የሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫ እጩዎችን እያስመዘገበ እንደሆነ ታወቀ
የሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫ የሚያደርገዉን እንቅስቃሴ በስፋት እንደቀጠለበት የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ፓርቲው የምርጫ ምልክት ከሌሎች ቀድሞ በማመልከቱ፣ ምልክት የሰጠው ሲሆን፣ በተናጥል ተወዳዳሪዎችን አዘጋጅቶ እያሰመዘገ እንደሚገኝም የአመራር አባላቱ ይናገራሉ።
የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ ሰማያዊ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውና የምርጫዉን ዘምቻ በጋራ ማቀናጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ ፣ ለሚሊዮኖች ድምጽ ጋዜጣ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሊቀመንበሩ፣ አቶ ይልቃል ጌትነት ፣ በዚሁ በሚሊዮኖች ድምጽ ጋዜጣ ላይ ቀርበው “የተናጥል ትግል ማድረግ ችግር የለውም” በሚል ፣ በተለይም ከመኢአድ እና ከአንድነት ጋር አብሮ የመስራቱን ነገር ማጣጣላቸው ይታወቃል።
የሕወሃት/ምርጫ ቦርድ “ስብሰባ ረግጣቹህ ወጥታቹሃል” የሚል ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ዉጭ፣ የድርጅቱን ሕጋዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ዉሳኔ ያልገለጸ ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድነት እና ከመኢአድ በተለየ ሁኔታ፣ የምርጫዉን ዘመቻ ለመቀጠል እድሉ የተመቻቸለት ይመስላል።
መኢአድ እና አንድነት እንኳን ተወዳዳሪዎችን ሊያስመዘግቡ ቀርቶ፣ ገና የምርጫ ምልክት ያልተሰጣቸው ሲሆን፣ በተለይም አንድነት ፓርቲን፣ የሕወሃት የደህንነት ቡድን፣ ከነጭራሹ በምርጫው እንዳይሳተፉ ለማገድ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም በግልጽ እየታየ ነው።
መኢአድ እና አንድነት ወደ ምርጫዉን እንዳይገቡ ምርጫ ቦርድ እያከላከለ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ ለመኢአድ እና ለአንድነት አጋርነቱን በማሳየት፣ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት፣ ትግሉን በጋር ማቀናጀት ሲገባው፣ የተናጥል ጉዞ መቀጠሉ ብዙዎችን እያስገረመ ነው።
ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አብሮ መስራት ያስፈልጋል የሚል ጥሪ እያሰሙ ሲሆን፣ በተለይም የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ታክቲክን ማምከን ካልተቻለ፣ የሕዙቡ ሰቆቃና መከራ ሊራዘም እንደሚችል የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም።
“የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች ከአንድነት እና ከመኢአድ ጋር አብረው መስራት አለባቸው። መኢአድም ሆነ አንድነት ፍቃደኞች ናቸው። መኢአድ እና አንድነት አብረው እየሰሩ ነው። ይልቃል ጌትነት “ መሪ አልሆንም። ስልጣን እጣለሁ” በሚል ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ ስልጣኑን ካልስቀደሙ በቀር፣ የሰማያዊ ፓርቲ አብሮ የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም” ያሉት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ “የተናጥል ጉዙ የሚጠቀመው ወያኔን ብቻ ነው” ብለዋል።