ሕግ የማይከበርበት አገር (ዞን ዘጠኞችን በተመለከተ) – ግርማ ካሳ

የተማሩ ናቸው። አገራቸውን የሚወዱ። በሕዝባቸውና በአገራቸው ዉስጥ የሚደረገዉ ግፍ እንዲቆም በጽሁፋቸው የሚመክሩ። ማንም ላይ ጥላቻ የሌላቸው። ኢፍትሃዊነትን የሚጠሉ ። አምባገነንነትን እንጂ ማንንም የማይጸየፉ። በጽሁፋቸው ፍቅርን ሰብከዋል። ነጻነትን አውጀዋል። «ዜጎች እንደ እንስሳ ታስረዉና ታፍነው መኖር የለባቸውም። ነጻነታቸውና ስብእናቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል» እያሉ ተከራክረዋል። ለሰብአዊነት ተሟግተዋል። ሰው ሲከብር እንጂ ሲዋረድ፣ ሲነሳ እንጂ ሲወድቅ፣ ሲድን እንጂ ሲሞት፣ ሲበለጸግ እንጂ ሲደኸይ ማየት አልፈለጉም። በቢሯቸው፣ በቤታቸው፣ ሴቶቹ በቦርሳቸው፣ ወንዶቹ ደግሞ በኪሳቸው ቦምብ ወይም ፈንጂ አልተገኘባቸው። በድብቅ የዶለቱት ወይንም የሰሩት ነገር የለም። የጻፉትና የተናገሩት ሁሉም በግልጽና በአደባባይ ነው። የተወሰኑቱ አርቲክል ዘጠኝ ከሚባል ድርጅት ጋር ግንኙነት አላቸው። እነዚህ ወገኖች የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ( bloggers) ናቸው።

አርቲክል ዘጠኝ እንደ አይሰስ፣ ወይም አልካይዳ ያለ ደርጅት አይደለም። የአርቲክል 19 ድርጅት አመጣጥ እንደዚህ ነው። የተባበሩት መንግስታት የሰባአዊ መብት ድንጋጌ (THE UNIVERSAL DECLARATION OF HUMAN RIGHTS የሚባል አለ። የዚህ ድንጋጌ አንቀጽ 19 ( አርቲክል 19) «Everyone has the right to freedom of opinion and expression; this right includes freedom to hold opinions without interference and to seek, receive and impart information and ideas through any media and regardless of frontiers.» ይላል።

በዚህ አንቀጽ ላይ የተጻፈው ነጻነት በአለም ዙሪያ ሁሉ እንዲከበር ለመርዳት (አድቮኬት ለማድረግ) የተቋቋመ የሲቪክ ማህበር ነው፣ አርቲክል ዘጠኝ። ይህ ማህበር አርቲክል 19 የሚል ስያሜ ይዞ፣ በአሜሪካ፣ በአዉሮፓ ባሉ በርካታ አገሮች፣ በኬንያ፣ በቱኒዚያ ፣ በባንግላዲሽ ሳይቀር እውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀስ ነው። በአገራችን ዉስጥ በኢሕአዴግ መንግስት ተጋብዞ በምርጫ ዙሪያ ስልጠናዎች የሰጠ ድርጅት ነው።

ይህ የተባበሩት መንግስታት አንቀጽ 19 ድንጋጌ በኢትዮጵያ ፌዴራል ሕገ መንግስት አንቀጽ 29፣ ንኡስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ በግልጽ ተቀምቷል። «Everyone shall have the right to hold opinions without any interference.Everyone shall have the right to freedom of expression without interference. This right shall include freedom to seek, receive and impart information and ideas of all kinds, regardless of frontiers, either orally, in writing or in print, in the form of art, or through other media of his choice.» ይላል የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29።

በተባበሩት መንግስታት የሰባአዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ ( አርቲክል 19) ወይንም የኢትዮጵያ መንግስት አንቀጽ 29፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጽፉ፣ የተደራጁ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው። ለሕገ መንግስቱ ፣ ለሕግ ከበሬታ ያላቸው ናቸው።

ነገር ግን ከዘመናዊነት ፍጹም የራቁ፣ በሚድል ኤጅ ይኖሩ ከነበሩ በአስተሳሰብ የማይተናነሱ፣ አዲስ አበባ ያሉ ገዢዎች ግን፣ ራሳቸው ያወጡትን ሕገ መንግስት ረጋግጠው ፣ ሽብርተኞች ናቸው በሚል ክስ ከሰዋቸው ከፍተኛ መከራና እንግልት እየፈጸሙባቸው ነው። ይኸው ለአሥራ ሰባተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ገና ጠፋተኛ ነኝ አይደለሉም የሚል ቃል አልሰጡም። አሥራ ሰባት ጊዜ ፍርድ ቤት ሄደዋል ? አዎን 17 ጊዜ።

እንግዲህ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ አሳዛኝና አሳፋሪ ግፎች የሚፈጸምባት አገር መሆኗን ነው። ኢትዮጵያ ለጥቂቶች ገነት፣ በአሥር ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ልጆቿ ሲኦል የሆነች እንደሆነች ነው። ይሄን ለመቀየር ሕጋዊ በሆነ መልኩ እንቅስቃሴ ተደረገ። ይሄን ለመቀየር እነ ጆን ኬሪ ጠየቁ። ነገር ግን የሕወሃት ሽፍቶች ሊሰሙ አልቻሉም። እነርሱ ማሰር እንጂ መፍታት፣ መደብደብ እንጂ የወቀደን ማንሳት፣ ዜጎችን እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ እንጂ ዜጎችን ማሰባሰብ አያወቁም። ጨካኞች ናቸው። ስብእና አይሰማቸው።

በመሆኑም እንደ አገር እንደ ህዝብ መቀጠል ከፈለግን እነዚህ ሰዎችን እነርሱ ካሰመሩት መስመር አልፈን መሄድ መቻል አለብን። የነርሱ ጭካኔ ሊያስፈራራን አይገባም። እነርሱ የፈለገ ጭራቅ ቢሆንም፣ ጥቂቶች ናቸው። እኛ ሚሊዮኖች ነን። በያዙት ጠመንጃ፣ አሁን እንደ ንስር ትልቅ ቢመስሉንም ፣ እኛ ሁላችንም ከተነሳም እንደ ዝንብ እናጠፋቸዋለን።