አንድነትና የስንብት ጉዞዉ….. -ከቶፋ ቆርቾ

የመሰንበቻዉ ጫጫታ ….

ሰሞኑን የሚሰማዉ ወሬ የኢትዮጲያን የዴሞክራሲያዊ ትንሳኤ እናይ ይሆናል ብለን ተስፋ ለምናደርግ የሰላማዊ ትግል ተስፈኞች ምኞታችንን የምድረ በዳ ጭኸት የሚያደርግ ነገር የመጣ አስመስሎታል….እዉነትም ያስፈራል ደግሞም ያሳዝናል፡፡ በተለይ ‘የሊብራል ዴሞክራሲ ተከታይ ነን’ እና ‘የግለሰብ መብት ቅድምያ ይሰጠዉ’ EPRDF…. ‘የኢትዮጵያ አንድነት እና የሉዓላዊነት መከበር ለድርድር መቅረብ የለበትም’ በሚለዉ አቛም ጽናታቸዉ በይበልጥ የሚታወቁት ሁለቱ ፓርቲዎች አንድነትና መኢአድ (መላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) ከዉስጥ በተፈጠረ ልዩነት በሚመስል… ነገር ግን ልዩነቱ እንዲሰፋና አደባባይ ወቶ የህዝብ መሳለቂያና መሳቀቅያ እንዲሆን በምንግስት ተቛማት እና ደገፊ ሚዲያዎች ይህን ያህል ጎልቶ መራገቡ ከበስተኋዋላ የነማን እጅ አለ ብሎ የሚያጠያይቅ አይደለም የኢትዮጲያ የመበላለትና የማባላለት (conspiracy) ፖለቲካ ለሚገባዉ ሁሉ፡፡ ይኼ ባይሆን ይህን ያህል የሚዲያ ዘመቻ መክፈት ባልተገባ ነበር፡፡ በተለይ ኢቢሲና ፋና ሬድዮ ቁጥር አንድ ስራቸዉ አድርገዉ የአንድ ወግን ደጋፊ መሆናቸዉን በሚያሳብቅ መልኩ ወገናዊነቱ ጎለቶ በታየበት ዘገባባ በተደጋጋሚ ማቅረባቸዉ የምር ለፓርቲዎቹ የዉስጥ ጉዳይ ተቆርቁረዉ እንዳልሆነ ማሰብ ከሚችል ከማንኛዉም ሰዉ የተሰወረ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ‘አይጥ ባጠፋ ዳዋ ተመታ’ አይነት ነገር ተተሮቶ ‘ምነዉ ተቀዋሚ ፓርቲዎቹ እርስ ብእርሳቸዉ በተሻኮቱ ኢህዴግ ስለምን ይወቀሳል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ መልሱ ቀላልና ግልፅ ነዉ፡፡ መንግስት የለሁበትም ካለ እጁን ያዉጣ፡፡ ጉዳዩን ለራሳቸዉ ለፓርቲዎቹና ለአባላቱ ትቶ እራሳቸዉ ችግራቸዉን ባሻቸዉ ምንገድ እንዲፈቱት ሊተዉላቸዉ ይገባል፡፡ ያልተስማሙ ከሆነም መሄድ የለባቸዉ ዳኝነት ወደሚያገኙበት ፍርድ ቤት እንጂ ‘እንዲ ተብለሃል… እነደዚህ ታምተሃል’ እያሉ የማዋጋት ስራን ወደሚሰራዉ ሬድዮ ፋና አይደለም፡፡ እንደ እብድ ገላጋይ ድንጋይ እያቀበሉ በነሱ ንትርክ የመገናኛ ብዙሃንን ወሬ ማደመቅ ባልተገባ ነበር፡፡ ገላጋይ ልሁን ካለም መንግስት ሊያደርገዉ የሚገባዉ ሚዛናዊ ሆኖ እንደ አባት አልያም እንደ ታላቅ ወንድም አንዱን ካንዱ ሳያበላልጥ አንተም ተዉ አንም ተዉ ማለት ሲሆን አንዱን አቀፎ ሌላዉ ላይ ሰይፍ ማሳረፍ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት አይኖረዉም፡፡ የፓርቲዎቹን የወስጥ ገበና ማጋለጡ የኢህዴግ የምረጡኝ ዘመቻዉ አንዱ ዘዴ  አድርጎ የወሰደዉ ከሆነ ከምር ይደብራል! ፍተሃዊ ስላልሆነ በጣጣጣጣ…..ም ያሳዝናል ከማለት በቀር ምን ይባል ይሆን?

የአማሳኞቹ ጉዞ እስከ…  

ለብዙዎች የአንድነት ምርጫ መሳተፍ አለመሳተፍ አነገብበጋቢ ጉዳይ አይደለም… ምርጫዉና ዉጤቱ ሳይተኛ የታለመ …ሰይታለም የተፈታ ለመሆኑ ነብይም ነጋሪም አያስፈልገዉም እና! ይልቅ የምር አንድነት እንደ ፓርቲ ሆኖ መዝለቁ ለብዙዎች ያሳስበቸዋል፡፡ ሌላ ‘አፈረሱሰት አሉ…..’ የቁጭት ዘፈን መስማት ያታክታል እና፡፡ ምርጫ ቦርድ ሰጠዉ የተባለዉ የጊዜ ገደብ አንድ ሳምንት ቀረዉ እያለ ወደታች መቁጠር (countdown) የጀመረዉ አካል (ለምሳሌ ሬድዮ ፋና እና መሰሎቹ) ምን ሊያደርግ ይችል ሆን ብሎ ብዙ መጔጔት አያስፈልግም፡፡ እነማን “በህጋዊነት” ካባ የፓርቲዉን ስም እንደ ሚረከቡት ፍንጭ ከወዲሁ እየታየም አይደል?

ከፓርቲዉ መዋቅር አኩረፈዉ የወጡት ከሳሽ …. አማሳኞች ይህን ያህል እርቀዉ የፓርቲያቸዉን ውስጠ ሚስጥር አዉጥተዉ በአደባበይ ማዝረክረካቸዉና ፓርቲዉን ማንኳሰሳቸዉ ወጪት ሰባሪ ብቻ ሳይሆን የሚያስበለቸዉ ሌላም ሌላም ነዉ፡፡ ነገ እነሱ ፓርቲዉን ቢመሩት የምር ህዝቡ ይቀበለናል ብለዉ ያስቡ ይሆን? ትላንት በደጉ ቀን አብረዉ ሲከኩ ሲያቦኩ የነበረዉን ነገር ሁሉ ዛሬ እኛ ፓርቲዉን ካልመራነዉ ብለዉ የዚህን ያህ ምሳር መወርወራቸዉ ‘እኔ ከሞትኩ’ አለች የሚበልላትን እንስሳ ከመሆን በምን ይተናነስ ይሆን? እንደዉ በግለሰቦች የግል ህይወት ገብቶ የትግል ባልደረቦቻቸዉን ለማንኳሰስ መሞከር ተገቢ ነዉን? ‘እከሌ እንትን አለዉ …እንትን ከፍቷል….’ እያለ አንድ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ግለሰብ የወረደ ንግግር በአደባባይ ያወራል? ከሆነስ በህግ አገባብ ጥያቄ ማንሳት ሲችል እንደ ምን ቀሊል ይሆናል? ሰዉ እንዴት እዳይታረቅ አደርጎስ በአደባባይ ሌላዉን እየዘለፈና እየዘረጠጠ በሌላ መልኩ የጋራ ምድረክ ፈጠረን የፓርቲያችንን ችግር እንፍታ ብሎ በአንድ አፍ ሁለት ቃል ይቀላምዳል? የሚገረም ዘመን ላይ ደርሰናል!

በሌላ በኩል ጽፈት ቤቱን የያዘዉ አመራር በሚሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫም ይሁን ቃለ ምልልስ ሲበዛ ስሜታዊነት ይታይበታል፡፡ በተለይ የተከበሩ አቶ ግርማ እና አቶ ስዩም የያዙትን እዉነት በሰከነ መንፈስ ለማስረዳትና ለማብራራት ከመሞከር ይልቅ ከአንድ ግለሰብ (የፋናዉ ብሩክ ከበደ) ጋር በእልህ እሰጣ ገባዉስጥ መገባታቸዉ ተገቢ አልነበረም፡፡ ፖለቲከኛ በሳል መሆን አለበት….ሚዛንኑን ጠብቆ ነጥብ ያስቆጥራል እንጂ እንደምን እንባ እየተናነቀዉ… አፉ እየተሳሰረ … በስሜት ጦፎ የሚናገረዉ ይጠፋወል? እንደኔ … እንደኔ እነ አቶ ግርማ ለሬዲዮ ፋና የሰጡት ቃለ ምልልስ የተገባ አልነበረም በቂርባቸዉ የሻል ነበር.….ለተቀናቃኞቻቸዉ የልብ ልብ ከመስጠት በቀር የነገሩን ቁምነገር አልነበርምና፡፡

ምርጫ ደረሰ….. ፓርቲ ፈረሰ

ጠንካራ የፖለቲካ ተቛማትን ለመገንባት የሚያስችል ምቹ ሁነታዎችን በመፍጠር የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እዉን ለማድረግ መደላደልን ቀመፍጠር ይልቅ ደካማና ተለጣፊ ምርጫ አዳማቂ ፓርቲዎችን መቀፍቀፍ አዋጭ ይሆናል ብሎ የመረጠዉ ገዢዉ ፓርቲ/መንግስት በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር በፓርቲዎች የዉስጥ አለመረጋጋትና ማዳከም የሚጠየቅበት ዘዴ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ምንግስት/አዉራዉ ፓርቲ ተቀዋሚ ፓርቲዎችን የመደገፍና የማጠናከር ሃላፊነት የለበትም ይባል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሰላመዊ የፖለቲካ መድረክ ጦር ሜዳ አይደለም፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ የመታገያ መድረክ ሁሉም ነገር በህግ መዕቀፍ ሊዳኝና ሊመራ የሚገባዉ ሲሆን ጉልበተኛዉ ጠላቴ የሚለዉን አካል ተዳክሞ ስላገኘዉ ብቻ ሊያጠፋዉ የመጨረሻዉን መት ለመምታት መሯሯጡ በምንም ሂሳብ በሰለጠነ የከተማ ፖለቲካ ጨዋታ ተቀባይነት ሊኖረዉ አይችልም፡፡ አንዱን በአንዱ ላይ አስነስቶ እርስ በርስ ማራኮት ዘዴ ሆኖ ተገኝቶ… እርስ በርስ እያጫረሱ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ነፃ ነኝ ለማት የሚደረገዉ ሙከራ የ”ፋራ ፉገራ” ከመሆን እንደማያለፍ ስናዉቀዉ ጭራሽ  “ሆደ ሰፊነት”… “የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት” ቅብርጥሶ… ቅብርጥሶ እየተባለ ታክስ ከፍለን በምናየዉ ቲቪ እጅጅ የሚል ድራማ ይሰራልናል፡፡  “ዴሞክራሲያዊ”….. “ነፃና ፍታሃዊ ምርጫ” አካሂዳለሁ እያለ ሲመሽ ሲነጋ የሚወተዉተዉ አካል የምር እንዳለሆነ ሁሉም ሆዱ የሚያዉቀዉ ቢሆንም እንደዉ ትንሽ ለማሰመሰል የሚያበቃ እንኳን ቀዳዳ ቢከፍት ብልጠት ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በግልፅ በሚያሳዉቅ መልኩ ድርጅቶቸን ለማዳከምና ብሎም ለማፍረስ ይህን ያህል ማይል መጔዙ የሚያስተዛዝብ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አያድንም፡፡ ደርጅቶቹ አያስፈልጉም ከተባለ በአንድ ብጣሽ ወረቀት መዝጋት ሲቻል (ለመንግስት ምን ይሳነዋል?) ይህን ያህል ጉንጭ ማልፋትና ህዝቡን ማደናቆር አያስፈልግም ነበር፡፡

በሃገራችን ስለ ዴሞክራሲ … ስለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሰል ነገሮች መወራት ከተጀመረበት የሃያ አራት ዓመታት ጉዞ ዉስጥ ለየት ብሎ የሚጠቀሰዉ ዘመን የ1997ቱ ሶስተኛዉ ሃገራዊ ምርጫ እንደነበር በርካቶች በአንድ ቃል ይስማሙበታል፡፡ በተለይ በቅድመ-ምርጫዉ የነበረዉ መነቃቃትና አንፃራዊ ነፃነት ፍጥሮት የነበረዉ መደላድል በኢትዮጵያ አማራጭ ሃይሎችን ለማየት አስችሎ ነበር፡፡ ያ-ጊዜ ታሪክ ሆኖ አስር ዓመታት አስቆጥሮ እነሆ ድሮ እያልን ልናዎራዉ ጀምረናል፡፡ በርግጥ ከዚያ ዘምን የተረፈን ትዝታዉና ሰቀቀኑ ብቻ ነዉ… ‘ነበር ባይሰበር’ የሚለዉ የብዙዎች ቁጭትን ጨምሮ፡፡ ታድያም የ97ቱ ገድል ሲታዎስ የወቀቱ ክሰተት የነበረዉ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ዛሬ ወዴት አለ? መልሱ መርጫዉ አፍሶታል ነዉ፡፡

በሚገረም አጋጣሚ ሃገራችን ፓርቲዎች የሚወለዱትም ሞተዉ የሚቀበሩትም የምርጫን መድረስና ማለፍ ተከትለዉ መሆኑን ስንታዘብ አረ ምን ጉድ ነዉ ማለታችን አይቀርም፡፡ ለዚህ አስረጂ የሚሆኑ በርካታ ምስሌዎችን መደረደር ይቻላል የቀርብ ትዉስታ ነዉና፡፡ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ አንጃ እየፈጠሩ የተሰነጠቁና ስምና አርማ ይዘዉ “ፓርቲ” ነን ብለዉ በየጎሬዉ የተወተፉ ፓርቲ መሰል ነገሮች ለመብዛታቸዉ ምስክር ቆጠራ አንወጣም፡፡ ይኄ ክስተት የማን ፍላጎት የማን የስራ ዉጤት እንደሆነም ከልባችን የማይጠፋ…ከአእምሯችን የማይሰወር የአደባባይ ሚስጢር ስለሆነ ብዙ አያባብልም፡፡

“ቅንጅት መንፈስ ነዉ” አይጠፋም ተብሎ በተነገረለት ትንቢት በርግጥም የትዝታዉ መንፈስ ከብዞዎች ጋር ለመዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ ወራሽ ነን ባሉት በአንድነትና መኢአድ ዉስጥ የመንፈሱ መናፍስት ይላወሱ እንደነበርም ምልክቶች ነበሩ፡፡ ይሆንና ይህን መንፈስ ለማጠፋት የ10 ዓመታት ጉዞ በኋላ የተሳካ የሚመስል ነገር ከሰሞኑ ታይቷል፡፡ በአስሩ ዓመታት ዉስጥ ብዙዎች ታስረዋል… በርካቶች ሃገር ጥለዉ ተሰደዋል….አንዳዶች ፖለቲካ ይብቃኝ በማለት ጡረታ ወተዉ ከድረጅቶቹ እየተገለሉ ሰንብተዋል፡፡ ከመሰንበቻዉ እንደሚታየዉ ከሆነ ግን የመንፈሱ መንፈስነት የሚያከተምበት ቀን የደረሰ ይመስላል፡፡ በሰላማዊ ሜዳ ንፁህ የፖለቲካ ትግል ተካሂዶ ለዉጥ ይመጣል ለምንል ማሳኞች ነገሩ ቀቢጠ ተስፋ ልሆን ይሆን እንዴ?

ጨለምተኛ አስባለም አላስባለም የአንድነት የሞት ጉዞ የተጀመረ ይመስላል…. ፍፃሜዉ አንድነትን ማፍረስ ነዉ አለያም ጥርስም ልብም የለለዉን አንድነትን በስም መፍጠር ይመስላል…. መጪዉ ሳምንት ምን ያሳየን ይሆን? የሆነዉ ሆኖ አንድነት የስንብት ጉዞ የጀመረ ይመስላል….. አይ የኛ ነገር!

ለሁሉም ቸር ያሰማን!

The post አንድነትና የስንብት ጉዞዉ….. -ከቶፋ ቆርቾ appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.