አንድነት እንዲጠፋ ሥርዓቱ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንዳሳለፈ አረጋግጠናል!! – ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በዚህ ዓመት በሚካሄደው ሃገራዊ ምርጫ ላይ የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ መጨረሻ እንዲሆን አደርጋለሁ ብሎ ቆርጦ በመነሳቱ ምክንያት ስርዓቱ ከምርጫው በፊት አንድነትን ለማጥፋት ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደወሰነበት በማያሻማ መልኩ ግልፅ ሆኗል። የአንድነት ፓርቲ አመራር፣ ብሄራዊ ምክር ቤቱ እና አባላቱ በምንም ሁኔታ ባልተከፋፈለበት ወቅት የተከፋፈለና ሁለት አንድነት ያለ በማስመስል በተላላኪዎቹ በእኩል ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ እንደተጠራ አስመስሎ በማወናበድ ላይ ይገኛል። አንድነት ለማፍረስ የስርዓቱ ዋነኛ መሳሪያ የሆነው ምርጫ ቦርድ ከአሁን በፊት ‹‹አቶ አየለ ስሜነህ የሚባል ሰው ሌላ ጉባኤ ስለጠራኝ›› ብሎ አንድነት በጠራው ጠቅላላ ጉባኤው ላይ አልገኝም ብሎ መቅረቱ የሚታወቅ ነው። አሁን አቶ አየለ ስሜነህ አንድነት ላይ የተደገሰውን የፖለቲካ ደባ ካረጋገጠ እና እየሄደበት ያለውን መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ከተረዳ በኋላ ወደ ፓርቲው በተመለሰበት ሁኔታም ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ለጥር 16/2007 እንዲካሄድ ምርጫ ቦርዱ እንዲያመቻች ተደርጎ አንድነትን ለተለጣፊዎቹ የማስተላለፉ ውንብድና በተሳካ ሁኔታ ለማስፈፀም ስርዓቱ ደፋ ቀና እያለ መሆኑ ለመረዳት ችለናል።
አንድነት ፓርቲ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ እንዲታይለት ቢጠይቅም በሚደንቅና በሚያሳዝን ሁኔታ ፍርድ ቤቱም ይህን ጉዳይ ማየት አልችልም የሚል ሀላፊነት የጎደለው እምቢተኝነት አሳይተዋል፤ ይህም የፍትህ ስርዓቱ ቀጭን ፖለቲካዊ ትዕዛዝ እየተሰጠው እንደሚሰራ ያረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር ስርዓቱ አንድነትን እስከዚህ ርቀት ሄዶ ለማጥፋት ቆርጦ እንደተነሳ የሚያረጋግጥ ነው። እንደ ምርጫ ቦርድ ሁሉ የፍትሕ ሥርዓቱም በድጋሚ ተፈትኖ ወድቋል፡፡ ሥርዓቱ ገለልተኛ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ተቋማት ሽባ እንዲሆኑ በማድረግ ሠላማዊና ሕጋዊ ትግል ፈተና ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡
አንድነት በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ለጥር 17 ታላላቅ ሰልፎችን ለማካሄድ በእንቅስቃሴ ላይ ነው የሚገኘው፤ ምንም ዓይነት ጠቅላላ ጉባኤ አልጠራም። በአንድነት ህገ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ እንዴት እንደሚጠራና ማን እንደሚጠራ በግልፅ የተቀመጠ ነገር ነው። ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ሙሉ ስልጣን ያለው የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት ሲሆን የኦዲትና ኢንስፔክሽን የፓርቲው አባላት በማንኛውም ምክንያት ጉባኤ እንዲጠራ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አንድ ሶስተኛ አስፈርመው ሲያቀርቡለትም እንደዚሁ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ጉባኤ እንዲጠራ ሊያዝ ይችላል። ብሄራዊ ምክር ቤቱ መጥራት ካልቻለም ራሱ የኦዲትና ኢንስፔክሽን በቀጥታ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ ይችላል። በአንድነት ህገ ደንብ መሰረት ከዚህ ውጪ የሚጠራ ጠቅላላ ጉባኤ ህገወጥ እንደሆነ እየታወቀ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ሰብስቦ በአንድነት ስም ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት መብቱም ስልጣኑም ሳይኖራቸው ጉባኤ የማድረግ ፍቃድና አዳራሽ ተስጥቷቸው ድራማው እንዲካሄድ እድል መሰጠቱ ሀገሪቷ በህግ ሳይሆን በውንብድና በስርዓት አልበኝነት ውስጥ እንዳለች የሚያሳይ ነው።
አንድነት ይህ ህገወጥ ድርጊት ሲፈፀም እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፤ ጉዳዩ ወደ ህዝቡ በመውሰድ ለውጥ ፈላጊው ህዝባችን ተቃውሞውን እንዲያሰማ በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ለጥር 17/2007 ዓም ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ጠርተዋል። በዚሁ የእሁዱ ሰልፍ የሚካሄዱባቸው ከተሞች አዲስ አበባ፣ ደብረማርቆስ፣ ጂንካ፣ ሸዋሮቢት እና በአርባ ምርጭ ከምባ ወረዳ ሲሆን በቀጣይነት ደግሞ በሌሎች የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ላይም ይካሄዳል። ይህን ህገወጥ የውንብድና አካሄድ እስኪቆም፤ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ ወደ ህጉ ማቀፍ ተመልሰው ይህን አፍራሽ እንቅስቃሴያቸውን እስኪያቆሙ ድረስ አንድነት ህዝባዊ ንቅናቄውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፤ በመሆኑም ለውጥ ፈላጊው ህዝባችን ይህ ጥሪ ተቀብሎ ከጎናችን በሙሉ ልብ እንዲቆምና የስርዓት ለውጥ በአጭር ጊዜ እንዲመጣ በማድረጉ ትግል ላይም በንቃት ይሳተፍ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ድል የህዝብ ነው!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አንድነት
ጥር 15 ቀን 2ዐዐ7 ዓም
አዲስ አበባ1779934_765373336880936_4788338795502799013_n

10947188_407060412791649_2770719439215446970_n