የኮሎኔል መንግስቱ መጽሀፍ “ትግላችን” እና የአምዕሮአዊ ንብረት መብት

ከታክሎ ተሾመ

ኮሎኔል መንግስቱ ኃ.ማርያም ትግላችን የተሰኘ ባለ 505 ገጽ መጽሀፍ ጽፎ ሎስ አንጀለስ (አሜሪካ) ፀኃይ አሳታሚና አከፋፍይ ድርጅት ታትሞ ገበያ ላይ ከዋለ ሰነባብቷል። ኮሎኔል መንግስቱ ጨካኝ ብቻ ሳይሆን የራሱን ህዝብ በጥይት ፈጅቶ አገሪቱን ለተገንጣይ አጋልጧል። በአፍሪካ ተወዳዳሪ ሊገኝለት ያልቻለ አብዮታዊ ሰራዊት በትኖ ሀረሬ ውስጥ የግል ህይወቱን እየኖረ ነው። ከስደት ሁኖ “ታሪክ” መተረኩ መልካም ነው።

እኔም የትላንቱ አምባገነን የዛሬው ደራሲ እሱ በመሪነት የተወናወነበትን የራሱን መጽሀፍ በምን አይነት ሁኔታ አስቀምጦት ይሆን በማለት መጽሀፉን ለማግኘት በጉጉት ሰጠባበቅ ቆየሁ። ይሁን እንጅ የኮሎኔል መንግስቱ ኃ.ማርያምን ባህሪ ለሚያውቅና አስቀድሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች (ለገነት አየለ) የሰጠውን ቃለ መጠይቅ ጨምሮ የሰጣቸውን አስተያየቶች ለተገነዘበ የመጽሀፉ ይዘት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም ነበር። በመሆኑም መጽሀፉን በማንበቤ ምንም ልጐዳ እንደማልችል በማወቅ በአካባቢ ወደሚገኝ የመጽሀፍ መደበር ጐራ ብየ በመግዛት አነበብኩት።

አስቀድሜ እንደጠበኩት መጽሀፉ ጥሩና መጥፎ ገጽታዎች እንዳሉ ተመልክቻለሁ። በተለይም መጽሀፉን በማንበቤ ከአየሁት ብዙ ነገሮችን መመልከት ብቻ ሳይሆን የግለሰቡን ችሎታና ባህሪ ይበልጥ ላውቅ ችያለሁ። ለማንኛውም የኮሎኔል መንግስቱን ባህሪና ምግባር እንደምጠላው ሁሉ መጽሀፉን ግን አልጠላሁትም። እንዲያውም ወድጀዋለሁ፤ እሰየው ጀባ ብየዋለሁ።

እጅግ በሚያሳዝን መልኩና እንደተለመደው አሁንም ቢሆን ኮሎኔል መንግስቱ ኃ.ማርያም ካለፈው ስህተቱ ባለመማሩ ራሱን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ በርካታ የአደባባይ እውነታዎችን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለመሸፋፍን ሲሞክር በማየቴ እውን መቸ ነው መሪዎቻችን ከስህተታቸው የሚማሩት በማለት እጅግ አዘንኩ።

ነገር ግን ማን ያውቃል በቀሪ ሁለት ቅጾቹ (ቮልዩም) ለታሪክና ለህሊናው ሲል እውነተኛ ታማኒነት ያለው ጽሁፍ ሊያቀርብልን ይችል ይሆናል በማለት ቀሪዎችን እስካነብ ድረስ በመጽሀፉ ዙሪያ አሉታዊ ትችት ከማቅረብ ትግስትን መርጫለሁ።

ኢትዮጵያ የተወሰኑ የእናት ጡት ነካሽ የሆኑ ልጆች እንዳሏት ሁሉ በርካታ ምሁራንም ለእውነት የቆሙ ባለታሪኮች አሏት። የኮሎኔል መንግስቱም ሆነ የሌላ ሰው መጽሀፍ እውነታ የሚገመገመው ደግሞ በአገር ወዳዶችና በባለሙያዎች እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ህዝዝብ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የታሪክ ባለሙያዎች መጽሀፉን አንብበው ታሪክ ተዛብቷል የሚሉትን ማስተካከል የአንባቢያን ድርሻ ይሆናል።

ነገር ግን ግለሰቡን በመጥላት ብቻ መጽሀፉ ከሰው እጅ ገብቶ እንዳይነበብ አፍራሽ ቅስቀሳ ማካሄድ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር የድርጊቱን ፈፃሚዎችም በህግ ማስጠየቁ አያጠያይቅም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የታሪኩ ባላደራ ለሆነው ህዝብ የማንበብ መብት መጋፋት ይመስላል።

እርግጥ ነው ከኮሎኔል መንስቱ ኃ.ማርያም የሚጠበቅ እውነት አይኖርም። ግን በመጽሀፍ ሽያጭ እንዳይከብር በሚል በጭፍን አመለካከት መጽሀፉ እንዳይነበብ ማድረግ ማንም ግለሰብ መብት አይኖረውም። በእርግጥ ጥላቻ አለኝ የሚል መጽሀፉን ላለማንበብ መብት አለው። ነገር ግን የሰውን ንብረት እስካን አድርጐ ዌብሳይት ላይ ማሰራጨት ህገ-ወጥ መሆኑን አለማወቃቸው እጅግ አስገረመኝ።

በአገራችን የፕሬስ ነፃነት የህግ የበላይነት ባለመኖሩ የኪነት ሰዎች ጉሮሮአቸው፤ ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ግጥም እያወጡ ብዙ ገንዘብ ከፍለው የሚያሳትሙትን ሌሎች ሳይሰሩና ሳይደክሙ በርካሽ ዋጋ ያውም ኢንተርኔት ላይ ኮፒ ማድረጋቸው ነው። ባለሙያዎች ወደፊት በስራቸው እንዳይተጉ የሚደርስባቸው በደል ከፍተኛ ነው።

ይህ ደግሞ በሀገር እድገት ላይም ከፍተኛ ማነቆ መሆኑን ያመላክታል። ታዲያ በ21ኛው ክፍለ ዘመንና በሰለጠነም አገር እየኖርን አዲስ አበባ መርካቶ ወይም ሶማሌ ተራ ተደብቀው የኮፒ ራይት እንደሚፈጽሙ ህገ-ወጥ ሰዎች ሁሉ አሜሪካ ወይም ፈረንሳይ ተቀምጦ ተመሳሳይ ህገ-ወጥ ስራ መስራት ምን ይባላል?

ይህን የሚያደርግ ሰው እንዴት ስለሰባዊ መብት (Human rights) እና ስለዴሞክራሲ ማውራት ይችላል? እነዚህ መብቶች እኮ አምዕሮአዊ ንብረቶችን (intellectual property rights) ማስጠበቅን ይጨምራሉ። እጣታቸዎችን ወደ ሌላ ከመቀሰራችን በፊት ራሳችን ምን እየሰራን ነው ማለት ይበጃል እላለሁ።

የመጽሀፉ እስካን መሆን ስለ ኮሎኔል መንግስቱ የሚቀይረው ነገር የለም። ኮሎኔል መንግስቱን መቃወም ማለት መጽሀፉን እስካን ማድረግ ማለት አይደለም። ምናልባት ደራሲው ይህ እንደሚመጣ አውቆ አስቀድሞ ኮፒውን ሽጦ ገንዘቡን ተቀብሎ ይሆናል። ተጐጅ የሚሆነው ግን ፀኃይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት ነው። “ዳዋ በበላ ጐመን በዱላ እንዲሉ”።

አንድ የንግድ ድርጅት እንደተቋም ሁኖ ሲቀጥል በሚኖርበት አገር ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት ታክስ እየከፈለ እለታዊ ስራውን ይሰራል። ይህ በውጭ አገር የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ማተሚያ ቤት ለኢትዮጵያዊያን ምን ያህል ጥቅም እንደሚሰጥ ሁሉም ያጣዋል ማለት አይደለም።

የአገራችን ደራሲያን ስደት ላይ ሁነው መጽሀፍ ጽፈው ለማሳተም ሲፈልጉ በሚኖሩበት አካባቢ ኢትዮጵያዊ የሆነ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት በሌለባቸው ስፍራዎች ለማሳተም እጅግ በጣም ከባድ መሆኑን እኔ ራሴ ልመሰክር እችላለሁ። በተለይም ኢትዮጵያዊያን የሌሉበት ማተሚያ ድርጅት አማርኛውን ፊደል ለማስተካከል ስለማይችሉ መጽሀፉ ሲታተም ፊደሎችን ለማስተካከል የጉዳዩ ባለቤት ስራ ፈትቶ ማተሚያ ቤት መቀመጥ ግድ ይለዋል። ያም ሁኖ ክፍያቸው ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር እንዴት እንደሚያትሙት ስለሚቸገሩ ጭራሽ አናትምም የሚሉበት አጋጣሚ አይጠፋም።

እንደሚታወቀው በተለይ መንግስትን የሚተቹ ወይም ደግሞ የመንግስት ‘ተቃዋሚ’ የሆኑ ሰዎች የሚጽፏቸውን ጽሁፎች አገር ቤት ማሳተም እንዳይችሉ አምባገነኑ መንግስት ፈቃደኛ አይሆንም። በዚህ ምክንያት የብዙ ደራሲያን የስራ ውጤቶች እየታፈኑ ነው። ስለዚህ ይህ ችግር ባለበት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ማተሚያ ቤቶች ሊበረታቱ ሲገባ በራሳቸው ሰዎች ኪሳራ እንዲደርስባቸውና ድርጅታቸውን እንዲዘጉ የሚደረገው ጥረት እጅግ አሳፋርና አሳዛኝ ነው።

ማንም ግለሰብ ወይም ድርጅት ዌብሳይት ማዘጋጀት ቢችልም የሚሰራቸው ሰራዎች ከህግ አንፃር መሆን እንዳለባቸው አያጠያይቅም።አላማውም ያላወቀ እንዲያውቅ በድረ-ገጾቻችን እንዲያነቡ በሚል እንጅ የግል ዝና ወይም ሌሎችን ለመደቆስ፤ሞራል ለመስበር፤የሌሎችን ስራ ለማፍረስ ከሆነ ያለ ጥርጥር የዌብሳይት ባለቤት ሊሆኑ ከቶ አይገባም።

የሰውን ንብረት እስካን ማድረግ ማባዛት ከሰው ቤት በሌሊት ገብቶ እንደሰረቀ ተቆጥሮ ህግ ይቀጣዋል።ህግ ሲባል የገደለ፤ የተደባደበ፤ ህዝብ ያወከ ሌሎችንም ህገወጥ ድርጊት ለፈጸመ ብቻ ሳይሆን የሰው ንብረት የነካ ህግ አይምረውም።

ለማጠቃለል እንዲህ የመስለው አጸያፊ ተግባር በፀኃይ አሳታሚና አከፋፋይ ተቋም ላይ የተፈጸመው እኩይ ተግባር በመላው ኢትዮጵያዊያን በተለይም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው። ወደፊት ለአገራችን ታሪክ ለሚጽፉ ሰዎች አደጋ ነው። ምክንያቱም ማንም ተነስቶ የሰው ንብረት እስካን እያደረገ የሚበትን ከሆነ ታሪክ ዘጋቢዎቸ ጃቸውን አጣጥፈው መቀመጣቸው አይቀሬ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የአገርና የህዝብ ታሪክ ሊመዘገብ አይችልም። ስለዚህ ግለሰቦች የሰው ንብረት ሲሰርቁና እስካን ሲያደርጉ ዝም ልንላቸው አይገባም። የህግ የበላይነትን ማሳየት ደግሞ የሁላችን ድርሻ መሆን አለበት።

በመጨረሻ ፀኃይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት ለኢትዮጵያዊያን የሚሰጠው ግልጋሎት እንዳያቋርጥብን አደራ እያልኩ ለዛሬ በዚህ እሰናበታለሁ።