ፈልጌ አስፈልጌ ያን ሰሞን አጣኋት… አቤ ቶኮቻው

ከአንድነት ጋር የሚሟገቱትን አካላት ባፈላልግ በድብቅ ከተነሳው ”የቃለ ማህላ” ፎቶግራፋቸው ውጪ ላገኛቸው አልተቻለኝም ነበር። ዛሬ በኢቲቪ መስኮት ግን በአቶ በላይ የሚመራው አንድነት ሀገወጥ ነው ሲሉ አፋቸውን ሞልተው…(አፋቸውን ሞለተው ለማለት እንኳ አያስደፍርም…) ብቻ ግን የሞሉትን ሞልተው ሲናገሩ አይቻቸዋለሁ። እንዲህ ያልኩት ከመሬት ተነስቼ አይደለም፤ ቪዲዮውን ጠቅ አድርጋችሁ ስትመለከቱት አቶ ትግስቱም ሆኑ ጎረምሳው ጸሃፊያቸው የሚናገሩት የራሳቸውን ሳይሆን እነደ ቴፕ የጎረሱትን ካሴት ነው የሚመስለው።

እንደ ምሳሌ የአቶ ትግስቱ ጸሀፊ የአንድነት ፕሪዘዳንታዊ ምርጫ ህገ ወጥ ነው… ሲል ይጀምርና እንዲህ የምንለው በርካታ ማስረጃዎችን ይዘን ነው… ሲል ይቀጥላል ከዛ፤ ለምሳሌ ያህል ብሎ ሊጠቅስልን ሲል ጉድ…ፈላ ብለን ማስረጃ ለመስማት ስናቆበቁብ… በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው… አራት ወይም አምስት ቢሆኑ ነው… ሲል ሊያቀርብ የነበረውን ማስረጃ ይረሳዋል። (አንድ ዝንጀሮ አለ አሉ… ሰዎች ሲያበሳጩት አርጩሜ ይቆርጣል… ከዛ የማያውቁ ሰዎች ገደለን በቃ ብለው ይሸሻሉ፤ ዝንጀሮው ግን አርጩሜውን ለምን እንደቆረጠው ወድያው ይረሳው እና ይጥለዋል። ከዛም ሲናደድ ድጋሚ ከዛፉ ይገነጥላል… ወድያው ግን ይረሳዋል።) የአቶ ትግስቱ ጸሀፊ እሱን ነው ያስታወሱኝ።

ሌላው በዚህ ቪዲዮ ውስጥ የታዘብኩት የራዲዮ ፋና ጋዜጠኛ የአንድነት ፓርቲ ተወካይ የሆኑትን አቶ ግርማ ሰይፉ ሲጠይቁ ሳቅ… እፍንንንን አድርጎት ይታያል። ልብ ብለው ይመልከቱልኝ… በርግጠኝነት የአለቆቹ ጨዋታ ገብቶታል።

በጥቅሉ እነ አቶ ትግስቱ ለዛውም ኢቲቪ ቆራርጦ አስተካክሎላቸው ራሱ አይደለም አንድነትን ያክል ፓርቲ የኛ ነው ለማለት ይቀርና ፖለቲከኛ የሚመስል ነገር እንኳ አላየሁባቸውም።

ምርጫ ቦርድ/ኢህአዴግ ለመኢአድም ሆነ ለአንድነት ሌላ ሰብብ ከሚፈልጉላቸው፤ በቃ ቆዳ ጫማችሁን ካላደወለቃችሁ አንችላችሁም። ብለው ከምርጫው ውጡልን ቢሉ የሚሻል ይመስለኛል። (ቆዳ ጫማ ካላወለቀ አልችለውም… ድሮ መደባደብ ስንፈራ የምሰጣት ምክንያት ነበረች።

አንዳንድ ልጅ፤ ሸራም አድርጎ ቢመጣ ሸራውን ካላወለቀ፤ አልጫወትም! ሞጋም ቢያደርግ ሞጋውን ያውልቅ እና ይሞክረኝ! ሞጋውን ቢያወልቅም ጥፍሩን ይቁረጥ እና ይሞክረኝ! ጥፍሩን ቢቆርጥም እግሩን ታጥቦ ይሞክረኝ… የሚባለላቸው ተፈሪዎች!

እንግዲህ አንደነቶች፤ ጉዳዩን ወደ ደጋፊዎቻችሁ ወስዳችሁ በሰላማዊ ሰልፍ አልያም በፊርማ ወይም በሌሎች ዘዴዎች በመጠየቅ ወደ ምርጫው ትራክ መመለስም ሌላው አማራጭ መሆኑን ልጠቁማችሁ እወዳለሁ… (ልል አሰብኩና እኔ ደቂቁ እናንተን እመክር ዘንድ ምንድነኝ…. ብዬ ተውኩት! )

ለማንኛውም ፈልጌ አስፈልጌ ያጣኋቸውን የአንድነት ተቀናቃኞች ቪዲዮ እንሆ… ትኩር ብለው ይመልከቱልኝ!

fana

The post ፈልጌ አስፈልጌ ያን ሰሞን አጣኋት… አቤ ቶኮቻው appeared first on ሳተናው (Satenaw) – Latest & Current Ethiopian News, Breaking News,.