ለህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ፥ ለኢ/ብ/ምርጫ ቦርድ፥ እና ለሬድዮ ፋና
ከተክሌ በቀለ – የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር
ይህ የናንተ ስራ ዉጤት ነዉ። ትናንት የፈሰሰዉ ደም አዲሰ አይደለም። ለነፃነት ከሚንዠቀዠቀዉ የወገን ንፁህ ደም መካከል የሚደመር ሲሆን የምርጫን ቦርድና የሬድዮ ፋናን በአንድነት ፓርቲ ላይ የሚያደርሱትን የማፍረስና ማዳከም እኩይ ድርጊት ለመኮነን በወጡ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ይህ ጭካኔ ባልተገባ ነበር። ማንም በዚህ ድርጊት ሊደሰት እንደማይችል ብረዳም በትግራዋይ ደም መነገድ የለመዱቱ ግን ዛሬም በሰላም እንደሚተኙ ልቤ ያምናል። በትላንትናው እለት የስለሺ ሓጎስ፤ የአስራት አብረሃም፤ የልእልና ጉግሳ፤ የዳግማዊ ተሰማ… ደም ልክ እንደነ አሞራዉ፤ ወዲቐሺ፤ ብረሃነ መስቀል ረዳ፤ መንግስቱ ነዋይ፤ ባሮ ቱምሳ… ለፍትህ፤ ለነፃነትና ለተሻለ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እዉን መሆን ፈሷል። ልዩነቱ የሞትና የመቁሰል ሲሆን የትግል ስለቱም ነዉ። ይህ አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጸም ህዝብ አይቷል። ቴክኖሎጂ ባፈራዉ መቅረጸ-መሳሪያ ሁሉ ተቀርጿል፡፡የስርአቱ ጥቅመኞች ሱፍ ለብሰዉ፤ ክራባት አስረዉ በደሃዉ ህዝብ ስም በመለመን፤ የድሃዉን ጉሮሮ ዘግተዉ ለካድሬዎቻቸዉ መፈንጫ የሚያዉሉቱን እርዳታ የሚለግሱት የአዉሮፓ ህብረት፤ የእንግሊዝና የአሜሪካ ተወካዮች ተገኝተዉ ታዝበዋል፡፡ የ7 ወር እርጉዝን (እታች የምታዩዋት እጥፍ ወርቅ በልስቲ ትባላለች፡፡ የአንድነት ኣባል ናት፡፡) መናገር አቅቷት በሲቃ እንባዋ ሲፈስ ማየት እንደአመራር ሆኜ ሳስበዉ የተሰማኝን ስሜት መግለፅ ያቅተኛል። ሰዉ ባገሩ፤ ባገሩ ሰዎች እንዴት!! ለሰልፍ የወጡ ሴት የፓርቲ አመራርና አባላትን ሆድና ኩላሊት ለይቶ እንዲመቱ የሚያዘምት የኮማንዶና የደህንነት አካልን ሓየሎም አርኣያ ቢመለከት ምን ይል ነበር ይሆን? በአዉሮፓና በሰሜን አሜሪካ ሆናችሁ ለጥቅማችሁ አለያም ጠባብ ጎጠኝነት ተጠናዉቶኣችሁ ይህን ስርአት ለምትደግፉ ሁሉ ስርኣታችሁ ይህን ይመስላል። አንድ ቀን በታሪክና በህግ ትፈረዳላችሁ፡፡






