናገኛለን፡፡
ቁም ነገር፡- በጄኔቲክ መዛባት ወይም ዲፌክት የተነሳ የሚመጡ የጤና ችግሮች ላይ በሀገራችን የጀመራችሁት አዲስ ስራ
ምንድነው?
ዶ/ር ዘውዱ፡- ከጳውሎስ ሆስፒታል ሀኪኮሞች ጋር በመሆን አንድ የጀመርነው ነገር አለ፡፡ ይህውም የጄኔቲክ ችግር ኖሮባቸው የሚወለዱ ህፃናት ምዝገባ ያስፈልጋል በሚል ለመጀመር እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ይህ ምዝገባ መኖሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የትኛው አይነት የጄኔቲክስ ችግር ነው በብዛት የሚታየው የሚለውን በቀላሉ ለማወቅ ይቻላል፡፡
የትኛው ክልልስ ነው በዝቶ የሚታየው የሚለውንና ለዚህ ህመም የሚሆነውን መድሃኒት ወደየት ነው በብዛት መላክ ያለብን የሚለውን ለማወቅ ይረዳል፡፡ የዲኤንኤ ምርመራ ለሁሉም ህመሞች ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ
በመሆኑ የሀገሪቱ የጤና መረጃ በሂደት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ይያዛል ብለን እንጠብቃለን፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡ቁ

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።