የዓለም ባንክ የሞራል ኪሳራ በኢትዮጵያ፣
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የሞራል ኪሳራ፣
ኢትዮጵያውያን/ት ለዓለም ባንክ የጭካኔ ቢሮክራሲያዊ የቀልድ ማካሄጃ የመድረክ ትወና ዒላማነት ተዳርገዋል፡፡
በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ እየተባለ በሚጠራው ክልል የዓለም ባንክ ቢሮክራቶች ዜጎችን ከሰፈሩበት ቦታ ያለፈቃዳቸው ወደ ሌላ ቦታ በማዛወር፣ የአካባቢው ዜጎች በቋሚነት ባህላቸውን አዳብረው ከሚኖሩበት ቦታቸው በግዳጅ በማፈናቀል እና የተለሳለሰና እና በጎ መስሎ በእሬት የተለወሰ የዘር ማጽዳት እኩይ ምግባር በማካሄድ “የማታለል ጨዋታ” በመጫወት ላይ መሆኑን አንድ ያለም ባንክ የራሱ የምርመራ ዘገባ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ በጋምቤላ ክልል በቋሚነት የሚኖሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የአኙዋክ ብሄረሰብ ተወላጆችን ጥንት ቀደምቶቻቸው ይኖሩበት ከነበረው ቀያቸው የሚያፈናቅል ፖሊሲን በመንደፍ ዓለም ባንክ ህገወጥ በሆነ መልኩ ምንም ዓይነት ውኃ በማይገኝበት እና ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎቶች ባልተሟሉበት አካባቢ በግዳጅ ተፈናቅለው እዲሰፍሩ በማድረግ በአሁኑ ጊዜ የተፈናቃዮች ህይወት በቋፍ ላይ ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ተስፋ ሊሰጥ በማይችል አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡
ለበርካታ ዓመታት የዓለም ባንክ ቢሮክራቶች እና በኢትዮጵያ ያሉ ተመሳሳዮቻቸው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) አምባገነናዊ ወሮ በላ ቡድን በመካሄድ ላይ ባለው “የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ፕሮጀክት” እየተባለ በሚጠራው እና “በመንደር ምስረታ ፕሮግራም” መካከል አለ እየተባለ የሚነገረውን መሰረታዊ ግንኙነት ሙልጭ አድርጎ በመካድ ህዝቡን በሚጎዳ ድርጊት ላይ ሙዝዝ ብለው ይገኛሉ፡፡ (“የመንደር ምስረታ ፕሮግራም” የሚለውን ቃል የአኟክ ብሄረሰብ ኗሪዎች ጥንታዊ ቀደምቶቻቸው ይኖሩበት ከነበረው ኋላቀር የአኗኗር ዘይቤ ተላቅቀው “በዘመናዊ መልክ በስልጣኔ” መኖር መቻል ነው ከሚለው ቃል ጋር መሳ ለመሳ ያደርጉታል፡፡) የዓለም ባንክ ዓይን ባወጣ መልኩ በጋምቤላ ክልል ከመሰረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮጀክት (መአጥፕ) ጋር በተያያዘ መልኩ የሚቀርቡበትን ትችቶች ባለመቀበል ምንም ዓይነት የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ለመፈጸማቸው ሊያመላክቱ የሚችሉ ማስረጃዎች የሉም በማለት በተደጋጋሚ በማስተባበል ላይ ይገኛል፡፡
የህዝቡ ፍላጎት ተገዥ ለመሆን ተባባሪ ያለመሆን፣ ህዝቡን ከፍላጎቱ ውጭ በኃይል በማስገደድ እንዲሰፍር ማድረግ እና ሆን ብሎ የሀሰት ወሬዎችን ማሰራጨት የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ እና በኢትዮጵያ የልማት እርዳታ ቡድን (27 የሁለትዮሽ እና የብዙሀን መንግስታትን አካትቶ የያዘ ስብስብ) እየተባለ የሚጠራው በኢትዮጵያ የተጠያቂነት ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል መፈጸማቸው እንዳይታወቅ ለመከላከያነት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ናቸው፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ ዓለም አቀፍ የልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ጌታ ማልኮም ብሩስ እ.ኤ.አ ማርች 2013 እንዲህ በማለት በድፍረት ተናግረዋል፣ “ስለመንደር ምስረታው የሚነገሩ አሉባልታዎች ሁሉ መሰረተቢስ ናቸው፣ እናም የእንግሊዝ ፕሮግራም ጥሩ ውጤት እየሰጠ ነው፡፡“
የአቤ ሊንኮልን አባባል በመዋስ “የዓለም ባንክ እና የድህነት ወትዋች አቃጣሪዎች “የልማት እርዳታ ቡድን” እየተባለ የሚጠራው የበርካታ ሀገሮች ስብስብ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን/ትን አንድ ጊዜ ሊያታልል ይችላል፣ እንደዚሁም ደግሞ ጥቂት ኢትዮጵያውያንን/ትን ሁልጊዜ ሊያታልል ይችላል፣ ሆኖም ግን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያውያት ሁልጊዜ ሊያታልል አይችልም፡፡“ እነዚህ የጉሮሮ ላይ አልቀቶች (ተባይ) በሚጫወቱት የማታለል ጨዋታ ምክንያት ኢትዮጵያውያን/ት ተታለዋል! ተጭበርብረዋል! እንዲሳሳቱ እና ግራ እንዲጋቡ ተደርገዋል፡፡ የማልኮምን አባባል በመዋስ “ኢትዮጵያውያን/ት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የጉልበታሙ የዓለም ባንክ መጫወቻ አሻንጉሊት ተደርገዋል፡፡“
ስለሆነም ከዓለም ባንክ ነጻ “የተጠያቂነት የምርመራ ቡድን” (ኢንስፔክሺን ፓኔል) (ምቡ) ጋር መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ ምቡ ንጹህ በሚመስል፣ በተበጣጠሰ እና ቢሮክራሲያዊ በሆነ የቋንቋ አገላለጽ ይናገራል፡፡ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ እና ስሜታዊነት የተሞላባቸው እንቆቅልሽ የሆኑ አስደንጋጭ የሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ቋንቋ በፍጹም አይጠቀሙም፡፡ የሰዎች ሰብአዊ መብቶች በይፋ እየተደፈጠጡ እያዩ ድርጊቱን የሞራል ኪሳራ ብለው አይናገሩም፡፡ ሸክስፒር በሮሚዮ እና ጁሌት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “እነዚህን እንቆቅልሾች ግልጽ እስከምናደርግ ድረስ ለጊዜው የሞራል ስብዕና ኪሳራን አፍ እንዲሸበብ ያደርጋሉ…” ይህንን አስደንጋጭ ሁኔታ እንዲዳፈን አላደርግም ምክንያቱም የዓለም ባንክ የእራሱ የምርመራ ቡድን ሁሉንም እንቆቅልሽ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ግልጽ አድርጎልኛልና!
እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2012 ሁለት ደርዘን እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ኢትዮያውያን/ት የመጠለያ ላይ ተረጅዎች ቀደምቶቻቸው ይኖሩበት ከነበረው መሬታቸው በግዳጅ እንዲፈናቀሉ ተደርገው የመሬት ይዞታቸው ለመሬት ነጣቂዎች የተሰጠ መሆኑን በመግለጽ ይህ እኩይ ድርጊት እንዲጣራላቸው ዓለም ባንክን ጠይቀው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 24/2012 አንድ ስሙ ባልተገለጸ የአኟክ ተረጅ በተጻፈ ደብዳቤ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት የሚተገበረው የኢትዮጵያ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ፕሮጀክት (መአጥፕ) እና በቀጥታ የኢትዮጵያን “መንግስት” የመንደር ምስረታ ፕሮግራም የሚረዳውን የዓለም ባንክን ክፉኛ ወንጅሏል፡፡ በተለይም፣
1ኛ) በመአጥፕ ፕሮግራም የአኟክ ቋሚ ኗሪዎች ይኖሩበት ከነበረው ለም ከሆነው መሬታቸው በግዳጅ እንዲፈናቀሉ ተደርገው መሬታቸው ኢንቨስተር እየተባሉ ለሚጠሩ መሬት ተቀራማቾች በርካሽ ዋጋ በኪራይ ይሰጣል፣
2ኛ) የአኟክ ማኅበረሰብ አባላት ለእርሻ ምቹ ባልሆኑ እና ለምነታቸው በተሟጠጠ ጠፍ መሬቶች ላይ እንዲሰፍሩ ሆኖ አዲስ መንደሮች እንዲመሰርቱ ይገደዳሉ፣
3ኛ) የተሻሻሉ የማህበራዊ አገልግሎቶችን ለህዝቡ በማቅረብ የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ እናሻሽላለን በሚል የውሸት ማደናገሪያ ብዙሀኑ ህዝብ ከኖረበት ቀየው በግዳጅ እንዲፈናቀል ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን ሰፋሪዎቹ አንድ ጊዜ ከሰፈራ ቦታው ከደረሱ በኋላ ለም የሆነ መሬት ብቻ አይደለም የማያገኙት ሆኖም ግን ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ የውኃ ጉድጓዶች ወይም ደግሞ ሌሎችንም መሰረታዊ አገልግሎቶች ጭምር አያገኙም እንጅ፣
4ኛ) አኟኮች የመኸር ሰብሎቻቸው ለመሰብሰብ በደረሱበት ጊዜ ሰብሎቻቸውን ሳይሰበስቡ እንዳለ ትተው በግዳጅ እንዲፈናቀሉ ይደረጋል፡፡ ሰፋሪዎች በመንግስት በግዳጅ እንዲንቀሳቀሱ በሚደረግበት ጊዜ ከመንግስት ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ አይሰጣቸውም፣ እና አብዛኞቹ ሰፋሪዎች በረሀብ አለንጋ እንዲገረፉ ይደረጋል፡፡ በመንደር ምስረታ ፕሮግራሙ ምክንያት ጥቂት ለአደጋ ተጋላጭ ህዝቦች እና ህጻናት በሚከሰተው ረሀብ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
5ኛ) ደመወዛቸው በህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ፕሮጀክት (መአጥፕ) እየተከፈላቸው በወረዳ የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ይህንን ፕሮግራም በተግባር ላይ እንዲያውሉት ይገደዳሉ፣
6ኛ) የሰፈራ ፕሮግራሙን የሚቃወሙ አርሶ አደሮች እና ፕሮግራሙን በስራ ላይ ለማዋል ተቃዋሚ የሆኑ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሰፈራ ጠያቂዎች እና የእነርሱን ዘመዶች ጨምሮ በቁጥጥር ስር የመዋል፣ የድብደባ፣ የማሰቃየት እና የግድያ ሰለባ ዒላማ የመሆን ዕድል ይጠብቃቸዋል፣
7ኛ) የሰፈራ ጠያቂዎች እነዚህ ሁሉ ጉዳቶች የሚመጡት ከዓለም ባንክ የትግበራ ፖሊሲዎች እና ከአሰራር ሂደቶች አናሳነት እና መስተጋብራዊ ቅንጅት ጉድለት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 “ሞትን ቁጭ ብሎ መጠበቅ፡ በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል ህዝቦችን ማፈናቀል እና የመንደር ምስረታ“ በሚል ርዕስ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባለ 115 ገጽ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ ያ ዘገባ በአኟክ ህዝቦች ቀርቦ የነበረውን ውንጀላ አግባብ በሆነ መልኩ የደገፈ እና የልማት ድጋፍ ቡድኑን ስህተቶች እና ጉድለቶች ነቅሶ በማውጣት በኢትዮጵያ በመንደር ምስረታ ፕሮግራም ሰበብ ታላቅ ውርደት እና ውደቀትን ያስከተለ መሆኑን ዘገባው ይፋ አድረጓል፡፡ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ እንዲህ በማለት የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥቷል፡
የኢትዮጵያ መንግስት በመንደር ምስረታ ፕሮግራሙ አማካይነት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩትን በምዕራብ ጋምቤላ ለዘመናት ከቀደምቶቻቸው ጀምሮ ሰፍረው ከቆዩባቸው ቀዬዎች በግዳጅ በማፈናቀል ወደ አልለመዱት እና አዲስ ወደሆኑ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ አድርጓል፡፡ እንደዚህ ያሉት ህዝቦችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የማፈናቀሉ ፕረግራም ምንም ዓይነት ጥናት እና ምክክር ያልተደረገበት እና ለግዳጅ መፈናቀሉ ሰለባ ለሆኑት ወገኖችም ምንም ዓይነት ካሳ ሳይሰጥ የተካሄደ ፕሮግራም ነበር፡፡
መንግስት መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን እና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማሟላት ቃል የገባ ቢሆንም አዲሶቹ የሰፈራ መንደሮች የምግብ እጥረት ያለባቸው፣ የግብርና ድጋፍ ጨርሶ የሌለበት፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶች ፈጽሞ የሌሉባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የሰፈራ ፕሮግራሙን የሚቃወሙ ካሉ እነዚህን ሰዎች በማስፈራራት፣ አደጋ በማድረስ፣ እና ከህግ አግባብ ውጭ የዘፈቀደ እስራትን በማካሄድ በግዳጅ በመከናወን ላይ የሚገኝ የሰፈራ ፕሮግራም ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የመንግስት የደህንነት ኃይሎች ቢያንስ 20 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን በመፈጸም የሰፈራ ፕሮግራሙን አስቸጋሪነት የበለጠ ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ፍርኃት እና ማስፈራራት በጥቃቱ ሰለባ ህዝቦች ላይ በገፍ ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ እየፈጸመ ባለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች ላይ ያለው እውነታ፣
የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን የአኟክ ህዝቦች ያቀረቡትን ቅሬታ በመቀበል አጣሪ ኮሚቴ እንዲሄድ እና እንዲያጣራ በማድረግ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 21/2014 የምርመራ ውጤት የሆነውን ዘገባ በማዘጋጀት ዘገባው ለውስጥ ፍጆታ ብቻ እንዲውል በማድረግ ለዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ለዋና አስፈጻሚ ዳሬክተሮች፣ ለመምሪያ ኃላፊዎች እና ለሌሎች እንዲደርስ አሰራጭቷል፡፡ ይህ ውሱን ስርጭት ያለው የምርመራ ዘገባ የዓለም ባንክ ስራ አስኪያጆችን የስራ ግድየለሽነት ደረጃን ለማሳየት እና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ስራ አስኪያጆች እና በሌሎች አገሮች ያሉት አለቆች ድርጊት በዓለም ህዝብ ዘንድ እንዲታወቅ በማሰብ ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ በድረ ገጽ ላይ እንዲለቀቅ ብቻ ነበር የተደረገው፡፡ ግን የሚስጥሩ ዘገባ ባልታወቀ መንገድ ለሕዝብ አንድከፋፈል ተደርግዋል ።
የምርመራ ቡድኑ “ኢትዮጵያ፡ ክፍል 3 የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት (P128891)” በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን እጅግ በጣም አስደንጋጭ እና ለህሊና የሚዘገንን ዘገባ አቅርቧል፡፡ (የጥናቱን ግኝት የበለጠ አጽንኦ ለመስጠት በማሰብ የፊደሎቹ ፎንቶች ደማቅ ቀለም እንዲሆኑ እና ልዩ የሆኑ ግኝቶችን ለማመላከት በተራ ቁጥርነት የሚያገለግሎ ቁጥሮችም በሮማውያን እንዲሆኑ አድርጊያለሁ፡፡)
[ለአንባቢዎቸ ማስታወሻ፡ በምርመራ ቡድኑ በቀረበው ዘገባ መሰረት አንባቢዎቸ የጥናቱን ግኝቶች በጥንቃቄ እና በጥሞና እንድታነቡ እጠይቃለሁ፡፡ አብዛኞቹ አንባቢዎች በቢሮክራሲያዊ የማደናገሪያ ቃላት እና ሀረጎች የቋንቋ አጠቃቀም ምክንያት ሊያደናግሩ እና በቀላሉም ግንዛቤ ለመውሰድ አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚቸሉ ይታመናል፡፡ ባለስልጣኖች የዘገባውን መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ወዲያውኑ ከስር የእንግሊዝኛውን (በቀላል አማርኛ) ትርጉም አዘጋጅቸዋለሁ፡፡]
[I]…የቡድኑ የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው የፕሮጅክቱ አስተዳደር በአራት ክልሎች ሊተገበር የተዘጋጀውን የክፍል 3 የመሰረታዊ አገልግሎቶች የጉዳት ትንተና/risk analysis ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ፈጽሞ አላከናወነም፣ ወይም ደግሞ በየጊዜው ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች ማቀለያ የሚሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ በቂ የሆኑ ዝግጅቶች አልተደረጉም፡፡ የምርመራ ቡድኑ እንዳረጋገጠው የአስተዳደሩ አቀራረብ ደረጃውን የጠበቀ ወይም ደግሞ የጉዳቱ ሰለባ ሊሆኑ ለሚችሉት የማህበረሰብ ክፍሎች አስቀድሞ በመከለካያነት ሊያገለግል የሚችል አጠቃላይ የሆነ የጉዳት ትንተና የድርጊት ማዕቀፍ መመሪያ (ጉትድማመ) በተሟላ መልኩ እና በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶ አልቀረበም፡፡ የምርራ ቡድኑ እነዚህ የተዘለሉ እና የተረሱ ነገሮችን በፕሮጀክት ሰነዱ 2.20 ከተቀመጠው ጋር ሊሄዱ እንዳልቻሉ እና ይልቁንም ከዚህ ጋር በተጻረረ መልኩ እንደሆኑ በግልጽ አሳይቷል፡፡
[II] … በህዝብ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ክፍል 3 ፕሮጀክት ማጽደቅ ወቅት እና ከላይ እንደተጠቀሰው ፕሮጀከቱን ለመተግበር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉት ጉዳቶች በቂ በሆነ መልኩ ጥናት ያልተካሄደባቸው ወይም ደግሞ በአግባቡ ያልተያዙ እንዲሁም በክፍል 3 የፕሮጀክት ትግበራ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉን ጉዳቶች እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ያልተየ እንደነበር የምርመራ ቡድኑ ግለጽ አድርጓል፡፡
[III] በማስፈጸሚያ የፕሮጀክት ሰነዱ ቁጥር 4.10 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የፕሮጀክት አስተዳደሩ ይህ የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎት ክፍል 3 ሰነድ ሲዘጋጅ ከዚህ ጋር እኩል ተመጣጣኝ የሆነ ወይም የበለጠ ጥቅም ለአካባቢው ህብረተሰብ ሊሰጥ ይገባ ነበር፡፡ የጥናት ቡድኑ ከአኟክ ህዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን እንደ የኑሮ ሁኔታ፣ ደህንነት፣ መሬት እና የተፈጥሮ ሀብቶች የማግኘት መብትን የፕሮጀክቱ ክፍል 3 የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ሰነድ ሲዘጋጅ እንዲካተቱ አላደረግም፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች እንዳሉ በሙሉ ከግንዛቤ ውስጥ ሳይወሰዱ የተዘለሉ ስለሆነ ከፕሮጀክት ሰነዱ ቁጥር 4.10 ጋር በተጻረረ መልኩ ተግባራዊ ሳይደረጉ ቀርተዋል፡፡
[IV] … ከባንኩ ፖሊሲዎች አንጻር የህብረተሰቡን የልማት ፕሮግራም እና የህዝቡን መሰረታዊ አገልግሎቶችን ከማረጋገጥ አኳያ በትግበራ አካሄዱ መካከል በፕሮጀክት ሰነድ ማጽደቅ እና በትግበራ ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶች እና ችግሮች በተለይም እንደ ጋምቤላ ባለ ክልል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ቤተሰብ የመንግስት የልማት የሰፈራ ፕሮግራም እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መታየት ነበረበት፡፡ በምርመራ ቡድኑ የጥናት ግኝት መሰረት በጋምቤላ መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን በግብርናው ዘርፍ እና በሌሎች የኑሮ ሁኔታዎች በጥራት እና በበቂ ሁኔታ ለማግኘት እንዲቻል የፕሮጀክቱ አስተዳደር በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮችን እና ችግሮቹን ለማስወገድ በስራ ላይ የሚውሉ የአካሄድ ስልቶችን ከግንዛቤ በማስገባት በሰነዱ ላይ እንዲካተቱ አላደረግም፡፡
[V]…የክፍል 3 የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ትግበራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 3 የጋራ የምክክር ፕሮግራሞች እና የትግበራ ድጋፍ ተልዕኮዎች ተካሂደዋል፣ ሆኖም ግን ከላይ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ የቀረቡ ዘገባዎች ምንም ነገር ትንፍሽ ሳይሉ እንዲታለፍ አድርገዋል፡፡ የምርመራ ቡድኑ የክትትል እና የቁጥጥር ስርዓቱ በፖሊሲው ላይ ከተጠቀሰው በተጻረረ መልኩ ተግባራዊ ሆኗል፡፡
[VI]… የምርመራ ቡድኑ ይፋ እንዳደረገው በሰነዱ ላይ በተራ ቁጥር 10.02 በተጠቀሰው መሰረት የፕሮጀክት አስተዳደሩ ከተቀመጡት መስፈርቶች አንጻር በህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ክፍል 3 ዝግጅት እና ማጽደቅ ጊዜ እየታዩ ተግባራዊ እንዲሆኑ አላደረግም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምርመራ ቡድኑ ለመጠቆም እንደሞከረው ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ የተመደበው ገንዘብ በወረዳ ደረጃ ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገበት በስራ ላይ ይውላል የሚለው የባንኩ እምነት ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ሊካሄድ እንደማይችል የጥናት ቡድኑ በግልጽ አሳውቋል፡፡
[VII]…የልማት ፕሮጀክት ቢሮው የውጤት አመልካቾች በመጀመሪያው የዕቅድ እና በተከታታይም የገንዘብ ብክነት አደጋ አናሳ መሆኑን ቢያመላክቱም በቀጣዮቹ ጊዚያት ሊፈጸም ስለሚችልበት ሁኔታ ግን የተዘጋጀ ነገር እንደሌለ የጥናት ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እነዚህ ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር እና ለመከታተል እየተደረገ ያለው ጥረት በፕሮጀክት ሰነዱ ላይ የተገለጸው ከባንኩ ፖሊሲ OP/BP 10.00 ጋር ተጻራሪ በሆነ መልኩ የተቀመጠ ነው፡፡
የምርመራ ቡድኑ ዘገባ በቀላል የእንግሊዝኛ (አማርኛ ) ቋንቋ ሲተረጎም፣
የቢሮክራቶች ቋንቋ ቢሮክራሲያዊ አገላለጽ ወይም ደግሞ ባለስልጣናዊነት መንፈስ የሰፈረበት ሆኖ ይገኛል፡፡ በቀላሉ ግንዛቤ ሊወሰድባቸው በማይችሉ፣ አደናጋሪ በሆኑ፣ በአዳዲስ የአባባል ቃላት እና ሀረጎች የተሞሉ፣ መንታ ምላሶች የሚግተለተሉባቸው፣ አዳዲስ ስያሜዎች የሚጎርፉባቸው፣ ቀጥተኛ ባልሆኑ አገላለጾች የተሸሞነሞኑ፣ እንደሰም እና ወርቅ ዓይነት አቀራረብ የታጀለባቸው እና በቀላሉ ግልጽ ሊሆኑ በማይችሉ አደናጋሪ አህጽሮተ ቃላት እና ሀረጎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ቢሮክራሲያዊነት ስለግልጽነት እጦት ጉዳይ ነው፣ ግልጽ ያለመሆን ወይም ደግሞ ቀጥተኛ ሆኖ ያለመቅረብ ጉዳይ ነው፡፡ ቢሮክራሲያዊ ዘገባዎች ሁልጊዜ ግልጽነት የጎደላቸው፣ የተጣመሙ እና የተንሻፈፉ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ለማንበብ ወይም ደግሞ አንብቦ ግንዛቤ ለመውሰድ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሰዎችን እንዲያደናግሩ እና ቀልብ እንዲያሳጡ ሆነው የተዘጋጁ የሸፍጥ ሰነዶች ናቸው፡፡
ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ በቢሮክራሲው የተካነ እና ቅስናውን የወሰደ የቢሮክራት ጠቢብ በፍጹም አካፋን አካፋ ብሎ በቀጥታ አይጠራም፡፡ ከዚህ ይልቅ አካፋን ጫፉ ስለትነት ያለው፣ አራት ማዕዘን የሆነ፣ በረዥሙ የእንጨት እጀታው ጫፍ ላይ ብረት የተሰካለት ወይም ደግሞ ጥብቅ የሆነ ፕላስቲክ የተገጠመለት እና ከበርካታ ተግባራቱ መካከል የከብቶችን አዛባ ለመፈንጨት ወይም ለመበተን የምተቂም መሳርያ በሚል መግለጽ እና ማደናገር ይቀናቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ቢሮክራቶች የተካኑበት እንደዚህ ያሉ አቀራረቦችን በማራመድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
[ጥቂቶች የአጥኝ ቡድኑን የጥናት ግኝት የቢሮክራሲ ዋና መለያ ባህሪ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርበው በጥናት ቡድኑ የምርመራ ግኝት ላይ ተመስርቶ ስለቢሮክራሲ የተገለጸ የእራሴ የእንግሊዝኛ (ያማርኛ ትርጉ) ትርጉም ነው፡፡ የምርመራ ቡድኑን ግኝት በተመለከተ ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው የሮማውያን ቁጥሮችን እንደዋቢ ማጣቀሻ መውሰድ ይቻላል፡፡]
[I] በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ አስተዳደር እና በሌሎች አገሮች የሚገኙት የባንኩ ኃላፊዎች የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚል ፕሮግራም ነድፈው በህዝቦች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ አያስከትልም ብለው በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች ምንም ዓይነት ስራ የማይሰሩ ለይስሙላ የተቀመጡ ናቸው ፡፡ ፕሮግራሙን በስራ ተርጉመው እንዲያሳዩ በኃላፊነት ቦታ ላይ ብቃት አላሳዩም፡፡
የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች ወይም ደግሞ ኃላፊዎች በጋምቤላ ህዝቦች የመንደር ምሰረታ ፕሮግራም ለውጥ አመጣ አላመጣ ወይም ደግሞ ፋይዳ ያለው ነገር አስገኘ አላስገኘ ደንታቸው አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ስለይፋ የፖሊሲ እና የመመሪያ ሰነዶቻቸው ስለጋምቤላ ህዝቦች መሰረታዊ አገልግሎቶች ለማቅረብ ጥናት ሲጠና በፕሮጀክት ትግበራ ሂደቱ ወቅት በአኟክ ማህበረሰብ ላይ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ጉዳቶች እና አደጋዎች የተጠናና እና በሰነዱ ላይ የተካተተ ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች ወይም ኃላፊዎች ይህን የመሰረታዊ አገልግሎቶች ፕሮግራም በአራት ክልሎች ላይ በአንድ ጊዜ ለመተግበር የመሞከራቸው ሁኔታ ሲታይ ሊውጡት ከሚችሉት በላይ እያኘኩ የሚገኙ መሆናቸውን በግልጽ ያመላክታል፡፡ በፕሮጀክት ማጽደቅ ወቅት በባንኩ የፖሊሲ ሰነድ በተራ ቁጥር 2.20 ላይ ከተጠቀሰው ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑ እየታወቀ ወደተግባር እንዲገባ መደረጉ የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች ወይም ኃላፊዎች ከሚከተሉት ውስጥ አንደኛውን ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመላክታል፡ የሙያ ብቃትየለሽነት፣ የለየላቸው የስራ ጸር የሆኑ ሰነፎች፣ ለምንም ነገር የማያስቡ ግዴለሾች፣ በቀጣይነት በህዝቦች ላይ ሊመጣ ስለሚችለው ጉዳት እና አደጋ የማያውቁ ክህሎቱ የሌላቸው ደንቆሮዎች፣ ምንም ዓይነት ደንታ የሌላቸው እና የሞራልም ሆነ የሙያ ስብዕና የሌላቸው ለህዝብ መብት ኬሬዳሽ የሚሉ ከንቱዎች መሆናቸውን ያሳያል፡፡ መፍትሄውን ከቦርጫቸው ስር ተወሽቆ ያገኙታል!
[II] የዓለም ባንክ ሀገራዊ ፕሮግራም ስራ አስፈጻሚዎች ወይም ኃላፊዎች ምንም ዓይነት ብቃት የሌላቸው እና ኃላፊነት የማይሰማቸው እንዲሁም ደንታ ቢስ የመሆን እና የሙያ ብቃት የሌላቸው፣ ፕሮጀክቱ በመተግበሩ ምክንያት በአኟክ ማህበረሰብ ላይ ወደፊት እና አሁንም በትግበራ ወቅት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እና አደጋ መለየት የማይችሉ እና የመሰረታዊ አገልግሎት ፕሮጀክቱ ሲተገበር ለህዝቡ ምን ፋይዳ ያለው ነገር እንደሚያመጣ ግንዛቤው የሌላቸው ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ ጉዳቱ መድረስ ከጀመረ እና የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች ነገሮች በመጥፎ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ካወቁ ስህተቶቻቸውን መቆጣጠር እና በእነርሱ ስር እንዲሆኑ ለማድረግ አይችሉም፣ ወይም ደግሞ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ አይችሉም ምክንያቱም ወደፊት ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ የሚያውቁት ነገር የሌላቸው የሙያ ብቃት የለሾች ናቸው፡፡ ስለሆነም እነርሱ ባለማወቅ ያደረሱትን ታላቅ ጥፋት ለመፍታት የሚችል ሌላ ኃይል የለም ብለው በማሰብ እጆቻቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ ወይም ደግሞ የስራ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባለመቻል በአቅመቢስነት መሳቂያ፣ ሰነፍ፣ የደከመ አቅመቢስ እና ተነሳሽነት የሌለው ሆነው በወራዳ ተግባራት ተፈርጅው ከመቀመጥ ምንም የጨመሩት ነገር የለም፡፡
[III] ፕሮጀክቱን ከማቀድ ጅምሮ እስከ ትግበራው ወቅት ጊዜ ድረስ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች አቅመ ቢሶች ነበሩ ወይም ደግሞ የባንኩን የፖሊሰ ሰነድ ተራ ቁጥር 4.10 [መመሪያዎች እና ፖሊሲዎች የባንኩ ፕሮግራም የሰዎችን ክብር ሙሉ በሙሉ እንዲያከብር፣ ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ የኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንዲያከብሩ የሚያረጋግጥ] የሚያስገድደውን ሰነድ ሆን ብለው የማያውቁ ደንቆሮዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እስከ አሁንም ድረስ በአኟክ ማህበረሰብ ላይ የደረሰውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት ተመጣጣኝ የሆነ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ ሁኔታውን እንደገና የማሻሻል እና ጉዳቱን የመቀነስ ስራ መስራት ይቻል ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች ተጠቃሚ ይሆናል የተባለውን ህዝብ በመሰብሰብ በጋራ ከህዝቡ ጋር መመካከር እና ወደፊት በዚህ ፕሮግራም ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ከሚባሉ ህዝቦች ጋር በመመካከር ባህሉን በማያዛባ መልኩ ጥቅሞቻቸውን ሊያስከብር የሚችል የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቋሚ ህዝቦችን ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው በማፈናቀል ከኖሩበት የተሻለ ጥቅም በሌለበት ሁኔታ ማንገላታት ተገቢ አይደለም፡፡
[IV] በኢትዮጵያ ያሉ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች ቆሎ አየቆረጠሙ መራመድ የማይችሉ ፍጡራን ናቸው፡፡ ቀኝ እጃቸው የግራ እጃቸው ምን እየሰራ እንደሆነ የሚያውቁ ናቸው ፡፡ የዓለም ባንክ የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያላገኙትን ማህበረሰቦች የኑሮ ሁኔታ ቀጣይነት ባለው መልኩ በማህበራዊ እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የመሰረታዊ ትምህርት፣ የጤና፣ ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ እና የህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ የጋምቤላ ህዝብ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ፕሮጀክት 3 የአቅም ግንባታ ስራ እንዲጠናከር፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ትክክለኛ የሆነ የገንዘብ አስተዳደር በየክልሎቹ እንዲኖር እና መሰረታዊ አገልግሎቶች ማለትም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ የውኃ አቅርቦት እና ንጽህና እንዲሁም የገጠር መንገዶች ተሟልተው እንዲቀርቡ ለማድረግ ነው፡፡
የባንኩ የስራ አስፈጻሚዎች በምቹ ወንበሮቻቸው ላይ ተንፈላስሰው በመቀመጥ ክትትል የማድረግ እና ሁለቱንም ፕሮግራሞች የማስተባበር ስራቸውን አልሰሩም፡፡ በዚህም መሰረት የአኟክ ማህበረሰብ ቅሬታውን እንዳቀረበው ሁሉ የጋምቤላ ህዝብ ከጉዳት እና ከአደጋ ላይ ተጥሎ ይገኛል፡፡ በሌላ አገላለጽ የባንኩ የስራ አስፈጻሚዎች ስራቸውን በአግባቡ ባለመስራታቸው ምክንያት የአኟክ ማህበረሰብ ለምነቱ ወደተሟጠጠ ጠፍ መሬት ላይ ተወስዶ እንዲሰፍር ተደርጓል፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ የውኃ ጉድጓዶች ወይም ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች የሌሉበት አዲስ መንደር በግዳጅ እንዲመሰርት ተደርጓል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥቂት የአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የአኟክ ማህበረሰብ አባላት እና ልጆቻቸው በመንደር ምስረታ ፕሮግራሙ ምክንያት በረኃብ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ሌሎቹ የግዳጅ የሰፈራ ፕሮግራሙን የተቃወሙትን የአኟክ ማህበረሰብ አባላት በቁጥጥር ስር በማዋል፣ የድብደባ፣ የስቃይ እና የግድያ ሰለባ ዒላማ እንዲሆኑ ተዳርገዋል፡፡ ይህ ድርጊት የጋምቤላ እና የዓለም ባንክ ከመሆኑ በስተቀር ጥንታዊ የሮማ ከተማ የሆነችውን የፖምፔ የእሳት ቃጠሎ እና እርባናየለሽ ድርጊትን ከመፈጸም የሚለየው ነገር የለም፡፡
በኢትዮጵያ ባሉ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጸሚዎች እጆች ላይ ደም አለ!
[V] በኢትዮጵያ በአኟክ ህዝብ ላይ የዓለም ባንክ ያደረሰውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለመደበቅ ሲባል ዓለም ባንክ እራሱ ጥፋተኝነቱ እንዳይተወቅ የዝምታ ሽረባ ዱለታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የጋራ ጉባኤ ተልዕኮ ዋና ዓላማው በፕሮጀክቱ ሁሉም አካሎች ላይ የሚታየውን መሻሻል ለመገምገም እና የትግበራ ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ መስከረም 2012 ለህዝቡ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ፕሮጀክት 3 ማስፈጸሚያ የሚውል 600 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል፡፡ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ፕሮጀክት 3 መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዓለም ባንክ ሶስት የጋራ ግምገማዎች ያደረገ ሲሆን በአኟክ ህዝቦች ላይ ስለደረሰው ጉዳት አንዳችም ቃል ትንፍሽ ሳይል አልፎታል፡፡ የዓለም ባንክ “የኢንቨስትመንት የማበደር ፖሊሲ (OP/BP 10.00)” ስለፖሊሲው፣ ስለአካሄድ ስርዓቱ፣ ስለፕሮጀክቱ አፈጻጸም እና ክትትል በተበዳሪው ወይም በፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች፣ ስለፕሮጀክቱ አፈጻጸም እና ስለስምምነቱ የተፈጻሚነት ደረጃ ዝርዝር የሆነ የፖሊሲውን መግለጫ ይሰጣል፡፡ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች በስራዎቻቸው ላይ ለጥ ብለው ተኝተዋል ወይም ደግሞ አውቀው ሆን ብለው ስለባንኩ የኢንቨስትመንት እና ክትትል ፖሊሲ ምንም አናውቅም በማለት አድፍጠዋል፡፡
[VI] በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች የባንኩ ገንዘብ በወረዳ ደረጃ ቁጥጥር ይደረግበታል ሲሉ ግልጽ የሆነ ውሸትን ዋሽተዋል እንዲሁም ታላቅ የልብ ወለድ ትረካን ተርከዋል፡፡ የዓለም ባንክ ሰነድ በተራ ቁጥር OMS 2.20 ላይ የተቀመጠው ባንኩ ከሁሉም ነገር በላይ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ተግባራት ከተበዳሪው ዓለም አቀፍ ስምምነት አንጻር አካባቢን፣ ጤናን፣ እና አጠቃላይ የህዝቦችን ደህንነት በሚያረጋግጥ መልኩ መታየት እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡ OP/BP 10.02 የሰነዱ ክፍል እንደሚያመላክተው በፕሮጀክት ትግበራ ወቅት ባንኩ የገንዘብ አጠቃቀሙን እና አያያዝ ሁኔታ እንዲሁም ያለው ገንዘብ በቂ መሆን አለመሆኑን መከታተል እና መገምገም እንዳለበት በግልጽ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የባንኩ ስራ አስፈጻሚዎች አቅመቢሶች ወይም ደግሞ ሆን ብለው ታላቅ ኃላፊነትን ይዘው ኃላፊነታቸውን ግን በአግባቡ ለመወጣት ግን ግድ የሌላቸው ደንታቢሶች ናቸው፡፡ ወረዳዎች ከክልሎች እና ከዞኖች በመቀጠል በሀገሪቱ ያልተማከለ አስተዳደራዊ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ወረዳዎች በጣም ጉልህ የሆነ የሙስና ወንጀል የሚፈጸምባቸው ማዕከላት ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለህወሀት 99.6 በመቶ የድምጽ ውጤት እንዲገኝ ያደረጉት የወረዳ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ያሉ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች የራሳቸው የሆነውን ስራ እና ሙያዊ ተግባራቸውን እርግፍ አድርገው ትተው በጭፍንነት ታማኝነት ለሌላቸው እና ስለገንዘብ አያያዝ እና አስተዳደር ምንም ዓነት እውቀት ለሌላቸው ለወረዳ ሙሰኛ ባለስልጣኖች ሰጥተው በህዝብ ስም ለህዝብ የመጣን የብድር ገንዘብ እንዲባክን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ (ምንድን ነበር የሚያስቡት? ያንን ጣያቄ እንዲጫር አድርግ!)
[VII] [ይህ ግኝት የገንዘብ ተጠያቂነት ጉዳይ እስከተነሳ ድረስ እጅግ በጣም የሚያስገርምና የሚያስደንቅ ነው፡፡] በኢትዮጵያ ያሉ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች የባንኩን ገንዘብ ከሙስና ለመከላከል የሰሩት አንዳችም ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው “በመጀመሪያ ብቁ ያልሆነ የፋይናንስ አደጋ“ የሚል ሀረግ የተጨመረው፡፡ የዓለም ባንክ OP/BP 10.00 እና የትንተና መሳሪያዎች (የህዝብ ወጭ እና የገንዘብ ተጠያቂነት) (ህወገተ) በተቀባይ ክልሎች የሚላከው ገንዘብ እንዳይባክን የተዘጋጀው፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች እና የትንተና መሳሪያዎች አጠቃላይ በሆነ መልኩ የሙስናን አደጋ ይከላከላሉ ባይባልም አጠቃላይ በሆነ መለኩ ግን ዕቅድ፣ ክትትል እና ግምገማዎች የሚካሄዱ ከሆነ በተቀባይ አገሮች ላይ አዎንታዊ የሆነ ውጤትን ያመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች ስለገንዘብ አደጋ የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ፕሮጀክት 3ን እንዳለ ለሙሰኞች እና ለዘራፊዎች ትተውታል!
ስለዓለም ባንክ የአሰራር ሁኔታ እና ቅዱስ ስላልሆነው ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች የልማት አጋርነት ቡድን እየተባለ ለሚጠራው መንግስታዊ ያልሆነ አካል አዲስ አይደለሁም፡፡ የእነዚህን አካላት ዘገባዎች አጥንቻለሁ፣ እናም ፖሊሲዎቻቸውን፣ የትግበራ ሰነዶቻቸውን፣ መመሪያዎችን እና ለህዝብ የሚሰጡ መግለጫዎችን እንዲሁም ሌሎችን ህትመቶች እስካሁን ድረስ አጥንቻለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር ስለፖሊሲዎቻቸው፣ ተሞክሯቸው እና በኢትዮጵያ እያከናወኗቸው ስላሉት ተግባራት ግንዛቤ አለኝ ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡
“በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የተለቀቀውን ባለ 417 ገጽ የዓለም ባንክን ዘገባ ከጸሀፊዎቹ በስተቀር ምናልባትም ከማንም በበለጠ ሁኔታ ለበርካታ ጊዜ ደግሜ እና ደጋግሜ ያነበብኩት እኔ እሆናለሁ የሚል ግምት አለኝ፡፡ በእርግጥ ያንን ዘገባ ለበርካታ ጊዜ አንብቤዋለሁ፣ እናም ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ለህዝብ ለመናገር ሀፍረት ይሰማኛል፡፡ ያንን ዘገባ በመጠቀም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የህወሀትን የሙስና ግዛት ለማጋለጥ በርካታ በሙስና ላይ ያነጣጠሩ ተችቶችን በማዘጋጅበት ጊዜ ተጠቅሜበታለሁ፡፡
የሙስና ዘገባ ማዘጋጀት ንጹህ አየር የመተንፈስ ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እቀበላለሁ፡፡ የዓለም ባንክ የሙስና ዘገባ እንደዚህ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጥልቀት፣ ወርድ እና ስፋት ያለው በሌሎች ሀገሮች ላይ እስከ አሁን ድረስ አላየሁም፡፡ አንድ ነገር ህልው ከሆነ ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን የሙስናን ጥልቀት እና ስፋት ጥልቀት ባለው ሁኔታ አጥንቶ በማቅረቡ እና የህወሀት የሙስና የግዛት አድማስ በመጋለጡ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፣ ከዚህም በላይ ይህንን ጥናት ያቀረበውን እና እውነታውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው ያደረገውን ዓለም ባንክን ከልብ አመስግኘ ነበር ፡፡ “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ የሚለው የዓለም ባንክ የጥናት ዘገባ የግልጽነት እና የተጠያቂነትን ጉዳይ አስመልክቶ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት እንደቻለ እምነት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ወይም በሌሎች ሀገሮች ያሉትን የባንኩን ፕሮግራሞችን የሚያስፈጽሙትን ሁሉንም የዓለም ባንክ ሰራተኞች የመክሰስ ዓላማ የለኝም፡፡ ጥቂት የሆኑ መልካም ስብዕናን የተላበሱ እና ስለኢትዮጵያ እውነቱን ብቻ የሚናገሩ እና በመሸበት ማደር የሚፈልጉ እውነተኛ እና ሀቀኛ የዓለም ባንክ ሙያተኞች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በዓለም ባንክ ውስጥ የሚገኙ ወልፍጋንግ ፌንግለር የተባሉት ታዋቂ የኢኮኖሚ ጠበብት አንዱ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ረኃብ እና የምግብ እህል እጥረት የለም በማለት ለመካድ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ ፌንግለር ግን ሽንጣቸውን ገትረው ፊትለፊት ተከራከሩት፡፡ ፌንግለር እንዲህ አሉ፣ “በአፍሪካ ቀንድ ያለው የረኃብ ቀውስ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ድርቆች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ፣ ሆኖም ግን ያንን ድርቅ ለማስወገድ በሚል ሌላ መጥፎ የሆነ እና ሌላ ድርቅ እና ረኃብን ሊያመጣ የሚችል ፖሊሲ ትነድፋላችሁ፡፡ በሌላ አባባል በኢትዮጵያ ለረሀብ በተደጋጋሚ መከሰት ትልቁ ችግር ድርቁ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር እጦት ነው::”
ሁልጊዜ ስለሚከሰተው ረኃብ ዓለም አቀፍ የእርዳታ እና የብዙህን አገሮች አንድ ዓይነት የቢሮክራሲያዊ ቋንቋን በመፍጠር ለማደናገሪያነት በመጠቀም ረሀብ የሚከሰተው በመልካም አስተዳደር እጦት እና ትክክለኛ ፖሊሲ ቀርጾ መንቀሳቀስ ሳይቻል በመቅረቱ የሚለውን ቸል በማለት ሌሎችን ፍሬከርስኪ ነገሮችን እያመጡ ህዝብን በማደናገር ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳሬክተር የሆኑት እንደ ጓንግ ዠ ቸን ረዥም ለብ ወለድ ትርኮችን መናገር የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2012 ቸን እንዲህ ብለው ነበር፣ “በኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት በመፈጠሩ ምክንያት የድህነት ደረጃውን እ.ኤ.አ በ2004/05 እና 2010/11 ባሉት ዓመታት መካከል ቀደም ከነበረበት ከ38.7 በመቶ ወደ 29.6 በመቶ በማውረድ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁለት ሚሊዮን ተኩል የሚሆኑ ዜጎች ከድህነት ተላቅቀዋል… መንግስት እ.ኤ.አ በ2014/15 ድህነትን ወደ 22.2 በመቶ ለማድረስ የያዘው ዕቀድ በጣም የተጋነነ ይመስላል፣ ሆኖም ግን ሊደረስበት የሚችል ነው፡፡“
እንደ አቡጀዴ ከመቀደድ በላይ የሚያሳፍር ምን ነገር ሊኖር ይችላል ወገኖቼ?!
በአሁኑ ጊዜ ያለንበት ዓመት 2015 ነው! ስለዚህ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ድህነት በ22.2 በመቶ ወርዶ ይታያልን!? አቤት ቅጥፈት! ወይ አይን ማውጣት!
ይገባኛል! በርግጥ ጉዳዩ ይገባኛል፡፡ የዓለም ባንክ ሰዎች ህወሀት እራሳቸውን ጥሩ አድርጎ እንዲስላቸው እነርሱ ደግሞ ህወሀትን ጥሩ ስዕል እንዳለው አድርገው ያቀርባሉ፡፡ የዓለም ባንክ ሰዎች ለህወሀት ትክክለኛውን ነገር ከተናገሩ ለእነርሱ ለእራሳቸውም ትክክለኛውን ነገር ይናገራሉ ማለት ነው፡፡ እነርሱ ስለህወሀት ስህተት ተናጋሪ ሆነው መቅረቡን አይፈልጉም ምክንያቱም እነርሱም የሚያደርጉትን ያውቃሉና፡፡ በዚህም መሰረት ህወሀትን ለመጠበቅ ሲሉ ህዝብ በረሀብ እያለቀ እና በድርቅ ሲጎዳ በዓይናቸው እየተመለከቱ ለዝምታ ጸጥታው ዱለታ ተባባሪ ሆነው ህሊናቸውን ሸጠው ይታያሉ፡፡
የህወሀት ሙስና፣ ኢኮኖሚውን ማስተዳደር ያለመቻል እና በጋምቤላ ክልል በሰው ልጆች ላይ እየፈጸሙ ያሉት የመብት ድፍጠጣ ተንሰራፍቶ እየታየ የዓለም ባንክ ሰዎች ዓይናቸውን ጨፍነው፣ ጆሯቸውን ደፍነው ሆኖም ግን አፋቸውን ከፍተው የቅጥፈት አፈታሪክ በማውራት በኢትዮጵያ ልብወለድ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳለ አድርገው ይነግሩናል፡፡
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2012 የዓለም ባንክ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ አህጉር የኢኮኖሚ ዕድገት ሁለት ጊዜ እጥፍ በሚሆን መልኩ እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ በየዓመቱ በአማካይ በ10.6 በመቶ የሀገር ውስጥ እድገት እያስመዘገበ የመጣ ሲሆን ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች 5.2 በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ትልቅ መሆኑን አንድ የዓለም ባንክ አዲስ ዘገባ ይፋ አድርጓል፡፡“
በእርግጥ የዓለም ባንክ የወያኔ ሸፍጥ እንደሆነ ያውቃል…! ከምንም ጥርጣሬ በላይ በሆነ መልኩ እንደሮኬት እየተተኮሰ የሚነገረን የቅጥፈት የኢኮኖሚ ዕድገት መጣኔ እና ሌሎችም ተመሳሳይ የሆኑ በህዝብ ላይ የሚደረጉ የቅጥፈት አሀዞች ሁሉ በመለስ ዜናዊ የቁጥር መመቀያ የስታቲስቲክስ ቢሮ እየተመረቱ እየወጡ ለዓለም ባንክ፣ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ለሌሎችም እንደ ሀገራዊ እና የውጭ ድርጅቶች እንደ በቀቀን እንዲደግሙት በጸጥታ እየወጡ የሚሰጡ እና በመጨረሻም መለስ ሁለተኛ ዘገባ አቅራቢ ሆኖ ባዶ የተፈበረከ ቁጥር እየጠራ እድገት ነው እያለ ከረባቱን እና መነጽሩን እያሳመረ ሲያሰለችን ኖሮ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ሲሰናበት አሁን ድግሞ የቅጥፈት ጓዶቹ የሆኑትን ደቀመዝሙሮቹን ተክቶልን አልፏል፡፡ “የመለስ ዜናዊ የቅጥፈት ኢኮኖሚክስ“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ ያቀረብኩትን ትንተና ከዓለም ባንክ ወይም ደግሞ ከሌላ በመምጣት ማንም ሙያው እና እውነታው አለኝ የሚል ቀርቦ ማስተባበል እንዲችል የመሞገቻ መድረክ ለመክፈት ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ ሙግቴንም ማንም ተቀበሎ ሊሞግተኝ አልቻለም። ሆኖም ዉቸት አንዴት ዉነትን ልሞግት ይችላል?
የሞተ እርዳታ/Dead Aid መጽሐፍ ደራሲ የሆነችው ዳምቢሳ ሞዮ በመጽሐፏ ላይ እንዲህ የሚል ጹሁፍ አስነብባለች፣ “…የዓለም ባንክ የጥናት ግኝት እንደሚያመለክተው 85 በመቶ የሚሆነው የልማት ዕርዳታ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ ነው የሚውለው፡፡ ለጋሽ ሀገሮች በጣም ሙሰኛ የሆኑ አገዛዞችን እየፈለፈሉ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 1996 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ የዓለም ባንክ 72 በመቶ የሆነው ዕርዳታ ለህጉ ለማይገዙ ሀገሮች የተሰጠ ነው፡፡ የለጋሽ ሀገሮችን መለገስ እንዲችሉ የሚቀርበው ዕርዳታ የመፈለግ ጥያቄ በምንም ዓይነት ሁኔታ እርካታን የሚያገኝበት ሆኖ አልተገኘም፡፡“
እ.ኤ.አ ህዳር 2014 በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን ዘገባ የሞዮን አባባል የሚደግፍ ንጹህ እና አወዛጋቢ ያልሆነ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ትንሽ ነገሮች ተለውጠዋል?!
የዓለም ባንክ አስመሳይነት በኢትዮጵያ፣
የዓለም ባንክ ተልዕኮ “በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ትውልድ የእድሜ ጣሪያ ስር አስከፊ የሆነውን ድህነትን ማጥፋት“ እና “የጋራ ብልጽግናን“ ማራመድ የሚል ነው፡፡ ባንኩ ይህንን ዓላማ ለማሳካት በሚል በኢትዮጵያ ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት ሲል የኢትዮጵያ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ የሚል ፕሮጀክት (መአጥፕ) ነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ እንደ የዓለም ባንክ ዘገባ ከሆነ መአጥፕ በኢትዮጵያ ውስጥ አራት ክፍሎች አሉት፡፡ እነርሱም፡
1ኛ) በክልል እና በአካባቢ መንግስታት የሚሰጡ መሰረታዊ አገልግቶችን የማከፋፈል ስራ መስራት እና መከታተል፣
2ኛ) ለመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አገልግሎት ንዑስ ፕሮግራሞች በጣም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለማቅረብ የሚያስችል አስተማማኝ የሆነ የገንዘብ እገዛ ማድረግ፣
3ኛ) በክልል፣ እና በከተማ አሰተዳደሮች፣ በወረዳ እና በንዑስ ወረዳ ደረጃ አጥጋቢ በሆነ መልኩ ግልጽነት እና የህዝብ በጀት አጠቃቀም ስርዓትን መጠበቅ እንዲሁም በበጀት ዝግጅት እና በአገልግሎት አቅርቦት ጊዜ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት እና ውክልናም እንዲኖራቸው ማድረግ፣ እና
4ኛ) የዜጎችን ድምጽ ለማጠናከር እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመውሰድ እንዲሁም ዜጎች በበጀት ዝግጅት ሂደት ላይ በንቃት መሳተፍ እንዲችሉ የተመረጡ አካሄዶችን በመውሰድ የናሙና ሙከራ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት፡፡
የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በኢትዮጵያ ለመአጥፕ ፕሮግራም እገዛ በማድረግ የ2 ቢሊዮን ዶላር ቃል ገብቶ እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ባንኩ ከፍተኛ የሆነ ማለትም 600 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጓል፡፡
እውነታው ግን የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች ተልዕኮ በአሳዛኝ ሁኔታ ከሽፏል፡፡ በአራቱ ክልሎች የሚካሄደውን የመአጥፕ የመንደር ምስረታ ፕሮጅከት 3 ዝርዝር የጉዳት ትንተና ሳይካሄድ በመቅረቱ ውድቀትን ተከናንበዋል፡፡ የባንኩን የድርጊት መርሀ ግብር እና መመሪያዎችን ሳይከተል የሚሰራ ስለሆነ ከባንኩ እምነት ውጭ ተጻራሪ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ስለሆነ ዓላማውን ስቷል፡፡ ባንኩ ፕሮግራሙን በሚተገብርበት ጊዜ ከአኟክ ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ መወያየት እና መመካከር ስላልቻለ በህዝቦች ላይ የሚመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ በመኖሩ ፕሮግራሙ ውድቀት ደርሶበታል፡፡ ስመአጥፕ ፕሮጀክት 3 እና ስለማህበረሰቡ የልማት ፕሮግራም ስለጉዳት ትንተና በሰነዱ ማዕቀፍ ላያ በተያዘው መሰረት ስላልተሰራ አቅመቢስ መሆናቸውን በግልጽ አመላክቷል፡፡ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚዎች ከአኟክ ማህበረሰብ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እና ጥብቅ ትስስር ካለው ከመሬት እና ከሌሎች ሀብቶች ከማግኘት አንጻር ስለህዝቡ የኑሩ መሻሻል ሁኔታ፣ ስለህዝቡ ደህንነት እና ስለመሰረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት ደንታ የላቸውም፡፡
በጋራ ግምገማቸው እና ፕሮጀክቱን በመተግበር ጊዜ ስለሚሰጡት እገዛ ዘገባዎች የይስሙላ እየቀባቡ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመስጠት ወይም አስፈላጊ ያልሆኑ እውነታዎች ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን በማጥፋት ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን እንዲጠፋ አድርገዋል፡፡ ብዙ የዕቅድ ስራዎችን፣ የክትትል ወይም የቁጥጥር ስራዎችን ባንኩ እየሰራ አይደለም፡፡ ሙያዊ የሆነ ስራቸውን እና ግዴታዎቻቸውን እርግፍ አድርገው በመተው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚካሄድ ፕሮግራም ማስፈጸሚያን ገንዘብ በሙስና እስከ አንገታቸው ድረስ ለተዘፈቁ የወረዳ ኃላፊዎች አስረክበዋል፡፡ እኔ ይኸ ጉዳይ በጣም ያሳስበኛል፣ ለምን እንደሆነ ለማወቅም ጉጉት ያድርብኛል፡፡ለመሆኑ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጸሚዎች በየዕለቱ ምን ሲሰሩ ነው የሚውሉት? (ነገስታታ ቀኑን ሙሉ ምን ይሰራልይ ብሎ መጠየቁ ይቀላል።)
ድምጼን ከፍ አድርጌ በመጮህ ምን ዓይነት ግራ የሚያጋባ መርሀግብር ነው የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በመተግበር ላይ ያለው?
እ.ኤ.አ ታህሳስ 2013 የዓለም ባንክ ቡድን ፕሬዚዳንት የሆኑት ጅምዮንግ ኪም እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮች ሙስና የህዝቦች ቁጥር አንድ ጠላት ነው… ሙስናን በምንም ዓይነት መንገድ ልንታገሰው አንችልም፣ እናም ባለን ስልጣን እና ኃይል ተጠቅመን ይህንን እኩይ ድርጊት ለማጥፋት ከእርሱ ጋር በጽናት መታገል አለብን… እያንዳንዷ ዶላር በሙስና የተዘፈቀ ባለስልጣን ወይም ደግሞ የቢዝነስ ሰው ወስዶ ከኪሱ የሚጨምራት ጤናዋን ለመጠበቅ ከተሰለፈችው ነፍሰጡር ሴት ወይም ደግሞ ትምህርትን ከምትፈልግ ልጃገረድ ወይም ልጅ፣ ወይም ውኃ፣ መንገድ፣ እና ትምህርት ቤቶችን ከሚፈልጉ ማህበረሰቦች ሰርቆ የሚውስዳት ናት፡፡ ከዓለምነው ግብ ለመድረስ እና አስከፊ የሆነውን ድህነት እ.ኤ.አ በ2030 ከዓለም ለማጥፋት እና የጋራ ብልጽግና ለማራመድ እያንዳንዷ ዶላር የወሳኝነት ሚና ትጫወታለች፡፡“
ኪም እ.ኤ.አ በ2015 ወደ ጋምቤላ መጥተው ወንድሞቼንና እህቶቼን ቢጎበኙ እና የእርሳቸው ባንክ ስንት ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ኪሊኒኮች፣ መንገድች እና የውኃ ግድጓዶች በ600 ሚሊዮን ዶላር እንደሰራላቸው ለወገኖቸ እንዲነግሯቸው ምኞቴ ነው፡፡
ድምጼን ከፍ አድርጌ በመጮህ: አዲስ አበባ ያለውን የዓለም ባንክ ሰራተኞች ቀኑን ሙሉ ሲያዛጉ ነው የሚዉሉት?!
(ይቀጥላል…)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም