ሕወሃት በሚቀጥሉት ሁለት ስስት ቀናት አስቦ ይወስን – ግርማ ካሳ

ወደ አስራ አንድ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች አንድ ኮሚቴ አዋቀሩ። ይህ ኮሚቴ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ ዶር ሰለሞን ተርፋና ዶር ስብሐት የሚመራ ነበር። ይህ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የነበረው አለመረጋጋት አገሪቷን ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እንዳይወስዳት፣ በወቅቱ ይገዛ ከነበረው ከኢሰፓ/ደርግ እንዲሁም ከሽምቅ ተዋጊዎች (ሻእቢያና ወያኔ) የተወጣጣ ፣ የሽማግሌ ጊዚያዊ መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ነበር። “ይቅር ለ እግዚአብሄር “ በሚል መንፈስ መቀባበል እንዲመጣ ነበር ምሁራኑ የጠየቁት። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ወያኔ ከትግራይ ፣ ሻእቢያ ደግሞ ከከረን አላለፉም ነበር። ያ ማለት ወታደራዊ የበላይነት የነበረው ደርግ ነበር ማለት ነው። ምሁራኑ ይሄንን የእርቅ ሐሳብ ሲያቀርቡ የሽምቅ ተዋጊዎችን ጥንካሬ በማየት ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ደርግ በሕዝብ እየተተፋ መምጣቱን በማየታቸው፣ አገሪቷም እንደ ላይቤሪያና ሶማሊያ እንዳትሆን በመፍራት ነበር።

አርብ ከሰዓት በኋላ ነው። መስሪያ ቤቶች የተዘጉ ይመስላል። ሁሉም በየቤቱ ገብቷል። ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ለሕዝብ ንግግር ሊያደርጉ ነው። በፊታቸው ለነርሱም መዉጭ መንገድ፣ ለሽምቅ ተዋጊዎችም እንደዚሁ የሚበጅ፣ የመፍቴሄ ሀሳብ ቀርቧል። “ኮሎኔሉ ለዚህ ቀና ሐሳብ ምን ይመልሱ ይሆን?” ብለን መጠባበቅ ጀመርን። አራት ሰዓት ሙሉ ተናገሩ። “የአገር ጉዳይ የባልና የሚስት ጉዳይ አይደለም፣ በይቅር ለእግዚአብሄር የሚፈታው” ብለው እነ ፕሮፌሰር መስፍንን ወረፏቸው። አንድ የብነመር ሰው የሰጠኝ ብለው አንድ ጊራጌ መዘዙና አሳዩን። አይ ፉከራ !. አይ ጀብደኝነት !!!!!

ብዙም አልቆየም፣ ሰራዊቱ እየተከፋፈለ፣ እየከዳቸው ፣ ሽምቅ ተዋጊዎችም ተዋግተው ሳይሆን እንደ ማራቶን እየሮጡ፣ ጎንደር፣ ወሎ …እያሉ አዲስ አበባ አካባቢ ደረሱ። እንደ አጼ ቴዎድሮስ እስከመጨረሻው ጥይት ጠጥቼ እሞታለሁ ያሉት ኮሎኔሉ ፈረጠጡ። “ብሶት የወለደው የኢሕአዴግ ሰራዊት” ብለው ራሳቸውን የጠሩት ወያኔዎችም፣ ስኳር እየቃሙ በጢቢጢቢ ጫማ፣ አዲስ አበባን ተቆጣጠሩ። የኢሰፓና የደርግ አመራሮች ከያሉበት እንደ ጥንቸል ታድነው ተያዙ። የነበራቸውን ነገር በሙሉ አጡ። ወደ ወህኒ ተወረወሩ።፡አይወድቁ አወዳደቅ ወደቁ።

አሁን ሕወሃቶች፣ ተመሳሳይ ጀብደኝነት እያሳዩ ናቸው። ህዝብ እየተፋቸው ነው። ሕዝብ በደርግ ላይ ከነበረው የበለጠ ጥላቻ በነርሱ ላይ እያደረበት ነው። ብዙ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች አገዛዙ ወደ ብሄራዊ መግባባት እንዲመጣ እየመከሩና እየተማጸኑ ነው። ሆኖም ሕወሃቶች ልባቸው በጣም አብጧል። ማሰብ ተሰኗቸዋል። የትላንትናዉን ረስተዋል። ኢትዮጵያዉያን ወደ አመጽና ጦርነት እየገፋፏቸው ነው። “እስቲ ወንድ ከሆናችሁ ኑና በጦርነት ግጠሙን” እያሉ ነው። የሰላም በሮችን በሙሉ እየዘጉ ነው። ከነርሱ የተለያ ሐሳብ ያላቸው በሚቆጣጠሩት ሜዲያ፣ ትላንት ደርግ የፍየ ወጠጤ እያለ ሲፊከርና ሲያስፈራራ እንደነበረው፣ ዶኩመንተሪ ምጥርቅሾ እያሉ፣ እያስፈራሩ ነው። ዜጎች በአገራቸው ተሸማቀው እንዲኖሩ እያደረጉ ነው። በአጭሩ አባባል ዳግማዊ ግራዚያኒ እየሆኑ ነው።

በአገር ዉስጥ በምርጫ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ህዝቡ የፈለገውን እንዲሽርና እንዲሾም የሚደረግበት ሲስተም ከሌለ፣ ሌላው አማራጭ ጦርነትና አመጽ ነው። “የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመጽ በሮች ይከፈታሉ” እንዳለው አብርሃ ደስታ። በአገር ቤት ጠንካራ የሚባለውን የአንድነት ፓርቲ በማገድ፣ የፓርቲዉን ሕጋዊ ሰርተፊኬት፣ እነርሱ ራሳቸው ላደራጁት ተለጣፊ አንድነት ለመስጠት ወስነዋል የሚል መረጃ አለ። የአንድነት ፓርቲም ይሄን በመቃወም ሕገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት፣ እሁድ ሰልፍ ጠርቷል። ለአስተዳደሩ አሳዉቋል። ሆኖ አገዛዙ በሜዲያ መዛቱን ቀጥሏል። አንድነቶ ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ቢወስዱም፣ ዳኞች ፈርተው ጉዳዩን ለማያተ ፍቃደኛ አልሆኑም።

እንግዲህ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚደረገው ትግል ጫፍ ላይ ደርሷል። ሕወሃት ተጠንቆ እርምጃ እንዲወስድ እመክራለሁ። በአንድነት ፓርቲ ላይ ማናቸዉንም አይነት ሕግ ወጥና አምባገነናዊ እርምጃ ቢወስድ፣ አመራር አባላቱ ቢታሰሩ፣ በአገራች ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዳከተመ፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የመታገል በር ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋ የሚገልጽ አዋጅ እንዳወጀ ነው የሚቆጠረው።

ወያኔዎች አዲስ አበባ ሲቆጣጠሩ «ብሶት የወለደው የኢሕአዴግ ሰራዊት» ነበር ያሉት። ልክ እንደያኔውም ብሶት፣ የግፍ ቀንበር፣ ጭቃና፣ ባርነት እጅግ በጣም ብዙ ሰራዊቶችን ይፍጥራል። ስለዚህ ረጋ ብለው እንዲያስቡ የኮሎኔል መንግስቱ አይነት ስህተትን እንዳይሰሩ እመክራለሁ። ጀብደኝነት ለማንም አይጠቅምም። እነርሱም ጥብቆ እንደታጠቁት ሌላው ጥብቆ ታጥቋል። ለሁላችንም ሰላምና መግባባት ይበጀናል። እሁድ የአንድነት ሰልፍ በሰላም ተጠናቆ (ለምን ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ነውና) ምርጫ ቦርድም በአንድነት ላይ የከፈተውን ዘመቻ አቁሞ፣ ምርጫው ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን ሥራ ይጀመር። አለበለዚያ ግን እነርሱ ራሳቸው በለኮሱት እሳት መጥፊያችውን እንዳወጁ ይወቁ።