Did you hear about twisted money awards given to artists? ይልቅ ወሬ ልንገርህ … ለአንጋፋ አርቲስቶቻችን ስለተሰጠው የገንዘብ ‹ሽልማት›

ቁም ነገር መፅሄት 196

መቼም የሀገራችን የመጀመሪያው እንደሆነ ስለሚነገርለት ቴአትር ቤት አላውቅም አትለኝም፡፡ አንጋፋው ቴአትር ቤት ሀገር ፍቅር በጠላት ፋሽስት ወረራ ወቅት ተቋቁሞ የተለያዩ አርበኝነትን የሚያበረታቱ ዜማችንንና ድራማዎችን ያቀርብ እንደነበር መቼም ታውቃለህ አይደል?
እናስ? አንጋፋው ቴአትር ቤት ምን ሆነ? ምንም አልሆነም፤ ቴአትር ቤቱ ዘንድሮ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ልደት ለማክበር ተፍ ተፍ እያለ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ እናስ? እናማ የዚሁ ክብረ በዓል አካል ይሆናል የተባለ አንድ ዝግጅት ላይ ባለፈው ሳምንት በቴአትር ቤቱ ቅጥር ግቢ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ እናስ? ተገኘኋ!
እናልህ በዚህ ዝግጅት ላይ ቴአትር ቤቱ ሲመሰረት የነበሩ ሰዎች በህይወት ባይኖሩም ከ60 እስከ 70 ዓመት ድረስ ከቴአትር ቤቱ ውስጥ ያልጠፉና በመድረክም ልዩ ልዩ ስራዎችን በማቅረብ ህዝቡን ሲያዝናኑ የነበሩ አንጋፋ አርቲስቶች ተገኝተው ነበር፡፡ አንጋፋ አርቲስቶቹ የጥንት ዜማዎችን በቡድን በቡድን ሆነው ሲጫወቱ ለተመለከተ ‹የሀገር ፍቅር እውነትም አልሞተም › ለማለት ይገደዳል፡፡
እናስ? እናማ እነዚያ አንጋፋ አርቲስቶች በየተራ እንዲሁም በቡድን ወደ መድረኩ እየወጡ ያንን በቲቪ ብቻ የምናውቀውን የድሮ ዘመን ሲያስታውሱን አምሽተዋል፡፡ ግን ግን አንዳንዶቹ በዕድሜ መግፋትም ይሁን በጤና መታወክ ሳቢያ እንደዚያ እንደ እንዝርት ሲሾሩበት በነበረው መድረክ ላይ መውጣት ሲያቅታቸውና በድጋፍ ወዲያና ወዲህ ሲሉ መመልከት ልብን ይሰብራል፡፡
ታዲያ አንጋፋው ቴአትር ቤት እነዚህን አንጋፋ የጥበብ ቤተሰቦች ጠርቶ መድረክ ላይ እንዲወዛወዙለት ብቻ እንዳይመስልህ የጠራቸው፡፡ እናስ ደግሞ ምን አደረገላቸው? ‹ዳጎስ› ያለ ሽልማትም አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡
እንደምታውቀው እነዚህ አንጋፋ አርቲስቶች ሙሉ ዕድሜያቸውን በመድረክ ላይ ጥበብን ብቻ ሲዘሩ ይህ ነው የሚባል ‹ፈረንካ› በእጃቸው እንዳልገባ ግልጽ ነው፡፡የሚተዳደሩትም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የጡረታ ገንዘብ ነው፡፡ እናስ? እናማ ይህንኑ ከግምት ያስገባ የሚመስለው አዲሱ የቴአትር ቤቱ ማኔጅመንት ‹ላይ- ታች› ወርዶ ስፖንሰር ፈልጎ ለአንጋፎቹ ሽልማት በእለቱ ሰጥቿቸዋል፡፡
ለመሆኑ ሞት ሳይቀድማቸው በአንጋፋው ቴአትር ቤት ልደት ላይ ለመታደም መድረክ ላይ የወጡት አንጋፋ አርቲስቶች ስንት እንደሆኑ አውቀሃል? እኔ እቴ አላወቅሁም 42 ያህል ናቸው፡፡ ታዲያ ለነዚህ 42 አንጋፋ አርቲስቶች ስፖንሰር ተፈልጎ ስንት ስንት ብር ሽልማት የተሰጣቸው ይመስልሃል? ካገለገሉበት ዕድሜ አንፃር ሽልማቱን ለመገመት ያስቸግራል፡፡
አትድከም፤ እኔ እነግርሃለሁ፤ 100 ሺህ ብር፡፡ ለእያንዳንዳቸው ወይስ ለሁሉም? ቴአትር ቤቱ በዚያ ምሽት ወደ ቤታቸው ለመመለስ የታክሲ አጥተው ሲቸገሩ ለተመለከትናቸው ለሁሉም አንጋፋ አርቲስቶች ያዘጋጀው አንድ መቶ ሺህ ብር ነበር፡፡ ስንት ሰንት ደረሳቸው? አካፍለዋ! 100 ሺህ ሲካፈል ለ42፤ ለዚያውም ብሩ የተሰጣቸው እንዳይመስልህ፤ እናስ? እናማ በብሩ የህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዙበት ተብለው ሰርተፍኬቱ ነው የተሰጣቸው፤ በል ቻዎ…

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።