ወደ እውቀትም ወደ ሽፍትነትም የሚኬደው ወይም የተኬደው፤ የአገርን ችግር ለመፍታት ነው፡፡ – ምንሊክ ሳልሳዊ

ሃሳብን ለመግለፅ መቻል መታደል ነው፡፡ የመናገር ነፃነት፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት፣ የመሰብሰብና የመደራጀት ጉዳዮች ሁሉም የዲሞክራሲ ልጅ-ልጆች ናቸው፡፡ የከፋው ኢ- ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት “ኦሆሆ አሃሃ!” ማለትንም እንደማይፈቅድ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ የተከለከለውን በማየት የተፈቀደውን የማየት እድል ይገኛል፡፡

ተበታትኖ ማሰብ የሃሳብ ልዩነትን ለማየት የሚያግዘንን ያህል፤ አንድ ላይ ሆነን ማሰብ የአንድነትን ጉልበት ያሳውቀናል፡፡ ዞሮ ዞሮ አንድነትም ልዩነትም በህብር መያዝ ያለባቸው የዲሞክራሲ ገፅታዎች ናቸው፡፡ ፈረሱን በትክክል መጋለብ የምንችለው ልጓሙን ለሌሎች ካልለቀቅን ነው፡፡ የምሁራን ሚና በተለይ ዛሬ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ለዋጭ አዕምሮ ያስፈልገናል፡፡ ጉዳዩን የሚያውቅ ምሁር ካልተሾመ ስንደናቆር መኖራችን ነው፡፡

አርበኝነት ወይም ሽፍትነት እንደሙያና እንደመፍትሄ ይቆጠር በነበረበት ዘመን፤ ሁሉም ትምህርቱን እየተወ ወደ ጦርነት ይሄድ ነበረና “ግቢ ተማሪ ቤት ተመለሺ ቅኔ – ወንዶች እዋሉበት እውላለሁ እኔ!” አሉ ይባላል፡፡ ወደ እውቀትም ወደ ሽፍትነትም የሚኬደው ወይም የተኬደው፤ የአገርን ችግር ለመፍታት ነው፡፡ መሪዎች፣ ኃላፊዎች፣ አለቆች፣ ፖለቲከኞች ይሰሙ ዘንድ ጆሮ፣ ያዩ ዘንድ ዐይን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ካልተጠቀሙበት አባክነውታል፡፡ ህዝቦች ሃሳባቸውን ይገልፁ ዘንድ ቅን ልቦና አላቸው – የተጠማ ከፈሳሽ፣ የተበደለ ከነጋሽ – ፈውሱን ማግኘት ይሻል፡፡ የህዝብን ችግር እናዳምጥ – የፖለቲካም ይሁን፣ የኢኮኖሚም ይሁን፣ የሃይማኖትም ይሁን የባህል፤ እናዳምጠው!!