በአዲስ አበባ ሴቶች በቤት ውስጥ በመውለድ ህይወታቸውን እያጡ ነው Moms in Addis Abeba die giving birth at home

በኢትዮጵያ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁንም ድረስ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።

     የጥር ወር የጤናማ እናትነት ሣምንትን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ትናንት በዮርዳኖስ ሆቴል ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተውጣጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው በአዲስ አበባ ብቻ ከአንድ መቶ ሺ እናቶች መካከል 420ዎቹ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ያጣሉ። እነዚህ እናቶችን ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ምክንያቶችም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ናቸው። ቀጥተኛ የተባሉት እና 82 በመቶውን ድርሻ የሚይዙት በወሊድ ወቅት የሚከሰት ከፍተኛ ደም መፍሰስ፣ ደም ግፊት፣ ኢንፌክሽን ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ ሲሆኑ፣ ቀጥተኛ ያልሆኑ ደግሞ እርግዝናን ተከትለው የሚመጡ የደም ማነስ፣ የስኳር ህመም እና ተያያዥ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮችም ከእነዚህ እናቶች ሞት 18 በመቶውን ይይዛሉ። ከዚህ በተጨማሪም እናቶች ለአደጋ ሲጋለጡ እና በምጥ ወቅት ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ ለመወሰን መዘግየት፣ ወደ ጤና ተቋማት ለመድረስ ያለው የገንዘብ እና ምቹ የሆነ ትራንስፖርት እጥረት እንዲሁም ወደ ጤና ተቋም ከሄዱ በኋላ አገልግሎቱን በአፋጣኝ አለማግኘት የእናቶች ሞትን ከሚያስከትሉ ምክንያቶች ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

     በአዲስ አበባ ብቻ በመውለድ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፤ የነፍሰጡሮች ቁጥር ደግሞ 76ሺ 916 እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል። የነፍሰ ጡሮች ቁጥር ይህን ያህል ይሁን እንጂ በከተማዋ ያሉት የእናቶች ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግን 143 ብቻ ናቸው። በከተማዋ ካሉ ነፍሰጡር ሴቶች መካከልም 96 በመቶዎቹ ቢያንስ አንድ ጊዜ ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ሲሆን፣ የሰለጠነ ባለሞያ እገዛ የሚያገኙት ግን 86 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።

     በጨቅላ ህፃናት እና እናቶች ሞት ላይ ብዙ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ የገለፁት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ በበኩላቸው፤ በእናቶች ዘንድ በጤና ተቋማት የመውለድ ባህሉ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። በ2011 በተጠና ጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለውም በአዲስ አበባ ከሚወለዱ ነፍሰጡር እናቶች መካከል 87 በመቶዎቹ በጤና ተቋማት የሚወልዱ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 13 በመቶ ግን በቤታቸው ውስጥ ይወልዳሉ። እነዚህ እናቶችም ያለ ህክምና ባለሞያ እገዛ በቤታቸው ውስጥ በመውለድ ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ ይገኛሉ።

    ወይዘሮ አለምፀሐይ አያይዘውም በአዲስ አበባ እየተሰጠ ያለው የሞዴል እናቶች ስልጠና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እየተከናወነ እንዳልሆነ ገልፀዋል። ስልጠናውን በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበረ የገለፁት ምክትል ኃላፊዋ፣ ስልጠናው አምስት ዓመታት የፈጀ ቢሆንም በአንዳንድ ወረዳዎች ግን አፈፃፀማቸው ዜሮ እንደሆነም ገልፀዋል። በአጠቃላይ ሲታይም በዚህ ዘርፍ ያለው አፈፃፀም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ወይዘሮ አለምፀሐይ ጨምረው የገለፁት።

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።