የጠቅላላ ጉባኤ ጨዋታ – አስራት አብርሃም

አስራት አብርሃም

ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድ ላይ የጠቅላላ ጉባኤ ጨዋታ ከጀመረ ቆዬ፤ እነዚህ ፓርቲዎች ባለፈው ዓመት ለመዋሃድ ተስማምተው ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ሲወስኑ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብቶ መኢአድ ከአሁን በፊት ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ኮረም ስለማይሞላ እሱ ሳታስተካክሉ ለመዋሃድ አትችሉም ብሎ ውህደቱን እንዲሰናከል አደረገ። በወቅቱ ይሄ ውሳኔ ፖለቲካዊ መሆኑ በደንብ ልብ ያለ ወገን ለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤ እኛም የመሰለን የራሱ የፓርቲው ችግር እንጂ የእጅ አዙር ፖለቲካዊ ደባ መሆኑ ግልፅ ብሎ አልታየንም፤ ያላሟሉት ነገር ባይኖር ነው የሚል ሰውም ቀላል አልነበረም።

 

EPRDF

እነዚህ ፓርቲዎች ከዚያ በኋላ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ገባኤ ቢያካሄዱም፤ ምርጫ ቦርድ እንዲሁ በቀላሉ ሊፋታቸው አልቻለም። አሁን ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንዲጠሩ ውሳኔና ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ የማይፈፀም ከሆነ ደግሞ የመጨረሻውን እርምጃ እወስዳለሁ እያለ ነው። ነገር ግን አሁን በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ የተያዘው አቋም ሶስተኛ አይደለም አስረኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቢካሄድም የሚለወጥ አይደለም። እነዚህ ፓርቲዎች በዘንድሮው ምርጫ እንዳይሳተፉ ከማድረግ ባሻገር ጭራሽ እንዲዘጉ ወይም ለሌላ ተለጣፊ ተላልፈው እንዲሰጡ ፖለቲካዊ ውሳኔ በገዥው ቡድን በእኩል የተላለፈባቸው ነው የሚመስለው። ይሄ ለምን ሆነ የሚል ካለ እኔ በአንድነት ፓርቲ በእኩል ከተያዘው የትግል እስትራቴጂ አንፃር ልተነትነው የምችለው።
በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በተለይ አሁን ወደ አመራር በመጣው የለውጥ ኃይል ሲራመድ የነበረው አቋም 2007 ምርጫ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚፈለግ ከሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያለው ደካማ አመራርና የትግል ስልት መቀየር አለበት የሚል ነው፤ በዚህ አቋም ላይ በአብዛኛው የፓርቲ ለውጥ ፈላጊ አባላት ዘንድ የነበረ ነው የሚመስለኝ። ከአንዳንዶቹ ጋር አደርገው በነበረው ውይይት እንደተረዳሁት መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ ተደርሶ ነበር። እኔ በግሌ በፊትም ለአንድነት የተለየ ፍቅር የነበረኝ ቢሆንም በአንድነት ፓርቲ ገብቼ ለመታገል እንድወስን ያደረግኝ ይሄ ውይይትና እስትራቴጂ ነበር ብል ማጋነን አይመስለኝም። ይሄ እስትራቴጂ ዋና ዋና የሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማዋሃድና ብሎም የአመራር ለውጥ ማምጣት መቻል የሚል ቁልፍ አላማ የነበረው ነው። ነገር ግን የውህደቱ ጉዳይ እንደተፈለገው ሳይሳካ ሲቀር በአድነት ፓርቲ ውስጣዊ የተሃድሶ አብዮት በማካሄድ እስትራቴጂው አሃዱ ብለን ጀመርነው፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን ስርዓቱ በቀላሉ ሊለቀን አልቻለም፤ በልዩ ልዩ መንገድ ለአዲሱ አመራር እውቅና ላለመስጠትና ወደ መደበኛ የትግል እንቅስቃሴ እንዳይገባ ለማድረግ ከውስጥም ከውጭም ሳንካ እየተፈጠሩ መሰናክል እንዲበዛበት ሆነ።
አዲሱ የለውጥ አመራር ከሁሉም አቅጣጫ ጠላት በዛበት፤ ጫጫታው በሁሉም አቅጣጫ በረከተ። ለምን ግን ይሄ ሊሆን ቻለ ብለን ብዙዎቻችን ጥያቄ ማንሳታችን አልቀረም፤ በሀሳብ እንጂ በዘር ወይም በቋንቋ ወይም በአከባቢያዊነት ምክንያት ያልተሰባሰብን መሆናችን አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ፖለቲካውን በዚህ መልኩ ለማስኬድ በሚፈልጉ ኃይሎች ዘንድ የተወደድን አይመስለኝም፤ ከሁሉም የከፋ የሆነው ግን ገዥው ፓርቲ በጥርሱ አስገብቶናል፤ በጣም ችግር የሆነብንም እርሱ ነው፤ ሊከፋፍለን፤ ጥርጣሬዎች በመሀላችን እንዲኖር ቢጥርም፤ ለዚህ ዓይነቱ ጥርጣሬ በር አልከፈትንም ነበር።
ከዚያ በኋላ ስርዓቱ ያመራው ወደ ምርጫ ቦርድ ነው፤ በምርጫ ቦርድ በእኩል የጠቅላላ ጉባኤ ካርድ መዞ መጫወት ጀመረ፤ የተወሰን አመራሮች አብዛኛው ማለት ይቻላል፤ ጠቅላላ ጉባኤ ብንጠራ ችግሩ ሁሉ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልንፈታው እንችላለን የሚል እምነት ነበረን። እንደተባለው የሚገርም እጅግ ደማቅ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄድን፤ ስርዓቱ የበለጠ እንዲደነግጥና በአንድነት ላይ በቻለው አቅም ሁሉ እንዲረባረብ አደረገው እንጂ ችግሩ ሊፈታ አልቻለም። እንዲያውም ተዳክመውና ተበትነው የነበሩ በራሳቸው ምክንያት ያኮረፉ የአንድነት አባላት በማሰባሰብና ሌሎችም እንዲጨመሩ በማድረግ ወደ ትልቅ እንቅስቀሴ አንድነትን የማፍረስ እንቅስቃሴ ገባ፤ነገሩ እየተካረረ ሲሄድ በተለይ ደግሞ አንድነት በባህርዳር ሰልፍ አደርጋለሁ የሚል ቁርጥ ያለ አቋም ለጥር ሶስት መያዙ ሲታወቅ፤ ምርጫ ቦርድ አንድነት በአራት ቀናት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄዶ ፕሪዚደንቱን በሚስጥር ድምፅ እንዲመረጥ ካላደረገ የመጨረሻውን ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ አዋጅ አስነገረ።
የምርጫ ቦርድን የመጨረሻ ካርድ ለማስጣል እንደገና ጠቅላላ ጉባኤ እናድርግ ተብሎ ለሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ሩጫ ተጀመረ። ፍሽካውም ተነፋ፤ አንድነት በምርጫ ቦርድ ደባ ሊዘጋ ስለሆነ ድንገት ዘመድ እንደሞተብህ ጨርቄን ከልቤን ሳትል በሁለት ቀን ድረስ ተብሎ ከመተማ እስከ ሰመራ፤ ከትግራይ እስከሞያሌ ያሉት የአንድነት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ጥሪ ተላለፈላቸው፤ እንደተባለውም ሌትና ቀን ተጉዘው፤ ቅዳሜ ማታ ጥር ሁለት በአንድነት ፅህፈት ቤት ተሰባሰቡ፤ በዚሁ የመኸር ብርድ በግቢው ውስጥ ነጠላቸውን አጥፈው ያገኙትን ቀምሰው አደሩና በድጋሜ በተጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከአሁን በፊት ያስተላለፉትን ውሳኔ ምንም ሳይቀይሩ በሚስጥር ድምፅ አሁንም መሪያችን በላይ ፍቃዱ ነው ብለው አረጋገጡ።
በሌላ በእኩል ምርጫ ቦርድ አስቸኳይ ጉባኤ ጥሩ ብሎ ሲያበቃ፤ ተጠርቷልና ና ተገኝ፤ ተወካይህ ላክ ሲባል፤ አየለ ስሜነህ የሚባል ሰው ሌላ ጉባኤ አለ ብሎ ጠርቶኛልና በሁለታችሁም ጉባኤ ላይ አልገኝም ብሎ በቀጣይ ሊያሴረው ያሰበውም ደባ ለማሳካት ሳይመጣ ቀረ። በአንድነት ህግ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ እንዴት እንደሚጠራና ማን እንደሚጠራ በግልፅ የተቀመጠ ነገር ነው። አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ሙሉ ስልጣን ያለው የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት ነው። የኦዲትና ኢንስፔክሽን የፓርቲው አባላት በማንኛውም ምክንያት ጉባኤ እንዲጠራ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አንድ ሶስተኛ አስፈርመው ሲያቀርቡለት በዚሁ መሰረት ብሄራዊ ምክር ቤቱ ጉባኤ እንዲጠራ ሊያዝ ይችላል አለበዚያም ራሱ በቀጥታ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ ይችላል፤ ብሄራዊ ምክር ቤቱ መጥራት ካልቻለ ማለት ነው።
ከዚህ ውጪ የሚጠራ ጠቅላላ ጉባኤ ደንባዊም ህጋዊም ሊሆን አይችልም። ምርጫ ቦርድ በእጁ ላይ ያለውም ሰነድ ማየት ይችላል፤ የአንድነት ህገ ደንብ የሚለው ይሄንኑ ነው። ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ውስጥ ያሉት አመራሮች እነርሱ ብቻ በሚያውቁት ምክንያት ሁለት አንድነት እንዳለ እና ሁለት ቦታ ጉባኤ እንደተጠራ እናም ጉባኤ የተካሄደ አስመስለው አሁን ደግሞ ሁለታችሁም አንድ ላይ ሆናችሁ ጉባኤ ጥሩ በሁለት ሳምንት ውስጥ እያሉን ነው፤ ሲጀመር እነዚህ ሌላ ቦታ ላይ ጉባኤ እንዲያካሄዱ የተፈቀደላችወ ሰዎች ፓርቲው በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፉ አልተከለከሉም፤ እንዲያውም እንዲገኙ እንደማነኛውም የጉባኤ አባላት ጥሪ ተላልፎላቸዋል፤ የሆነው ግን ሌሎች አባላት ያልሆኑ ሰዎች አብሯቸው እንዲገኙ ተደርጎ አቶ ትግስቱ አወሉ የተባለ ከአሁ በፊት ከአቶ በላይ ጋር ተወዳድሮ የራሱ አንድ ድምፅ ብቻ ያገኘ ሰው ፕሬዚደንት አድርጎ እንዲመረጥ አድርጓል። በዚህ የውንብድና ድራማ ላይ የምርጫ ቦርድ ሚና እጅግ የጎላ ነው።
የዚህ ቡድን አደረጃጀትና የገንዘብ ምንጭ አብረው ሲሳተፉ የነበሩ አባላት በኋላ በማስረጃ እንዲጋለጥ አድርጓል፤ አቶ ትዕግስቱም ቃለ መሀላ ሲፈፅም የሚያሳይ ፎቶ በፌስቡክና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ተለቀቀ ምን ብሎ መሀላ እንደፈፀመ አላወኩም፤ ምናልባት ወያኔ በሰጠኝ ተልዕኮ አንድነትን ለማፍረስ ቃል እገባለሁ ብሎ እንደሆነ አላውቅም፤ እዚያ የነበሩ ሊነግሩን ይችላሉ። የሚገርመው ነገር እዚህ በአንድነት ላይ ባሰማራቸው ሰዎች ያለምንም ማህተምና ሀላፊነት ደብዳቤ እየተቀበለ፤ አዳራሻ እንዲፈቀድላቸውና ስብሰባም እንዲያደርጉ እየፈቀደ፤ ለመኢአድ አዲሱ አመራር ግን ማህተሙ በመሰረቁ ሌላ ማህተም አሰርቶ ደብዳቤ ሲልክ ህጋዊ ማህተም አይደለም ብሎ አልቀበልም ማለቱ ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች መስጠቱ ምርጫ ቦርድ double standard የሚባለውን አሰራር እንደተከተለ ማየት የሚቻል ነው።
ከዚህ በኋላ ሌሌች አማራጮች ካሉ መፈለግ ነው እንጂ በየጊዜው ጠቅላላ ጉባኤ እየጠሩ መጓዝ የሚቻል አይመስለኝም ወይም የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከየአሉበት ቦታ ለቀው በቀዋሚነት በዋናው ፅህፈት ቤት እንዲኖሩና ምርጫ በርድ በየቀኑም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ ከወሰነ ይትግሉ ወደ ጠቅላላ ጉባኤ ማካድ አውርዶ መሰብሳብ ይቻል ይሆናል፤ ከዚህ ሁሉ ግን ስርዓቱ የወሰነ ይወስን ብሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ መዘጋጀትና ወደ መደበኛ የፖለቲካ ስራ መመለስ ነው የተሻለ የሚሆነው፤ ምክንያቱም ጠቅላላ ጉባኤ ብትጠራም እነዚያ በስርዓቱ እንዲደራጁ የሆኑ ወገኖች እንዲመጡና አንድ ላይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲካሄድ ማድረግ አይቻልም፤ ጠቅላላ ጉባኤ ቢጠራም ምርጫ ቦርድ ሊገኝ አይችልም፤ ስለዚህ ከንቱ ድጋም ነው የሚሆነው። ወይም ምርጫ ቦርድ የሚፈልጋቸቸው፣ ሰዎች ወደ አመራር ምጥቶ አሁን ያለትን እውርዶ ፓርቲው ተለጣፊና ተንበርካኪ ፓርቲ እስኪሆን ድረስ ኢህአዴግም ምርጫ ቦርድም የሚተኙለት እየሀንም፤ ጥላቸው አዲሱ የአንድነት አመራር ከያዘ የትግል መስመርና እስተራቴጂ ጋር ነው፤ ይሄ እስራቴጂ ምርጫ ቦርድ አሉ ብሎ ወደምርጫ እንድንገባ የሚያደርገን አይደለም፤ ይሄ እስታቴጂ ህዝቡን አደራጅቼ፣ ካርድ እንዲወስድ፣ እንዲመርጥና እንዲታዘብ ብሎም ድምፁን እንዲያስከብር አድርጌ በ2007 ምርጫ ለውጥ አመጣለሁ ነው የሚለው፤ ይሄ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ኢህአዴግ እንደተለመደው የህዝብ ድምፅ የሚዘርፍ ከሆነ ደግሞ የመረጠውን ህዝብ ድምፄን አሳልፌ አልሰጥም ብሎ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንዲካሄድ አድርጋለሁ፤ በዚህ ጊዜ የሚኖረው ህዝባዊ እምቢተንኘቱም አንድነት እንዲመራው ይሆናል የሚል ነው።

 

The post የጠቅላላ ጉባኤ ጨዋታ – አስራት አብርሃም appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.