አስተዳደሩ ያወጣው ‹‹ሕገወጥ›› ቤቶችን ‹‹ሕጋዊ›› የሚያደርገው ደንብ የተደበላለቀ ስሜት ፈጠረ Addis Abeba Offers to Legalize Illegal Land Grabbers

ይህን ፅሁፍ ሪፖርተር ያወጣው ባለፈው ዓመት ቢሆንም አዲስ  ፎርቹን ሕጋዊ ሰንድ መስጠት መጀመሩን የዘገበው በዚህ ሳምንት ነው Read in English
15 MAY 2013 ተጻፈ በ  

አስተዳደሩ ያወጣው ‹‹ሕገወጥ›› ቤቶችን ‹‹ሕጋዊ›› የሚያደርገው ደንብ የተደበላለቀ ስሜት ፈጠረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ይዞታ ይዘው የሚገኙ ነዋሪዎችን ሕጋዊ የሚያደርግ ደንብ ማፅደቁ የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሯል፡፡ 

የተደበላለቀ ስሜት የተፈጠረባቸው ነዋሪዎች በሦስት የሚከፈሉ ሲሆን፣ የመጀመርያዎቹ በአስተዳደሩ ያልተጠበቀ ውሳኔ ደስታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ መሬት ‹‹በግዥ›› እና ‹‹በወረራ›› ይዘው በአስተዳደሩ በዘመቻ መልክ የፈረሰባቸው ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ውስጥ ያልተሰማሩ ነዋሪዎች የአስተዳደሩ ውሳኔ ግርምትን እንደፈጠረባቸው የሚገልጹ ናቸው፡፡ ‹‹የመኖርያ ቤት ባለቤት ለመሆን ሕገወጥ ተግባር ውስጥ መሳተፍ ነበረብን?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ 

የአዲስ አበባ አስተዳደር ረዥም ጊዜ በመውሰድ በከተማው የአስተዳደር ክልል ውስጥ በተለይ በማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ መሬት በግዥ ወይም በዘፈቀደና በወረራ የያዙ ነዋሪዎችን፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ነገር ግን የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ችግር በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም ያለ በመሆኑ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ወጥ የሆነ አሠራር በአገር አቀፍ ደረጃ ማስፈን የሚያስችለውን ሕግ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ሕግ መነሻነት የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ የክልል ከተሞች ካቢኔዎች እንደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አዋጁን በመንተራስ ደንብና መመርያ እያዘጋጁ ነው፡፡ 

የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ያፀደቀው ደንብ እንደሚለው እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. ድረስ መሬት በሕገወጥ መንገድ የያዙ ባለይዞታዎች የያዙት መሬት ከማስተር ፕላኑ ጋር የሚጣጣም ከሆነ ሕጋዊ ይደረጋሉ፡፡ ቀደም ሲል በአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 1997 ዓ.ም. ድረስ በሕገወጥ መንገድ መሬት የያዙ ሰዎችን ሕጋዊ ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ይህም የሆነው ከግንቦት 1997 ዓ.ም. በኋላ ከተነሳው የምርጫ ቀውስ ጋር ተያይዞ ‹‹መንግሥት የለም›› በሚል በሕገወጥ መንገድ ቦታ የያዙ አካላትን ለመቅጣት በማሰብ ነው ተብሎ ነበር፡፡ 

በዚህ መሠረትም በባለአደራው አስተዳደርና በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር ወቅቶች በተለይ በ1998 ዓ.ም.፣ በ2000 ዓ.ም.፣ በ2001 ዓ.ም. በዘመቻ መልክ በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ይህንንም ሪፖርተር በየወቅቱ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ መሀል ግን በተለያዩ ምክንያቶች ቤቶቻቸው በተካሄዱት ዘመቻዎች ያልፈረሱባቸው ነዋሪዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ 

ነገር ግን አስተዳደሩ አዲስ ያወጣው ደንብ ቤቶች ያልፈረሱባቸውን የሚጠቅም፣ ነገር ግን የፈረሰባቸው ነዋሪዎች የሚጎዳ መሆኑን ሁኔታውን በቅርብ የሚያውቁ እየገለጹ ነው፡፡ አስተዳደሩ ሁሉንም ነዋሪዎች በእኩል ሊመለከት ይገባል የሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚገልጹት፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዘው መሬት ከማስተር ፕላኑ ጋር የሚጣጣም ከሆነ፣ ቀደም ሲል የፈረሰውም ቤት ሕጋዊ መሆን እንዳለበትና ቅጣት ካለም ወጥ በሆነ መንገድ ሊተገበር እንደሚገባ አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ 

የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ይህ የአስተዳደሩ ደንብ መፅደቁ ከተነገረ በኋላ መኖርያ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች በድጋሚ ቤታቸውን ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ተስፋ ያደረጉትም ቀደም ሲል በተለያዩ ወቅቶች የተነሱትን የከተማው የአየር ካርታዎችን (ጂአይኤስ) ነው፡፡  

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።