ይች መልእክት ለሕወሃት የመጨረሻ ልትሆን ትችላለች – ግርማ ካሳ
ነገ ቀኑ ጥር 19 ቀን ነው። ሕወሃት አንድ አዋጅ በምርጫ ቦርድ በኩል ያስተላልፋል። ወይ የአንድነትን ፓርቲ ኦፌሴላዊ በሆነ መንገድ በማገድ ፣ የድርጅቱን ሰርተፊኬትና ወረቀት (እውቅና ) ጠፍጥፎ ላደራጃቸው ተለጣፊዎች ይሰጣል። አሊያም በምርጫው መወዳደር እንደማይችሉ ያስታወቃል። የአንድነት ፓርት በአገሪቱ ጠንካራ ድርጅት የሚባል ድርጅት ነው።ከእነዚህ ከሁለቱ ዉሳኔዎች አንዱን፣ በስለጣን ለመቆየት ብሎ ወይም ስልጣንን ላለማካፈል ብሎ፣ ከወሰነ፣ በኢትዮዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዳከተመ (በፊት በስም እንጂ አለነበረም)፣ ሕጋዊ የሰላማዊ ተቃዋሞ እንዳበቃለት አረጋገጠ ማለት ነው።
ከዚያ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አያስቸግረም። ጆን ኤፍ ኬነዲ እንዲህ ብለው ነበር ። “Those who make peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable.” (ለዉጭ በሰላማዊ መንገድ እንዳይመጣ እንቅፋት የሚሆኑ፣ ለዉጥ በአምጽ እንዲመጣ ያደርጋሉ) ። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህሩም አክትቪስት አብርሃ ደሳታ” የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመጽ በሮች ይከፈታሉ” ነበር ያለው። ሕወሃት በሰላም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲውፕችን፣ ከአሁን ለአሁን ያሸንፉባል ብሎ ካገደ፣ ሕዝቡ አማራጭ አጣ ማለት ነው። መቼም ምናምንቴና ኮልኮሌ ድርጅቶችን በማሰለፍ “ዲሞክርሲ አለ” እንደማይሉን ነው።
ነገ የምንሰማው ነገር የአገርችን ፖለቲካ በእጅጉ የሚቀየር ነው የሚሆነው። ነገ ህወሃት ወይም አገሪቷን ወደ ጦርነት አዘቅት ዉስጥ ይከታታል፤ አሊያም ለአፍታም ቢሆን የሰላማዊ ሽግግር እድል እንዲያገኝ ይረዳል።
ለህዝቤ፣ ለአገሬ፣ ለሰላም ስል፣ ሕወሃቶች ወሰነዉታል የተባለው ዉሳኔ ቀልብሰው፣ ለሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲክ እንቅስቃሴ በር እንዲከፍቱ ዛሬ እጸልያለሁ። ያ ካልሆነ የሚታየኝ ጦርነት ነው። የሚታየኝ ዉድመት ነው። አንድ ነገር ለመገንባት ከባድ ነው። ለማፍረስ ግን ቀላል ነው። እስከ አሁን አገራችን በሰላም ያለችው፣ የእነርሱ ጥበቃ የረቀቀ ስለሆነ አልነበረም። ህዝቡ ጨዋ ስለሆነ እንጂ። ከአሁን በኋላ ግን ሕወሃቶች እንደ ጣሊያን ግራዚያኒ ስለሚታዩ ነገሮች ከቁጥጥር ዉጭ ነው የሚሆኑት። በአማራዉ ክልል ያለው አምርሯል። በኦሮሚያ ያለው አምርሯል። ሰው በሚሰሩት ሥር እንዴት እንደ ጠላቸው ባወቁ! በአምቦ፣ በጊምቢ፣ በባህር ዳር፣ በአዲስ አበባ … ያፈሰሱት ደም እንደገና ይቀሰቀሳል። ነገሮች ወደ ዘርም ሊሄዱ ይችላሉ። አስፍሪ ሁኔታ ነው ከፊት የሚጠብቀን።
በአንድነት ፓርቲ ላይ የፖለቲካ ዉሳኔ የወሰኑበትን ቀን የተረገምች ትሁን እስኪሉ ድረስ ነገሮች ከቁጥጥር ዉጭ ይሆንባቸዋል። ላለፉት 24 ያካበቱት ሃብት፣ የገነቡት ቢዝነስ ይወረሳል ወይንም ይወድማል። የተቆጣና የተናደደ በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን በጭራሽ ሊቆጣጠሩት አይችሉም። በዉጭ አገርም ቢሄዱ አያመልጡም። አለም ትንሽ በሆነችበት አለም ክፉ ስራቸውና ያፈሰሱት ደም በሄዱበት ቦታ ይከተላቸዋል።
ለዚህም ነው ከፊቴ የሚታየኝ ከፍተኛ ደም መፍሰስ ስለሆነ፣ ሕወሃቶች የወሰኑትን ዉሳኔ ቀልብሰው በርጋታ ነገሮች እንዲወስኑ የምጸልየው። የሰላም መንገድ፣ የፖለቲክ ልዩነቶች በሰለም የመፍታት ነገር በአገራችን ከሌለ፣ ነገሮች ያበቃሉ ወገኖቼ! አማራጩ አመጽና ጦርነት ነው። ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዳለው ህወሃቶች ሕዝቡን ወደ አላስፈላጊ ጫፍ እየገፉት ነው። ያ በአስቸኳይ መቆም አለበት።
ለአገር ሰላም የምናስብ፣ ይችን መልእክት ያነበብን ሁሉ፣ በርከክ ብለን ጸሎት አናድርግ። ለባለስልጣን ጸልዩ ስለተባለ እንጸልይላቸው። እነርሱንም አገሪቷን ወደ ገደል ከመክተታቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ። ሰላም ፣ መግባባት፣ ወንድማማችነት ይሻለናል። ያንን ካልፈለጉ ግን ፣ እነርሱን በማንኛውም መንገድ ማስቆሙ ግን የግድ ነው የሚሆው !