ድል በትግል ( ሄኖክ የሺጥላ )
( ሄኖክ የሺጥላ )
ወያኔ በብረት ትግል ይወድቃል ። በብረት ትግል ብቻ አላልኩም ። ይሄማ ግብጽንም ፣ ቱንዝያንም ፣ ሊብያንም ፣ ቦርኪና ፋሶንም አረ እኛነታችንንም አለማወቅ ነው ። አሁን አሁን የምሰማው አስተያየት ግን የሚገርም ነው ። አባላትና ደጋፊዎች የኢትዮጵያ ነጻነት ከትጥቅ ትግል ውጪ ምንም ፋይዳ የሌለው አይነት ሆነው ተጠምቀዋል ። እንበልና ኢሳያስ አልፈልግም በቃ ውጡ ቢለን ባርያ ሆነን እንኖራለን ማለት ነው ? ይሄ ልክ አይመሰለኝም ።
አንድን ነገር እንደ አንድ ብቸኛ አማራጭ አድርገህ ስታየው ማምለክ ትጀምራለህ ። አሁን የማየው ደሞ እሱን ነው ። ለምሳሌ ኢሳያስ አማርኛ መነገር አይችልም ብዬ ጽፌ ነበር ። ጽሑፍን ካለመረዳት ሳይሆን ሆን ብሎ በማጣመም ” እንዴት ለምን በአማርኛ አልተናገረም ትላለህ ” የሚል አስተያየቶች ሰማሁ ። እንደዛ የሚል ነገር ከጽሑፌ ውስጥ መዞ አውጥቶ መውቀስ የቻለ ግን አንድም ሰው የለም ። ምክንያቱም ስላላልኩ ።
እኔ ያልኩት የኢሳያስ በ አማርኛ ቃለ መጠይቅ አለመስጠት ምክንያት ተደረጎ የቀረበልን ነገር እጅግ በጣም አሳፋሪ ነው ። እንደ ምክንያት ያንን ተቀብሎ ማቅረብ ሕዝቡን መናቅና ማስናቅ ነው ። ሲጀመር አላማው ምንድን ነው ? እንደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሣያስ አማርኛ ለምን እንደማይናገር ይጠፋዋል ወይ ። እኔ ያልኩት በመጀመሪያ ደረጃም ቢሆን ስለሱ አማርኛ መናገር እና አለማናገር ማወቅ አያስፈልገንም ። ግን እንደዚህ እወቁ ካላችሁ የምትሉን ነገር ውሃ አያነሳም ነው ። አሁንም እደግመዋለሁ በፈለገው መንገድ መናገር መብቱ ነው ። ምክንያቱ ግን አያገባኝም ። አይ ምክንያት ስላለው ነው ካልከኝ ግን ምክንያቱን ግራና ቀኝ ተመልክቼ ተአማኒ ነው ወይም አይደልም የማለት መብት ያለኝ መሰለኝ ። በተረፈ ግን አንድ ነገር በተነሳ ቁጥር ፣ አንድ ነገር በተጻፈ ቁጥር እሳቸው ይቀየማሉ ፣ ትግሉን ምን ይጠቅመዋል ምናምን እያልን የማይገናኙ ነገሮች ባናገናኝ መልካም ይመስለኛል ። በሃሳባችን እርግጠኞች ሳንሆን ፣ እንዴት ስለ አላማችን መናገር እንችላለን ።
ዔርትራ ውስጥ አንድ መንግስቱ የሚባል ሰው ( አርበኛ ) የዛሬ ዓመት ደውሎ አናግሮኝ ነበር ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም አገኘው ነበር ፣ ታዲያ ይህ ሰው አስመራ ቁጭ ብሎ የኤርትራ መንግስት ስህተቶች ሀ ፣ ለ ፣ ሐ እያለ ሲያወራ ተደመምኩ ። በሕይወት አለ ይሄንንም ያነበዋል
እንዲህ ነው ያለኝ
እኔ ” አረ እንዳይሰሙህ ?”
እሱ ” ይሰማሉ ! ያውቃሉ እንደዚህ እንደሚሰማኝ !” ሌላውን መናገር አግባብ አይደለም !
ስለዚህ እውነት እውነት እላችሁዋለሁ ኢሳያስ በኔ ጽሑፍ አይደልም ውስጡ ባሉ አርበኞች ቢሰደብ እንኩዋ ይሄ ሰው ካልሞተ ወይ ምናምን የሚል ሰው አይደለም ። ከምትገምቱት በላይ ማንን ማጥፋት ማንን መተው እንዳለበት በደንብ የሚያውቅ ሰው ነው ። ስለዚህ ስለ ኢሳያስ መናገርን ቀጥታ ከትግሉ ጋ ማያያዝ ዋጋ ያለው ጉዳይ አይመስለኝም ። ይልቁንም ይሄን የ አንወቀስም አንከሰስም የብረት አጥር ሰርተን ፣ አንድ ነገር በተጻፈ ቁጥር ከዳር ዳር ኢ- ምክንያታዊ በሆነ አስተያየት መጠመድ ልክ አይመስለኝም ።
ለምሳሌ እኔ ግንቦት ሰባት ልሁን፣ አልሁን በምን ታውቃለህ ? ጽሁፌ በእርግጥ ግንቦት ሰባትን ለማጥፋት ከማሰብ የመነጨ ከመሰለህ ተሳስተሃል ። ኢሳትን ለማጥላላት ከመሰለህ ተሳስተሃል ። ሶስት ዓመት ያልሞላት ልጅ አለችኝ ፣ አንድ ዓመት ያልሞላው ልጅ አለኝ ። ኢሳትና ግንቦት ሰባት ለኔ ከነሱ የተለዩ አይደሉም ። ልጆቼ ናቸው ። ያም ማለት ደሞ ሲያጠፉ የማይገሰጹ ፣ ሲሳሳቱ የማይታረሙ ልጆች እንዲኖሩኝ አልሻም ። በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ፖለቲከኞች ክደው ስላሳሳቱን የኔንም ጉዳይ እዛ ጫፍ ላይ ወስዶ መስጋት ስህተት አይደልም ። ግን ያን ያህል የወረደ ፣ ስብእና እንደሌለኝ ለመረዳት ብዙ መታተር አይኖርባችሁም ። አሁንም ወደፊትም ፣ የህዝቡን ህልውና የሚጋፋ ዜና ከሰማሁ ዝም አልልም ! አንድም ሰው ያንብበው እጽፋለሁ ። ነጻነት የሚጀምረው ከራስ ነውና ።