ማርቲን ሉተር ኪንግ፡ “መቼ ነው እናንተ እርካታን ልትጎናጸፉ የምትችሉት?”
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ (ማሉኪ) እ.ኤ.አ በ1963 “ህልም አለኝ“ በሚለው ትንቢታዊ ንግግራቸው ላይ እራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ለነበሩ የሲቪል መብቶች ተከራካሪ ወገኖች እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር፣ “መቼ ነው እናንተ እርካታን ልትጎናጸፉ የምትችሉት?“
ለዚህ ጥያቂያቸው ከተሰጡት ምላሾች መካከል እንዲህ የሚለው አንደኛው በጣም አስደማሚ ነበር፣ “ጥቁሮች ለመናገር ለሚዘገንነው እና እጅግ አስደንጋጭ ለሆነው የፖሊስ የጭካኔ እርምጃ ሰለባ መሆናቸው እስካልቆመ ድረስ በምንም ዓይነት መልኩ እርካታ ልንጎናጸፍ አንችልም፡፡“ ማሉኪ በተለይም ደግሞ በፖሊስ ኃላፊነት የጎደለው የጭካኔ የድብደባ ማዕበል በተደጋጋሚነት ሲሰቃዩ የቆዩትን እና በመሬት ላይ ለመዘረር ሲንገዳገዱ ይመለከቷቸው በነበሩ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ወገኖቻቸው የተለየ አጽንኦ በመስጠት ንግግር አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ላይ ፖሊስ ህግን በጣሰ መልኩ ሲያካሂድ የነበረው የጭካኔ የማሰቃየት እርምጃ እጅጉን ያሳስባቸው ነበር፡፡ እንደዚያ ዓይነቱን ጭካኔ የተሞላበት የፖሊስ የማሰቃየት እኩይ ድርጊት ማንም ሰው ሳይነግራቸው ወይም ደግሞ ሌላ የመረጃ ምንጭን ሳይጠቀሙ እራሳቸው በዓይናቸው በብሌኑ ይመለከቱ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 የበጋው ወራት በበርሚንገሀም አላባማ ከተማ በእብሪት በተሞላው እና ጽንፈኛ ዘረኛ በነበረው የፖሊስ ኮሚሽነር (አዛዥ)ኮነር ሰላማዊ ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር ምርጫ ለማድረግ በጠየቁ የጦር መሳሪያ ትጥቅ በሌላቸው ንጹሀን ዜጎች ላይ የጦርነት ውሾቹን በፍጥነት በማሰማራት ያደረሰው እልቂት እጅግ የሚዘገንን ነበር፡፡ ኮነር የፖሊስ ኃላፊዎቹን ሙሉ ትዕዛዝ በመስጠት በማያቋርጥ እና ጭካኔን በተመላበት ሁኔታ ጸረ ዘረኝነትን በመቃወም ሰላማዊ ተቃውሞ ባሰሙት ዜጎች ላይ ከፍተኛ ግፊት ያለው ውኃ በመርጨት፣ የፖሊስ ውሾችን በሰዎች ላይ በመልቀቅ፣ በፖሊስ ቆመጦች በመደብደብ እና አስለቃሽ ጋስ በመርጨት እና ሌሎችንም ተመሳሳይ የማሰቃያ ድርጊቶችን ሲያስፈጽም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሰላማዊ ተቃዋሚዎች በጽናት በመቆም “ምንም ይደረግ ምን ለማንም አንበገርም፣ ከዓላማችንም ንቅንቅ አንልም“ በማለት ጩኸታቸውን ያሰሙ ነበር፡፡
በርካታ የሆኑ የደቡብ የኃይማኖት ሰዎች የዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን የመምረጥ ህገመንግስታዊ መብት የመጠቀም እና ሰላማዊ የሆነ የተቃውሞ የትግል ስልት የማድረግ እንቅስቃሴዎችን በመቃወም አወንታዊ ምላሽ አልሰጡም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኮነር ህግ እና ስርዓትን ለማስከበር ሲባል የሚወስዳቸውን የማሰቃየት ዘዴዎች ደግፈው አጸደቁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ከበርሚንገሀም እስር ቤት በጻፉት ደብዳቤ የዘረኝነትን ኢፍትሀዊነት ለማጥፋት በጽናት ቆመው እየተጋሉት ያለውን ሊያስቀይር የማይችለውን የተሳሳተ እና የከሰረ ግልጽነት የጎደለውን አቋማቸውን በጽናት ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል፡፡ ማሉኪ በዚህ ደብዳቢያቸው እያወቁ በዘረኝነት የታወሩ መሰሪዎች የሚያደርጉትን የድንቁርና እና የአስመሳይነት እኩይ ተግባራት በማጋለጥ ከህዝቡ የህሊና ፍርድ አደባባይ ፊት እንዲቀርብ አድርገዋል፡፡ ማሉኪ “የበርሚንገሀም የፖሊስ ኃይል ስርዓት ለማስከበር እና ማንኛውንም የአመጽ እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚል የወሰደውን እርምጃ ያደንቁ የነበሩ ሰዎች በሌላው መልኩ በጥቁሮች ላይ የተለቀቁትን እና ጥርሶቻቸው በሰላማዊ አመጸኛ ጥቁሮቹ ሰዎች አካላት ላይ እንደ ቀስት የተሰኩትን የውሾቹን ጥርሶች ቢመለከቱ ኖሮ፣ በዚያ ከተማ እስር ቤት ላይ ጥቁሮችን ከሰውነት በወረደ መልኩ እንዴት ያሰቃዩአቸው እንደነበር ቢያዩ ኖሮ እና አሮጊት ሴቶችን እና ልጃገረዶችን እንዴት ይገፈትሯቸው እንደነበር እንዲሁም አሮጌት እና ወጣት ወንዶችን በጥፊ ሲያጠናግሯቸው እና በካልቾ ሲጠልዟቸው እንዲሁም እምነታችንን የሚገልጸውን መዝሙራችንን በጋራ በመዘመራችን ብቻ ምግብ እንዳናገኝ መከልከላችንን ቢያስተውሉ ኖሮ ድምዳሚያቸው ሁሉ የተለየ ይሆን ነበር” በማለት ሞግተዋል፡፡
እ.ኤ.አ ማርች 1965 የደም ጎርፍ በታየበት ዕለተ እሁድ (የቪዲዮ ምስሉን ለመመልከት እዚህ ጋ ይጫኑ) የአላባማ ግዛት በፈረስ ላይ የተቀመጡ ፖሊሶች እና ጥቁሮችን እንዲያጠቁ የተመረጡ የነጮች የዘረኛ ቡድን የፖሊስ አባላት በፈረስ ጀርባ ላይ እየተቀመጡ በጣም ኋላቀር እና ጭካኔነት በተመላበት መልኩ የሲቪል መብት ታጋዮችን በኢድመንድ ፔተስ ድልድይ አካባቢ የዓለም ህዝብ በታላቅ ድንጋጤ እየተመለከተው ያሰቃዩአቸው ነበር፡፡ ማክሰኞ ዕለት የተደረገውን ሁለተኛውን እና 2,500 ጥቁሮች የተሳተፉበትን የአመጽ እንቅስቃሴ የመሩት እራሳቸው ዶ/ር ኪንግ ነበሩ፡፡ የኮነር ከተማ ፖሊሶች አመጸኞች የአመጽ ድርጊቱን እንዲቀጥሉ እና ፊት ለፊት መጋፈጡን ለማስወገድ በሚል ከድልድዩ ዘወር አሉላቸው፡፡ ዶ/ር ኪንግ ፖሊሶችን ከዳር በኩል ሆነው ለጥቃት መዘጋጀታቸውን በተመለከቱ ጊዜ አጭር የሆነ የጸሎት ስነስርዓት እንዲካሄድ አደረጉ፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ እራስን በመቆጣጠር የሰላማዊ አመጽ መርሆዎችን በይፋ በመተግበር ዶ/ር ኪንግ ከወገኖቻቸው መካከል በመሆን አመጹን እየመሩ ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡ በቀናት ጊዜ ውስጥ ዶ/ር ኪንግ ወደ 25 ሺ የሚሆኑ ሰላማዊ አመጸኞችን ስኬታማ በሆነ መልኩ በመምራት ከሰላማ እስከ አላባማ ግዛት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ከዩኤስ ወታደራዊ ኃይል፣ የአልባማ የፌዴራል ብሄራዊ ጥበቃ ጦር፣ ከኤፍቢ ወኪሎች፣ እና ከፌዴራል ማርሻሎች ኃይል ከሚጠብቀው በሞንትጎመሪ የህግ ማውጫ ህንጻዎች ድረስ ያለውን 54 ማይሎች ርቀት ጉዞ አጠናቀቁ፡፡ እዚያ ከደረሱ በኋላ ዶ/ር ኪንግ እንዲህ የሚለውን ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ንግግር አሰሙ፣ “እኛ ልናሳካ የምንፈልገው ዋና ዓላማ ሰላሙ የተረጋጋ እና ለህሊናው የሚኖር ህብረተሰብ ለመፍጠር ነው…በአሁኑ ጊዜ እንዲህ የሚል ጥያቄ እንደምትጠይቁ በትክክል አውቃለሁ “ይህ ትግል ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል?“ እኔ የምሰጠው ምላሽ ግን ጊዜው ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም ወይም ደግሞ ሰዓቱ ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ዛሬ ከሰዓት በኋላ ልላችሁ እችላለሁ፣ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት እሩቅ አይሆንም…“
ሁሉም በኋላቀርነት እና በጭካኔ የተሞሉ የፖሊሲ መርሆዎች በሳልማ ከተማ የአመጸኞች ጉዞዎች ጊዜ ተዳስሰዋል ምክንያቱም በ15ኛው የዩኤስ ህገመንግስት ማሻሻያ ላይ ዜጎች ድምጽ የመስጠት መብት እንዳላቸው በግልጽ ተቀምጧለና፡፡ ፕሬዚዳንት ሊንደን ጆንሰን በኋላ እንዲህ የሚል አዋጅ አውጀዋል፣ “ድምጽ መስጠት የኢፍትሀዊነትን ቅስም ለመስበር እና ሰዎች ከሌሎች ሰዎች የተለየ አመለካከት ስላላቸው ብቻ አስሮ የያዘውን ግድግዳ ለመናድ ከሚያስችሉ እስከ አሁን ድረስ በሰው ልጆች ከተዘየዱት ነገሮች ሁሉ ጠንካራ የሆነ መሳሪያ ነው፡፡“
ዶ/ር ኪንግ የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት አካሄድ ሰዎችን በማሰቃየት አካላዊ ድብደባ ማካሄድ እና በሰዎች ህይወት ላይ እልቂትን በመፈጸም ጉዳይ ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ግንዛቤ ወስደዋል፡፡ ሆኖም ግን ዶ/ር ኪንግ ርህራሄ በሌላቸው የፖሊስ ኃይሎች የሚፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት የዘረኝነት የማሰቃየት ድርጊት የሚያስከትለውን ስነልቦናዊ ቀውስ ከምንም በላይ ተገንዝበውታል፡፡ የፖሊስ ኃይል የዘረኝነት መከፋፈያ መሳሪይ ህግ (ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ፍጻሜ በኋላ በደቡብ አሜሪካ እ.ኤ.አ እስከ 1965 ድረስ በተግባር ላይ ሲውል ለቆየው የዘር መድልኦ ህግ የተሰጠ መጠሪያ ስም) ዋና ማስፈጸሚያ መሳሪያ ነበር፡፡ የፖሊስ ኃይሉ የህዝብ ትምህርት ቤቶችን፣ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችን እና የመጓጓዣ አገልግሎቶችን፣ የምግብ ቤቶችን፣ የማረፊያ ቦታዎችን እና የመጠጥ ውኃ ማደያ ቦታዎችን ከማንኛውም ከሚሰነዘር ጥቃት ለመጠበቅ በመጀመሪያው እረድፍ ላይ የተቀመጡ የተደራጁ የህዝብ አገልጋዮች ናቸው፡፡
ዶ/ር ኪንግ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የዘረኝነት ጭካኒያዊ ድርጊት በመሰረታዊ ደረጃ በሰው ልጅ ስነልቦናዊ ባህሪያት ላይ ጥቁር ጠባሳ የሚጥል እና ውርደትን፣ ፍርኃትን እና ጥላቻን የሚያስከትል አደገኛ ሁኔታ እንደሆነ በውል ተገንዝበውታል፡፡ አካላዊ ቁስል እንዲያውም የጥይት ቁስል እንኳ ቢሆን በእርግጠኝነት መዳኑ ባይቀርም ጠባሳው ግን ለተፈጸመው ወንጀል መለያ ምልክት ሆኖ ይቀራል፡፡ ሆኖም ግን የስነልቦና ጥቃት የደረሰበት ሰው፣ “ድንገት እራሱን ለመናገር ወይም ደግሞ ለመጥራት የሚያስቸግሩ ቃላት ወይም ሀረጎች እንደዚሁም በቴሌቪዥን በተነገረ ወደ መዝናኛ ፓርክ መሄድ አትችይም ብሎ ለስድስት ዓመት ልጅ መግለጽ እና ይህ ለጥቁሮች አልተፈቀደም ተብሎ ሲነገራት እና በዓይኖቿ እንባዎቿ ሲያቀሩ መመልከት፣ እንደዚሁም በዚህ የዘረኝነት አካሄድ በህጻኗ አዕምሮ ውስጥ የበታችነት ስሜት ሲፈጠር ማየት እና በነጮች ላይ ሊቆጣጠሩት የማይችል የጥላቻ ስሜት ሲፈጠር መመልከትን ማስተናገድ ይሆናል…” የስነልቦና ጥቃት ሰለባ የሆነ ሰው እንዲህ የሚለውን በስህተት ላይ የተመሰረተ የአምስት ዓመት ህጻን ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል፣ “‘አባባ ነጭ ህዝቦች ጥቁሮችን ከነጮች የሚነጥሏቸው እና ጭካኔ የሚያደርጉባቸው ለምንድን ነው?‘”
ዶ/ር ኪንግ “ነጮች እና ጥቁሮች” የመጀመሪያ ስሙ “ጥቁር” የሆነ የመካከለኛ ስሙ ምንም ያህል በእድሜ ትልቅ ሰው ቢሆንም እንኳ የ“ልጅ” ዓይነት የመጠሪያ ማዕረግ እንደሚኖረው እና የመጨረሻ ስሙ ደግሞ “ጆን” በሚል የሚጠናቀቅ ከሆነ እና ለአንድ ሚስት ወይም ባል ወ/ሮ/አቶ (Mrs) የሚል የማዕረግ ስም እንደማይሰጥ እና ጥቁሮች ቀን በቀን እንደሚዋረዱ በውል ተገንዝበውታል፡፡ እንደዚሁም ዶ/ር ኪንግ ጭካኔ የተሞላበት የዘረኝነት የስነልቦና ቀውስ ምን ማለት እንደሆነ እና ይህንንም በማናቸውም ጊዜ ታግሎ ማሸነፍ እንዲሁም ማንም ከማንም እንደማይበልጥ ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ ተገንዝበውታል፡፡ ለዚህም ነው ጥቁር ህዝቦች ለለውጥ መዘግየት የለባችሁም በማለት ምክንያትን እንዲህ በሚል ያስቀመጡት፣ “የግፍ ዋንጫ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፣ ስለሆነም ሰዎች በተስፋ መቁረጥ ባህር ውስጥ ገብታችሁ መዳከር የለባችሁም፡፡“
ዶ/ር ኪንግ ብዛት ያለው የፍቅር መድኃኒት በመርፌ መውጋት እስካልተቻለ ድረስ የወንዶች እና የሴቶች የክብር የስነልቦና ስብራት ሊፈወስ እንደማይችል በውል አጢነውታል፡፡ ገጣሚ የሆኑት ላንግሰተን ሁግ እንዳሉት ከፍቅር ውጭ የዘረኝነት የስነ ልቦና ቀውስ “እንደ ቁስል ይጠነባል-/ እንደገናም ይቀጥላል/…/… ታላቅ ክብደት እንደተጫነ ነገር ይለነበጣል… እናም በመጨረሻ … ይፈነዳል…“
የጸረ ዘረኝነትን ባሩድ ክብሪት ሆና በመጀመሪያ ያቀጣጠለችው በሙያዋ የልብስ ስፌት ሙያ የነበራት የ42 ዓመት ጎልማሳ የሆነችው በስም ሮዛ ፓርክስ የተባለች አቅም የሌላት ደካማ ሴት ነበረች፡፡ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 1/1955 ፓርክስ የአውቶብስ የጉዞ አግልግሎት ለማግኘት ተሰልፋ በነበረበት ወቅት የተከሰተባትን የዘረኝነት ስነልቦናዊ ቀውስ የጭቃ ጅራፍ ከዚህ በኋላ መታገስ እንደማትችል በተግባር አሳየች፡፡ በየዕለቱ የሚፈጸምባትን ውርደት፣ ክብረነክ ነገር እና በአውቶብስ የጉዞ አግለግሎት ላይ እየተደረገ ያለውን አድልኦ ለማስወገድ በጽናት መቆሟን አስመስክራለች፡፡ ከአውቶብሱ የፊት ለፊት መቀመጫ እረድፍ ላይ ለመቀመጥ የመሳፈሪያ ቲኬት ስትቆርጥ ዓላማዋ በዚያው በተራዋ መሰረት ከፊት ወንበር ላይ ለመቀመጥ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፓርክስ በአውቶብሱ ሾፌር አማካይነት ከአውቶብሱ ኋላ ሄዳ እንድትቀመጥ የነገራትን ትዕዛዝ በመቃወም መሰረታዊ የሆነ ተቃውሞዋን በማንሳት ለዚህ ዓላማዋም በጽናት እንደምትቆም እና እንደማታፈገፍግ ግልጽ አደረገች፡፡ ፖሊስ ወዲያውኑ ከመቅጽበት ፓርክስን በቁጥጥር ስር በማዋል ወስዶ ከእስር ቤት አስገባት፡፡
“ሁከት ያልተሰሙ ድምጾች የመግባቢያ ቋንቋ ነው፡፡” ማሉኪ
ዶ/ር ኪንግ እንዲህ በማለት ለአንድ ጋዜጠኛ ተናግረው ነበር፣ “ሁከት ያልተሰሙ ድምጾች የመግባቢያ ቋንቋ ነው፡፡ እናም አሜሪካ ለመስማት የተሳናት ነገር ምንድን ነው? ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የደኃ ጥቁሮች የኢኮኖሚ ዕድል አስከፊ በሆነ ሁኔታ እየተበላሸ መጥቷል፡፡”
ያ ሁሉ ነገር ምንም እንዳልሆነ ነበር የተወሰደው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ በፖሊሶች ቆመጥ እንደ እባብ እየተቀጠቀጡ ሲጠወልጉ የጥቁር ልጆቿን ጩኸት እና ስቅስቅ የሚል ለቅሶ ማዳመጥ አልቻለችም፡፡ በየጎዳናው በአደባባይ ህይወት አልባ ለሆኑ በትከሻቸው በርካታ ትላልቅ ዱላዎችን የተሸከሙ የፖሊስ የጭካኔ ሰለባ ለሆኑ ምህረት እንዲያደርጉላቸው የሚጠይቁትን ጥቁር ወጣት ዜጎቿ የሰቆቃ ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች፡፡
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካ አስከፊ “የዘር ሁከቶች” መነሻቸው ጭካኔ የተሞላበት የፖሊስ ድርጊት ነው፡፡ (እንደዚህ ያሉት አለመረጋጋቶች ለምን “የዘር ሁከት” እንደሚባሉ በእርግጠኝነት አላውቅም፡፡ በእርግጥ “የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ድርጊት ሁከቶች” ቢባሉ የበለጠ ተስማሚ ይሆናል፡፡)
እ.ኤ.አ ጁላይ 1964 “በኒዮርክ በሀርለም ከተማ የዘር ሁከት” በሚል የተፈጠረው ሁከት የ15 ዓመት እድሜ ያለውን አፍሪካ አሜሪካዊ ልጅ የልጁ ጓደኞች እና ሌሎች በርካታ ምስክሮች ባሉበት በአንድ የፖሊስ ሌውተናንት መኮነን በጥይት መገደሉን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች በኒዮርክ ከተማ በሀርለም እና በቤድፎርድ ስቱቬሳንት አካባቢዎች ለሳምንት ያህል በዘለቀው ሁከት አንድ ሰው ሲሞት 118 ሰዎች ቁስለኛ እና ከ450 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በከፍተኛ የዘረፋ ቅሌት ተብሎ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር፡፡
የ ”ሀርለም ሁከቶች” ሌሎች ሁከቶችን ፈጠሩ፡፡ እ.ኤ.አ ጁላይ 1964 በኒዮርክ በሮቸስተር ከተማ የተካሄደው የዘር ሁከት የዚያች ከተማ ፖሊሶች የ19 ዓመት እድሜ ያለውን የአፍሪካ አሜሪካዊ ወጣት በመንገድ ላይ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ሙከራ ባደረጉበት ወቅት የተፈጠረ ነበር፡፡ በዚያች ከተማ የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በአፍሪካ አሜሪካውያን ማህበረሰብ ላይ እየተካሄደ ነው የሚለው ሽክሹክታ እንደተሰማ ማህበረሰቡ ንዴት በተቀላቀለበት መልኩ ቁጣውን ገልጿል፡፡ በተከታዩ ሁከት በርካታ የሆኑ ሰዎች ተገድለዋል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል፣ እንደዚሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ አመጸኞች ንብረትን በማውደም በሚል ምክንያት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡
እ.ኤ.አ ኦገስት 1964 በተከሰተው “የፊላደልፊያ የዘር ሁከት” ፖሊስ ለበርካታ ጊዚያት ሲያካሂደው ከነበረው ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ረገጣ በኋላ ነበር ሁከቱ በግብታዊነት ሊፈነዳ የቻለው፡፡ በርካታ ቀናትን በወሰደው በዚያ ሁከት 341 ሰዎች ቁስለኛ፣ 774 ደግሞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በ225 መጋዘኖች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ደግሞ በዚያ ረዥም ጊዜ በወሰዱ ሁከቶች ወቅት ወድመዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በኒው ጀርሲ እና በችጋጎ የተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ የሆኑ የአመጽ ሁከቶች ተካሂደዋል፡፡
እ.ኤ.አ ኦገስት 1965 ሁለት የነጭ ፖሊሶች በጥቁር ሞተረኛ ከተገፉ በኋላ “የዋትስ ሁከት” ወይም ደግሞ “የዋትስ አመጽ” የሚል ሁከት ወዲያውኑ ተከስቷል፡፡ የተቆጡ የማህበረሰቡ አባላት ለሳምንት ያህል በአካባቢው የዘለቀውን አመጽ ተቀላቅለዋል፡፡ በመጨረሻም 34 ሰዎች የተገደሉ፣ 1,032 ደግሞ ቁስለኛ፣ እንደዚሁም 3,438 በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን 40 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
እ.ኤ.አ በ1967 “የዴትሮት ሁከት” የተባለው አመጽ ፖሊስ በአንድ ፈቃድ ባላወጣ የህግ ባለሙያ ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጉዳት ሰበብ ፖሊሱ በርካታ አፍሪካዊ አሜሪካውያንን ገድሏል የሚል ሹክሹክታ በመሰራጨቱ የተከሰተ ሁከት ነበር፡፡ ያ ሁከት ወደ አንድ ሳምንት ያህል ጊዜ የወሰደ ሲሆን እንደ ታይም መጸሔት ዘገባ ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሞት እና ታላቅ ወጭን የጠየቀ ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 ረዥም ጊዜ በወሰደው ሞቃታማ የበጋ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ወደ 159 የሚሆኑ ሁከቶች ተከስተዋል፡፡
የሲቪል አመጾችን በተመለከተ እ.ኤ.አ የ1967 የተፈጸሙ ሁከቶችን መንስኤ እንዲያጣራ እና ለወደፊቱም ሊያገለግሉ የሚችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችን መቅረብ የሚችል ብሔራዊ የሲቪል አመጾች አማካሪ ኮሚሽን/ National Advisory Commission on Civil Disorders የተባለ አካል በፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ተቋቋመ፡፡ የዘገባው ዋነኛ መልዕክት እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠ፣ “ሀገራችን አንድ ጥቁር፣ ሌላ ደግሞ ነጭ ማህበረሰብን ለየብቻ የምታስተናግድ እና አኩልነት የራቃት ሆናለች፡፡“ ዘገባው በአሜሪካ በከተሞች አካባቢ ለሚነሳው ሁከት ዋነኛ መንስኤ የነጮች ዘረኝነት መሆኑን በመጠቆም ጣቱን በዚሁ እኩይ ምግባር ላይ አነጣጥሯል፡፡ ዘገባው ከበርካታዎቹ መካከል ከተለያዩ በርካታ ማህበረሰቦች የተውጣጡ እና መርህን የሚከተሉ እውነተኛ የፖሊስ ኃይል መመልመል እንዳለበት በመፍትሄ ሀሳብነት አቅርበዋል፡፡
የፖሊስ ጭካኔነት የተሞላበት የሰብአዊ መበት ረገጣ ሁከት የክብሪት ጭረቶች እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የመጀመሪያዎቹ እና በ1970ዎቹ ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች ቀጥለው ቆይተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1968 በደቡብ ካሮላይና ዩኒቨርስቲ ውስጥ በአንድ የተማሪዎች የመረብ ኳስ ጨዋታ ውድድር ጊዜ በሰው ዘር የቆዳ ልዩነት ላይ ባነጣጠረ መልኩ ቡድኖች መከፈል የለባቸውም በሚል በተከሰተው እና የኦራንጅበርግ እልቂት (በደቡብ ካሮሊና በኦራንጅበርግ ከተማ) እየተባለ የሚጠራው ሁከት ተፈጠረ፡፡ የደቡብ ካሮላይና አውራ መንገድ ጠባቂ ፖሊሶች በአፍሪካ አሜሪካውያን ተማሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈት 3 ተማሪዎችን የገደሉ ሲሆን 27 ደግሞ ቁስለኛ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ያ ጊዜ ፖሊስ በተማሪዎች ላይ በአሜሪካ የከፍተኛ ትምህርት ግቢ ውስጥ ተኩስ ሲከፍት እ.ኤ.አ በሜይ 1970 ከሁለት ዓመታት በኋላ ከተደረገው ከኬንት ስቴት ዩኒቨርስቲ ግድያዎች በፊት በታሪክ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ በፖሊስ የሚካሄዱት ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ከአጉስታ ጆርጅያ እስከ ጃክሰን ምሲሲፒ ከተሞች ድረስ የተካተቱ ሆነው አልፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 ሌላ ከፍተኛ የሆነ ሁከት የነጻነት ከተማ እየተባለች በምትጠራው በሚያሚ እና አካባቢዋ አራት የፖሊስ ኃላፊዎች በተጠረጠሩበት በአንድ የአፍሪካ አሜሪካዊ ግድያ ወንጀል ነጻ ናቸው ተብለው ከተለቀቁ በኋላ ተከሰተ፡፡ ከሶስት ቀናት የሁከት ጊዜ በኋላ 18 ሰዎች ተገድለዋል፣ በርካታዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፡፡
እ.ኤ.አ በኤፕሪል 1992 ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ በ1991 ሮድነይ ኪንግ በተባለ ሰው ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩትን አራት የፖሊስ ኃላፊዎችን ከጥፋተኝነት ነጻ አድርጎ ከለቀቀ በኋላ በሎስ አንጀለስ መጠነ ሰፊ የሆነ ሁከት ተፈጠረ፡፡ በዚህ ሁከት 55 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 2,000 የሚሆኑት ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ እንደዚሁም በተለያዩ ቀናት በተካሄዱት ሁከቶች 10 ሺ የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በሎስ አንጀለስ አካባቢ በሚገኙ ከ1,000 በላይ በሚሆኑ ህንጻዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ግምቱ 1 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ነበር፡፡
“የፖሊስ ሁከት?“
እ.ኤ.አ የ1968 የዴሞክራሲያዊ ብሄራዊ ስምምነት/Democratic National Convention ፕሬዚዳንት ለመጠቆም ታላቅ የሆነ የፖለቲካ የትግል አውድማ መድረክ ሆኖ ነበር፡፡ በርካታ የሆኑ ከተለመደው ባህል ውጭ የሆኑ ቡድኖች ያንን ስምምነት ለማቃወስ እራሳቸውን በማደራጀት ተንቀሳቀሱ፡፡ የችጋጎ የህግ እና ስርዓት ከንቲባ የነበሩት ሪቻርድ ዳሌይ ህግን እና ስርዓትን ለማስከበር በሚል በአመጹት ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ለፖሊሶች ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ያ ድርጊት የመንገዶች ላይ ጦርነቶች እንዲካሄዱ በሩን ወለል አድርጎ ከፈተ፡፡
የጭጋጎ ጥናት ቡድንን እንዲመሩ እና በዴሞክራሲያዊ ብሄራዊ ስምምነት ጊዜ የተፈጠረውን ህገወጥ ድርጊት መነሻ እና የመከላከያ ስልቱን በመመርመር ዘገባ እንዲያቀርቡ የኢሊኖይስ ግዛት የህግ ባለሙያ እና የፖለቲካ ሰው የሆኑት ዳንኤል ዋከር በቡድን መሪነት በብሄራዊ ኮሚሽኑ ተሾሙ፡፡ የዋከር ዘገባ (“የግጭት መብቶች“) እንደሚያመላክቱት አማጺዎች ሆን ብለው ፖሊስን አስፈራርተዋል፣ እናም ፖሊስ እርምጃ እንዲወስድ ገፋፍተዋል የሚል አወዛጋቢ የድምዳሜ ዘገባ በማቅረቡ ፖሊስ አጻፋውን ለመመለስ ሲል በአማጺያኑ እና በህገወጦች ላይ የእሩምታ ተኩስ ከፍቷል የሚል ዘገባ አቅርቧል፡፡ ዘገባው በማከልም ፖሊሶች ሁከትን ሲፈጥሩ የህግ አስፈጻሚ አካሎች በቸልታ ማየት አልነበረባቸውም በማለት ከሷቸዋል፡፡ ዘገባው በርካታ የሆኑ የፖሊስ ኃላፊዎች ወንጀሎችን የፈጸሙ መሆናቸው እየታወቀ እና ባለስልጣኖች ለህግ አቅርበው እንዲቀጡ አለማድረጋቸውን አውግዘው ወይም ደግሞ ፖሊሶቹ ስነስርዓት እንዲይዙ አለማድረጋቸውን በዘገባው አካትተው አቅርበዋል፡፡ ዘገባው በአጭሩ እንዲህ የሚል ነበር፡
…ያ የተወሰደው የፖሊስ የኃይል እርምጃ እውነታው ሲታይ በጣም አስደንጋጭነቱ የበለጠ የሚጎላው ምንም ዓይነት ህግ ባልጣሱ ሰዎች ላይ፣ ትዕዛዝ እና ስርዓት አናከብርም ባላሉት ላይ፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት የማስፈራራት ድርጊት ባልፈጸሙት ዜጎች ላይ የመፈጸሙ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች፣ ሰላማዊ አመጸኞች፣ ተመልካቾች እና በአካባቢው ኗሪ ሆነው በመንገድ ላይ ሲያልፉ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ወይም ደግሞ ግጭቱ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ይኖሩ በነበሩ ሰዎች ላይ ነው፡፡
ሁኔታውን ለመዘገብ በዚያ የነበሩ ጋዜጠኞች እና ክስተቱን በካሜራዎቻቸው ለመቅረጽ ሲሞክኑ በነበሩት ፍቶ አንሽዎች ላይ አንጠርጥረው እንዲወጡ በማድረግ አደጋ አድረሰውባቸዋል፣ በመሳሪያዎቻቸው ላይም ሆን ብለው አቅደው ጉዳት አድርሰዋል፡፡ መሰረታዊ የሆኑ የፖሊስ ስልጠናዎች ተዘለዋል፣ እናም የፖሊስ ኃላፊዎች አብዛኛውን ጊዜ የእራሳቸውን ሰዎች መቆጣጠር አልቻሉም ነበር፡፡ አንድ የፖሊስ ኃላፊ በትክክል እንዳስቀመጠው፣ “የተፈጸሙት ድርጊቶች ሁሉ ከፖሊስ ስራ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም“…
እንደ ህግ ባለሙያ እ.ኤ.አ በ2014 በዩናይትድ ስቴትስ በፖሊስ የተፈጸሙት ጥቂት ክስተቶች ትክክለኛ በሆነ መልኩ “የፖሊስ ሁከቶች” ናቸው ብሎ ለመመደብ የሚቻል አይሆንም ነበርን? ኤሪክ ጋርነር በካሊፎርኒያ (በኒዮርክ ሳይሆን) በፖሊስ ኃላፊዎች እጅ መገደሉ እና በእርሱ ግድያ እጃቸው ያለበት “በፖሊስ ሁከት” ወንጀል ቀርበው አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆን አልነበረባቸውምን?
እንደካሊፎርኒያ የወንጀለኛ መቅጫ ክፍል 404 “ማንኛውንም ዓይነት ኃይል ወይም ደግሞ የአመጽ ድርጊት መጠቀም፣ የህዝቡን ሰላም ማናጋት፣ ወይም ደግሞ ኃይል ወይም አመጽ ለማካሄድ ማስፈራራት፣ በሁለት ወይም ከሁለት በላይ በአንድነት ሆነው ከህግ አግባብ ውጭ ወዲያውኑ ግድያ ቢፈጽሙ ያ ድርጊት ሁከት ነው፡፡“ እነዚያ ኃላፊዎች በካሊፎርኒያ የሚገኙ ቢሆን እና ምክንያታዊ ባልሆነ እና ከህግ አግባብ ውጭ ህገወጥ በሆነ ተግብራት ላይ ተሳታፊ ሆነው ቢገኙ ኖሮ ለምሳሌ ያህልም ህገወጥ በሆነ መልኩ የሰውን ጉሮሮ አንቆ መግደል፣ እውን በእርግጠኝነት የሰው ህይወት አጥፍተዋል በማለት በፖሊስ ሁከት ክስ ሊመሰርትባቸው ይችል ነበርን?
የባራክ ኦባማ “የፀጽታ ሁከቶች”፣
ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ ጁን 2007 በሀምፕተን ዩኒቨርስቲ ዓመታዊ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ በቬርጂኒያ ተገኝተው ንግግር አድርገው ነበር፡፡ በዚያ ንግግራቸው ላይ በሎስ አንጀለስ በጥቁር አሜሪካውያን መካከል ፍጹም ሁከት ያለ መሆኑን በመጠቆም እንዲህ ብለው ነበር፡፡
… ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሎስ አንጀለስ በሚገኝ አንደኛ ኤ.ኤም.ኢ ቤተክርስቲያን የኤል ኤ ሁከቶችን 15ኛ መታሰቢያ በዓል ላይ በመገኘት ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት ተከታትየ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ሮድነይ ኪንግ የተባለውን ሰው አራት የፖሊስ ኃላፊዎች ደብድበው ገለዋል በሚል እና ድብደባውም በፊልም እና በፍላሽ ተቀርጾ ማስረጃ ሆኖ በቀረበበት ሁኔታ ተወንጅለው ክስ ቀርቦባቸው ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ አራቱም ፖሊሶች ከጥፋቱ ነጻ ናቸው ተብለው ሲለቀቁ በሎስ አንጀለስ ይህንን ያዩ ሰዎች እንዳለ ገነፈሉ፡፡ በዚህ በአሜሪካ ከታላላቅ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው እና በእሳት ቃጠሎ ነበልባል በተያያዘችው ከተማ የነበረውን ተስፋቢስነት እና ኃይልየለሽ አቅመቢስነት አስታውሳለሁ…
… በዚህ ክፍል ያሉት ብዙዎቹ ህዝቦች የት እንደነበሩ ያውቃሉ፣ ሁከቱ በሎስ አንጀለስ በተጀመረበት ጊዜ እና አሰቃቂው ተውኔት የፍሎረንስን እና የኖርማንዲን ማዕዘኖች ሲለበልብ ያስታውሱ ነበር፡፡ እናም በዚህ ሰብሰባ ላይ የተገኙ ሁሉም ሚኒስትሮች እነዚያ ሁከቶች በአንድ ጀንበር ምሽት የተከሰቱ ዱብ እዳዎች እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ፣ ሆኖም ግን እነዚያ ሁከቶች በሎስ አንጀለስ እና ለዘመናት በመላ ሀገሪቱ ሲከማቹ እና እያደጉ በመምጣት ለዚህ እንደበቁ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡
ወደ ችጋጎ፣ ባቶን ሩጅ ወይም ሀምፕተን– የመንገዶች ጠርዝ ላይ ወጣ ብትሉ እና ብታዩ በህይወት የመኖር እና ያለመኖር ጠርዝ ላይ የህግ ጠርዝ፣ የኢኮኖሚ ጠርዝ፣ የቤተሰብ ሁኔታ ጠርዝ እና የማህበረሰብ ጠርዝ ላይ የሚገኙ እና ምንም ዓይነት ተስፋ፣ ተዓምር እና ዕድሎች የሌላቸውን ሴቶች እና ወንዶች ትመለከታላችሁ::
እ.ኤ.አ ጃኗሪ 20/2015 በኮንግረሱ የመንግስታቸውን የፖለቲካ ህብረት በማስመልከት ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ፕሬዚዳንት ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በጥቁር ማህበረሰቦች ላይ እየተካሄደ ያለውን “የፀጽታ ሁከት” በማስመልከት ምን ሊሉ እንደሚችሉ ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ምናልባትም “የፀጽታ ሁከቶች” በቡሽ የአስተዳደር ዘመን ጊዜ ቀስ በቀስ ጠፍተዋል፡፡ እንጃ የማውቀው ጉዳይ የለኝም፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ወደ ችጋጎ፣ ባተን ሮግ ወይም ደግሞ ወደ ሀምፕተን ማዕዘን አካባቢዎች በቅርቡ ተመልሰው መጥተው ከሆነ (ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ማለቴ ነው) ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ መጥተው ከሆነ እና እ.ኤ.አ በ2007 ምንም ዓይነት ተስፋ፣ ተዓምር እና ዕድል የሌላቸውን አሁንም ቢሆን በዚያው ወይም በከፋ መልኩ ያሉ ወጣት ወንዶችን እና ሴቶችን አይተው ተመልክተው ከሆነ ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንዲህ የሚል አንድ ግምታዊ የሆነ ጥያቄ ልጠይቃቸው ወደድሁ፡ “ለመሆኑ አስፈላጊ ያልሆነው የፀጽታ ሁከት ከምን ደረሰ“? “እንደ ዱር ሙጫ በጸሐይ ኃይል ብው ብሎ ደረቀን? ወይስ ደግሞ እንዳመረቀዘ ቁስል ጠነባ? እናም ብን ብሎ ጠፋ? ወይም እንደበሰበሰ ስጋ ይገማልን” ወይም እንደ ጣፋጭ ጭማቂ እና እንደ የስኳር አገዳ እንክብል ጣፋጭ ሆነ? ምናልባትም ክብደት እንደበዛበት ጭነት ተለምብጦ ይሆን? ወይም ደግሞ አቅም እንደከዳው ጎማ ዷ ብሎ ይፈነዳ ይሆን?”
የሁለት ማህበረሰቦች ሀገር፣ አንዱ ጥቁር ሌላው ነጭ – በ2015 የተነጣጠሉ እና እኩል ያልሆኑ ማህበረሰቦች ወይስ ደግሞ አንድ የተባበረች እና የተከበረች ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እውን ትሆናለችን?
እ.ኤ.አ በ2004 በዴሞክራሲያዊ ብሄራዊ ስምምነት/Democratic National Convention በቦሰተን በመገኘት ሴናተር ባራክ ኦባማ እንዲህ በማለት ቀልብን የሚገዛ እና ስሜትን የሚኮረኩር ንግግር አድርገው ነበር፡ “መልካም እንግዲህ ለእነርሱ (እኛን ለመከፋፈል ዝግጅት ለሚያደርጉት) በዚህ ምሽት እንዲህ እላቸዋለሁ፣ ነጻ ወይም ደግሞ አጥባቂ አሜሪካ የሚባል ነገር የለም- ያለችው አንዷ የተባበረች ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ነች፡፡ ጥቁር አሜሪካ እና ነጭ አሜሪካ እንዲሁም የላቲን አሜሪካ እና የኤሽያ አሜሪካ የሚባል ነገር የለም- ያለችው አንዷ እና የተባበረችው እንዲሁም የተከበረችው ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ናት፡፡“
እ.ኤ.አ በ1967 የከርነር ኮሚሽን እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፣ “ሀገራችን ወደ ሁለት ማህበረሰቦች አቅጣጫ ትሄዳለች፣ አንድ ነጭ፣ አንደ ደግሞ ጥቁር- የተለያዩ እና እኩል ያልሆኑ::“ እራሴን እንዲህ በማለት እጠይቃለሁ፣ “አሜሪካ ለእኔ ምኔ ናት?“
በህግ የበላይነት የምትገዛ ሉአላዊ ሀገር ናትን ወይስ ደግሞ ጥቂት የተዛባ አመለካከት ያላቸው እና ከህግ በላይ በመሆናቸው ምክንያት ሀገሪቱን የሚገዙ እና በተጨባጭነት እራሳቸውን ህግ የማድረግ እምነትን በሚያራምዱ ሰዎች የምትገዛ ምክንያቱም ህጉን ለእራሳቸው መጠቀሚያ በማድረግ ለመግደል እና የዜጎችን ሰብአዊ መብትን ለመደፍጠጥ ህጋዊ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሀገር ናት?
አሜሪካ የጀግኖች እና የነጻ ህዝቦች ሀገር አይደለችምን?
የኃይማኖት አባል እና ሚኒስትር እንዲሁም ገጣሚ የሆኑት ሄነሪ ቫን ዳይክ ለዚህ ጥያቄ እንዲህ የሚል ምላሽ አላቸው፣ “…አሜሪካ ለእኔ ቤቴ እንደገናም ቤቴ ናት! ልቤ እንደገና ወደ ቤቴ ተመለሰ እናም እዚያ ለብዙ ጊዜ እቆያለሁ/ የወጣቶች እና የነጻ ህዝቦች ሀገር ከውቅያኖስ ባሻገር ያለች/ ከባቢ አየሯ የተሟላ የጸሐይ ብርሀን ያላት እና ባንዲራዋ በበርካታ ከዋክብት ምስሎች የተሞላ ሀገር ናት!…/“
ላንግስተን ሁስ እንዲህ በማለት ተቃውሟቸውን አቅርበዋል፣ “አሜሪካ ለእኔ በፍጹም አሜሪካ አልነበረችም፡፡“ ሁስ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፣ “አሜሪካ እንደገና አሜሪካ እንድትሆን እንፍቀድ፣ ከዚህ ቀደም አሜሪካ የእነርሱ እንዳልሆነች ሲያስቡ የነበሩት ዜጎች አሁን የእነርሱ እንደሆነች እንዲሰማቸው እናድርግ፡፡“
ስሜትን በሚማርክ መልኩ ሁስ ፍቅርን በተላበሱ ቃላት በመታጀብ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፣ “አሜሪካ እንደገና አሜሪካ እንድትሆን እንፍቀድ፡፡/“ መሆን ስትፈልግ የነበረውን ህልሟምን እንድታሳካ እናድርግ፡፡/ አሜሪካ ለአላሚዎች እና ነጻ ለሆኑ እና እራሳቸውን ነጻ ላደረጉ ህዝቦች እንድትሆን እንፍቀድ…/ አሜሪክ ህልም ለሚያልሙ አላሚዎች እንድትሆን እንፍቀድ–/አሜሪካ ታላቋ በንጉሶች የማትፐወዝ እና በአምባገነኖች የማትዘወር በፍቅር የተሞላች ምድር እንድትሆን እንፍቀድ/ ምንም ዜጋ ቢሆን ከላይ በተጠቀሱት ኃይለኞች ክብሩ እና መብቱ የማይደፈር እና የማይገሰስ እንዲሆን እንፍቀድ…/ ኦ ሀገሬ ነጻነት የሰፈነባት/ በውሸት የጀግንነት ባዶ ተደጋጋሚ አዙሪት ያልወደቀች/ ሆኖም ግን በእውነተኛ ዕድል ላይ ያማተረች እና ህይወት ነጻ የሆነባት ሀገር/ እንዲሁም እኩልነት ከምንተነፍሰው አየር ጋር ሰም እና ወርቅ ሆኖ የተዋኸደባት ሀገር እንድትሆን እንፍቀድ…/
እኔ ሁስን ተቀላቅያለሁ፡፡ እንፍቀድ “አሜሪካ እንደገና አሜሪካ እድትሆን እንፍቀድ“ ቀደም ሲል አሜሪካ አሜሪካ አልነበረችም ለሚሉት አሁን አሜሪካ እውነት አሜሪካ እንድትሆን እንፍቀድ::”
እ.ኤ.አ በ2015 እርካታን ልናገኝ እንችላለን?
በዶ/ር ኪንግ 86ኛ የልደት በዓላቸው ህይወት ፈዋሽ የሆኑ ጥያቄዎቻቸውን መልሰን የምናነሳበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ “መቼ ነው እርካታን ልትጎናጸፉ የምትችሉት?“ “መቸ ነው እርካታን ልንጎናጸፍ የምንችለው?” ለእነዚህ ጥያቄዎች እ.ኤ.አ በ2015 የሚሰጠው መልስ እ.ኤ.አ በ1963 ከተሰጡት መላሾች ጋር አንድ አና መሳ ለመሳ ነው፡፡ “ጥቁር ህዝቦች ለመናገር በሚዘገንን መልኩ የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሰለባ ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ በምንም ዓይነት መልኩ ልንረካ አንችልም፡፡“ በግድያ ማዕበል እና በፖሊስ የጭካኔ ድርጊት በሚነዳ የነፋስ ውሽንፍር እስከተመታን እና በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ህገመንግስት ውስጥ በመታቀፍ ሰላማዊ የሆነ የወደብ መጠለያ እስካላገኘን ድረስ እንዲሁም ጥቁሮች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው እስካልቆመ ድረስ በምንም ዓይነት ሁኔታ ልንረካ አንችልም!
እ.ኤ.አ በ2014 የፖሊስ ጭካኔዎች የተሞሉባቸው የነፋስ ወዠቦዎች ነበሩ፡፡ ሚካኤል ብራውን የተባለ የ18 ዓመት እድሜ የነበረው ጥቁር ወጣት ዳረን ዊልሰን በተባለ የ28 ዓመት ነጭ ወጣት በጥይት በመተኮስ በፈርግሰን ከተማ ወዲያውኑ ገደለው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ኤሪክ ጋርነር የተባለ የ43 ዓመት እድሜ ያለው ጥቁር ጎልማሳ ፖሊስ ጉሮሮውን አንቆ ይዞት ከቆየ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኒዮርክ በስታተን ደሴት ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ለሁለቱም የግድያ ጉዳዮች ድርጊቱን በፈጸሙት የፖሊስ ኃላፊዎች ላይ ክስ ለመመስረት ተቃውሞ አደረጉ፡፡ በመላ ሀገሪቱ በይፋ ዘገባ የቀረበባቸው እና ያልቀረበባቸው ተመሳሳይነት ያላቸው ፖሊስ በዜጎች ላይ ዘርን ማዕከል ባደረግ መልኩ በርካታ ግድያዎችን እና የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የብራውን እና የጋርነር ግድያዎች መጠነ ሰፊ የሆኑ የጎዳና ላይ ተቃውሞዎችን ቀሰቀሱ፡፡ በቴሌቪዥን ወንጌልን በመስበክ ሙያቸው ታዋቂ የሆኑት አፍሪካ አሜሪካዊ ጳጳስ ተ.ዲ ጃክስ ለአማኞቻቸው ጥቁር አሜሪካውያን/ት “በእግረኞች መንገድ” ላይ የጥቁሮች ነፍስ አንዳይጠፋ ብለዋል፡፡
በካሊፎርኒያ የሪችመንድ የፖሊስ ሹም የሆኑት ክሪስ ማግነስ የጥቁሮቸ ህይወት አሳሳቢ ሆኗል የሚል መልክት ያለው ጽሁፍ ይዘው ከእግረኞች መንገድ ዳር ቆመው በፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ካደረጉት ዜጎች ጋር በመቆም አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፖሊስን ጭካኔ የተሞላበት እኩይ ድርጊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስቆም እንዲቻል ለማስተባበር የሚችል “የጥቁሮች ሕይወት ጉዳይ አሳሳቢነት” የሚባል ድርጅት ተቋቁሞ ስራውን ጀምሯል፡፡ የሴንት ሉዊስ ተጨዋቾች “እጅ ወደላይ አትግደሉ” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ “መተንፈስ አልቻልኩም” የሚል መፈክር በአደባባይ የሩጫ መንገድ ላይ በመያዝ የፖሊስን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ጩኸታውን አሰምተዋል፡፡
በስራ ገበታቸው ላይ ለብዙ ጊዜ የማይቆዩ ሰዎች እንዲህ በማለት ይናገራሉ፣ “ምንም ዓይነት እርካታን አላገኝም… ሁልጊዜ እያጣሁ ነው…“
እ.ኤ.አ በ2014 ያጣነውን ነገር በ2015 ለማስመለስ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ እንደ አሜሪካዊነታችን መነሳት አለብን፣ በግድያ እልቂት የሚፈጽሙብንን ግፈኞች ለመቋቋም እና ፍትህ የሰፈነበት አየር መተንፈስ እንድንችል እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲከበር ለዘለቄታው ከነብሳችን ጋር መኖር እንድንችል እጆቻችንን ተያያዘን በአንድነት መቆም አለብን፡፡ እ.ኤ.አ ከዚህ ቀደም አሜሪካ አሜሪካ አልነበረችም የሚል እምነት የሚያራምዱትን ሰዎች አስተሳሰብ ለመቀየር እንድንችል በ2015 “አሜሪካ እንደገና አሜሪካ እንድትሆን” የየበኩላችንን ጥረት እናድርግ፡፡
በጣም ትንሽ የሆነችዋ መከላከያ እጅግ በጣም ብዙ ለሆነ ፈውስ ትዳርጋለች፡፡ ዶ/ር ኪንግ ለመስማማት በጣም ፈጣኖች እና ለመጣላት ደግሞ በጣም የዘገየን መሆን ይኖርብናል ሲሉ አስተምረዋል፡፡ አ.ኤ.አ በ2015 በአስከፊው የፖሊስ ህገወጥነት ኢፍትሀዊነት ከቆሸሸው መንገድ ጋር ተደራድረን ሰምምነት ማድረግ አለብን፡፡ የመሰቃየት፣ የመከዳት እና የመገደል ስሜት ከሚሰማቸው ወገኖቻችን ጋር በመነጋገር እና በመተማመን በአሜሪካ ህገመንግስት እንዲጠበቁ ለማድረግ ወደ አንድ ዓይነት ሰምምነት ላይ መድረስ አለብን፡፡ በፖሊስ እና በህዝቡ መካከል የሚታየውን ውጥረት ለማርገብ እና በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ ላይ የወንዶችን እና የሴቶችን መብት ለማስከበር የእኛን የፈጠራ አድማስ ማስፋት አለብን፡፡
ፖሊስ እና ማህበረሰቡ የማይሞቱ ጠላቶች አይደሉም፡፡ ጥቂት የፖሊስ ኃላፊዎች የፖሊስ ስልጣን የሚመነጨው ከጠብ መንጃ አፈሙዝ ነው ብለው የሚያስቡ ምግባረ ብለሹዎች አሉ፡፡ ተሳስተዋል፡፡ ጥቂት ዜጎች ፖሊስ የማይሳሳት ትክክለኛ ነው ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡ እንዚህም እንደዚሁ ተሳስተዋል፡፡ ፖሊስ የህዘብ አገልጋይ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ የሙያ ተልዕኳቸው እና የገቡት ቃል ኪዳን “ማገልገል እና መጠበቅ” የሚል ነው፡፡
ዜጎች አገልጋዮቻቸውን ያለምንም ንቀት በማክበር እና በአድናቆት ማስተናገድ እንደሚኖርባቸው የሲቪክ እና የሞራል ግዴታ አለባቸው፡፡ ዜጎች አገልጋዮቻቸው ላከናወኗቸው ምስጋናየለሽ፣ አስቸጋሪ እና አደገኛ ስራዎች ሁልጊዜ ምስጋና ማቅረብ አለባቸው፡፡
ሁሉም የፖሊስ ኃላፊዎች የመለያ ባጅ በትከሻቸው ወይም ደግሞ በደረታቸው ላይ ያደርጋሉ፣ ሆኖም ግን ምግባረ ብልሹዎቹ ፖሊሶች ህዝብን የሚደበድቡበት በርካታ ዱላዎችን በትከሻዎቻቸው ላይ ይይዘሉ፡፡ ለበጎ ነገር የመንፈስ ጥንካሬ ያላቸውን ሁሉንም የፖሊስ አባላት እና ብዙ መስዋዕትነትን ለሚከፍሉት ምስጋና ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ሆኖም ግን የሙያዊ እና የታማኝነት መገለጫ የሆኑትን የመለያ ባጃቸውን ሁልጊዜ በኩራት እንዲለብሱ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡
ፖሊሶች አንዳንድ ጊዜ ዜጎችን ከወንጀለኞች ለመከላከል የመጨረሻው የተከላካይነት ምልክቶች በመሆናቸው ምክንያት ቀጭን ሰማያዊ መስመር የሚል መጠሪያ ስም ይሰጣቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ሁሉንም አሜሪካውያን/ት የህገወጥ ወንጀለኞች ሰለባ ከመሆን ለማዳን እንዲቻል መጠነ ሰፊ የሆነ የቀይ፣ የነጭ እና ሰማያዊ መስመር ያለው ልብስ እንዲለብሱ እንፈልጋለን፡፡
ዶ/ር ኪንግ ምንጊዜም ቢሆን ድህነት፣ ኃይል፣ ኢፍትሀዊነት እና ዘረኝነት በሁሉም መገለጫዎቻቸው እንዳይከሰቱ ትግስት የሌለው የፍቅር ማህበረሰብ እንዲኖር ያልማሉ፡፡ በፍቅር በተሞላው ማህበረሰባቸው ግጭቶች ቀውስ አልባ የሆኑ የአካሄድ ስልቶችን በመከተል በመወያየት እና በመተማመን ለውይይት ክፍት በሆነ መልኩ እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡
በዶ/ር ኪንግ ፍቅር የተላበሰ ማህበረሰብ ስምምነት ማለት የአንድ ሰው የአድራጊነት የፈጣሪነት ጨዋታ፣ የታዕይታ እና ስልታዊ የአካሄድ ጥበብን በማመቻቸት በልጦ ለመገኘት የሚደረግ አካሄድ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ስለእውነት እና ስለእርቅ የሚደረግ ጉዳይ ነው፡፡ ስምምነቶች የሚመሩት እንዲህ በሚል በአንድ ነጠላ መርህ ላይ ተመስርተው ነው፡ ተቃራኒ ወገን ከሚያደርገው በተለየ መልኩ በእያንዳንዱ ድርጊት እና መግለጫ ላይ በአዎንታዊ ነገሮች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 አሜሪካውያን/ት የዶ/ር ኪንግን ህልም እውን ለማድረግ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ውድድር ብቻ ማድረግ የለባቸውም፣ ሆኖም ግን ፍቅር እንደ ሸማ የተላበሰውን ማህበረሰብ ለመፍጠር እንዲቻልም ጭምር ስምምነት ማድረግ አለባቸው፡፡ ስምምነቱ በበጎ ነገሮች እና በሰይጣናዊ ነገሮቸ መካከል የሚደረግ መሆን የለበትም፡፡ ሆኖም ግን መጥፎ ነገሮችን ለማስወገድ በበጎ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡
ስምምነቱ አንደኛውን ወገን ጠላሸት በመቀባት ወይም ደግሞ ሌላኛውን ወገን በማመስገን የሚደረግ ስምምነት አይደለም፣ ሆኖም ግን ሁለቱንም ወገኖች በአንድነት የፍቅር ስብዕናን በማላበስ ከልብ እና ከእውነት በመነጨ መልኩ ስምምነት እንዲያደርጉ ሲቻል ነው፡፡ ስምምነቶች የፖሊስን ተጠያቂነት እና የዜጎችን ስልጡንነት የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸው እምነት አለኝ፡፡ ስምምነቶች የጭራቃዊነት የጥላቻ ስርዓት ወጥመድ ሰለባ የሆኑትን እና ከሰብአዊነት በወረደ መልኩ በስቃይ ላይ የሚገኙትን ተስፋየለሽ ወገኖች ወደ ነጻነት ሊመሩ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡
አንድ ድርድር ሊቀርብበት የማይችል ጉዳይ አለ፡፡ በጭራቃዊ ስርዓት ላይ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይቀመጥ የሰውን ልጅ ኢሰብአዊነት ድርጊቶች በማስወገድ፣ የማይገሰሰው የአሜሪካውያን/ት የመኖር፣ የነጻነት እና በደስታ የመኖር መብት በምንም ዓይነት መልኩ ለድርድር አይቀርብም፡፡ የዶ/ር ኪንግን 86ኛ ዓመት የልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ የሚከተሉትን ድፍረት የተሞላባቸውን ጥያቄዎች ይጠይቁናል ብዬ አስባለሁ፡ በዚህ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ መቸ ነው እርካታን ለመጎናጸፍ የማትችሉት? የእናንተን ጥቀር ወጣቶች እና ፖሊሶችን ጥላሸት በመቀባት መቸ ነው እርከታን ለመጎናጸፍ የማትችሉት? የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ የሚያሳየውን ኢሰባዊነት በማየት እና የጭራቃዊነትን ስርዓት በመመልከት ጣት መቀሰሩን፣ ጥርስ መንከሱን፣ የልብ መሰበሩን እና የሆድ ቁርጠቱን በማስወገድ መቸ ነው እርካታን ለማስወገድ የማትችሉት? እውነታው በስቃይ ሰለባዎቹ እንባ ታጅቦ ከፊት ለፊታችሁ ቆሞ ሳለ የእናንተ የመጨረሻውን ህይወት ፈላጊነት ከግንዛቤ በማስገባት መቸ ነው እርካታን ልትጎናጸፉ የማትችሉት? በእናንተ የአስመሳይነት ባህሪያት፣ በቦቅቧቃ ፈሪነት እና በኢፍትሀዊነት ማስመሰያነት መች ነው እናንተ እርካታን ልታገኙ የማትችሉት? መቸ ነው ስምምነት ማድረግን የምትጀምሩት?
እ.ኤ.አ በ2014 የፖሊስን ህገወጥ የማሰቃየት የጭካኔ እርምጃን ከግንዛቤ በማስገባት እንዲህ የሚል ጩኸታችንን እናሰማለን፣ “እኔ (እኛ) መተንፈስ አልቻልኩም/ንም፡፡ እ.ኤ.አ 2015 ለሁሉም አሜሪካውያን/ት የመተንፈሻ ጊዜ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፍትህን እና የእውነትን ንጹህ አየር ለመሳብ ጥልቅ የሆነ አተነፋፈስን የምናደርግበት ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድነት መተንፈስ ካልቻልን በተናጠል እንታነቃለን፡፡ በ86 ዓመታቸው ዶ/ር ኪንግ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ እንዲህ በማለት ይተቹን እና ይዘለፉን ነበር፣ “ሁሉም የእግዚአብሄር ልጆች ህይወቶች ያሳስቡናል!“
ሁሉም አንባቢዎቸ “ሰልማ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ተንቀሳቃሽ ምስል/ፊልም እንድትመለከቱት በአጽንኦ እጋብዛለሁ፡፡ ለማየት ግዴታ ነው – መልካም የሆነ ታሪክን የሚነግር ማራኪ የፊልም ስራ ነው፡፡ ዲቪዲው እስከሚወጣ ድረስ ለመቆየት አልችልም፣ ትዕግስቱም የለኝም!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም